የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አዲስ ቪዲዮ
በjw.org/am ላይ የወጣው መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የሚል ርዕስ ያለው አጭር ቪዲዮ ብዙ ተመልካቾችን እያገኘ ነው። ይህ ቪዲዮ የተዘጋጀው ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ለማነሳሳት ነው። ቪዲዮውን ለማግኘት በመነሻ ገጹ ግርጌ ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚቻልበት ዝግጅት” የሚለውን ሊንክ ጠቅ ማድረግ ይቻላል፤ ወይም ደግሞ በአዲሶቹ ትራክቶች የጀርባ ገጽ ላይ ያለውን QR (ክዊክ ሪስፖንስ) ኮድ አስነብቡ። ይህን ቪዲዮ በጥሩ ሁኔታ መጠቀም የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርጉ ለምታነጋግሩት ሰው እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ “መጽሐፍ ቅዱስን አስመልክቶ ለሚፈጠሩብህ ጥያቄዎች እንዴት መልስ ማግኘት እንደምትችል የሚጠቁም አንድ አጭር ቪዲዮ ላሳይህ?” ግለሰቡ ፈቃደኛ ከሆነ ቪዲዮውን በሞባይል ስልካችሁ ወይም በያዛችሁት ሌላ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ አሊያም በራሱ ኮምፒውተር ላይ ልታሳዩት ትችላላችሁ።
መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ወይም የአደባባይ ምሥክርነት ስንሰጥ ከአዲሶቹ ትራክቶች አንዱን ካበረከትን፣ ግለሰቡ QR ኮዱን በሞባይል ስልኩ ወይም ሌላ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ አማካኝነት እንዲያስነብብ ልናበረታታው እንችላለን። በብዙ ቋንቋዎች QR ኮዱ ቪዲዮው ወዳለበት የድረ ገጹ ክፍል በቀጥታ ስለሚወስድ እዚያው በቆማችሁበት ቪዲዮውን በሞባይል ስልካችሁ ወይም በያዛችሁት ሌላ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ማጫወት ትችላላችሁ።
ለሥራ ባልደረቦቻችሁ፣ አብረዋችሁ ለሚማሩ ልጆች፣ ለዘመዶቻችሁ ወይም ለምታውቋቸው ሌሎች ሰዎች ስለ ቪዲዮው ንገሯቸው፤ ፈቃደኛ ከሆኑም አሳዩአቸው። ወይም ደግሞ ቪዲዮውን ራሳቸው እንዲመለከቱት የቪዲዮውን ሊንክ በኢ-ሜይል ላኩላቸው።
ይህን አዲስ ዝግጅት የምንጠቀምበት ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ልናገኝ ብሎም “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን በመንፈሳዊ ልንረዳቸው እንችላለን።—ሥራ 13:48