የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 5:- 1000–31 ከዘአበ ገደማ—ከንቱ የሆኑ አፈ ታሪካዊ አማልክት
“ማንኛውም ሃይማኖት የመነጨው ከእስያ ነው።” የጃፓናውያን ምሳሌ
ጃፓናውያኑ አልተሳሳቱም። የሃይማኖት ሥረ መሠረቱ የሚገኘው እስያ ውስጥ ነው። በተለይም በዓለም ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ የሆኑ ትምህርቶችና ሃይማኖታዊ ልማዶች የመጡት በእስያ ከምትገኘው ከጥንቷ ባቢሎን ነው።
ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎንያ ኤንድ አሲሪያ የተባለው መጽሐፍ ይህን ሐቅ ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል:- “ግብጽ፣ ፋርስና ግሪክ የባቢሎናውያን ሃይማኖት አሻራውን ጥሎባቸዋል . . . ሴማዊ ትምህርቶች ከጥንቱ የግሪክ አፈ ታሪክ ጋርም ሆነ ከግሪካውያን የጣዖት አምልኮ ጋር በእጅጉ የተቀላቀሉ ለመሆኑ ምንም ተጨማሪ አስተያየት እንደማያሻው በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን በአሁኑ ጊዜ በጥቅሉ ታምኖበታል። እነዚህ ሴማዊ ትምህርቶች በአብዛኛው ባቢሎናዊ ናቸው።”
በግሪክ አፈ ታሪክ ውስጥ ያሉት እነዚህ ባቢሎናዊ ትምህርቶች በቀላሉ ወደ ጥንቱ የግሪክ ሃይማኖት ገብተዋል። ስለ ጥንቱ የግሪክ ሃይማኖት ሲናገር ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ይላል፤ “ለሁልጊዜው ቋሚ ሆኖ የሚያገለግል እውነት የሰፈረበት አንድም ቅዱስ መጽሐፍ አልነበረም . . . አንድ ሰው በልጅነቱ የተማራቸውን እጅግ ብዙ አፈ ታሪኮች እንደሚያምንባቸው ለማሳየት አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን መፈጸሙ በቂ ነበር። እነዚህ ታሪኮች እያንዳንዳቸው በተለያየ መልክ ይቀርቡ ነበር፤ ይህም ለብዙ ዓይነት አተረጓጎም ሰፊ በር ከፍቷል።”
በስምንተኛው ወይም በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር እንደነበር የሚነገርለት የታወቀው ግሪካዊ ባለቅኔ ሆሜር በጻፋቸው በኢልያድና በኦዲሴ ውስጥ ይህን የመሰሉ ታሪኮች ይገኛሉ። በኦሊምፐስ ተራራ አፈ ታሪካዊ አማልክትና እንደ ጀግና ተቆጥረው ከፍተኛ ክብር የሚሰጣቸውን አምላክ መሰል ግለሰቦችን ጨምሮ በሰዎች መካከል ያለውን ዝምድና የሚያጎሉት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ ለግሪክ ሃይማኖት ጥሩ መሠረት ሆኑ። ጂ ኤስ ኪርክ የተባሉት ጸሐፊ “አፈ ታሪክና ሃይማኖት የተሳሰሩ ነገሮች ናቸው” በማለት የገለጹት በዚህ ምክንያት ነው።
ለግሪክ ሃይማኖት መገኛ የሆኑ ሌሎች ምንጮችም ነበሩ። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ይህን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ “ልዩ የሆነ ቅንዓት በማሳየት ለምሥጢራዊ ሃይማኖቶች ከፍተኛውን ቦታ የሰጠው የጥንቱ የግሪክ ትውልድ የኦስሪስን፣ የአይሲስንና የሆረስን የጣዖት አምልኮ [ከግብጽ] ወርሷል።” ከዚያ ተነስተው “በመላው የሮማ ግዛት ውስጥ ተሰራጩ።” ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
የግሪክ አፈ ታሪክ ሮምን ምርኮኛው አደረገ
የጥንቶቹ የሮማውያን አባቶች ብዙም ያልተወሳሰበ ሃይማኖት ነበራቸው። አማልክታቸው የሕያው አካልነት ባሕርይ የሌላቸውና በሁሉም ዓይነት ግዑዛን ነገሮች ውስጥ የሰረጹ መናፍስት እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር። ሃይማኖታቸው እፀዋትና እንስሳት ገድ አላቸው የሚልና አስማቶችን ያካተቱ አጉል እምነቶች ነበሩት። ሰዎች ስጦታ የሚለዋወጡበትን በታኅሣሥ የሚከበረውን ሳተርናሊያን የመሰሉ ዓመታዊ በዓሎች ይከበሩ ነበር። ኢምፔሪያል ሮም የተባለው መጽሐፍ ይህን ሁኔታ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል:- “በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እምብዛም ትኩረት የማይሰጥበት የወጎችና የሥርዓት ሃይማኖት ነው። ሮማዊው ሰው እናንተ እንዲህ ታደርጉልኛላችሁ፤ እኔ ደግሞ ለእናንተ እንዲህ አደርግላችኋለሁ ብሎ ለአማልክቱ ይሳላል። ለዚህ ሰው ሃይማኖቱ ይህን ስለቱን በጥንቃቄ መጠበቅ ነው።” በዚህም ምክንያት ሃይማኖቱ በመንፈሳዊ ገጽታው ባዶ ሆነ፤ ይህም ሮማውያን መንፈሳዊ ምግብ ፍለጋ እንዲባዝኑ አደረጋቸው።
ከጊዜ በኋላ ኤትሩስካኖች ይበልጥ የተወሳሰቡ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እንዲሁም ቤተ መቅደስ፣ ሐውልቶችና ምስሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአካባቢው ሥራ ላይ እንዲውሉ አደረጉ።a ይኸው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይናገራል፤ እነዚህ ሰዎች “ሮም ጥንት ከግሪክ የወንድና የሴት አማልክት ጋር ከፍተኛ የሆነ ዝምድና እንድታበጅ ያደረጉ ናቸው፤ ከጊዜ በኋላም ሮማውያን ከእነዚህ አማልክት መካከል አብዛኛዎቹን እንደያዙ ቀሩ።” ብዙም ሳይቆይ “ሃይማኖት በሮም ውስጥ ብዙ ስምና መልክ ያለው ሆነ፤ ሮማውያን በጦርነት ወይም በንግድ የያዟቸው አዲስ ሕዝቦች ሁሉ በሮማውያን አማልክት ላይ ሌሎች ተጨማሪ አማልክት የጨመሩ ይመስላል” ብሎ መናገር ይቻላል።
የጥንቶቹ የሮማ ቀሳውስት መንፈሳዊ ወይም ሥነምግባራዊ መሪዎች እንዲሆኑ አይጠበቅባቸውም ነበር። “አንድን አምላክ ለማነጋገር ምን ብሎ መጥራት እንደሚገባ፣ ከአምልኮው ጋር በተያያዘ የሚፈቀዱትንና የማይፈቀዱትን ነገሮችና የተወሳሰቡትን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች” ማወቁ ለእነርሱ በቂ ነበር ሲል ኢምፔሪያል ሮም የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። የዝቅተኛው ኅብረተሰብ ክፍል ናቸው ከሚባሉትና ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ለመውጣት አይበቁም ከሚባሉት ተራ ሰዎች ጋር ሲወዳደር በአመራር ቦታ ላይ ያሉ ቀሳውስት ከፍተኛ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሥልጣን ኮርቻ ላይ በቀላሉ መፈናጠጥ ይችሉ ነበር።
በዚህ መንገድ ሆሜር ከኖረበት ዘመን ጀምሮ ለአንድ ሺህ ዓመታት ያህል የግሪክ አፈ ታሪክ በግሪክም ሆነ በሮም ሃይማኖቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚህም ምክንያት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይናገራል፤ “የምዕራባውያንን የትምህርት፣ የሥነ ጥበብና ስሜት ቀስቃሽ ታሪክ ለመቅረጽ የግሪካውያን አፈ ታሪክ የተጫወተው ሚና በቀላሉ የሚገመት አልነበረም።” ቢያንስ ቢያንስ በሃይማኖታዊ ዓይን ሲታይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረው የላቲን ባለቅኔ ሆሬስ “ምርኮኛዋ ግሪክ ሮምን ምርኮኛዋ አደረገች” ብሎ መናገሩ ትክክል ነው ለማለት ይቻላል።
አንድ የግሪክ አምላክ ተነሣ
እስክንድር ሦስተኛ በ356 ከዘአበ በፔላ መቄዶንያ ውስጥ ተወለደ። ያደገው በንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ ስለሆነ በፍልስፍና፣ በሕክምናና በሳይንስ ረገድ ፍላጎቱ እንዲያድግ በረዳው በታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ በአሪስቶትል የመማር አጋጣሚ አግኝቷል። የአሪስቶትል የፍልስፍና ትምህርቶች የእስክንድርን አስተሳሰብ ምን ያህል እንደቀረጹት በትክክል አይታወቅም። ሆኖም እስክንድር የንባብ ጥማት የነበረው ሰው በመሆኑና ለሆሜር አፈ ታሪካዊ ጽሑፎች ልዩ ፍቅር ስለነበረው ሆሜር በእርሱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣቱ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲያውም ኢሊያድን በቃሉ እንዳጠና ይነገርለታል። ይህም 15,693 የግጥም መስመሮችን በቃል ማጥናትን የሚጠይቅ በመሆኑ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
እስክንድር አባቱ ከተገደለ በኋላ በእርሱ እግር ተተክቶ በ20 ዓመቱ የመቄዶንያን ዙፋን ተቆናጠጠ። ወዲያውኑም የድል ዘመቻ ጀመረ። በዚህም ምክንያት ታላቁ እስክንድር የሚል ስም ተሰጠው። በአጠቃላይ በምድር ላይ ከተነሱት ታላላቅ የጦር ሰዎች መካከል አንዱ ሆነ። ታላቅነቱ ወደ መመለክ ደረጃ አደረሰው። ከመሞቱ በፊትም ሆነ በኋላ የመለኮትነት ባህርይ እንዳለው ተደርጎ ይቆጠር ነበር።
እስክንድር ፋርሳውያንን ከግብጽ ቀንበር አላቀቃቸው። በዚህም ምክንያት በግብጻውያን ዘንድ ነፃ አውጪ ተብሎ ተወደሰ። ማን ሚት ኤንድ ማጂክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፤ “ልክ እንደ ፈርዖን ተደርጎ ተቆጠረ፤ ቄሶች አሞን ከተባለው አምላክ ጋር ይነጋገሩበታል የሚባለውን ሥፍራ ሲጎበኝም . . . ቄሱ ‘የአሞን ልጅ’ ብሎ በይፋ በመጥራት አወደሰው።” እስክንድር የጥንት ግሪክ አማልክት የበላይ አምላክ የሆነው የዚየስ ልጅ እንደሆነ የሚነገርለት ምናልባት በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
እስክንድር በምሥራቅ በኩል እየገፋ በመሄድ በመጨረሻ ህንድ ደረሰ። እግረ መንገዱንም በትውልድ አገሩ አፈ ታሪክና ሃይማኖት ውስጥ የሚገኙት ብዙ ሐሳቦች የመነጩባትን ባቢሎንን ድል አደረጋት። የግዛቱ መናገሻ ሊያደርጋት ማቀዱ ተገቢ የሆነው ለዚህ ነው። ይሁን እንጂ ከ12 ዓመታት ብዙም ለማይበልጡ ጊዜያት ከገዛ በኋላ ታላቁ የግሪክ አምላክ ሰኔ 13,323 ከዘአበ በ32 ዓመቱ ተቀጨ!
ታላቅ አክብሮት የተሰጠው ሮማዊ አምላክ
የሮም ከተማ አጎራባች በሆነው የኢጣሊያ ባህረ ገብ መሬት ላይ የተቆረቆረችው ግሪክ በእስክንድር አመራር ሥር ሆና የዓለምን ኃይል ከመጨበጧ ከብዙ ዘመናት በፊት በስምንተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ከዘአበ ነበር። እስክንድር ከሞተ በኋላ የዓለም ኃይል ሚዛን ቀስ በቀስ ወደ ሮም አዘመመ። የሮማ ግዛት መሪ የነበረው ጄነራል ጁሊየስ ቄሣር በ44 ከዘአበ ተገደለ። ከ13 የሽብርና የሁከት ዓመታት በኋላም የእርሱ የማደጎ ልጅ የነበረው ኦክታቪያን ተቀናቃኞቹን ድል አደረገና በ31 ከዘአበ የሮማን ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት አቋቋመ።
ኢምፔሪያል ሮም የተባለው መጽሐፍ “ሮማውያን ኦገስተስ ብለው ሰይመውታል፤ ትርጓሜውም ‘የተከበረው’ ማለት ነው። የገጠሩ ሕዝብ ደግሞ እንደ አምላክ አድርጎ ያወድሰው ነበር” በማለት “ከብዙዎቹ የሮም ገዥዎች ሁሉ የላቀ” ብሎ ይጠራዋል። እነዚህን ሐሳቦች ለመደገፍ የተደረገ ይመስል፣ ኦገስተስ እላዩ ላይ የእሱንና ከእሱ በፊት ሕይወቱ ያለፈውን የእስክንድርን ምስል የያዘ ማኅተም አሰርቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ የሮማ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ኦገስተስን እንደ አምላክ ተደርጎ እንዲታይ ወሰነ። ለእርሱ ክብር ሲባልም በመላው ግዛት ውስጥ ቅዱስ የአምልኮ ቤት ተሠራለት።
የተሰጣቸው ስም የሚገባቸው ነበሩን?
በዛሬው ጊዜ የሮማ ወይም የግሪክ አማልክት ለዓለም ሰላምና ደህንነት ያመጣሉ ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ማንም የለም። ከኦሊምፐስ ተራራ ሆነው ይገዙ ነበር በሚባልላቸው አፈ ታሪካዊ አማልክትም ላይ ሆነ በፖለቲካዊ ሥልጣን መንበር ላይ ሆነው በገዙት ሰብአዊ ፍጡሮች ላይ ማንም ተስፋውን አይጥልም። ይሁንና የሐሰት ሃይማኖቶች ከእስያ ከመነጩበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ስሙን በተሸከሙ ብቃቱ ግን በሌላቸው አፈታሪካዊ አማልክት እንዲያምኑ በማድረግ ሰዎችን በተሳሳተ መንገድ መምራታቸውን ቀጥለዋል። በአሌክሳንደር ዘንድ ተወዳጅ የነበረው ሆሜር በኢሊያድ ላይ “ያለ ሥራ የሚሰጥ ስም ዋጋ የለውም” ብሎ መጻፉ ተገቢ ነው።
ጥንታውያን ግሪኮች ኢሊያድን “የጥሩ ሥነ ምግባር ምንጭ፣ አልፎ ተርፎም ተግባራዊ የሆነ መመሪያ አድርገው” ይመለከቱት እንደነበር ይነገራል። ዛሬም በዚሁ መንገድ የሚታዩ ሌሎች ብዙ ጽሑፎች አሉ። በሚቀጥለው እትም ላይ የሚወጣው ርዕስ እንዲህ ዓይነቶቹን በብዙ ቅጂዎች የተሰራጩ ሃይማኖታዊ መጻሕፍት እንዴት በትክክል መመዘን እንደሚቻል የሚያብራራ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢትሩስካኖች ከየት የመጡ ሕዝቦች ናቸው? ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አወዛጋቢ ነው፤ ሆኖም በስምንተኛው ወይም በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እስያዊ ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን ይዘው ከግሪክ በደቡብ ምሥራቅ ከሚገኘው ሥፍራ ወደ ኢጣሊያ የፈለሱ ሕዝቦች ናቸው በማለት የሚናገረው ታሪክ ሰፊ ድጋፍ አግኝቷል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በየስፍራው የተሰራጨው የግሪክ እምነት
የጥንቶቹ ግሪኮች ሃይማኖት ለሚለው ቃል ራሱን የቻለ አንድ ቃል አልነበራቸውም። ይህን ለማመልከት ዩሴቢያ የተባለውን ቃል ይጠቀሙ ነበር። ይህ ቃል “እምነት”፣ “በአማልክቱ ዓይን ጥሩ የሆነ ምግባር”፣ “ተገቢ አክብሮት ማሳየት” እና “ለአምላክ ያደሩ መሆን” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።b
ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ምንም እንኳን የግሪክ ሃይማኖት ከብዙ ዘመናት በፊት ያቆጠቆጠ ቢሆንም በደንብ በደረጀ መልኩ ሆሜር ከኖረበት ዘመን ጀምሮ (በ9ኛው ወይም በ8ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሳይሆን አይቀርም) እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ጁሊያን የግዛት ዘመን ድረስ (በ4ኛው መቶ ዘመን እዘአ) ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዓመታት ቆይቷል። በዚያ ወቅት በምዕራብ እስከ ስፔይን፣ በምሥራቅ እስከ ኢንደስ ወንዝ እንዲሁም በሜድትራኒያን አካባቢ ወዳሉ አገሮች ድረስ በመዛመት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። የግሪክ ሃይማኖት የጣለው አሻራ አማልክቶቻቸው ከግሪክ አማልክት ጋር አንድ እንደሆኑ አድርገው በሚያምኑት ሮማውያን ላይ ይበልጥ ጎላ ብሎ ያታያል። በክርስትና ዘመን በደቡብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የነበሩት የማርያም ምስሎች ልዩ የሆነውን የአካባቢውን የጣዖት አምልኮ ሲያንጸባረቁ የግሪክ ጀግኖችና አልፎ ተርፎም ጣዖቶቻቸው ግን እንደ ቅዱስ ተደርገው በመቆጠር ወደ ክርስትና መዝለቃቸው አልቀረም ነበር።”
የጥንት ክርስቲያኖች የግሪክና የሮማ የሐሰት አማልክት አምልኮ በአገልግሎታቸው ወቅት ብዙ ጊዜ ያጋጥማቸው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሊቃኦንያ ቋንቋ:- አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል አሉ፤ በርናባስንም ድያ [ዚየስ አዓት ] አሉት [የግሪክ አማልክት መሪ የሆነ አምላክ ነው]፤ ጳውሎስንም እርሱ በመናገር ዋና ስለነበረ ሄርሜን አሉት [ለሌሎች አማልክት መልእክተኛ ሆኖ የሚያገለግል አምላክ ነበር።] በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፣ እንዲህም አሉ:- እናንተ ሰዎች፣ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፣ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ እንሰብካለን።” — ሥራ 14:11–15
[የግርጌ ማስታወሻ]
b ኒውዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው ዘ ኪንግደም ኢንተርሊንየር ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ግሪክ ስክሪፕቸርስ በተባለው መጽሐፍ ላይ 1 ጢሞቴዎስ 4:7,8ን ተመልከት።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የግሪክና የሮማ አማልክት
ብዙዎቹ የግሪክ አፈ ታሪክ ተባዕትና እንስት አማልክት በሮማውያን አፈ ታሪክ ውስጥ አንድ ዓይነት ቦታ ተሰጥቷቸዋል። አንዳንድ የግሪክና የሮማውያን ዋና ዋና አማልክት ከታች ባለው ሰንጠረዥ ላይ ተዘርዝረዋል።
የግሪክ የሮማውያን የአማልክቱ ቦታ
አፍሮዳይት ቬነስ የፍቅር እንስት አምላክ
አፖሎ አፖሎ የብርሃን፣ የሕክምናና የግጥም አምላክ
አርስ ማርስ የጦርነት አምላክ
አርጤምስ ዲያና የአደንና የወሊድ እንስት አምላክ
አስክሌፒየስ ኤስኩላፒየስ የፈውስ አምላክ
አቴና ሚኔርቫ የእጅ ሙያ፣ የጦርነትና የጥበብ እንስት አምላክ
ክሮነስ ሳተርን በግሪክ አፈ ታሪክ የቲታንስ አለቃና የዚየስ አባት፤ በሮማ አፈ ታሪክ የእርሻ አምላክ
ዲሜተር ሴሬስ የሚያድጉ ነገሮች እንስት አምላክ
ዳዮኒሰስ ባቸስ የወይን፣ የመራባትና የአውሬያዊ ጠባይ አምላክ
ኤሮስ ኩፒድ የፍቅር አምላክ
ጌአ ቴራ የመሬት ተምሳሌት፣ የኡራነስ እናትና ሚስት
ሄፔስተስ ቩልካን የአማልክቱ ቀጥቃጭና፣ የእሳትና የብረታ ብረት ሙያ አምላክ
ሄራ ጁኖ ጋብቻንና ሴቶችን የምትጠብቅ። በግሪክ አፈ ታሪክ የዚየስ እህትና ሚስት፤ በሮማ አፈ ታሪክ የጁፒተር ሚስት
ሄርሜን ሜርኩሪ የአማልክቱ መልእክተኛ፤ የንግድ ሥራና የሳይንስ አምላክ፤ መንገደኞችን፣ ሌቦችንና ወመኔዎችን የሚጠብቅ
ሄስታ ቬስታ የምድጃ እንስት አምላክ
ሃይፕኖስ ሶምነስ የእንቅልፍ አምላክ
AT,ፕሉቶ ወይም ሔድስ ፕሉቶ የታችኛው ዓለም አምላክ
ፖዚደን ኔፕትዩን የባሕር አምላክ። በግሪክ አፈ ታሪክ የመሬት መንቀጥቀጥና የፈረሶችም አምላክ ነው
ሬአ ኦፕስ የክሮነስ ሚስትና እህት
ኡራነስ ኡራነስ የጌአ ልጅና ባል እንዲሁም የቲታንስ አባት
ዚየስ ጁፒተር የአማልክት አለቃ
በ1987 ከታተመው “ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ” ጥራዝ 13, ገጽ 820 ላይ የተወሰደ
[ሥዕል]
ሄርሜን
ዲያና
አስክሌፒየስ
ጁፒተር
[ምንጭ]
Photo Sources:Hermes,Diana,Jupiter—Courtesy of British Museum,London
Asclepius—National Archaeological Museum,Athens,Greece
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጀርመን ዌዝል ከተማ መግቢያ ላይ ሐውልቷ ጉብ ብሎ የሚታየው የጦርነትና የጥበብ እንስት አምላክ አቴና