ትልቅ ምሥክርነት ይሰጣል
1. በበዓሉ ላይ ከሚቀርበው ንግግር በተጨማሪ የትኞቹ ነገሮች እንግዶችን ሊማርኩ ይችላሉ? አብራራ።
1 መቼ? የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ምሽት። እስከ አሁን ድረስ ሰዎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። እንግዶችን የሚማርካቸው የሚሰሙት ነገር ብቻ አይደለም። አንዲት ሴት በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኘች በኋላ ያየችውን ነገር በተመለከተ ይኸውም የወንድሞችንና የእህቶችን ተግባቢነት እንዲሁም በፈቃደኛ ሠራተኞች የተገነባውንና በየጊዜው እድሳት የሚደረግለትን ሕንፃ ውበትና ንጽሕና በተመለከተ አስተያየት ሰጥታለች። በመሆኑም በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚህ ቀን ተናጋሪው ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ምሥክርነት ለመስጠት የበኩላችንን ድርሻ እናበርክት።—ኤፌ. 4:16
2. እያንዳንዳችን ለእንግዶች ምሥክርነት መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
2 እንግዶችን ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበሉ፦ ፈገግ ብለን ሞቅ ባለ ስሜት ለእንግዶች ሰላምታ መስጠታችን በራሱ ትልቅ ምሥክርነት ነው። (ዮሐ. 13:35) እያንዳንዱን ሰው ማነጋገር ባትችሉም እንኳ እናንተ አካባቢ ለተቀመጡት እንግዶች ሞቅ ባለ ስሜት ራሳችሁን ማስተዋወቅ ትችላላችሁ። (ዕብ. 13:1, 2) አንዳንድ ሰዎች ከተሰብሳቢዎች መካከል የሚያውቁት ሰው እንደሌለ ከተሰማችሁ የበለጠ ትኩረት ለመስጠት ጥረት አድርጉ። ምናልባት እነዚህ ሰዎች የመጡት በዘመቻው ወቅት የመጋበዣው ወረቀት ደርሷቸው ሊሆን ይችላል። “እንዲህ ዓይነት ስብሰባ ላይ ሲገኙ የመጀመሪያዎት ነው?” ብላችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። አብረዋችሁ እንዲቀመጡ ልትጋብዟቸው እንዲሁም ጥያቄዎች ካሏቸው መልስ ልትሰጧቸው ትችላላችሁ። የመሰብሰቢያ ቦታውን ሌላ ጉባኤ የሚጠቀምበት ከሆነና ጉባኤያችሁ ቶሎ አዳራሹን መልቀቅ ካለበት እንግዳውን እንዲህ ልትሉት ትችላላችሁ፦ “ፕሮግራሙን አስመልክቶ ምን እንደተሰማዎት ባውቅ ደስ ይለኛል። ሌላ ጊዜ መገናኘት እንችል ይሆን?”
3. ለቀዘቀዙ አስፋፊዎች ምን ዓይነት አቀባበል ልናደርግላቸው እንችላለን?
3 የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን በደስታ ተቀበሏቸው፦ ከጉባኤ የቀሩ ሆኖም በመታሰቢያው በዓል ላይ ብቻ የሚመጡትን ጨምሮ አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች በበዓሉ ላይ እንደሚገኙ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ያሉትን ሰዎች በደንብ ተቀበሏቸው፤ እንዲሁም በበዓሉ ላይ በመገኘታቸው ከልብ እንደተደሰታችሁ ንገሯቸው። (ሮም 15:7) ሽማግሌዎች ጊዜ ሳያጠፉ ወደ እነዚህ ግለሰቦች ቤት በመሄድ ከጉባኤው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ሊያበረታቷቸው ይችላሉ። በበዓሉ ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች በሚሰሙት ነገር ብቻ ሳይሆን በገዛ ‘ዓይናቸው በሚያዩት መልካም ሥራችን የተነሳ አምላክን ለማክበር’ እንዲነሳሱ ምኞታችን ነው።—1 ጴጥ. 2:12