“መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ” ሁኑ
1 ኢየሱስ፣ አዲስ የስብከት ዘመቻ ሲጀምር ጊዜ መድቦ ደቀ መዛሙርቱን አዘጋጅቷቸው ነበር። (ማቴ. 10:5-14) ሁላችንም ሥራ የሚበዛብን ቢሆንም እንኳ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ከመጀመራችን በፊት ጥቂት ደቂቃዎችን መድበን መዘጋጀታችን አስደሳች በረከቶችን እንድናጭድ ይረዳናል።—2 ቆሮ. 9:6
2 መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ጥሩ ዝግጅት የሚጀምረው ልናበረክተው ያሰብነውን ጽሑፍ በሚገባ በማንበብ ነው። በተጨማሪም በክልላችን ውስጥ ስላሉ ሰዎች ማሰብ ይኖርብናል። እነዚህ ሰዎች የሚያሳስባቸው ጉዳይ ምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥሙን ሰዎች ምን ዓይነት ሃይማኖታዊ አመለካከት ያላቸው ናቸው? በመንግሥት አገልግሎታችን እና ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን የናሙና አቀራረቦች መከለሳችን ጥሩ ሐሳብ ለማግኘት ያስችለናል።
3 በአገልግሎት ስብሰባ ላይ የሚቀርቡትን ሠርቶ ማሳያዎች በጥሞና ማዳመጣችንም ይረዳናል። መግቢያዎችን በመጠቀም ረገድ ጥሩ ልምድ እያገኘን ስንሄድ ለዝግጅት የምናውለው ጊዜም እየቀነሰ ይሄዳል። ይሁንና አገልግሎት ከመውጣታችን በፊት ምንጊዜም ስለምንናገረው ነገር የምናስብ እንዲሁም አቀራረባችንን ለማሻሻል የምንጥር ከሆነ ይበልጥ ውጤታማ እንሆናለን። በተጨማሪም በቦርሳችን ውስጥ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉንን ጽሑፎች በሙሉ መያዛችንን ማረጋገጥ ይገባናል።
4 የተዘጋጀነውን መግቢያ እንዳንረሳው ምን ሊረዳን ይችላል? የመግቢያ ሐሳቡ ከአእምሯችን እንዳይጠፋ የሚረዳን አንደኛው መንገድ ድምፃችንን ከፍ አድርገን መለማመድ ነው። አንዳንዶች በቤተሰብ ጥናታቸው ወቅት መለማመዳቸው ጠቅሟቸዋል። ሌሎች ደግሞ መግቢያቸውን አጠር አድርገው በትንሽ ወረቀት ላይ መጻፋቸውና ወደሚያንኳኩት ቤት ከመድረሳቸው በፊት መከለሳቸው ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።
5 መዘጋጀት የሚያስገኘው ጥቅም:- ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማና ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል። እንዲሁም በር ስናንኳኳ ዘና እንድንል ብሎም እንዳንርበተበት ይረዳናል። ስለምንናገረው ነገር ከመጨነቅ ይልቅ ለቤቱ ባለቤት የበለጠ ትኩረት እንድንሰጥም ያስችለናል። ጽሑፉን በሚገባ ማንበባችን ደግሞ ለሰዎች ስናበረክተው በግለት እንድንናገር ያስችለናል።
6 መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ” እንድንሆን ያበረታታናል። (ቲቶ 3:1) ምሥራቹን ለሌሎች ከመናገር የበለጠ ምን መልካም ነገር አለ? ጥሩ ዝግጅት በማድረግ፣ እኛን ለመስማት ፍላጎት ላሳየው የቤት ባለቤትም ሆነ ለወከልነው ለይሖዋ አምላክ አክብሮት እንዳለን እናሳይ።—ኢሳ. 43:10