የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 4/14 ገጽ 5
  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2014
የመንግሥት አገልግሎታችን—2014
km 4/14 ገጽ 5

ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ

ውድ የጌታ አገልጋዮች

ታሪካዊ በሆነው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ይህን ደብዳቤ ስንጽፍላችሁ እጅግ ደስ ይለናል! የምንወደው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጠላቶቹ መካከል መግዛት ከጀመረ በ2014 ማብቂያ ላይ ድፍን መቶ ዓመት ይሆነዋል።—መዝ. 110:1, 2

ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ በዚህ የአገልግሎት ዓመት መጀመሪያ ባካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ፣ የአዲስ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ እስከ ዛሬ ከተተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱሶች ሁሉ በጥራቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተሻሽሎ መውጣቱን አስታውቆ ነበር። ይሖዋ፣ የመጀመሪያው አዲስ ዓለም ትርጉም እንዲዘጋጅ ያደረገው በመንፈስ የተቀቡ ልጆቹን ተጠቅሞ ነው። (ሮም 8:15, 16) ይህ በራሱ ትርጉሙን ልዩ ያደርገዋል፤ በዚህ አትስማሙም?

የበላይ አካል የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ ላለፉት በርካታ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎሙ ሥራ ቅድሚያ ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዛሬው ጊዜ አዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል በ121 ቋንቋዎች ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችሁ በመኖሩ ያላችሁን ጥልቅ አድናቆት ለይሖዋ እንድታሳዩ እናበረታታችኋለን። በየቀኑ አንብቡት፤ እንዲሁም አሰላስሉበት። እንዲህ ማድረጋችሁ የዚህ መጽሐፍ ባለቤት ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንድትቀርቡ ይረዳችኋል።—ያዕ. 4:8

ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እየደረሰባቸው ያለውን መከራ ስንሰማ በጣም እናዝናለን። እነዚህ ወንድሞቻችን አንዳንድ ጊዜ ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር መደሰት ከባድ ቢሆንባቸው የሚገርም አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በእስያ የሚገኝ አንድ ቤተሰብ እናትየዋ በድንገት ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆነች፤ በዚህ ጊዜ የቤተሰቡ ሕይወት ተመሰቃቀለ። የጤና ባለሙያዎች ሁኔታው ግራ ያጋባቸው ከመሆኑም በላይ ጤንነቷ እንዲስተካከል ማድረግ አልቻሉም። እንዴት የሚያሳዝን ነው! በአሁኑ ጊዜ ባለቤቷ ቀኑን ሙሉ ከአጠገቧ ሳይለይ እሷን በመንከባከብ ላይ ይገኛል። ወንዱ ልጃቸውና ሁለቱ ሴቶች ልጆቻቸው ለወላጆቻቸው ፍቅራዊ ድጋፍ በማድረግ ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ሆነዋል። ይህን ቤተሰብ ጨምሮ የሚደርሱባችሁን የተለያዩ መከራዎች ተቋቁማችሁ እየኖራችሁ ያላችሁ ሁሉ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም የሚገኘውን ደስታ ማጣጣም ትችላላችሁ። (ያዕ. 1:2-4) ይሖዋ፣ ቅቡዓን ቀሪዎችም ሆንን ሌሎች በጎች ፈተናዎችን ተቋቁመን በጽናት የምንቀጥል ከሆነ ደስታ እንደምናገኝ ማረጋገጫ ሰጥቶናል፤ ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል።—ያዕ. 1:12

ባለፈው ዓመት በመታሰቢያው በዓል ላይ 19,241,252 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተዋል። በዓመት ውስጥ ከምናደርጋቸው ስብሰባዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚህ ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በመገኘት ይሖዋንና ኢየሱስን ሲያከብሩ መመልከት የሚያበረታታ ነው! በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ረዳት አቅኚ ሆነው በማገልገላቸው በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ለይሖዋ የሚቀርበው የውዳሴ ድምፅ ከፍ ብሎ እንዲሰማ አድርገዋል። ይህ በጣም የሚደነቅ መንፈስ ነው! በወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ወቅት ረዳት አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች፣ ጉብኝቱ የሚውለው በመጋቢትና በሚያዝያ ወር ላይ ባይሆንም እንኳ በአቅኚዎች ስብሰባ ላይ ሙሉውን መካፈል እንደሚችሉ ስታውቁ አልተደሰታችሁም? መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች፣ በስብከቱ ሥራና በጉባኤ እንቅስቃሴዎች መጠመድ ያለውን ጥቅም ይረዳሉ። በሥራ መጠመዳችን ሰይጣን እምነታችንን ለማዳከምና ከመንገዳችን ለማሳት የሚያደርገውን ጥረት በማክሸፍ ሳንነቃነቅ ጸንተን እንድንቆም ይረዳናል።—1 ቆሮ. 15:58

ባለፈው የአገልግሎት ዓመት 277,344 የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት በማሳየት በዓለም ዙሪያ ካሉ ወንድሞቻቸው ጋር በሕይወት መንገድ ላይ እየተጓዙ መሆናቸው እንዴት የሚያበረታታ ነው! (ማቴ. 7:13, 14) እነዚህ አዲሶች ‘በእምነት ጸንተው መኖራቸውን እንዲቀጥሉ’ የእኛ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። (ቆላ. 2:7) እስከ መጨረሻው መጽናት እንድንችል እርስ በርስ መበረታታችንን እንቀጥል። (ማቴ. 24:13) “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።” (1 ተሰ. 5:14) እንዲሁም ሁላችንም “መንግሥትህ ይምጣ” እያልን ‘ያለማቋረጥ እንጸልይ።’—1 ተሰ. 5:17፤ ማቴ. 6:10

ወንድሞቻችሁ

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ