የጥናት ርዕስ 27
መዝሙር 79 ጸንተው እንዲቆሙ አስተምሯቸው
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ እርምጃ እንዲወስዱ እርዷቸው
“በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፤ . . . ብርቱዎች ሁኑ።”—1 ቆሮ. 16:13
ዓላማ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ትክክለኛውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስፈልጋቸውን እምነትና ድፍረት እንዲያዳብሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
1-2. (ሀ) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እርምጃ ለመውሰድ የሚያመነቱት ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሳላችሁ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን አመንትታችሁ ነበር? ምናልባትም የሥራ ባልደረቦቻችሁ፣ ጓደኞቻችሁ ወይም ቤተሰቦቻችሁ ሊቃወሟችሁ እንደሚችሉ በማሰብ ፈርታችሁ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ የአምላክን ብቃቶች ማሟላት እንደማትችሉ ተሰምቷችሁ ሊሆን ይችላል። ከሆነ፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እርምጃ ለመውሰድ የሚያመነቱበት ምክንያት ይገባችኋል።
2 ኢየሱስ እንዲህ ያሉት ስሜቶች አንድ ሰው መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት ሊሆኑበት እንደሚችሉ ተገንዝቦ ነበር። (ማቴ. 13:20-22) ያም ቢሆን እሱን ለመከተል ያመነቱትን ሰዎች ተስፋ አልቆረጠባቸውም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ያሉት ሰዎች (1) ለእድገታቸው እንቅፋት የሆነባቸውን ነገር ለይተው እንዲያውቁ፣ (2) ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ፣ (3) ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር እንዲያስተካክሉ እንዲሁም (4) ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲያሸንፉ መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ አሳይቷቸዋል። እኛስ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን ጥናቶቻችን እርምጃ እንዲወስዱ በምንረዳበት ወቅት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን ምክር በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?
ጥናቶቻችሁ ለእድገታቸው እንቅፋት የሆነባቸውን ነገር እንዲለዩ እርዷቸው
3. ኒቆዲሞስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዳይሆን እንቅፋት የሆነበት ምን ሊሆን ይችላል?
3 ታዋቂ የአይሁዳውያን ገዢ የሆነው ኒቆዲሞስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዳይሆን እንቅፋት የሆነበት ነገር ነበር። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረ ስድስት ወር ገደማ እንደሆነው ኒቆዲሞስ ኢየሱስ የአምላክ ወኪል መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐ. 3:1, 2) ያም ቢሆን ኒቆዲሞስ ‘አይሁዳውያንን ስለፈራ’ ከኢየሱስ ጋር በድብቅ ለመገናኘት መርጧል። (ዮሐ. 7:13፤ 12:42) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑ ብዙ ነገር እንደሚያሳጣው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል።a
4. ኒቆዲሞስ አምላክ የሚጠብቅበትን ነገር እንዲያስተውል ኢየሱስ የረዳው እንዴት ነው?
4 ኒቆዲሞስ የሙሴን ሕግ በሚገባ ያውቅ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ የሚጠብቅበትን ነገር በትክክል መረዳት እንዲችል እርዳታ አስፈልጎታል። ታዲያ ኢየሱስ የረዳው እንዴት ነው? ኢየሱስ ጊዜውን በልግስና ሰጥቶታል። እንዲያውም እሱን በማታ ለማግኘት ፈቃደኛ ሆኗል። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ኒቆዲሞስ የእሱ ደቀ መዝሙር ለመሆን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገው በግልጽ ነግሮታል፤ ለኃጢአቱ ንስሐ መግባት፣ በውኃ መጠመቅና በአምላክ ልጅ ማመን አለበት።—ዮሐ. 3:5, 14-21
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዳያደርጉ እንቅፋት የሆነባቸውን ነገር እንዲያስተውሉ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
5 ጥናቶቻችን ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ቢኖራቸውም እንኳ እድገታቸውን የገታው ነገር ምን እንደሆነ ማስተዋል እንዲችሉ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ሥራቸው ወይም የቤተሰብ ተቃውሞ መንፈሳዊ ግባቸው ላይ እንዳይደርሱ ትኩረታቸውን ከፋፍሎት ይሆናል። እንግዲያው ለጥናቶቻችሁ ጊዜያችሁን ስጧቸው። አብራችሁ ሻይ ቡና ልትሉ ወይም በእግር ልትንሸራሸሩ ትችላላችሁ። እንዲህ ባለው ዘና ያለ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ስላጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች መናገር ቀላል ሊሆንላቸው ይችላል። አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ አበረታቷቸው፤ ይህን የሚያደርጉት እናንተን ለማስደሰት ሳይሆን ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት ብለው እንደሆነ አስታውሷቸው።
6. ጥናቶቻችን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ድፍረት እንዲኖራቸው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 16:13)
6 ጥናቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች እንዲመሩ ይሖዋ እንደሚረዳቸው ሲተማመኑ የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ድፍረት ይኖራቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:13ን አንብብ።) የእናንተ ሚና ከመምህራን ሚና ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ተማሪ ሳላችሁ በጣም የምትወዱት ምን ዓይነት አስተማሪ ነበር? ባላችሁ ችሎታ እንድትተማመኑ በትዕግሥት የረዳችሁን አስተማሪ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም አንድ ጎበዝ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ለጥናቱ ይሖዋ የሚጠብቅበትን ነገር ከመንገር ባለፈ በይሖዋ እርዳታ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንደሚችል እንዲተማመን ይረዳዋል። ታዲያ እንዲህ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?
ጥናቶቻችሁ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ እርዷቸው
7. ኢየሱስ አድማጮቹ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እንዲያድግ የረዳቸው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለአምላክ ያላቸው ፍቅር የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል እንደሚያነሳሳቸው ያውቅ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ የሰማዩን አባታቸውን ይበልጥ እንዲወዱት የሚያደርግ ትምህርት ብዙ ጊዜ ያስተምር ነበር። ለምሳሌ ይሖዋን ለልጆቹ መልካም ነገሮችን ከሚሰጥ አባት ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 7:9-11) ከኢየሱስ አድማጮች መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ ያለ አፍቃሪ አባት አላሳደጋቸው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች፣ መጥፎ ጎዳና ሲከተል የቆየውን ልጁን በደስታ ስለተቀበለው ሩኅሩኅ አባት የሚገልጸውን ምሳሌ ሲሰሙ ምን ተሰምቷቸው ይሆን! ይሖዋ ለምድራዊ ልጆቹ ያለውን ርኅራኄ በግልጽ ማየት ይችላሉ።—ሉቃስ 15:20-24
8. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?
8 እናንተም ጥናቶቻችሁን በምታስተምሩበት ወቅት የአምላክን ባሕርያት ጎላ አድርጋችሁ በመግለጽ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። በእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራም ወቅት፣ በሚማሩት ነገርና በይሖዋ ፍቅር መካከል ያለውን ተያያዥነት እንዲያስተውሉ እርዷቸው። ስለ ቤዛው በምትወያዩበት ጊዜ ቤዛው ለእነሱ በግለሰብ ደረጃ ምን ትርጉም እንዳለው ጎላ አድርጋችሁ ግለጹላቸው። (ሮም 5:8፤ 1 ዮሐ. 4:10) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ባሳያቸው ፍቅር ላይ ካሰላሰሉ እሱን ለመውደድ እንደሚነሳሱ ምንም ጥያቄ የለውም።—ገላ. 2:20
9. ማይክል አኗኗሩን እንዲቀይር ያነሳሳው ምንድን ነው?
9 በኢንዶኔዥያ የሚኖረውን ማይክልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ማይክል በልጅነቱ እውነትን ያውቅ ነበር፤ ግን አልተጠመቀም። በ18 ዓመቱ የከባድ መኪና ሹፌር ሆኖ ለመሥራት ወደ ሌላ አገር ሄደ። ከጊዜ በኋላ ትዳር ለመመሥረት ወደ አገሩ ቢመለስም በውጭ አገር መሥራቱን ለመቀጠል ቤተሰቡን ትቶ በድጋሚ ሄደ። በዚያ መሃል ሚስቱና ሴት ልጁ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና እድገት ማድረግ ጀመሩ። እናቱ ከሞተች በኋላ ማይክል አባቱን ለመንከባከብ ወደ አገሩ ለመመለስ ወሰነ። በዚህ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 27 ላይ “ጠለቅ ያለ ጥናት” የሚለውን ክፍል ሲያጠና ልቡ በጥልቅ ተነካ። ይሖዋ ልጁ ሲሠቃይ ሲመለከት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ሲያሰላስል ማይክል ማልቀስ ጀመረ። ለቤዛው ጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜት አደረበት። በዚህም የተነሳ አኗኗሩን ለመቀየርና ለመጠመቅ ተነሳሳ።
ጥናቶቻችሁ ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር እንዲያስተካክሉ እርዷቸው
10. ኢየሱስ ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር እንዲያስተካክሉ የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርቱን የረዳቸው እንዴት ነው? (ሉቃስ 5:5-11) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን ወዲያውኑ ተገንዝበው ነበር። ሆኖም ለአገልግሎት ቅድሚያ መስጠት እንዲጀምሩ እርዳታ አስፈልጓቸዋል። ጴጥሮስና እንድርያስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሆኑ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው እንዲከተሉት ጋበዛቸው። (ማቴ. 4:18, 19) በወቅቱ የተደራጀ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ነበራቸው፤ ያዕቆብና ዮሐንስም አብረዋቸው ይሠሩ የነበረ ይመስላል። (ማር. 1:16-20) ጴጥሮስና እንድርያስ “መረቦቻቸውን ትተው” የሄዱት ኢየሱስን በሚከተሉበት ወቅት ቤተሰባቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት የሆነ ዕቅድ አውጥተው መሆን አለበት። ቅድሚያ የሚሰጡትን ነገር እንዲያስተካክሉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? የሉቃስ ዘገባ እንደሚገልጸው ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው እንዲተማመኑ የሚረዳ ተአምር አሳይቷቸዋል።—ሉቃስ 5:5-11ን አንብብ።
ኢየሱስ ቅድሚያ በሚሰጡት ነገር ረገድ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ደቀ መዛሙርቱን ከረዳበት መንገድ ምን እንማራለን? (አንቀጽ 10ን ተመልከት)b
11. የራሳችንን ተሞክሮ ተጠቅመን ጥናቶቻችን እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
11 እኛ እንደ ኢየሱስ ተአምራትን መፈጸም አንችልም። ሆኖም ይሖዋ በሕይወታቸው ውስጥ እሱን የሚያስቀድሙትን ሰዎች እንዴት እንደሚረዳቸው የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን ለጥናቶቻችን ልንነግራቸው እንችላለን። ለምሳሌ በስብሰባዎች ላይ መገኘት በጀመራችሁበት ወቅት ይሖዋ የረዳችሁ እንዴት እንደነበር ታስታውሳላችሁ? ምናልባትም አለቃችሁ ጋ ቀርባችሁ ከስብሰባ ሰዓት ጋር የሚጋጭባችሁ ከሆነ ትርፍ ሰዓት መሥራት እንደማትችሉ መናገር አስፈልጓችሁ ይሆናል። ተሞክሯችሁን ለጥናቶቻችሁ በምትናገሩበት ወቅት ይሖዋ የእሱን አምልኮ ለማስቀደም ስትሉ ያደረጋችሁትን ውሳኔ ሲባርክላችሁ ማየታችሁ እምነታችሁን ያጠናከረላችሁ እንዴት እንደሆነ አስረዷቸው።
12. (ሀ) የተለያዩ አስፋፊዎችን ጥናት መጋበዝ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ጥናቶቻችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር ቪዲዮዎችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
12 ጥናቶቻችሁ ሌሎች ክርስቲያኖች ቅድሚያ በሚሰጡት ነገር ረገድ ማስተካከያ ያደረጉት እንዴት እንደሆነ መስማታቸውም ይጠቅማቸዋል። በመሆኑም የተለያየ አስተዳደግና ባሕል ያላቸውን ክርስቲያኖች ጥናት ጋብዙ። ወደ እውነት የመጡት እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ የይሖዋን አገልግሎት ማስቀደም የቻሉት እንዴት እንደሆነ ጠይቁላቸው። በተጨማሪም ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ላይ “ጠለቅ ያለ ጥናት” እና “ምርምር አድርግ” በሚሉት ክፍሎች ውስጥ ያሉትን ቪዲዮዎች ጊዜ ወስዳችሁ ከጥናቶቻችሁ ጋር ተመልከቱ። ለምሳሌ ምዕራፍ 37ን ስታጠኑ ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያሟላልናል ከሚለው ቪዲዮ የምታገኟቸውን ትምህርቶች ልታጎሉ ትችላላችሁ።
ጥናቶቻችሁ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲያሸንፉ እርዷቸው
13. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለተቃውሞ ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?
13 ኢየሱስ ተከታዮቹ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ተቃውሞ እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 5:11፤ 10:22, 36) በአገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ሞትንም እንኳ መጋፈጥ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴ. 24:9፤ ዮሐ. 15:20፤ 16:2) አገልግሎታቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ጠንቃቃ እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል። ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ንትርክ ውስጥ እንዳይገቡ መክሯቸዋል። በተጨማሪም መስበካቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ ዘዴኞች እንዲሆኑ ነግሯቸዋል።
14. ጥናቶቻችን ለተቃውሞ እንዲዘጋጁ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (2 ጢሞቴዎስ 3:12)
14 ጥናቶቻችንን ለተቃውሞ ለማዘጋጀት የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ምን ሊሏቸው እንደሚችሉ አስቀድመን ልንነግራቸው እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:12ን አንብብ።) አኗኗራቸውን በማስተካከላቸው አንዳንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው ሊያሾፉባቸው ይችላሉ። የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነታቸውን ሊተቹ ይችላሉ። ጥናቶቻችንን ከመነሻው ለተቃውሞ ካዘጋጀናቸው ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችል የተሻለ ብቃት ይኖራቸዋል።
15. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን የቤተሰብ ተቃውሞን እንዲቋቋሙ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
15 ጥናቶቻችሁ የቤተሰብ ተቃውሞ ካጋጠማቸው ቤተሰቦቻቸው የተበሳጩት ለምን ሊሆን እንደሚችል እንዲያስቡ አበረታቷቸው። ጥናት የጀመሩት ተታለው እንደሆነ አስበው ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ መረጃ ሰምተው ይሆናል። ኢየሱስም እንኳ ከቤተሰቦቹ ተቃውሞ ደርሶበታል። (ማር. 3:21፤ ዮሐ. 7:5) ጥናቶቻችሁ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ሌሎችን በሚይዙበት መንገድ ትዕግሥተኞችና ዘዴኞች እንዲሆኑ አስተምሯቸው።
16. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በዘዴ ስለ እምነታቸው እንዲያስረዱ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
16 ጥናቶቻችሁ ቤተሰቦቻቸው ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜም እንኳ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማብራራት አለመሞከራቸው ጥበብ ይሆናል። አለዚያ ዘመዶቻቸው መረጃ ሊዥጎደጎድባቸውና ሌላ ጊዜ ለመወያየት ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ጥናቶቻችሁ ለተጨማሪ ውይይት በር በሚከፍት መንገድ እምነታቸውን እንዲያካፍሉ አበረታቷቸው። (ቆላ. 4:6) ምናልባትም jw.orgን እንዲመለከቱ ቤተሰቦቻቸውን ሊጋብዟቸው ይችሉ ይሆናል። ይህም በፈለጉት ጊዜና በፈለጉት መጠን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንዲማሩ ያስችላቸዋል።
17. ጥናቶቻችሁ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ ማሠልጠን የምትችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ጥናቶቻችሁ ቤተሰቦቻቸው ወይም የሥራ ባልደረቦቻቸው ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ቀለል ያለ መልስ እንዲዘጋጁ ለመርዳት jw.org ላይ የሚወጣውን “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች” የሚለውን ዓምድ መጠቀም ትችላላችሁ። (2 ጢሞ. 2:24, 25) ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ስታጠኑ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ “አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ” የሚለውን ክፍል ተጠቅማችሁ ተወያዩ። ጥናቶቻችሁ በራሳቸው አባባል ምላሽ መስጠትን እንዲለማመዱ አበረታቷቸው። የሚሰጡትን ምላሽ ማሻሻል የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ ምክር ከመስጠት ወደኋላ አትበሉ። በዚህ መልኩ አብራችሁ መለማመዳችሁ ጥናቶቻችሁ በልበ ሙሉነት ለእምነታቸው ጥብቅና እንዲቆሙ ይረዳቸዋል።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁ ጋር አስቀድማችሁ በመለማመድ እምነታቸውን በይፋ እንዲሰብኩ አበረታቷቸው (አንቀጽ 17ን ተመልከት)c
18. ጥናቶቻችሁ ያልተጠመቀ አስፋፊ እንዲሆኑ ማበረታታት የምትችሉት እንዴት ነው? (ማቴዎስ 10:27)
18 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ምሥራቹን በይፋ እንዲሰብኩ አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 10:27ን አንብብ።) ጥናቶቻችሁ ስለ እምነታቸው ቶሎ መስበክ መጀመራቸው በይሖዋ መታመንን ቶሎ እንዲማሩ ይረዳቸዋል። ጥናቶቻችሁ አገልግሎት ለመጀመር ግብ እንዲያወጡ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? የስብከት ዘመቻ ሊካሄድ እንደሆነ ለጉባኤው ማስታወቂያ ሲነገር ጥናቶቻችሁ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን ማሟላት ይችሉ እንደሆነ እንዲያስቡበት አበረታቷቸው። ብዙዎች እንዲህ ባሉት ዘመቻዎች ወቅት አገልግሎት መጀመር የቀለላቸው ለምን እንደሆነ አብራሩላቸው። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ የተማሪ ክፍል ማቅረባቸውም ሊረዳቸው ይችላል። ክፍል ለማቅረብ በሚዘጋጁበት ወቅት እምነታቸውን በልበ ሙሉነት ማብራራት የሚችሉበትን መንገድ ይማራሉ።
በጥናቶቻችሁ እንደምትተማመኑ አሳዩ
19. ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
19 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት፣ ወደፊት አብረውት እንደሚሆኑ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። በዚህ ጊዜ፣ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ መናገሩ እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱ አልተገነዘቡም ነበር። ያም ቢሆን ኢየሱስ በጥርጣሬያቸው ላይ ሳይሆን በታማኝነታቸው ላይ አተኩሯል። (ዮሐ. 14:1-5, 8) ስለ ሰማያዊ ተስፋ የሚገልጸውን ሐሳብ ጨምሮ አንዳንድ ነገሮችን ለመረዳት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐ. 16:12) እኛም ጥናቶቻችን ይሖዋን ማስደሰት እንደሚፈልጉ እንደምንተማመን ማሳየት እንችላለን።
ጥናቶቻችሁ ስለ እምነታቸው ቶሎ መስበክ መጀመራቸው በይሖዋ መታመንን ቶሎ እንዲማሩ ይረዳቸዋል
20. በማላዊ የምትኖር አንዲት እህት በጥናቷ እንደምትተማመን ያሳየችው እንዴት ነው?
20 ጥናቶቻችን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ እንደሚነሳሱ እንተማመናለን። በማላዊ የምትኖረውን ቺፉንዶ የተባለች እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅማ አሊናፌ ከተባለች ወጣት ካቶሊክ ሴት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ምዕራፍ 14ን አጥንተው ሲጨርሱ ቺፉንዶ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን በተመለከተ ምን እንደሚሰማት ጥናቷን ጠየቀቻት። በዚህ ጊዜ አሊናፌ ስሜታዊ ሆና “ይህ የራሴ ውሳኔ ነው” አለች። ቺፉንዶ፣ አሊናፌ ከዚያ በኋላ ማጥናቷን ልታቆም እንደምትችል አስባ ነበር። ሆኖም ውሎ አድሮ ነጥቡን እንደምትገነዘብ ተስፋ በማድረግ አሊናፌን በትዕግሥት ማስጠናቷን ቀጠለች። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ቺፉንዶ በምዕራፍ 34 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ጥያቄ ጠየቀቻት፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስና እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ መማርህ እስካሁን ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል?” ቺፉንዶ፣ አሊናፌ የሰጠችውን ምላሽ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ግሩም ነጥቦችን ጠቀሰች። ከጠቀሰቻቸው ነገሮች መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ በሚከለክለው በማንኛውም ተግባር የማይካፈሉ መሆኑ ነው።” ብዙም ሳይቆይ አሊናፌ ምስሎችን መጠቀሟን አቆመች፤ ከዚያም ለመጠመቅ ብቃቱን አሟላች።
21. ጥናቶቻችን እርምጃ ለመውሰድ ይበልጥ እንዲነሳሱ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
21 “የሚያሳድገው” ይሖዋ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን። (1 ቆሮ. 3:7) አምላክ ምን እንደሚጠብቅባቸው በማስተማር ብቻ አንወሰንም። ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር እንዲያዳብሩ እንረዳቸዋለን። ቅድሚያ በሚሰጡት ነገር ረገድ ማስተካከያ በማድረግ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳዩ እናበረታታቸዋለን። በተጨማሪም ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በይሖዋ መታመን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እናስተምራቸዋለን። እንደምንተማመንባቸው መግለጻችን እነሱም በይሖዋ መሥፈርቶች መመራትና ትክክለኛውን እርምጃ መውሰድ እንደሚችሉ እንዲተማመኑ ይረዳቸዋል።
መዝሙር 55 አትፍሯቸው!
a ኒቆዲሞስ ከኢየሱስ ጋር ከተነጋገረ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላም የአይሁዳውያን ከፍተኛ ሸንጎ አባል ነበር። (ዮሐ. 7:45-52) አንድ ማመሣከሪያ ጽሑፍ አንዳንድ መረጃዎችን መሠረት አድርጎ እንደገለጸው ኒቆዲሞስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ነው።—ዮሐ. 19:38-40
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ጴጥሮስና ሌሎቹ ዓሣ አጥማጆች ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ትተው ኢየሱስን ተከትለውታል።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት፣ እምነቷን በይፋ እንድታካፍል ጥናቷን ስትረዳት።