ክርስቲያናዊ ሕይወት
ባለትዳሮች ትዳራቸውን ማጠናከር የሚችሉት እንዴት ነው?
አብርሃምና ሣራ እርስ በርስ በመዋደድና በመከባበር ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ባልና ሚስት ናቸው። (ዘፍ 12:11-13፤ 1ጴጥ 3:6) እንዲህ ሲባል ግን ትዳራቸው ፍጹም ነበር ማለት አይደለም፤ በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ባለትዳሮች የአብርሃምንና የሣራን ታሪክ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?
እርስ በርስ ተነጋገሩ። የትዳር ጓደኛችሁ ተማርሮ ወይም ተበሳጭቶ በሚናገርበት ጊዜ አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ በትሕትና ምላሽ ለመስጠት ጥረት አድርጉ። (ዘፍ 16:5, 6) አብራችሁ ጊዜ የምታሳልፉበት ፕሮግራም ይኑራችሁ። ለትዳር ጓደኛችሁ ያላችሁን ፍቅር በንግግራችሁም ሆነ በድርጊታችሁ ግለጹ። ከሁሉ በላይ ደግሞ አብራችሁ በማጥናት፣ በመጸለይና በአምልኮ እንቅስቃሴዎች በመካፈል ይሖዋ በትዳራችሁ ውስጥ እንዲኖር አድርጉ። (መክ 4:12) ጠንካራ ትዳር፣ የዚህ ቅዱስ ዝግጅት መሥራች የሆነውን ይሖዋን ያስከብራል።
የትዳርን ጥምረት ማጠናከር የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከቱ፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሩ፦
በቪዲዮው ላይ፣ ሻን እና ኪያራ እየተራራቁ እንዳሉ የሚጠቁሙ ምን ምልክቶችን አስተውላችኋል?
በትዳር ውስጥ በሐቀኝነትና በግልጽነት መነጋገር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የአብርሃምና የሣራ ምሳሌ ሻን እና ኪያራን የጠቀማቸው እንዴት ነው?
ሻን እና ኪያራ ትዳራቸውን ለማጠናከር ምን እርምጃዎች ወስደዋል?
ባለትዳሮች በትዳራቸው ውስጥ ፍጽምናን መጠበቅ የሌለባቸው ለምንድን ነው?
ትዳራችሁን ማጠናከር ትችላላችሁ!