ክርስቲያን አገልጋዮች መጸለይ ያስፈልጋቸዋል
1. አገልግሎታችንን ማከናወን እንድንችል ምን ያስፈልገናል?
1 አገልግሎታችንን በራሳችን ችሎታ ማከናወን አንችልም። ይሖዋ ሥራውን ማከናወን እንድንችል ኃይል ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:13) በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን እንድናገኝ በመላእክቱ አማካኝነት ይረዳናል። (ራእይ 14:6, 7) ያም ሆኖ የተከልነውንና ያጠጣነውን የእውነት ዘር የሚያሳድገው ይሖዋ ነው። (1 ቆሮ. 3:6, 9) በመሆኑም ክርስቲያን አገልጋዮች በሰማይ ወደሚገኘው አባታቸው በመጸለይ በእሱ እንደሚመኩ ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው!
2. ስለ የትኞቹ ነገሮች መጸለይ እንችላለን?
2 ለራሳችን፦ ከመስበካችን በፊት በእያንዳንዱ አጋጣሚ መጸለይ ይኖርብናል። (ኤፌ. 6:18) ስለ የትኞቹ ነገሮች መጸለይ እንችላለን? ስለ ክልላችን አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝና ድፍረት እንዲኖረን መጸለይ እንችላለን። (ሥራ 4:29) መጽሐፍ ቅዱስ ልናስጠናቸው ከምንችላቸው ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር እንዲያገናኘን ይሖዋን መጠየቅ እንችላለን። የቤቱ ባለቤት ጥያቄ ከጠየቀን ይሖዋ ተገቢውን መልስ መስጠት እንድንችል እንዲረዳን በልባችን አጭር ጸሎት ማቅረብ እንችላለን። (ነህ. 2:4) ለአገልግሎቱ ቅድሚያ እንድንሰጥ የሚያስችል ጥበብ እንዲኖረንም መጠየቅ እንችላለን። (ያዕ. 1:5) ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን ያገኘነውን መብት እንደምናደንቅ የሚገልጽ ሐሳብ በጸሎታችን ውስጥ ስናካትት ይሖዋ ይደሰታል።—ቆላ. 3:15
3. ለሌሎች መጸለያችን የስብከቱ ሥራ እንዲስፋፋ የሚረዳው እንዴት ነው?
3 ለሌሎች፦ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የእምነት ባልደረቦቻችንን በስም እየጠራን ‘አንዳችን ለሌላው መጸለይ’ ይኖርብናል። (ያዕ. 5:16፤ ሥራ 12:5) የጤና እክል በስብከቱ ሥራ እንደልባችሁ እንዳትካፈሉ እንቅፋት ሆኖባችኋል? እንደዚያ ከሆነ ጥሩ ጤንነት ላላቸው የእምነት ባልደረቦቻችሁ ጸልዩ። ስለ እነሱ የምታቀርቡት ጸሎት ያለውን ኃይል ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱ። በተጨማሪም ባለሥልጣናት ለስብከቱ ሥራ በጎ አመለካከት እንዲኖራቸው መጸለያችን ተገቢ ነው፤ ይህም ወንድሞቻችን “በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ” መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል።—1 ጢሞ. 2:1, 2
4. በጽናት መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
4 ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ማወጅ ከባድ ሥራ ነው። ‘በጽናት የምንጸልይ’ ከሆነ በይሖዋ እርዳታ ሥራውን ማከናወን እንችላለን።—ሮም 12:12