የአደባባይ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አዳዲስ ዘዴዎች
1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ምን ምሳሌ ትተዋል?
1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ከቤት ወደ ቤት በመስበክ ብቻ አልተወሰኑም። በአደባባይም ሰብከዋል። (ሥራ 20:20) ለምሳሌ ያህል፣ ወደ ቤተ መቅደስ በመሄድ አገልግለዋል፤ ምክንያቱም በዚህ ቦታ ብዙ ሰዎች እንደሚገኙ ያውቃሉ። (ሥራ 5:42) ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና በነበረበት ወቅት በገበያ ሥፍራ ለሚያገኛቸው ሰዎች በየቀኑ ይሰብክ ነበር። (ሥራ 17:17) ዛሬም ቢሆን ምሥራቹን የምናሰራጭበት ዋነኛው መንገድ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ነው። ይሁን እንጂ በመኪና ማቆሚያዎች፣ በንግድ አካባቢዎች፣ በመናፈሻዎች፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው መንገዶች ላይና ሰዎች ሊገኙባቸው በሚችሉ ሌሎች ቦታዎችም እንሰብካለን። ሁሉም አስፋፊዎች የአደባባይ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ እንዲካፈሉ የሚበረታቱ ቢሆንም የተወሰኑ አስፋፊዎች የአደባባይ ምሥክርነት መስጠት የሚችሉበት አጓጊ የሆኑ ሁለት አዳዲስ ዘዴዎችን የመጠቀም አጋጣሚ ተከፍተውላቸዋል።
2. ኅዳር 2011 ለሙከራ ያህል ሥራ ላይ መዋል የጀመረው ዘዴ የትኛው ነው?
2 ሕዝብ በሚበዛባቸው ትላልቅ ከተሞች የሚሰጥ ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት፦ በ2013 የዓመት መጽሐፍ ገጽ 16 እና 17 ላይ እንደተገለጸው የአደባባይ ምሥክርነት የሚሰጥበት አዲስ ዘዴ ለሙከራ ያህል ኅዳር 2011 ላይ በኒውዮርክ ሲቲ ሥራ ላይ ውሏል። በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን በሚያምር ሁኔታ በተዘጋጁ ጠረጴዛዎችና ጋሪዎች ላይ በመደርደር ከፍተኛ የእግረኛ ፍሰት ባለባቸው መተላለፊያዎች ላይ አመቺ በሆኑ ቦታዎች ተቀምጠው ነበር። ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩትንና ብዙውን ጊዜ ቤታቸው የማይገኙትን ጨምሮ በየቀኑ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በዚያ አካባቢ ያልፋሉ። የተገኘው ውጤት በጣም የሚያስገርም ነው። በቅርቡ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ 3,797 መጽሔቶች እና 7,986 መጻሕፍት ተበርክተዋል። በዚያ የሚያልፉ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ዋነኛው ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር በመሆኑ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የሰጧቸውን አድራሻዎች ወዲያውኑ ወደሚመለከታቸው ጉባኤዎች በመላክ ጉባኤዎቹ ተከታትለው እንዲረዷቸው ተደርጓል።
3. አዲሱ ዘዴ በሌሎች አካባቢዎችም እየተስፋፋ ያለው እንዴት ነው?
3 ይህ ዘዴ ውጤት በማስገኘቱ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሰው የሚበዛባቸው ሌሎች ትላልቅ ከተሞችም ሥራ ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው። ይህ ዘዴ በየትኞቹ ከተሞች ቢሠራበት ጥሩ እንደሆነ የሚወስነው በዚያ አገር ያለው ቅርንጫፍ ቢሮ ነው። ብዙውን ጊዜ ለዚህ ዓላማ የሚመረጡት ከተሞች የትራንስፖርት ጣቢያዎች ወይም በርካታ መሥሪያ ቤቶች አሊያም የመኖሪያ ሕንፃዎች በመኖራቸው ምክንያት ከፍተኛ የእግረኛ ፍሰት ያለባቸው ናቸው። ከተሞቹ ከተለዩ በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው ከጉባኤዎች ጋር በመነጋገር በዚህ ሥራ የሚካፈሉ አስፋፊዎችን ይመርጣል፤ እንዲሁም ተጨማሪ መመሪያዎችን ይሰጣል። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ሥራ ላይ የሚካፈሉት ልዩ አቅኚዎችና የዘወትር አቅኚዎች ሲሆኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ረዳት አቅኚዎችም ሊመደቡ ይችላል።
4. ሰው በሚበዛባቸው ትላልቅ ከተሞች የሚሰጠው ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት የሚካሄደው እንዴት ነው?
4 ምሥክርነቱ የሚሰጠው እንዴት ነው? ሰው በሚበዛባቸው ትላልቅ ከተሞች በሚሰጠው ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት የሚካፈሉ አስፋፊዎች በአብዛኛው አንድ ሰው እነሱ ወዳሉበት ጠረጴዛ ወይም ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያ መጥቶ እስኪያናግራቸው ይጠብቃሉ። ከዚያም ሰው ሲመጣ የሚፈልገውን ጽሑፍ መርጦ እንዲወስድ ይጋብዙታል። ግለሰቡ ማንኛውም ጥያቄ ካለው አቅኚዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው በደስታ መልስ ይሰጡታል። ሰውየው ጽሑፍ መውሰድ ከፈለገ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚቻልበት ዝግጅት እንዳለ አይናገሩም። ግለሰቡ ራሱ ሥራው የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ ከጠየቀ ግን በጽሑፉ ላይ ባለው አድራሻ ተጠቅሞ አስተዋጽኦ መላክ እንደሚቻል ሊገልጹለት ይችላሉ። ሁኔታው አመቺ ከሆነ ደግሞ “አንድ ሰው ቤትዎ መጥቶ እንዲያነጋግርዎት ይፈልጋሉ?” ወይም “እነዚህን ጽሑፎች ከማሰራጨት በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንደምናስተምር ያውቃሉ?” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ።
5. አንድ ባልና ሚስት በዚህ አዲስ ዘዴ መካፈል የሚክስ ሆኖ ያገኙት እንዴት ነው?
5 በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል በጣም የሚክስ ነው። አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ጠረጴዛው አጠገብ ቆመን በየቀኑ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲተላለፉ ማየታችን በዓለም ዙሪያ ላሉ ሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ እየተደረገ ያለውን መጠነ ሰፊ ሥራ ከልብ እንድናደንቅ አድርጎናል። እነዚህን ሰዎች መመልከታችን እንዲሁም ይሖዋ ለእያንዳንዱ ሰው ምን ያህል እንደሚያስብ ማሰላሰላችን በሕይወታችን ውስጥ ምንጊዜም ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ ለመስጠት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ አጠናክሮልናል። ይሖዋ በጽሑፍ መደርደሪያው አጠገብ የሚያልፈውን የእያንዳንዱን ሰው ልብ በመመርመር የሚገባውን ሰው እየፈለገ እንደሆነ ይሰማናል። የሥራ ባልደረቦቻችን ከሆኑት ከመላእክት ጋር በጣም ተቀራርበን እየሠራን እንደሆነ እንደ አሁኑ ተሰምቶን አያውቅም።”
6. (ሀ) ብዙ ጉባኤዎች የአደባባይ ምሥክርነት ለመስጠት እየተጠቀሙበት ያለው ሌላ ዘዴ ምንድን ነው? ይህ ዘዴ በትላልቅ ከተሞች ከሚሰጠው ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት የሚለየውስ እንዴት ነው? (ለ) የአደባባይ ምሥክርነት በሚሰጥበት ጊዜ ጉባኤዎች እርስ በርስ መተባበር የሚችሉት እንዴት ነው?
6 በጉባኤ ደረጃ የሚዘጋጅ የአደባባይ ምሥክርነት፦ በትላልቅ ከተሞች ከሚሰጠው ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት በተጨማሪ በርካታ የሽማግሌዎች አካላት በክልላቸው ውስጥ ሌላ ዓይነት አዲስ ዘዴ ማደራጀት ጀምረዋል። ይህ አዲስ ዘዴ አስፋፊዎች በጉባኤያቸው ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰው የሚበዛባቸው ቦታዎች ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያዎችን በመጠቀም መስበክ የሚችሉበት ዝግጅት ነው። ይህ ዝግጅት በትላልቅ ከተሞች ከሚሰጠው ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት የተለየ ነው፤ ምክንያቱም ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት በሚሰጥበት ወቅት ከተለያዩ ጉባኤዎች የመጡ ተሳታፊዎች ቅርንጫፍ ቢሮው በመረጣቸው ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ሰው የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ በተመሳሳይ ቦታ ማገልገል ይችላሉ።—“ጥሩ ትብብር አስፈላጊ ነው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
7. የአደባባይ ምሥክርነት ለመስጠት አመቺ የሆኑ ቦታዎች የትኞቹ ናቸው? ሽማግሌዎች ይህን ሥራ ማደራጀት የሚችሉትስ እንዴት ነው?
7 ሽማግሌዎች በጉባኤው ክልል ውስጥ ከፍተኛ የእግረኛ ፍሰት ያለባቸው ቦታዎች መኖር አለመኖራቸውን ያጣራሉ፤ ከዚያም በእነዚህ ቦታዎች የአደባባይ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉ የሚያዋጣ መሆኑን ይወስናሉ። ጠረጴዛ ወይም ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያ ተጠቅሞ ለመመሥከር አመቺ ከሆኑት ቦታዎች መካከል ትራንስፖርት የሚያዝባቸው ቦታዎች፣ አደባባዮች፣ መናፈሻዎች፣ ሰው የሚበዛባቸው መንገዶች፣ የገበያ ማዕከሎች፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮችና ትላልቅ ሕንፃዎች ይገኙበታል። የጽሑፍ መደርደሪያ ጠረጴዛውን በተመሳሳይ ቀናት፣ በተመሳሳይ ሰዓትና በተመሳሳይ ቦታ ማስቀመጡ ጥቅም አለው። በአንዳንድ ቦታዎች ለምሳሌ ሰው በሚበዛባቸው የእግረኛ መንገዶች ላይ አነስ ያሉ ተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያዎችን መጠቀሙ ይበልጥ አመቺ ሊሆን ይችላል። ሽማግሌዎች የመጠበቂያ ግንብና የንቁ! መጽሔትን ጨምሮ የሌሎች ጽሑፎችን ፖስተሮች ለማተም የሚረዱ ፋይሎችን ከድረ ገጻችን ላይ ማውረድ ይችላሉ። በዚህ ሥራ የሚካፈሉ አቅኚዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በትላልቅ ከተሞች በሚሰጠው ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት ከሚካፈሉት ወንድሞች ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ሲሆን የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ የሚሰጣቸውን መመሪያ በጥንቃቄ መከተልም ይኖርባቸዋል። ከክልላቸው ውጪ የሆነ ፍላጎት ያለው ሰው አድራሻውን ከሰጣቸው እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለውን ቅጽ ወዲያውኑ ሞልተው ለጸሐፊው መስጠት ይኖርባቸዋል።
8. በክልላችሁ ውስጥ የአደባባይ ምሥክርነት ለመስጠት በጉባኤ ደረጃ የተደረገ ዝግጅት ከሌለ በአደባባይ ለመስበክ በየትኞቹ አጋጣሚዎች መጠቀም ይቻላል?
8 የአደባባይ ምሥክርነትን በመደበኛ አገልግሎታችን ውስጥ ማካተት የምንችልበት አጋጣሚ፦ አንዳንድ ጉባኤዎች በክልላቸው ውስጥ በጠረጴዛ ወይም በተንቀሳቃሽ የጽሑፍ መደርደሪያ ተጠቅሞ የአደባባይ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ ሰው የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይኖራቸው ይችላል። ያም ቢሆን እንዲህ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች የአደባባይ ምሥክርነትን በመደበኛው አገልግሎታቸው ውስጥ ማካተት ይችሉ እንደሆነ እንዲያስቡበት እናበረታታቸዋለን። በክልላችሁ ውስጥ የገበያ ቦታዎች አሉ? ወይም ደግሞ መናፈሻዎችና ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች አሉ? በክልላችሁ ውስጥ በየተወሰነ ጊዜ የሚካሄዱ ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ዝግጅቶችስ አሉ? ከሆነ እናንተም በእነዚህ አጋጣሚዎች ተጠቅማችሁ የአደባባይ ምሥክርነት መስጠት ትችላላችሁ።
9. ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ለመስበክ ንቁዎች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
9 የይሖዋ “ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:4) በመሆኑም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙ የተቻለንን ያህል ጥረት እናደርጋለን። (ማቴ. 24:14) በብዙ አካባቢዎች ሰዎችን ቤታቸው ሄዶ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ይሁንና ከቤታቸው ውጪ አደባባይ ላይ ስናገኛቸው ከእነሱ ጋር መነጋገር እንችል ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ምሥራቹን ሊሰሙ የሚችሉበት ብቸኛው አጋጣሚ በአደባባይ በሚሰጠው ምሥክርነት ወቅት ሊሆን ይችላል። እንግዲያው ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ በመስበክ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ እንፈጽም።—2 ጢሞ. 4:5
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝሣጥን]
ጥሩ ትብብር አስፈላጊ ነው
በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች፣ በአንድ መንገድ ላይ ወይም በአንድ የመኪና ማቆሚያ፣ በአንድ የንግድ አካባቢ ወይም በአንድ የትራንስፖርት መያዣ ቦታ ላይ ሆነው የአደባባይ ምሥክርነት የሚሰጡበት ጊዜ እንዳለ ተስተውሏል። ከተለያዩ ጉባኤዎች የመጡ አስፋፊዎች በተመሳሳይ የእንግዳ ማቆያ ወይም የሕዝብ ልብስ ማጠቢያ ቦታዎች መጽሔቶችን ያስቀምጣሉ፤ እንዲሁም በአንድ የንግድ አካባቢ ይሰብካሉ። ይህም በንግድ ሥራ የተሰማሩትም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሰላቹ አልፎ ተርፎም እንዲበሳጩ ሊያደርግ ይችላል፤ አስፋፊዎቹ የሚያገለግሉበት ሰዓት የተለያየ ቢሆንም እንኳ ሰዎቹ እንዲህ ሊሰማቸው ይችላል። በመሆኑም አንድ አስፋፊ የአደባባይ ምሥክርነት በሚሰጥበት ጊዜ ለጉባኤው በተመደበው ክልል ውስጥ ብቻ ማገልገሉ በአብዛኛው የተሻለ ነው።
አስፋፊዎች በጎረቤት ጉባኤ ክልል ውስጥ የአደባባይ ምሥክርነት መስጠት በሚፈልጉበት ጊዜ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቻቸውን ማነጋገር አለባቸው። እሱም ከሌላኛው ጉባኤ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች ጋር ተነጋግሮ ፈቃድ ካገኘ በኋላ አስፋፊዎቹ ማገልገል ይችላሉ። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚመሩ ጉባኤዎች በተመሳሳይ አካባቢ እንዲያገለግሉ ከተመደቡ ግን በተቻለ መጠን የአካባቢውን ሰዎች ላለማስቆጣት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾቹ እርስ በርስ ተገናኝተው መነጋገር ይገባቸዋል። ጥሩ ትብብር ካለ “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት” ይካሄዳል።—1 ቆሮ. 14:40