የመስክ አገልግሎት ጎላ ያሉ ገጽታዎች
በሚያዝያ 3, 2015 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ በኢትዮጵያ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ቁጥር 25,323 መሆኑን ስናሳውቃችሁ ደስ ይለናል። የመጋበዣ ወረቀቱ በጣም ርቀው በሚገኙ ገጠራማ መንደሮች ሳይቀር ተሰራጭቶ ነበር፤ በመታሰቢያ በዓሉ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ሰዎች መገኘታቸው በጣም የሚያስደስት ነው። ጌዶ በተባለች ከተማ ሁለት ልዩ አቅኚዎች ብቻቸውን ባደረጉት ጥረት 307 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል! በተመሳሳይም በአገረ ሰላም ሁለት ልዩ አቅኚዎች ባካሄዱት ዘመቻ 200 ተሰብሳቢዎች በበዓሉ ላይ ሊገኙ ችለዋል። በስተ ደቡብ በኦሞ አካባቢ በምትገኘው በማጂ ከተማ ደግሞ የመታሰቢያው በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረ ሲሆን 50 ሰዎች ተገኝተዋል። ከዚህም ሌላ 30 አስፋፊዎች ባሉት አንድ ጉባኤ በመታሰቢያው በዓል ላይ 327 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። ይህ ሁሉ ወደፊት ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚኖር የሚጠቁም ነው! እነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች “ከጌታ ጋር በተያያዘ” ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ ያሳያሉ።—1 ቆሮ. 15:58