ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝ ሥራ
1. በዘመናችን ምን ዓይነት መንፈሳዊ ፈውስ እየተካሄደ ነው?
1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተከናወነውን አካላዊ ፈውስ የተመለከቱ ሰዎች ልባቸው በታላቅ ደስታ ተሞልቶ ነበር። (ሉቃስ 5:24-26) እኛም በዘመናችን ሰዎች መንፈሳዊ ፈውስ ሲያገኙ ማየት ያስደስተናል። (ራእይ 22:1, 2, 17) የይሖዋ ቃልና መንፈስ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት እንደለወጡ የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ማንበብ እንዴት የሚያስደስት ነው! እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት በዚህ ሥራ መካፈል ደግሞ የበለጠ ደስታ ያስገኛል።
2. አንድን ሰው እውነትን ስናስተምር ምን ዓይነት ደስታ ልናገኝ እንችላለን?
2 የአምላክ ስም ማን ነው? አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘሮች ምን ያከናውናል? ደስታ የምናገኘው የምናስጠናው ሰው ለሚነሱበት እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ግለሰቡ እውነትን ሲማር ፊቱ ላይ የሚነበበውን ደስታ በማየት ጭምር ነው። (ምሳሌ 15:23፤ ሉቃስ 24:32) ተማሪው እድገት እያደረገ ሲሄድ የይሖዋን ስም መጠቀም ሊጀምር፣ አለባበሱንና አጋጌጡን ሊያስተካክል፣ መጥፎ ልማዶቹን ሊተውና ለሌሎች ለመመሥከር ሊነሳሳ ይችላል። እድገት በማድረግ ራሱን ወስኖ ከተጠመቀ ደግሞ ወንድማችን ብሎም የሥራ አጋራችን ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የሚወስደው ከላይ የተገለጸው እያንዳንዱ እርምጃ ለደስታችን ምክንያት ይሆናል።—1 ተሰ. 2:19, 20
3. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ምን ዓይነት ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን?
3 አንተስ የበኩልህን ድርሻ ማበርከት ትችላለህ? ከሁሉ የላቀ ደስታ በሚያስገኘው በዚህ ሥራ መካፈል የምትፈልግ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድታገኝ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው እንዲሁም ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ ጥረት አድርግ። (1 ዮሐ. 5:14) ሰዎች በሚገኙበት ጊዜና ቦታ ስበክ። አጋጣሚው ምቹ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ጋብዝ። (መክ. 11:6) ፍላጎት ያለው ሰው አግኝተህ የእውነትን ዘር ዘርተህ ከሆነ ዘሩን ለማጠጣት ተመልሰህ ሂድ።—1 ቆሮ. 3:6-9
4. ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ መጋበዛችን አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ጽድቅን የተራቡና የተጠሙ በጣም ብዙ ሰዎች በዙሪያችን ይገኛሉ። ታዲያ እነዚህን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን እንዲያረኩ ማን ሊረዳቸው ይችላል? (ማቴ. 5:3, 6) የመከሩ ጊዜ ከማለፉ በፊት የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ከፍጻሜ ለማድረስ ራሳችንን በፈቃደኝነት እናቅርብ።—ኢሳ. 6:8