የጥያቄ ሣጥን
◼ ወላጆች ልጆቻቸውን ያስጠኑበትን ሰዓት ሁለቱም ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ?
ምንም እንኳ ልጆችን ‘በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ’ የማሳደጉ ዋነኛ ኃላፊነት የአባቶች ቢሆንም ሁለቱም ወላጆች ልጆቻቸውን በማሠልጠኑ ሥራ ድርሻ አላቸው። (ኤፌ. 6:4) መጽሐፍ ቅዱስ “የአባትህን ምክር አድምጥ፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው” በማለት ልጆችን ያበረታታል። (ምሳሌ 1:8) ወላጆች ለልጆቻቸው ሥልጠና ከሚሰጡባቸው ወሳኝ መንገዶች አንዱ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው።
ከዚህ ቀደም ሁለቱም ወላጆች ያልተጠመቁ ልጆቻቸውን በማስጠናቱ ሂደት እየተካፈሉም እንኳ ሰዓቱን ሪፖርት የሚያደርገው የቤተሰብ ጥናቱን የሚመራው ወላጅ ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ማስተካከያ ተደርጎበታል። በቤተሰብ ጥናቱ ወቅት ሁለቱም ወላጆች ልጆቻቸውን በማስተማሩ ሥራ እስከተካፈሉ ድረስ ሁለቱም በሳምንት እስከ አንድ ሰዓት ድረስ በመስክ አገልግሎት ሪፖርታቸው ላይ መመዝገብ ይችላሉ። በአብዛኛው ወላጆች ልጆቻቸውን በማስተማሩ ሥራ በሳምንት ከአንድ ሰዓት በላይ እንደሚያጠፉ የታወቀ ነው። ሁለቱም ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሠልጠን ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ይጠይቅባቸዋል። (ዘዳ. 6:6-9) ይሁን እንጂ በየወሩ የሚመልሱት የመስክ አገልግሎት ሪፖርት በዋነኝነት በመስኩ ላይ ያከናወኑትን እንቅስቃሴ የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል። በመሆኑም ወላጆች ጥናቱ ከአንድ ሰዓት የበለጠ ጊዜ ቢወስድም ወይም ጥናቱን በሳምንት ከአንድ ጊዜ በላይ ቢመሩም አሊያም እያንዳንዱን ልጅ ብቻውን ቢያስጠኑም በሳምንት ከአንድ ሰዓት የበለጠ ጊዜ መቁጠር የለባቸውም። የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ሪፖርት የሚያደርገው አንደኛው ወላጅ ብቻ ሲሆን ይህ ወላጅ ጥናቱ በተደረገበት በእያንዳንዱ ሳምንት የሚመዘግበው አንድ ተመላልሶ መጠይቅ ብቻ ነው።