የጥር የአገልግሎት ሪፖርት
◼ ቲኦክራሲያዊ ዜናዎች
“በሕይወቴ እንደዚህ ዓይነት አገልግሎት አጋጥሞኝ አያውቅም።” “በአገራችን እንዲህ የመሰለ የአገልግሎት ክልል መኖሩን አላውቅም ነበር።” “ሁሉም ሰዎች የተቀበሉን በጥሩ ሁኔታ ነበር፤ እንዲህ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም!” “በርካታ ሰዎች እረኛ እንደሌላቸው በጎች እርዳታ ለማግኘት የሚጓጉ መሆናቸውን በቀላሉ መመልከት ይቻላል።” “ቀኑን ሙሉ ከሰዎች ጋር ስንነጋገር ስለምንውል ማታ ላይ ይደክመናል፤ ሆኖም ውስጣችን የደስታ ስሜት ይሰማን ነበር!” “በጣም የከበደን ነገር ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን መሰናበት ነበር።” “ከስብከቱ ሥራ በተጨማሪ ከልዩ አቅኚዎች ጋር መሥራት ያስደስታል።” “ገና በመጀመሪያው ሳምንት አሥር የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አግኝቼ ነበር።” “አሁንም፣ ገና ብዙ ሥራ አለ!” እነዚህ፣ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ልዩ የስብከት ዘመቻ ላይ የተካፈሉት ወንድሞችና እህቶች ከሰጧቸው አስተያየቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ይህ ዘመቻ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ በማገልገል ላይ የሚያተኩር ሲሆን በተለምዶ “መቄዶንያ” ተብሎ ይጠራል።—ሥራ 16:9, 10
በአጠቃላይ ወደ አርባ የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ከውጭ አገር የመጡ ሲሆን አንዳንዶቹ እንደ ምሥራቃዊው አውስትራሊያ እና ምዕራባዊው ሰሜን አሜሪካ ከመሰሉ ሩቅ ቦታዎች የመጡ ነበሩ። ከእነዚህ ወንድሞች ጋር ደግሞ በዋና ከተማችን ከሚገኙት የአገልግሎት ክልላቸውን በየጊዜው ከሚሸፍኑት ጉባኤዎች የተውጣጡ ወደ አራት መቶ የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች በዘመቻው ተካፍለዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች መሥዋዕትነት ለመክፈል ይኸውም የራሳቸውን ወጪ ለመሸፈን፣ ከመሥሪያ ቤታቸው የዓመት ፈቃድ ለመውሰድ እንዲሁም ምቾቶቻቸውን ለመተው ፈቃደኞች ነበሩ። ልዩ አቅኚዎችና በአካባቢው የሚገኙ አስፋፊዎች በዘመቻው ለተካፈሉት ወንድሞች ድጋፍ በመስጠታቸው በርካታ አነስተኛ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በዘመቻው ሊሸፈኑ ችለዋል። አንዳንዶቹ ቦታዎች የስብከቱ መልእክት የደረሳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። በዘመቻው የተካፈሉ ወንድሞች፣ ከዚህ በፊት ጥናት ጀምረው ያቋረጡ ግለሰቦችን ያገኙ ሲሆን ሰዎቹም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደገና በመገናኘታቸው እጅግ ተደስተዋል። ሌሎች ደግሞ እውነትን ለመጀመሪያ ሲሰሙ በደስታ ከመዋጣቸው የተነሳ በየቀኑ ያጠኑ ነበር!
ይህ ሁሉ ምን ይጠቁማል? ኢየሱስ በማቴዎስ 9:36-38 ላይ እንደተናገረው በእርግጥም መከሩ ብዙ ነው። ፍላጎት ያሳዩ እነዚህ ሰዎች እርዳታ ያሻቸዋል፤ አንተም እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ራሳቸውን ከሚያቀርቡት መካከል አንዱ መሆን ትችል ይሆናል። ልዩ አቅኚዎች ሊመደቡ የሚችሉት በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ ነው። አቂላና ጵርስቅላ ድንኳን ይሰፉ እንደነበረ ሁሉ የራሳቸው መተዳደሪያ ኖሯቸው የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች በብዙ ቦታዎች ላይ ያስፈልጋሉ። (ሥራ 18:2, 3) በአገራችን የሚገኘውን ሰፊ የአገልግሎት ክልል የመሸፈኑንና የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች የመፈለጉን ጉዳይ በጸሎታችሁ እንድታስቡበት እናበረታታችኋለን። ከዚህም በተጨማሪ፣ “ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደህ ማገልገል ትችላለህ?” የሚለውን በሐምሌ 2001 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 4 ላይ የወጣውን ርዕስ እባካችሁ ከልሱት። ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደህ ለማገልገል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ትችላለህ?