በስልክ የሚሰጥ ምሥክርነት ውጤታማ ሊሆን ይችላል
1. በስልክ የሚሰጥ ምሥክርነት በአገልግሎታችን ከምንጠቀምባቸው አስፈላጊ ዘዴዎች መካከል አንዱ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
1 በስልክ ምሥክርነት ስለ መስጠት በቁም ነገር ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰዎች ለመዳን የሚያስችላቸውን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት የሚቻልበት አንዱ መንገድ ስለሆነ ነው። (2 ጴጥ. 3:9) የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ የምንጠቀምበት ዋነኛው መንገድ ከቤት ወደ ቤት ቢሆንም ቤታቸው ሄደን ልናገኛቸው የማንችላቸውን ሰዎች ለማነጋገር ሌሎች አማራጮችንም መጠቀም ይኖርብናል።—ማቴ. 24:14፤ ሉቃስ 10:1-7፤ ራእይ 14:6
2. በስልክ የሚሰጠውን ምሥክርነት ማደራጀት የሚቻለው እንዴት ነው?
2 ማደራጀት የሚቻልበት መንገድ፦ ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው አገልግሎት ክልል እንደሚዘጋጅ ሁሉ በስልክ ምሥክርነት ለሚሰጡ አስፋፊዎችም ክልል ይዘጋጅላቸዋል። አንድ አስፋፊ ብቻውን አሊያም ከአንድ ወይም ከሁለት አስፋፊዎች ጋር በመሆን በስልክ መመሥከር ይችላል። በስልክ ምሥክርነት የመስጠቱ ሥራ ጸጥታ በሰፈነበት ቦታ መከናወን ይኖርበታል። ብዙ አስፋፊዎች በስልክ ምሥክርነት በሚሰጡበት ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ የሚጠቀሙባቸውን ጽሑፎች ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው መመሥከራቸው ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።
3. በስልክ ስንመሠክር ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል?
3 በስልክ መመሥከር የሚቻልበት መንገድ፦ በስልክ በምንመሠክርበት ጊዜ አቀራረባችን የጭውውት ይዘት ሊኖረው ይገባል። በዚህ የአገልግሎት መስክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካፈሉ አንዳንድ አስፋፊዎች መግቢያቸውን በማንበብ ውይይታቸውን ይጀምሩ ይሆናል፤ ሆኖም ውይይታቸው የጭውውት ይዘት እንዲኖረው ጥረት ያደርጋሉ። መግቢያዎችን ለማዘጋጀት ማመራመር መጽሐፍ፣ የመንግሥት አገልግሎታችን እና እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የተባለው ትራክት ሊረዱን ይችላሉ። አቀራረባችሁን ስትዘጋጁ ርዕሰ ጉዳዩን ምረጡ፣ ጥያቄ አዘጋጁ እንዲሁም ለጥያቄው መልስ የሚሆኑ ጥቂት ጥቅሶችን አዘጋጁ። ለምታነጋግሩት ሰው ከቤት ወደ ቤት ስታገለግሉ የምታበረክቱትን ጽሑፍ ልታስተዋውቁት ትችላላችሁ። የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች ልብ በሉ፦ ዘና ብላችሁ በእርጋታ ተናገሩ። በስልክ የምታነጋግሩት ሰው ሁኔታውን መረዳት ስለሚችል ሥርዓት ባለው መንገድ ተናገሩ እንዲሁም ታጋሾችና ተግባቢዎች ሁኑ። የምታነጋግሩት ሰው ሐሳቡን ሲገልጽ በጥሞና አዳምጡት፤ ከዚያም አመለካከቱን ስለገለጸላችሁ አመስግኑት። ግለሰቡ በስልክ እርዳታ የምናሰባስብ ሊመስለው ስለሚችል በዚህ ጊዜ መዋጮ እንዲያደርግ መጠየቅ አያስፈልጋችሁም።
4. በስልክ ለመመሥከር የምናደርገው ጥረት በክልላችን ውስጥ ምን ዓይነት ሰዎችን እንድናገኝ ያስችለናል?
4 በስልክ ስትመሠክሩ በመታመሙ ወይም የአካል ጉዳተኛ በመሆኑ ምክንያት ከቤት መውጣት የማይችል ሰው አሊያም በሥራው ባሕርይ ምክንያት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ፈጽሞ ቤት ሊገኝ የማይችል ሰው ታገኙ ይሆናል። በተጨማሪም በቀላሉ መግባት በማይቻልባቸው ግቢዎችና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ታገኙ ይሆናል። በመሆኑም አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም እንድንችል ግሩም ውጤት ሊያስገኝ የሚችለውን በስልክ የመመሥከር ዘዴ ጥሩ አድርገን መጠቀም ይኖርብናል።