የአገልግሎት መብታችሁን እንደ ውድ ሀብት አድርጋችሁ ተመልከቱት
1. በዓለም ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የስብከት ሥራችንን የሚመለከቱት እንዴት ነው?
1 በሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የስብከት ሥራችንን እንደ “ሞኝነት” ይቆጥሩታል። (1 ቆሮ. 1:18-21) እኛም ብንሆን ጥንቃቄ ካላደረግን ይህ የተዛባ አመለካከት ተስፋ እንድንቆርጥ በማድረግ ቅንዓታችንን ሊያቀዘቅዝብን ይችላል። (ምሳሌ 24:10 NW፤ ኢሳ. 5:20) የይሖዋ ምሥክር የመሆን መብታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንድንመለከተው የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?—ኢሳ. 43:10
2. አገልግሎታችን “ቅዱስ ሥራ” ተብሎ መጠራት የሚችለው ለምንድን ነው?
2 “ቅዱስ ሥራ”፦ ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎታችንን “ቅዱስ ሥራ” በማለት ጠርቶታል። (ሮም 15:15, 16) አገልግሎታችን “ቅዱስ ሥራ” የሆነው እንዴት ነው? በአገልግሎት መካፈላችን “ቅዱስ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ ጋር ‘አብረን እንድንሠራ’ የሚያስችለን ከመሆኑም ሌላ ለስሙ መቀደስ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (1 ቆሮ. 3:9፤ 1 ጴጥ. 1:15) በተጨማሪም ይሖዋ የስብከት ሥራችንን “የምስጋና መሥዋዕት” እንደሆነ አድርጎ ስለሚመለከተው አገልግሎታችን የአምልኳችን ዋነኛ ክፍል ነው።—ዕብ. 13:15
3. ምሥራቹን መስበክ ታላቅ መብት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
3 ምሥራቹን የመስበክ ሥራ ጥቂቶች ብቻ ያገኙት ታላቅ መብት ነው። ሥራው ለመላእክት ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ እነሱ በደስታ እንዲሁም ውጤታማ በሆነ መንገድ ያከናውኑት እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ጴጥ. 1:12) ሆኖም ይሖዋ ይህን ታላቅ መብት “በሸክላ ዕቃ” ለተመሰልነውና ፍጽምና ለሚጎድለን ሰዎች ሰጥቶናል።—2 ቆሮ. 4:7
4. አገልግሎታችንን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሥራ፦ አገልግሎታችንን እንደ ውድ ሀብት ስለምንመለከተው በሕይወታችን ውስጥ ‘ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች’ መካከል አንዱ እንደሆነ ይሰማናል። (ፊልጵ. 1:10) በመሆኑም በየሳምንቱ በአገልግሎት ለመካፈል ጊዜ እንመድባለን። ዓለም አቀፍ ዝናን ባተረፈ ኦርኬስትራ ውስጥ የመጫወት መብቱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት አንድ ሙዚቀኛ ለእያንዳንዱ ኮንሰርት ዝግጅት የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ችሎታውን ለማዳበር ጥረት ያደርጋል። እኛም በተመሳሳይ “የእውነትን ቃል በአግባቡ [መጠቀም]” እንድንችል አገልግሎት ከመውጣታችን በፊት ጥሩ ዝግጅት እናደርጋለን እንዲሁም ‘የማስተማር ጥበባችንን’ ለማዳበር እንጥራለን።—2 ጢሞ. 2:15፤ 4:2
5. ለአገልግሎታችን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ማን ነው?
5 ብዙ ሰዎች ለአገልግሎታችን ያላቸው አሉታዊ አመለካከት ተስፋ እንዲያስቆርጥህ አትፍቀድ። አሁንም ቢሆን በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ለሥራችን አድናቆት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ አትዘንጋ። እርግጥ ነው፣ ዋነኛው ፍላጎታችን ሰዎችን ማስደሰት ሳይሆን ይሖዋን ማስደሰት ነው። እሱ ደግሞ የምናደርገውን ትጋት የተሞላበት ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች ነን።—ኢሳ. 52:7