የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w23 ታኅሣሥ ገጽ 2-7
  • ጻድቅ ለመሆን እምነትና ሥራ ያስፈልጋል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጻድቅ ለመሆን እምነትና ሥራ ያስፈልጋል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጻድቅ ለመሆን እምነት አስፈላጊ ነው
  • በእምነትና በሥራ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?
  • ተስፋ እምነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል
  • ይሖዋ “ወዳጄ” በማለት ጠርቶታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • “ልባችሁን አጽኑ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • እምነት ለሥራ ያንቀሳቅሰናል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ‘በማየት ሳይሆን በእምነት መመላለስ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
w23 ታኅሣሥ ገጽ 2-7

የጥናት ርዕስ 50

ጻድቅ ለመሆን እምነትና ሥራ ያስፈልጋል

‘አባታችን አብርሃም የነበረውን እምነት ተከትላችሁ በሥርዓት ተመላለሱ።’—ሮም 4:12

መዝሙር 119 ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል

ማስተዋወቂያa

1. ስለ አብርሃም እምነት ስናስብ ምን የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል?

ብዙ ሰዎች ስለ አብርሃም ሰምተው ቢያውቁም አብዛኞቹ ስለ እሱ የሚያውቁት ነገር ውስን ነው። አንተ ግን ስለ አብርሃም ብዙ ነገር ታውቃለህ። ለምሳሌ አብርሃም ‘እምነት ላላቸው ሁሉ አባት’ ተብሎ እንደተጠራ ታውቃለህ። (ሮም 4:11) ይሁንና እንዲህ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል፦ ‘እኔስ የአብርሃምን ፈለግ መከተልና የእሱ ዓይነት እምነት ማዳበር እችል ይሆን?’ በሚገባ!

2. አብርሃም የተወውን ምሳሌ ማጥናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ያዕቆብ 2:22, 23)

2 የአብርሃም ዓይነት እምነት ማዳበር የምንችልበት አንዱ መንገድ የእሱን ምሳሌ በማጥናት ነው። አብርሃም አምላክን በመታዘዝ ወደ ሩቅ አገር ሄዷል፤ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በድንኳን ውስጥ ኖሯል፤ እንዲሁም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆኗል። እነዚህ ነገሮች አብርሃም ጠንካራ እምነት እንደነበረው ያሳያሉ። አብርሃም የነበረው እምነትና ያከናወነው ሥራ የአምላክን ሞገስ ያስገኘለት ከመሆኑም ሌላ የእሱ ወዳጅ ለመባል አብቅቶታል። (ያዕቆብ 2:22, 23⁠ን አንብብ።) ይሖዋ አንተን ጨምሮ ሁላችንም እነዚህን በረከቶች እንድናገኝ ይፈልጋል። በመሆኑም ጳውሎስንና ያዕቆብን በመንፈሱ በመምራት አብርሃም ስለተወው ምሳሌ እንዲጽፉ አድርጓቸዋል። በሮም ምዕራፍ 4 እና በያዕቆብ ምዕራፍ 2 ላይ የተጠቀሰውን የአብርሃምን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። ሁለቱም ምዕራፎች ስለ አብርሃም በተነገረ አንድ አስደናቂ ሐሳብ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

3. ጳውሎስም ሆነ ያዕቆብ የትኛውን ጥቅስ ጠቅሰዋል?

3 ጳውሎስም ሆነ ያዕቆብ ዘፍጥረት 15:6⁠ን ጠቅሰው ጽፈዋል። ጥቅሱ “[አብርሃም] በይሖዋ አመነ፤ አምላክም ይህን ጽድቅ አድርጎ ቆጠረለት” ይላል። አንድ ሰው ጻድቅ የሚባለው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ካገኘ አልፎ ተርፎም ነቀፋ የሌለበት ተደርጎ ከተቆጠረ ነው። ፍጽምና የጎደለው ኃጢአተኛ ሰው በአምላክ ዘንድ ነቀፋ እንደሌለበት ተደርጎ መቆጠር መቻሉ ምንኛ አስደናቂ ነው! አንተም እንዲህ እንዲባልልህ እንደምትፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ደግሞም ሊባልልህ ይችላል። ጻድቅ ሆነን መቆጠር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በመጀመሪያ አብርሃም ጻድቅ ሆኖ የተቆጠረው ለምን እንደሆነ መመልከታችን ጠቃሚ ነው።

ጻድቅ ለመሆን እምነት አስፈላጊ ነው

4. ሰዎች ጻድቅ እንዳይሆኑ የሚያግዳቸው ምንድን ነው?

4 ጳውሎስ በሮም ላሉ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ተናግሯል። (ሮም 3:23) ታዲያ አንድ ሰው ጻድቅ ወይም ነቀፋ የሌለበት ተደርጎ መቆጠርና የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ይህን ጥያቄ ለመመለስ የአብርሃምን ምሳሌ ጠቅሷል።

5. ይሖዋ አብርሃምን ጻድቅ አድርጎ የቆጠረው ምንን መሠረት አድርጎ ነው? (ሮም 4:2-4)

5 ይሖዋ፣ አብርሃም ጻድቅ እንደሆነ የተናገረው በከነአን ምድር ይኖር በነበረበት ወቅት ነው። ይሖዋ አብርሃምን ጻድቅ አድርጎ የቆጠረው ለምንድን ነው? አብርሃም የሙሴን ሕግ ሙሉ በሙሉ ስለጠበቀ ነው? እንዳልሆነ የታወቀ ነው። (ሮም 4:13) ሕጉ ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው አምላክ አብርሃምን ጻድቅ ብሎ ከጠራው ከ400 ዓመት በኋላ ነው። ታዲያ አምላክ አብርሃምን ጻድቅ አድርጎ የቆጠረው ምንን መሠረት አድርጎ ነው? የጸጋ አምላክ የሆነው ይሖዋ፣ አብርሃም እምነት በማሳየቱ ጻድቅ አድርጎ ቆጥሮታል።—ሮም 4:2-4⁠ን አንብብ።

6. ይሖዋ ኃጢአተኞችን እንደ ጻድቃን ሊቆጥር የሚችለው እንዴት ነው?

6 ጳውሎስ አንድ ሰው በአምላክ የሚያምን ከሆነ ‘እምነቱ እንደ ጽድቅ እንደሚቆጠርለት’ ተናግሯል። (ሮም 4:5) አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ይህም ዳዊት፣ አምላክ ያለሥራ እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥረው ሰው ስለሚያገኘው ደስታ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ ‘የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው፤ ይሖዋ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ደስተኛ ነው።’” (ሮም 4:6-8፤ መዝ. 32:1, 2) አምላክ በእሱ የሚያምኑ ሰዎችን ኃጢአታቸውን ይሰርዝላቸዋል ወይም ይሸፍንላቸዋል። ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላቸዋል፤ እንዲሁም ኃጢአታቸውን አይቆጥርባቸውም። እንዲህ ያሉትን ሰዎች፣ እምነታቸውን መሠረት በማድረግ ነቀፋ የሌለባቸው ወይም ጻድቃን አድርጎ ይቆጥራቸዋል።

7. ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጻድቃን ተብለው የተጠሩት ከምን አንጻር ነው?

7 አብርሃም፣ ዳዊትና ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጻድቃን ተደርገው ቢቆጠሩም ፍጽምና የጎደላቸው ኃጢአተኞች ነበሩ። ሆኖም በእምነታቸው ምክንያት አምላክ ነቀፋ የሌለባቸው አድርጎ ቆጥሯቸዋል። በተለይ በእሱ ላይ እምነት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ሲወዳደሩ ጻድቃን ተደርገው መቆጠራቸው ተገቢ ነው። (ኤፌ. 2:12) ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ በግልጽ እንደተናገረው ከአምላክ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረት እምነት የግድ አስፈላጊ ነው። አብርሃምና ዳዊት የአምላክ ወዳጅ መሆን የቻሉት እምነት ስለነበራቸው ነው። እኛም ብንሆን የአምላክ ወዳጅ ለመሆን እምነት ያስፈልገናል።

በእምነትና በሥራ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

8-9. አንዳንዶች ጳውሎስና ያዕቆብ ከጻፉት ሐሳብ በመነሳት ምን የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል?

8 በእምነትና በሥራ መካከል ያለው ዝምድና ላለፉት በርካታ መቶ ዘመናት በሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት መካከል አከራካሪ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንድ ቀሳውስት ለመዳን የሚያስፈልገው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ምናልባትም “ጌታን ተቀበል፤ ትድናለህ” ሲሉ ሰምተህ ይሆናል። እነዚህ ቀሳውስት፣ ‘አምላክ ያለሥራ እንደ ጻድቅ አድርጎ እንደሚቆጥር’ የሚገልጸውን ጳውሎስ የጻፈውን ሐሳብ ይጠቅሱ ይሆናል። (ሮም 4:6) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች፣ በመንፈሳዊ ጉዞዎች በመካፈል ወይም ቤተ ክርስቲያኗ የምትጠይቃቸውን ሌሎች ነገሮች በማድረግ “ራሳችንን ማዳን” እንደምንችል ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች በያዕቆብ 2:24 ላይ የሚገኘውን “ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር [ነው]” የሚለውን ሐሳብ ይጠቅሱ ይሆናል።

9 እንዲህ ያሉ ተቃራኒ አመለካከቶች በመኖራቸው የተነሳ አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን በእምነትና በሥራ መካከል ያለውን ዝምድና በተመለከተ ጳውሎስና ያዕቆብ የተለያየ አመለካከት ነበራቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ቀሳውስት፣ ጳውሎስ አንድ ሰው ያለሥራ በእምነቱ ብቻ ጻድቅ ሆኖ መቆጠር እንደሚችል ያምን እንደነበር፣ ያዕቆብ ግን የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ሥራ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ያምን እንደነበር ይናገሩ ይሆናል። አንድ የሥነ መለኮት ፕሮፌሰር “ያዕቆብ፣ ጳውሎስ [ጻድቅ መሆን የሚቻለው] በሥራ ሳይሆን በእምነት ብቻ እንደሆነ የተናገረበት ምክንያት አልገባውም” ብለዋል። ይሁንና ጳውሎስም ሆነ ያዕቆብ መልእክታቸውን የጻፉት በይሖዋ መንፈስ መሪነት ነው። (2 ጢሞ. 3:16) ስለዚህ እነሱ የተናገሯቸውን ሐሳቦች ማስታረቅ የሚቻልበት ቀላል መንገድ መኖር አለበት። ደግሞም አለ፤ የጻፉትን ሐሳብ ከነአውዱ መመርመራችን ይህን ለማድረግ ይረዳናል።

ሥዕሎች፦ ሐዋርያው ጳውሎስ እና በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩ ሦስት ‘የሕጉ ሥራዎች።’ 1. አንድ ሰው በልብሱ ላይ ሰማያዊ ጥለት ሲሰፋ። 2. የተጠበሰ በግ፣ ቂጣ እና መራራ ቅጠሎችን ያካተተው የፋሲካ ማዕድ። 3. አንድ ሰው ሌላ ሰው ውኃ እያፈሰሰለት እጁን ሲታጠብ።

ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ አስፈላጊው ነገር የሙሴን ሕግ መጠበቅ ሳይሆን እምነት እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጾላቸዋል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)b

10. ጳውሎስ በዋነኝነት እየተናገረ የነበረው ስለ ምን ዓይነት “ሥራ” ነው? (ሮም 3:21, 28) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ጳውሎስ በሮም 3 እና 4 ላይ እየተናገረ የነበረው ስለ ምን ዓይነት “ሥራ” ነው? በዋነኝነት ያተኮረው ‘በሕግ ሥራ’ ማለትም በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ ላይ ነበር። (ሮም 3:21, 28⁠ን አንብብ።) በጳውሎስ ዘመን አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሙሴ ሕግ እንደተሻረ እንዲሁም ክርስቲያኖች የሙሴን ሕግ መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው መቀበል ከብዷቸው የነበረ ይመስላል። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ የአብርሃምን ምሳሌ በመጥቀስ፣ በአምላክ ዘንድ ጻድቅ ሆኖ መቆጠር የሚቻለው “የሕግን ሥራ በመፈጸም” እንዳልሆነ ገለጸ። ከዚህ ይልቅ በእምነት ነው። ይህን ማወቃችን በጣም ያበረታታናል፤ ምክንያቱም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻል ነገር እንደሆነ ያረጋግጥልናል። ስለዚህ በአምላክና በክርስቶስ ላይ እምነት ማዳበርና በውጤቱም የይሖዋን ሞገስ ማግኘት እንችላለን።

ሥዕሎች፦ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እና ክርስቲያኖች መልካም ነገር ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አንድ ባልና ሚስት ለአንዲት ድሃ አረጋዊት ሴት ምግብና ልብስ ሲሰጡ፤ ከበስተ ጀርባቸው ጥሩ ልብስ የለበሱ ሰዎች ሲያወሩ ይታያል።

ያዕቆብ፣ ክርስቲያኖች እምነታቸውን በሥራ እንዲያሳዩ፣ ለምሳሌ ሳያዳሉ ለሌሎች መልካም ነገር እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)c

11. ያዕቆብ እየተናገረ የነበረው ስለ ምን ዓይነት ሥራ ነው?

11 በሌላ በኩል ደግሞ፣ በያዕቆብ ምዕራፍ 2 ላይ የተጠቀሰው “ሥራ” ጳውሎስ ከጠቀሰው ‘የሕግ ሥራ’ የተለየ ነው። ያዕቆብ እየተናገረ የነበረው ክርስቲያኖች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ስለሚያከናውኑት ሥራ ነው። እንዲህ ያለው ሥራ፣ አንድ ክርስቲያን በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት ያለው መሆን አለመሆኑን ያሳያል። ያዕቆብ የጠቀሳቸውን ሁለት ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት።

12. ያዕቆብ በእምነትና በሥራ መካከል ያለውን ዝምድና የገለጸው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 በመጀመሪያው ምሳሌው ላይ ያዕቆብ፣ ክርስቲያኖች ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ መያዝ እንዳለባቸው ገልጿል። ይህን ነጥብ ለማጉላት፣ ለሀብታም ሰው ደግነት እያሳየ ድሆችን ስለሚንቅ ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል። እንዲህ ያለው ሰው እምነት አለኝ ቢልም እንኳ ሥራው በእርግጥ ይህን ያሳያል? (ያዕ. 2:1-5, 9) በሁለተኛው ምሳሌው ላይ ደግሞ ያዕቆብ፣ ‘አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ልብስ ወይም ምግብ እንደተቸገሩ’ አይቶ ምንም እርምጃ ስላልወሰደ ሰው ተናግሯል። እንዲህ ያለው ሰው እምነት አለኝ ቢልም እንኳ እምነቱ በሥራ አልተደገፈም፤ ስለዚህ እምነቱ ምንም ዋጋ የለውም። ያዕቆብ እንደጻፈው “በሥራ ያልተደገፈ [እምነት] በራሱ የሞተ ነው።”—ያዕ. 2:14-17

13. ያዕቆብ በሥራ የተደገፈ እምነት በማሳየት ረገድ የማንን ምሳሌ ጠቅሷል? (ያዕቆብ 2:25, 26)

13 ያዕቆብ በሥራ የተደገፈ እምነት በማሳየት ረገድ ረዓብ ጥሩ ምሳሌ እንደሆነች ገልጿል። (ያዕቆብ 2:25, 26⁠ን አንብብ።) ረዓብ ስለ ይሖዋ ሰምታለች፤ እሱ እስራኤላውያንን እየረዳቸው እንደሆነም ተገንዝባለች። (ኢያሱ 2:9-11) ከዚያም አደጋ ላይ የነበሩትን ሁለቱን እስራኤላውያን ሰላዮች በመታደግ እምነቷን በሥራ አሳየች። በዚህም የተነሳ፣ እስራኤላዊ ያልሆነችው ይህች ፍጽምና የጎደላት ሴት ልክ እንደ አብርሃም ጻድቅ ሆና መቆጠር ችላለች። እሷ የተወችው ምሳሌ እምነታችንን በሥራ መደገፍ ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል።

14. ጳውሎስና ያዕቆብ የጻፉት ሐሳብ እርስ በርሱ የሚስማማው እንዴት ነው?

14 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሆኑት ጳውሎስና ያዕቆብ ስለ እምነትና ስለ ሥራ የተናገሩት ከተለያየ አቅጣጫ ነበር። ጳውሎስ፣ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ላይ የተደነገጉትን ሥራዎች በመፈጸም ብቻ የይሖዋን ሞገስ ማግኘት እንደማይችሉ እየነገራቸው ነበር። ያዕቆብ ደግሞ ሁሉም ክርስቲያኖች ለሌሎች መልካም በማድረግ እምነታቸውን በሥራ ማሳየት እንዳለባቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል።

ፎቶግራፎች፦ ወንድሞችና እህቶች እምነታቸውን በሥራ ሲያሳዩ። 1. በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ያለ ወንድምና አስታማሚው ወደ ጉባኤ ስብሰባ ሲሄዱ አንድ ወንድም ሰላም ሲላቸው። 2. አንዲት እህት ፖስት ካርድ ላይ ስትጽፍ። 3. አንድ ባልና ሚስት በጋሪ ምሥክርነት ሲካፈሉ።

እምነትህ ይሖዋን የሚያስደስቱ ሥራዎችን ለማከናወን ያነሳሳሃል? (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. እምነታችንን በሥራ ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

15 ይሖዋ ጻድቅ ሆነን ለመቆጠር አብርሃም ያደረገውን እያንዳንዱን ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። እምነታችንን በሥራ ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ወደ ጉባኤያችን የሚመጡ አዲሶችን ጥሩ አድርገን መቀበል፣ የተቸገሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መርዳት እንዲሁም ለቤተሰቦቻችን መልካም ነገር ማድረግ እንችላለን፤ ይህም አምላክን የሚያስደስትና የእሱን በረከት የሚያስገኝ ነገር ነው። (ሮም 15:7፤ 1 ጢሞ. 5:4, 8፤ 1 ዮሐ. 3:18) እምነታችንን ማሳየት የምንችልበት ሌላው ወሳኝ መንገድ ምሥራቹን ለሌሎች በቅንዓት ማካፈል ነው። (1 ጢሞ. 4:16) ሁላችንም ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እንዲሁም የእሱ መንገዶች ከሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ እምነት እንዳለን በሥራችን ማሳየት እንችላለን። እንዲህ ካደረግን አምላክ ጻድቅ አድርጎ እንደሚቆጥረን እንዲሁም ‘ወዳጆቼ’ ብሎ እንደሚጠራን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ተስፋ እምነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል

16. የአብርሃም እምነት ከተስፋ ጋር ምን ተያያዥነት ነበረው?

16 ሮም ምዕራፍ 4 ከአብርሃም የምናገኘውን ሌላ ወሳኝ ትምህርት ይኸውም ስለ ተስፋ አስፈላጊነት ይናገራል። ይሖዋ በአብርሃም አማካኝነት “ብዙ ብሔራት” እንደሚባረኩ ቃል ገብቶ ነበር። አብርሃም የነበረው ተስፋ ምንኛ አስደናቂ ነው! (ዘፍ. 12:3፤ 15:5፤ 17:4፤ ሮም 4:17) ይሁንና አብርሃም 100 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሞልቷቸውም እንኳ ልጅ አልወለዱም። ከሰብዓዊ እይታ አንጻር አብርሃምና ሣራ ልጅ መውለድ የሚችሉ አይመስልም ነበር። ይህ ለአብርሃም ትልቅ ፈተና ነበር። ያም ቢሆን አብርሃም “የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል።” (ሮም 4:18, 19) ደግሞም ይህ ተስፋ ተፈጽሞለታል። ለረጅም ጊዜ ተስፋ ሲያደርግ እንደቆየው ይስሐቅን መውለድ ችሏል።—ሮም 4:20-22

17. የአምላክ ወዳጆች በመሆን እንደ ጻድቃን መቆጠር እንደምንችል እንዴት እናውቃለን?

17 እንደ አብርሃም የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንዲሁም የእሱ ወዳጆች በመሆን እንደ ጻድቃን መቆጠር እንችላለን። እንዲያውም ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “‘ተቆጠረለት’ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ጻድቃን ስለምንቆጠረው ስለ እኛም ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ጌታችንን ኢየሱስን ከሞት ባስነሳው በእሱ እናምናለን።” (ሮም 4:23, 24) እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም እምነትና ሥራ እንዲሁም ተስፋ ያስፈልገናል። ጳውሎስ በሮም ምዕራፍ 5 ላይ ስለ ተስፋችን ተናግሯል፤ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንመለከታለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ጳውሎስ “አንድ ሰው ጻድቅ ነህ የሚባለው የሕግን ሥራ በመፈጸም ሳይሆን በእምነት [ነው]” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

  • ያዕቆብ ከጻፈው ሐሳብ አንጻር በእምነትና በሥራ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?

  • እምነታችንን በሥራ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

a የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንዲሁም በእሱ ዘንድ እንደ ጻድቅ መቆጠር እንፈልጋለን። ይህ ርዕስ ጳውሎስና ያዕቆብ የጻፉትን ሐሳብ በመጠቀም፣ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት እምነትም ሥራም የሚያስፈልገው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ ጳውሎስ፣ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ‘የሕግን ሥራ’ በመፈጸም ላይ ሳይሆን በእምነት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል፤ ይህም በልብሳቸው ላይ ሰማያዊ ጥለት ማድረግን፣ ፋሲካን ማክበርን እንዲሁም የመንጻት ሥርዓትን ለመፈጸም መታጠብን ይጨምራል።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ ያዕቆብ፣ ክርስቲያኖች ለሌሎች መልካም በማድረግ እምነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ አበረታቷቸዋል፤ ይህም ድሆችን መርዳትን ይጨምራል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ