የጥሩ አስተማሪ መለያ ባሕርይ
1. የጥሩ አስተማሪ መለያ ባሕርይ ምንድን ነው?
1 አንድን ሰው ጥሩ አስተማሪ እንዲሆን የሚያስችለው ነገር ምንድን ነው? ዓለማዊ ትምህርት፣ ግለሰቡ ያካበተው ተሞክሮ ነው ወይስ ያለው የተፈጥሮ ችሎታ? አንድን ሰው ጥሩ አስተማሪ የሚያደርገው ፍቅር ነው። ፍቅር የሕጉ ማጠቃለያ ሲሆን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተለይተው የሚታወቁትም በዚህ ባሕርይ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ካሉት ዋና ዋና ባሕርያት መካከል ጎልቶ የሚጠቀሰውና ማራኪ የሆነው ይህ ባሕርይ ነው። (ዮሐ. 13:35፤ ገላ. 5:14፤ 1 ዮሐ. 4:8) ጥሩ አስተማሪዎች ፍቅርን ያንጸባርቃሉ።
2. ለሰዎች ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ሰዎችን ውደዱ፦ ታላቅ አስተማሪ የሆነው ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር አሳይቷል፤ እንዲህ ማድረጉ ሰዎች እንዲያዳምጡት አነሳስቷቸዋል። (ሉቃስ 5:12, 13፤ ዮሐ. 13:1፤ 15:13) ለሰዎች የምናስብ ከሆነ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንመሠክራለን። ስደትም ሆነ የሰዎች ግድየለሽነት ከመስበክ ወደኋላ እንድንል አያደርገንም። ለምንሰብክላቸው ሰዎች ከልብ የመነጨ አሳቢነት የምናሳይ ከመሆኑም ሌላ ሁኔታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት አቀራረባችንን እንቀያይራለን። እያንዳንዱን ጥናት ለመምራት ብቻ ሳይሆን ከእያንዳንዱ ጥናት በፊት ለመዘጋጀትም ጊዜ እንመድባለን።
3. ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለን ፍቅር ለአገልግሎታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
3 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ውደዱ፦ ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ይወድ የነበረ ሲሆን እነዚህን እውነቶች እንደከበረ ሀብት ይመለከታቸው ነበር። (ማቴ. 13:52) እውነትን የምንወድ ከሆነ ከልብ በመነጨ ስሜት ስለምንናገር ሰዎች በጉጉት ያዳምጡናል። የዚህ ዓይነቱ ፍቅር ድክመቶቻችን ላይ ከማተኮር ይልቅ ለሰዎች በምንሰብከው ውድ የሆነ መልእክት ላይ እንድናተኩር ያደርገናል፤ ይህ ደግሞ በአገልግሎት ላይ ስንሆን የሚሰማንን ፍርሃት ይቀንስልናል።
4. ፍቅርን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
4 ፍቅርን አዳብሩ፦ ለሰዎች ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋና ልጁ ባሳዩን ፍቅር ላይ በማሰላሰል እንዲሁም በክልላችን ያሉ ሰዎች አሳዛኝ በሆነ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በማሰብ ነው። (ማር. 6:34፤ 1 ዮሐ. 4:10, 11) አዘውትረን የግል ጥናት ማድረጋችንና ማሰላሰላችን ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለን ፍቅር እንዲያድግ ይረዳናል። ፍቅር ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው። (ገላ. 5:22) በመሆኑም ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን እንዲሁም ፍቅርን ማዳበር እንድንችል እንዲረዳን መለመን እንችላለን። (ሉቃስ 11:13፤ 1 ዮሐ. 5:14) ስለዚህ የትምህርት ደረጃችን፣ በእውነት ቤት ያሳለፍነው ተሞክሮ እንዲሁም የተፈጥሮ ችሎታችን ምንም ይሁን ምን ፍቅርን በማንጸባረቅ ውጤታማ አስተማሪዎች መሆን እንችላለን።