የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት
1. ጥናት ያላቸው አስፋፊዎች ምን ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል?
ይሖዋ “ካልሳበው” በስተቀር አምላክን ማገልገል የሚችል የለም። (ዮሐ. 6:44) ያም ሆኖ አስፋፊዎች፣ ጥናቶቻቸው በሰማይ ወደሚኖረው አባታቸው መቅረብ እንዲችሉ የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። (ያዕ. 4:8) ይህ ደግሞ ጥሩ ዝግጅት ይጠይቃል። አንቀጾቹን አንብቦ በጽሑፉ ላይ የሚገኘውን ጥያቄ መጠየቅ ብቻውን ጥናቶቻችን መልእክቱን ተረድተው እድገት እንዲያደርጉ አያስችልም።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመምራት ምን ነገር ማሳካት ይኖርብናል?
2 አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት ከፈለጉ ጥናቶቻቸው (1) የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲረዱ፣ (2) የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት እንዲቀበሉና (3) የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይገባል። (ዮሐ. 3:16፤ 17:3፤ ያዕ. 2:26) አንድ ሰው እነዚህን እርምጃዎች እንዲወስድ ለመርዳት ብዙ ወራት ሊፈጅ ይችላል። ያም ሆኖ እያንዳንዱ እርምጃ፣ ግለሰቡ ከይሖዋ ጋር ዝምድና እንዲመሠርትና ራሱን ለእሱ እንዲወስን በመርዳት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
3. ውጤታማ አስተማሪዎች የአመለካከት ጥያቄ የሚጠቀሙት ለምንድን ነው?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ምን ያስባል? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን የሚማረውን ነገር ተረድቶትና ተቀብሎት እንደሆነ ለማወቅ እንድትችሉ ብዙ አታውሩ፤ ከዚህ ይልቅ ግለሰቡ የውስጡን እንዲናገር አበረታቱት። (ያዕ. 1:19) የምትወያዩበትን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን እንደሆነ ተረድቷል? ትምህርቱን በራሱ አባባል መግለጽ ይችላል? ስለሚማረው ነገር ምን ይሰማዋል? መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት ምክንያታዊ እንደሆነ ያምናል? (1 ተሰ. 2:13) እየተማረ ካለው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወቱን መምራት እንዳለበት ገብቶታል? (ቆላ. 3:10) እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የአመለካከት ጥያቄዎችን በዘዴ መጠየቅ እንዲሁም ግለሰቡ የሚሰጠንን መልስ ማዳመጥ አለብን።—ማቴ. 16:13-16
4. ጥናታችን ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚማረውን ነገር መቀበል አሊያም ተግባራዊ ማድረግ ቢከብደው ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 ብዙውን ጊዜ የሰዎችን ልማድና አስተሳሰብ መቀየር በጣም ከባድ በመሆኑ ይህን ማድረግ ጊዜ ይወስዳል። (2 ቆሮ. 10:5) ታዲያ ጥናታችን የሚማረውን ነገር መቀበል አሊያም ተግባራዊ ማድረግ ቢከብደውስ? የአምላክ ቃልና መንፈስ ቅዱስ በግለሰቡ ልብ ውስጥ እንዲሠሩ የሚያስችል በቂ ጊዜ ለመስጠት ትዕግሥተኞች መሆን አለብን። (1 ቆሮ. 3:6, 7፤ ዕብ. 4:12) ተማሪው አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መረዳት ወይም ተግባራዊ ማድረግ ሲከብደው ጫና ከማድረግ ይልቅ ወደ ሌላ ርዕስ ማለፋችን የተሻለ ነው። በትዕግሥትና በፍቅር መጽሐፍ ቅዱስን ለእሱ ማስተማራችንን የምንቀጥል ከሆነ በጊዜ ሂደት አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ሊነሳሳ ይችላል።