“ቀንበሬን ተሸከሙ”
1 ዓለማችን በውጥረትና በጭንቀት የተሞላ ቢሆንም ኢየሱስ፣ ቀንበሩን በመሸከም ለነፍሳችን እረፍት እንድናገኝ ያቀረበውን ፍቅራዊ ግብዣ መቀበላችን እፎይታ አስገኝቶልናል። (ማቴ. 11:29, 30) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የመሆንን ቀንበር መሸከም ተፈታታኝ ሆኖም እረፍት በሚሰጥ አንድ ሥራ መካፈልን ይጨምራል። ይህ ሥራ ደግሞ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክንና ሰዎች የኢየሱስን ልዝብ ቀንበር በመሸከም እንደኛው ለነፍሳቸው እረፍት እንዲያገኙ መርዳትን ያካትታል።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
2 አገልግሎት የሚያስገኘው እረፍት:- ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከራሳቸው ሸክም በተጨማሪ የእሱን ሸክም እንዲሸከሙ አልጠየቀም። ከዚህ ይልቅ የራሳቸውን ከባድ ሸክም አውርደው የእሱን ቀላል ሸክም እንዲሸከሙ ጋብዟቸዋል። በመሆኑም ይህ ሥርዓት በሚያመጣቸው አስጨናቂና ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ነገሮች ልባችን እንዲዝል ማድረግም ሆነ አስተማማኝነት የሌለውን ሀብት ለማግኘት መድከም አይኖርብንም። (ሉቃስ 21:34፤ 1 ጢሞ. 6:17) ምንም እንኳ በሥራ የተወጠርን ብንሆንና የዕለት ጉርሳችንን ለማግኘት መሯሯጣችን የግድ ቢሆንም እንኳ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ለይሖዋ አምልኮ ነው። (ማቴ. 6:33) ይበልጥ አስፈላጊ ለሆነው ነገር ትክክለኛ አመለካከት ካዳበርን ምንጊዜም ቢሆን አገልግሎት ሸክም ሳይሆን እረፍት የሚሰጥ ይሆንልናል።—ፊልጵ. 1:10
3 አብዛኛውን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ስለምንሰጣቸው ነገሮች ማውራት ያስደስተናል። (ሉቃስ 6:45) በሁሉም ክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚይዙት ደግሞ ይሖዋ እና እሱ ተስፋ የገባቸው የመንግሥቱ በረከቶች ናቸው። በመሆኑም አገልግሎት ላይ ስንሆን የዕለት ተዕለት ጭንቀታችንን ትተን ወደፊት የተሻለ ነገር እንደሚመጣ “የምሥራች” መናገራችን በእርግጥም እረፍት የሚሰጥ ነው! (ሮሜ 10:15) በአንድ ሥራ ላይ ይበልጥ ስንቆይ ብቃታችንም ሆነ የምናገኘው ደስታ የዚያኑ ያህል ይጨምራል። በመሆኑም በተቻለ መጠን ጊዜያችንን ይበልጥ በአገልግሎት የምናሳልፍ ከሆነ የምናገኘው እርካታም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። አንዳንድ ሰዎች ለስብከቱ ሥራችን ምላሽ ሲሰጡ ማየት ምንኛ የሚያበረታታ ነው! (ሥራ 15:3) ይሖዋ በጥረታችን እንደሚደሰትና በጎ ውጤት ሁሉ የሚገኘው ከእሱ እንደሆነ ዘወትር የምናስታውስ ከሆነ፣ አገልግሎታችን ግድየለሽ ወይም ተቃዋሚ ሰዎች ቢያጋጥሙንም እንኳ መንፈስን የሚያድስ ይሆንልናል።—ሥራ 5:41፤ 1 ቆሮ. 3:9
4 የኢየሱስን ግብዣ የምንቀበል ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን ከእሱ ጋር አብረን የማገልገል መብት ይኖረናል። (ኢሳ. 43:10፤ ራእይ 1:5) ከዚህ የበለጠ እረፍት የሚሰጥ ምን ነገር ይኖራል?