መልስ መስጠት ያለብን እንዴት ነው?
1. በአገልግሎታችን ላይ ጥያቄ ስንጠየቅ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ያለብን ለምንድን ነው?
1 እስከ ዛሬ ድረስ ሰዎች፣ ኢየሱስ ጥያቄዎችን በመለሰበት መንገድ በጣም ይደነቃሉ። እኛም በአገልግሎታችን ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ስንጠየቅ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን የተገባ ነው።—1 ጴጥ. 2:21
2. ለሚቀርቡልን ጥያቄዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ መልስ ለመስጠት ምን ሊረዳን ይችላል?
2 በቅድሚያ አዳምጡ፦ ኢየሱስ የግለሰቡን አመለካከት ከግምት ያስገባ ነበር። የግለሰቡን ትክክለኛ አመለካከት ለማወቅ አንዳንድ ጊዜ ጥያቄ መጠየቅ ያስፈልግ ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ሰው “በኢየሱስ ታምናላችሁ?” ብሎ ሲጠይቅ ‘ገናን የማታከብሩት ለምንድን ነው?’ ብሎ መጠየቁ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡን ያሳሰበው ነገር ምን እንደሆነ መረዳት ከቻልን ውጤታማ በሆነ መንገድ መልስ ልንሰጠው እንችላለን።—ሉቃስ 10:25-37
3. በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት የሚያስችሉ ምን መሣሪያዎች አሉን?
3 መልሳችሁ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ይሁን፦ ለቀረበላችሁ ጥያቄ መልስ በምትሰጡበት ጊዜ ምንጊዜም መጽሐፍ ቅዱሳችሁን መጠቀማችሁ ተገቢ ነው። (2 ጢሞ. 3:16, 17፤ ዕብ. 4:12) ማመራመር መጽሐፍና በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘው “ለውይይት የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶች” የሚለው ክፍል ትክክለኛ መልስ በመስጠት ረገድ ግሩም እርዳታ ያበረክታሉ። ጥያቄ የጠየቃችሁ ግለሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምን ቢሆን እንኳ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን እንደሚያስተምሩ በዘዴ ልትነግሩት ትችሉ ይሆናል። ግለሰቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ለዘመናት የተፈተነ ጥበብ በቁም ነገር እንዲመረምር አበረታቱት። ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ከተከተልን የምንሰጠው መልስ “በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ” ውድ ብሎም ግርማና ውበት የተላበሰ ይሆናል።—ምሳሌ 25:11
4. ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ ከመስጠት መቆጠባችን የተሻለ የሚሆነው በየትኞቹ አጋጣሚዎች ነው?
4 እያንዳንዱን ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል? የቀረበላችሁን ጥያቄ መልስ የማታውቁት ከሆነ “መልሱን አላውቀውም፤ ይሁን እንጂ በጥያቄህ ላይ ምርምር አድርጌ ያገኘሁትን ውጤት ሌላ ጊዜ ልነግርህ እችላለሁ” ማለት ሊያሳፍራችሁ አይገባም። በዚህ መንገድ ትሑት መሆናችሁና ለግለሰቡ አሳቢነት ማሳየታችሁ፣ ግለሰቡ በሌላ ጊዜ ተመልሳችሁ እንድትመጡ ፈቃደኛ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። ጥያቄውን ያነሳው ግለሰብ ጭቅጭቅ ለመፍጠር የሚፈልግ ተቃዋሚ እንደሆነ ካስተዋላችሁ ብዙ ከመናገር በመቆጠብ ኢየሱስን ምሰሉ። (ሉቃስ 20:1-8) በተመሳሳይም አንድ ሰው ለእውነት ምንም ፍላጎት ሳይኖረው ክርክር ውስጥ ሊከታችሁ የሚፈልግ ከሆነ ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ውይይታችሁን አቋርጣችሁ ጊዜያችሁን ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችን ለመፈለግ ተጠቀሙበት።—ማቴ. 7:6
5. ኢየሱስ ለጥያቄዎች መልስ በመስጠት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
5 ኢየሱስ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ‘ስለ እውነት እንዲመሠክር’ የተሰጠውን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ በይሖዋ ላይ መታመኑ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 18:37) “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ያላቸው ሰዎች ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ በመስጠት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል መቻላችን እንዴት ያለ መብት ነው!—ሥራ 13:48