“ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል”
1. አንዳንዶች ስለ ሥራችን ምን አመለካከት አላቸው?
1 አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎት ላይ ስለ እኛ የተዛባ አመለካከት ያላቸው ወይም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ ነገር የሰሙ ሰዎች ያጋጥሙናል፤ በመሆኑም ስናነጋግራቸው አሉታዊ ምላሽ ይሰጡን ይሆናል። ምናልባት እንዲህ ያለ አመለካከት የኖራቸው ከመገናኛ ብዙኃን የተዛባ ሪፖርት ሰምተው ሊሆን ይችላል። እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች “አደገኛ ኑፋቄ” የሚል ስያሜ ሰጥተውናል። እንዲህ ዓይነት ነቀፋ ሲሰነዘርብን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
2. ነቀፋ ሲሰነዘርብን ተስፋ እንዳንቆርጥ ምን ሊረዳን ይችላል?
2 አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች፣ ኢየሱስንም ሆነ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ይረዷቸው ብሎም ስማቸውን ያጠፉ ነበር። (ሥራ 28:22) ነገር ግን የደረሰባቸው ነቀፋ በአገልግሎታቸው እንዲያፍሩ አላደረጋቸውም። ኢየሱስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል። (ማቴ. 11:18, 19) እውነትን ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎች ምሥራቹ ያለውን ጠቀሜታ እንደሚገነዘቡ በመተማመን የአባቱን ፈቃድ በቅንዓት መፈጸሙን ቀጥሏል። የአምላክ ልጅም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት እንደነበረ ማስታወሳችን ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል።
3. ስለ እኛ መጥፎ ወሬ መወራቱም ሆነ ተቃውሞ የሚያጋጥመን መሆኑ ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ ዓለም እሱን እንደጠላው ሁሉ ተከታዮቹንም እንደሚጠላቸው ተናግሯል። (ዮሐ. 15:18-20) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ስለ እኛ መጥፎ ወሬ ቢወራም ሆነ ተቃውሞ ቢያጋጥመን ሊያስደንቀን አይገባም። እንዲያውም ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት ዘልቀን በገባንና የሰይጣን ቁጣ እየተባባሰ በሄደ መጠን እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚሄድ መጠበቅ አለብን። (ራእይ 12:12) እነዚህ ነገሮች የሰይጣን ዓለም በቅርቡ እንደሚጠፋ የሚጠቁሙ በመሆናቸው ልንደሰት እንችላለን።
4. ምሥራቹን ስንሰብክ መጥፎ ምላሽ ቢያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 በደግነት መልስ ስጡ፦ መጥፎ ምላሽ ሲያጋጥመን ምንጊዜም ደግነት የሚንጸባረቅበት የለዘበ መልስ መስጠት ይኖርብናል። (ምሳሌ 15:1፤ ቆላ. 4:5, 6) ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነና የቤቱ ባለቤት ቅን ከሆነ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ የተሳሳተ ወሬ እንደሚወራ ልንገልጽለት ወይም ደግሞ እንዲህ እንዲሰማው ያደረገው ምን እንደሆነ ልንጠይቀው እንችላለን። የምንሰጠው የለዘበ ምላሽ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በሰማው ነገር ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበትና በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሲያነጋግሩት ጆሮ እንዲሰጣቸው ምክንያት ሊሆነው ይችላል። ይሁንና የቤቱ ባለቤት በጣም ከተናደደ ይቅርታ ጠይቀነው ትተነው መሄዳችን የተሻለ ይሆናል። የሰዎች አመለካከት ምንም ይሁን ምን ይሖዋ አገልግሎታችንን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳ. 52:7