የአገልግሎት ጓደኛችሁን አበረታቱ
1. ከሌሎች ጋር አብረን ስናገለግል ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረው ዓይነት አመለካከት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ አድርጎ ይመለከተው ነበር። (ሮም 1:12) ከሌሎች ጋር በምታገለግሉበት ጊዜ አጋጣሚውን እነሱን ለማበረታታትና ለመርዳት ትጠቀሙበታላችሁ? ውጤታማ አስፋፊ እንድትሆኑ የረዳችሁ ምን እንደሆነ ለምን አትነግሯቸውም?
2. የአገልግሎት ጓደኛችንን ለማደፋፈር ምን ማድረግ እንችላለን? እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
2 አደፋፍሯቸው፦ አንዳንድ አስፋፊዎች በራሳቸው የመተማመን ስሜት የሚጎድላቸው ሲሆን ይህም ፊታቸው ላይ በሚነበበው ስሜት ወይም በድምፅ ቃናቸው ሊገለጽ ይችላል። እነዚህን አስፋፊዎች ለሚያደርጉት ጥረት ከልብ በማመስገን በራስ የመተማመን ስሜታቸው እንዲጨምር ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ማድረግ የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው? አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አብረውት ለሚያገለግሉት ወንድሞች እንደሚፈራና ይህን ስሜቱን ለማሸነፍ ደጋግሞ ወደ ይሖዋ እንደሚጸልይ በግልጽ ይናገራል። ሌላ ወንድም ደግሞ ድፍረት እንዲያገኝ የረዳው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ለማድረግ የሚረዳን ቀዳሚው ነገር ፈገግታ ማሳየት ነው። ሆኖም ይህን ቀላል ነገር ለማድረግ እንኳ መጸለይ የሚያስፈልገኝ ጊዜ አለ።” እናንተስ በድፍረት ማገልገል እንድትችሉ የረዳችሁ ነገር ይኖራል? ከሆነ ለአገልግሎት ጓደኛችሁ አጫውቱት።
3. የአገልግሎት ጓደኛችን በአገልግሎት ውጤታማ እንዲሆን ሊረዱት የሚችሉ ምን ነገሮችን ልንነግረው እንችላለን?
3 ስለምትጠቀሙበት የስብከት ዘዴ ንገሯቸው፦ ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመር ውጤታማ ሆኖ ያገኛችሁት ቀለል ያለ የመግቢያ ሐሳብ ወይም ጥያቄ አሊያም ደግሞ በአካባቢያችሁ የተፈጸመ ክንውን ይኖር ይሆን? አንድን የአቀራረብ ናሙና ትንሽ ለወጥ አድርጋችሁ በማቅረብ ጥሩ ውጤት ማግኘት ችላችኋል? ከሆነ ለአገልግሎት ጓደኛችሁ ንገሩት። (ምሳሌ 27:17) ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ እየሄዳችሁ ከሆነ ዓላማችሁ ምን እንደሆነና ዓላማችሁን ዳር ለማድረስ ምን ዘዴዎችን እንደምትጠቀሙ ልታጫውቱት ትችላላችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመሩ የተማሪያችሁን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አንድ ነጥብ አንስታችሁ ወይም አንድ ጥቅስ አብራርታችሁ አሊያም ደግሞ አንድ ዓይነት የማስተማሪያ ዘዴ ተጠቅማችሁ ከነበረ ይህን ያደረጋችሁበትን ምክንያት ከጥናቱ በኋላ ለአገልግሎት ጓደኛችሁ ንገሩት።
4. የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ወንጌላውያን አማኝ ያልሆኑትን ሰዎች በመርዳት ላይ ብቻ የተወሰኑ አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ አንዳቸው ሌላውን ለማበረታታትና ለማጠናከር ትኩረት ይሰጡ ነበር። (ሥራ 11:23፤ 15:32) ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱ ጢሞቴዎስን ያሠለጠነው ሲሆን ያወቀውንም ነገር ለሌሎች እንዲናገር አበረታቶታል። (2 ጢሞ. 2:2) በአገልግሎት ላይ በምንሠማራበት ጊዜ ለክርስቲያን ባልንጀሮቻችን መልካም የምናደርግ ከሆነ ደስታቸው እንዲጨምርና ውጤታማ ሰባኪዎች እንዲሆኑ የምንረዳቸው ከመሆኑም በላይ የሰማዩ አባታችንን ልብ ደስ እናሰኛለን።—ዕብ. 13:15, 16