አዲሶች የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ እንዲቋቋሙ አዘጋጇቸው
1 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ሲጀምሩና ‘ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር ሲፈልጉ’ ሰይጣን ዋነኛ የጥቃት ዒላማ ያደርጋቸዋል። (2 ጢሞ. 3:12) እነዚህ ሰዎች ከሥራ ባልደረቦቻቸው፣ አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች ወይም ከጎረቤቶቻቸው ተቃውሞ ሊገጥማቸው ይችላል። በተለይ ደግሞ እንዲህ ያለው ተቃውሞ አሳቢ ከሆኑ የቅርብ ዘመዶቻቸው በሚመጣበት ጊዜ በጣም ፈታኝ ይሆንባቸዋል።—ማቴ. 10:21፤ ማር. 3:21
2 ተቃውሞ እንደሚኖር አስቀድሞ ተነግሯል፦ አዲሶች ስደት ሊደርስባቸው እንደሚችል መጠበቅ ያለባቸው ከመሆኑም ሌላ ይህም እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ዮሐ. 15:20) አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ተቃውሞ የሚሰነዝሩት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ አመለካከት ስላላቸው ሊሆን ይችላል። የክርስቶስ ተከታዮች በመሆናችንና አምላክን በመታዘዛችን የተነሳ ውርደት መቀበላችን ከፍተኛ ደስታ እንደሚያስገኝ መዘንጋት አይኖርብንም። (ሥራ 5:27-29, 40, 41) አዲሶች የይሖዋ ፍቅራዊ ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጡላቸው። (መዝ. 27:10፤ ማር. 10:29, 30) ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊነት አስመልክቶ በተነሳው ክርክር ረገድ ከይሖዋ ጎን መቆማቸውን ያሳያል።—ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም
3 ትክክለኛ እውቀት የሚጫወተው ሚና፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችሁ የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ ትክክለኛ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠላቸው አስፈላጊ መሆኑን በሚገባ አስገንዝቧቸው። ሰይጣን ተቃውሞን እንደ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም እየተማሩት ያለው ነገር በምሳሌያዊ ልባቸው ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ለማድርግ ይሞክራል። (ምሳሌ 4:23፤ ሉቃስ 8:13) በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል ይገባቸዋል።—መዝ. 1:2, 3፤ ቈላ. 2:6, 7
4 መጽናት አስፈላጊ ነው፦ ምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን ጽናት አስፈላጊ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። (ሉቃስ 21:16-19) አዲሶች የሚደርስባቸውን ተቃውሞ መቋቋማቸው እነሱንም ሆነ ሌሎችን ይጠቅማል። ይሖዋ በታማኝነት የሚጸኑ አገልጋዮቹን አትረፍርፎ እንደሚባርካቸው ከራሳቸው ተሞክሮ ያያሉ።—ያዕ. 1:12
5 ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚኖሩ ወንድሞቹ ባደረጉት መንፈሳዊ እድገት ተደስቶ ነበር። አብዛኞቹ እውነትን እንዲያውቁ የረዳው እሱ ሲሆን ስላደረጉት እድገትም አምላክን አመስግኗል። (2 ተሰ. 1:3-5) እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ተቃውሞን እንዲጋፈጡና እንዲጸኑ አስቀድመን የምናዘጋጃቸው ከሆነ ተመሳሳይ ደስታና እርካታ እናገኛለን።