“መያዝ ያለብኝ ምን ያህል ሰዓት ነው?”
ይህን ጥያቄ ጠይቀህ ታውቃለህ? የመስክ አገልግሎት ሪፖርትን የተመለከተ ጠቅለል ያለ መመሪያ የተደራጀ ሕዝብ በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 86-87 ላይ ይገኛል። በመስከረም 2008 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን የጥያቄ ሣጥን የመሳሰሉ ተጨማሪ መመሪያዎች አልፎ አልፎ ሊሰጡን ይችላሉ። በዚህ ረገድ ዝርዝር ደንቦች ያልተሰጡን እያንዳንዱ ሰው የሚያጋጥመው ሁኔታ ስለሚለያይ ነው። በመሆኑም ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች አስፋፊዎች ተጨማሪ መመሪያዎችን ማውጣታቸው ተገቢ አይሆንም።
ይሁንና ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ቢነሳና በጉዳዩ ላይ ግልጽ የሆነ የተጻፈ መመሪያ ማግኘት ባይቻል እያንዳንዱ አስፋፊ የሚከተለውን ጥያቄ ሊያስብበት ይችላል፦ ጊዜውን ያሳለፍኩት በአገልግሎት ነበር ወይስ ከስብከቱ ሥራ ጋር ግንኙነት የሌለው ሌላ ጉዳይ በማከናወን? የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን በምንሞላበት ጊዜ በቅጹ ላይ የምናሰፍረው ነገር ደስታ ሊሰጠን እንጂ የሕሊና ወቀሳ ሊያስከትልብን አይገባም። (ሥራ 23:1) እንግዲያው በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ሰዓት የመቁጠሩ ጉዳይ ሳይሆን በአገልግሎት የምንሳልፈውን ሰዓት ምን ያህል በአግባቡ እንጠቀምበታለን የሚለው ነው።—ዕብ. 6:11