የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 9:- ከ551 ከዘአበ ጀምሮ—በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ትክክለኛውን መንገድ ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
“የእውነት መንገድ እንደ ትልቅ ጎዳና ነው።”—መንግ–ጹ፣ በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረ ቻይናዊ ፈላስፋ
መዳንን የሚያስገኘው የእውነት መንገድ የእኛ ነው የሚሉ ሃይማኖቶች ቁጥር በጣም ብዙ ነው። ለምሳሌ ያህል ኮንፊሽያኒዝም፣ ታኦኢዝምና ቡድሂዝም የቻይና “ሦስት መንገዶች” ተብለው ተጠርተዋል። የጃፓንና የኮሪያ ሃይማኖቶችም በተመሳሳይ ቃላት ይጠቀማሉ። ታዲያ እነዚህ የተለያዩ “መንገዶች” ልዩነት ይኖራቸዋልን? የሚለያዩትስ እንዴት ነው?
ኮንፊሽያኒዝም፣ የሰው መንገድ
ስለ ኮንፊሽየስ የሚታወቀው በጣም ጥቂት ቢሆንም አንድ የታወቀ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “በዓለም ታሪክ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩት ሰዎች እንደ አንዱ መቆጠር ይኖርበታል” ይላል። ይህ መምህር፣ ፈላስፋና የፖለቲካ ሐሳብ አመንጪ የነበረ ሰው በሕይወት የኖረው ከ551 ከዘአበ እስከ 479 ከዘአበ ነበር። የቤተሰብ ስሙ ኩንግ ይባል ስለነበረ ከጊዜ በኋላ ኩንግ–ፉ–ጹ ተብሎ ተጠርቷል። ትርጓሜውም “ጌታ ኩንግ” ማለት ነው። በላቲኑ አጠራር ኮንፊሽየስ ይባላል።
ኮንፊሽየስ አዲስ ሃይማኖት አላቋቋመም። ዘ ቫይኪንግ ፖርተብል ላይብረሪ ወርልድ ባይብል እንደሚለው “ከጥንት ዘመን ጀምሮ በትውልድ አገሩ የነበረውን በማደራጀት ለመጻሕፍቱ መልክና ቅርጽ፣ ለአከባበር ሥርዓቶቹ ክብር፣ ለሥነ ምግባር ጽንሰ ሐሳቦች የበለጠ ትኩረት ሰጥቷል።” ዋነኛ ትኩረቱ በሃይማኖታዊ ትምህርት ላይ ሳይሆን በሰብዓዊ ባሕርይ ላይ ነበር። ትምህርቱ ቅድሚያ የሰጠው ለማኅበራዊ ሥነ ምግባር ነበር። የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት ሙከራ ያደረገው የሕዝቡን ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው ነበር። ስለዚህ የዚህ ሃይማኖታዊ መሪ ከመሆን ይልቅ ሙከራው ያልተሳካለት ፖለቲከኛ ፍልስፍና “ኮንፊሽየሳዊ የሰው መንገድ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።
ኮንፊሽየስ በዘመኑ ለነበረው ሃይማኖት ትልቅ አክብሮት አልነበረውም፤ አብዛኛው ሃይማኖት መሠረት በሌለው አጉል እምነት ላይ የተመሠረተ ነው ይል ነበር። በአምላክ ያምን እንደሆነ ሲጠየቅ “ይህን ጥያቄ ባልመልሰው እመርጣለሁ” እንዳለ ይነገራል። ይሁን እንጂ “ሰማይ” የሚል ትርጉም ያለውን ቲየን የሚል ቃል ደጋግሞ መጥቀሱን አንዳንዶች አካል ከሌለው ታላቅ ኃይል በበለጠ ነገር ያምን ነበር የሚል ትርጉም ሰጥተውታል።
ኮንፊሽየስ በቤተሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባ ሥነ ምግባር፣ ባለ ሥልጣኖችን ስለ ማክበርና ስለ ማኅበረሰባዊ ስምምነት አጥብቆ ይገልጽ ነበር። ሌሎችን ለማገልገል የሚያስፈልጉትን ችሎታዎችና የግል ባሕርያት ለማዳበርና ለማጠናከር ትምህርት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያሳስብ ነበር። ለሰው ልጆች በአጠቃላይ በጎ ማድረግ፣ በተለይ ደግሞ ለቅርብ ዘመዶች የወንድምነት ፍቅርና አክብሮት ማሳየት የሚል ትርጉም ስላለው ጄን የተባለ ቃል አጥብቆ ይናገር ነበር። የቀድሞ አባቶችን አምልኮ ያበረታታ ነበር።
እነዚህ የኮንፊሽየስ ትምህርት መለያ የሆኑት ባሕርያት አሁንም በኮንፊሽየስ ትምህርት ተኮትኩተው ባደጉ እስያውያን ላይ ይታያሉ። በቺካጎ የኤሊኖይስ ዩኒቨርስቲ ሶሺዮሎጂስት የሆኑት ዊልያም ሊው “የኮንፊሽየስ ሥነ ምግባር ሰዎችን ለሥራ ይገፋፋል፣ ከወላጆቻቸው እንዲበልጡና ወላጆቻቸው የጣሉባቸውን ዕዳ እንዲከፍሉ ይገፋፋል” ብለዋል። በዚህ ምክንያት የኮንፊሽየስ ተጽዕኖ አይሎ ከሚታይባቸው አገሮች የመጡ ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በጣም ከፍተኛ በሆነ የትምህርት ደረጃ ላይ በመድረስ የታወቁ ሆነዋል።
የኮንፊሽየስ ፍልስፍና የተመሠረተው ው ቺንግ (አምስቱ ክላሲኮች) በሚባሉት የመጻሕፍት ስብስብ ላይ ነው። በ12ኛው መቶ ዘመን የተጨመሩት “አራቱ መጻሕፍት” ወይም ሱ ሹ የሚባሉት ለኮንፊሽየስ ፍልስፍና እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ ይቆጠራሉ። የአጻጻፋቸው ስልት በጣም አጭርና ክትት ያለ በመሆኑ ምክንያት መጻሕፍቱን ለመረዳት ያስቸግራል።
በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ በሰሜን ኮሪያ በሚገኘው በኮኩሪዮ ንጉሣዊ መንግሥት ውስጥ የኮንፊሽየስ ፍልስፍና ትምህርት ይሰጥ ነበር። በተጨማሪም የኮንፊሽየስ ትምህርት ወደ ጃፓን የተዛመተው ምናልባት በአምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። በዚሁ ጊዜ ላይ ግን በቻይና ሌላ ዓይነት “መንገድ” መስፋፋት ጀምሯል።
ታኦኢዝም፣ የተፈጥሮ መንገድ
በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት የቻይናውያን አስተሳሰብ መሠረት ሆኖ የቆየው ታኦ “መንገድ” ወይም “ጎዳና” ማለት ነው። ማንኛውንም ነገር ጽንፈ ዓለሙ ከሚንቀሳቀስበት የተፈጥሮ መንገድ ጋር ተስማምቶ በትክክል መፈጸሙን የሚያመለክት ቃል ነው። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አፈ ታሪክ እንደሚለው የታኦኢዝም መሥራች ኮንፊሽየስ ይኖር በነበረበት ዘመን የኖረ ላኦ ጼ የሚል የማዕረግ ስም የነበረው ሰው ነው። ትርጉሙም “ሽማግሌው ልጅ” ወይም “አዛውንቱ (ሊከበር የሚገባው) ፈላስፋ” ማለት ነው። አንዳንዶች ይህ ስም ለላኦ ጼ የተሰጠው እናቱ በተአምር ከፀነሰች በኋላ ለብዙ ዓመታት በማኅጸኗ ውስጥ ከማርጀቱ የተነሣ ፀጉሩ ሸብቶ ስለተወለደ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ የማዕረግ ስም የተሰጠው ጥበብ ለተሞላባቸው ትምህርቶቹ አክብሮት ለማሳየት ነው ይላሉ።
ታኦኢዝም አንድ ሕፃን በሚወለድበት ጊዜ “የመጀመሪያ እስትንፋስ” ወይም የሕይወት ኃይል እንደሚሰጠው ያስተምራል። በተመስጦ እንደማሰላሰል፣ የተወሰኑ ምግቦችን እንደ መመገብና፣ ትንፋሽንና የጾታ ስሜትን እንደ መቆጣጠር ባሉ የተለያዩ መንገዶች ይህ የሕይወት ኃይል አላግባብ እንዳይባክን ማድረግ ይቻላል። በዚህ መንገድ ረዥም ዕድሜ ከቅድስና ጋር ተመሳሳይ ነው ብሎ ያስተምራል።
የሰው አካል ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ እንዲኖር መደረግ ያለበት ራሱን የቻለ አነስተኛ ጽንፈ ዓለም እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ይህ ደግሞ ቻይናውያን ዪን እና ያንግ የሚሉት ነው። ቃል በቃል ሲተረጎም ፀሐይ የሚያርፍበትና ጥላ የሚያርፍበት የኮረብታ ክፍል ማለት ነው። እነዚህ ለቻይናውያን ፍልስፍና መሠረት የሆኑት ዪን እና ያንግ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮች በሙሉ የተገነቡባቸው እርስበርሳቸው የሚቃረኑ ግን አንዳቸው ለሌላው ማሟያ የሚሆኑ ንጥረ ነገሮች ናቸው። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ዪን ጨለማ፣ ጥላ፣ ቀዝቃዛ፣ እርጥብ፣ እየከሰመ በሚሄድ፣ በሚጎብጥ፣ ምድራዊና አነስታይ በሆነ ነገር ሁሉ ላይ የሚሠለጥን ሲሆን ያንግ ደግሞ ብሩህ፣ ትኩስ፣ ደረቅ፣ እያደገ በሚሄድ፣ ግትርና ጠበኛ፣ ሰማያዊና ተባዕት በሆነ ነገር ሁሉ ላይ ይሠለጥናል።” ፌንግ–ሹዊ የሚባለውና በእንግሊዝኛ ጂኦማንሲ ተብሎ የሚጠራው የጥንቆላ ዓይነት ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ሥራ ላይ ከዋለባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ይህ የጥንቆላ ዓይነት ከተሞችና ቤቶች፣ በተለይም የመቃብር ቦታዎች የሚሠሩበትን አመቺ ቦታ ለመምረጥ የሚጠቀሙበት ነው። የሚመረጠውን ቦታ የዪን እና ያንግ ኃይሎችን ከነዋሪዎቹ ጋር ማስማማት የነዋሪዎቹን ደህንነት እንዲጠበቅ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። የፕሪንስተን ዩኒቨርስቲዋ ሄለን ሃርዳክር “የጠፈር ኃይላት ጥምረት የሚሞተውን ሰው እንደሚጠቅምና በሌላው ዓለም ውስጥ የሚያገኘውን ዕድገት እንደሚያፋጥንለት ይታመናል” በማለት ያብራራሉ።
ይሁን እንጂ የዪን–ያንግ ኃይላትን ሚዛን ለመጠበቅ ጥረት ቢደረግም በተፈጥሮ ያሉበትን ሁኔታ በግድ ለመለወጥ ሙከራ መደረግ አይኖርበትም። ይህን ማድረግ ያልተፈለገ ውጤት ያስከትላል ተብሎ ስለሚታመን የሚመጣውን ሁሉ በእሺታ መቀበልን የሚያደፋፍር እምነት ነው። አንድ አረጋዊ መነኩሴ በ1986 እንዲህ በማለት አስረድተዋል:- “ታኦኢዝም የሚያስተምረው ፀጥ ማለትንና ምንም ነገር አለማድረግን ነው። ምንም ነገር አለማድረግ ሁሉንም ነገር ማድረግ ነው።” በዚህ ምክንያት የታኦኢዝም ኃይል ለስላሳ ሆኖ ፍጥረትን ሁሉ በሚጠቅመው በውሃ ተመስሏል።
የታኦን ፍልስፍና (በ4ኛ/በ3ኛ መቶ ዘመን ከዘአበ) ከታኦ ሃይማኖት (በ2ኛ/በ3ኛ መቶ ዘመን እዘአ) መለየት የተለመደ የነበረበት ጊዜ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ አይታይም። ምክንያቱም የታኦ ሃይማኖት የመነጨው ከእርሱ በፊት ከነበረው የታኦ ፍልስፍና ነው። የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ሃንስ–ጆአኪም ሾየፕስ የታኦኢዝም ሃይማኖት “የጥንቱ የቻይናውያን ባህላዊ ሃይማኖት ቅጥያ ነው። የሃይማኖቱ እምብርት መናፍስትነት ነው። . . . [እነዚህ መናፍስት] በማንኛውም ቦታ እየኖሩ በሰው ሕይወትና ጤንነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ይላል። . . . በዛሬይቱ ቻይና ሰፊው ሕዝብ ታኦኢዝምን የሚመለከተው በአጉል እምነት ላይ እንደተመሠረተ ሃይማኖት አድርጎ ነው” ብለዋል።
ሺንቶ፣ የካሚ መንገድ
ጃፓን በአንድ ሌላ ሃይማኖትም ትታወቃለች። ይህ ሃይማኖት አንድ ደራሲ እንደገለጹት “የብዙ አማልክትን አምልኮና የቀድሞ አባቶችን አምልኮ የሚያጣምር ነው።” በመጀመሪያ ይህ ባሕላዊ ሃይማኖት መጠሪያ ስም አልነበረውም። ቡድሂዝም በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ ወደ ጃፓን በገባ ጊዜ ለቡድሂዝም ከተሰጡት ስሞች አንዱ ባትሱዶ ነበር። ትርጉሙም “የቡድሃ መንገድ” ማለት ነው። ስለዚህ ይህንን ሃይማኖት አገር በቀል ከሆነው ሃይማኖት ለመለየት ሲባል ለጃፓናውያኑ ሃይማኖት ሺንቶ የሚል ስም ተሰጠ። ትርጉሙም “የካሚ መንገድ” ማለት ነው።
የሺንቶ ዋነኛ ትኩረት ካሚ (የተለያዩ ብዙ አማልክት) ነው። ካሚ ማንኛውንም ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ወይም አምላክ፣ የተፈጥሮ አማልክትን፣ ታላላቅ ሰዎችን፣ የአምላክነት ክብር የተሰጣቸውን የቀድሞ አባቶች፣ “አንድን ዓላማ የሚያስፈጽሙ ወይም አንድን ረቂቅ ኃይል የሚወክሉ አማልክትን” ጭምር የሚያመለክት ቃል ሆኗል። (ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ) ያኦዮሮዙ–ኖ–ካሚ የሚለው ቃል ቃል በቃል ሲተረጎም ስምንት ሚልዮን አማልክት ማለት ቢሆንም በሺንቶ ሃይማኖት የሚመለኩት አማልክት በየጊዜው የሚጨምሩ በመሆኑ ቃሉ የሚያመለክተው “ብዙ አማልክትን” ነው። ሰዎች የካሚ ልጆች በመሆናቸው በዋነኛነት መለኮታዊ ባሕርይ አላቸው። ስለዚህ መሠረታዊው አስተሳሰብ ከካሚ ጋር ተስማምቶ በመኖር የእነርሱን ጥበቃና ሞገስ ማግኘት ይቻላል የሚል ነው።
ሺንቶ ጠንከር ያለ ቀኖና ወይም ሃይማኖታዊ ትምህርት ባይኖረው ም በጃፓናውያን ባሕርይ፣ አስተሳሰብና ሥነ ምግባር ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሎአል። በፈለጉበት ጊዜ የአምልኮ ሥርዓት የሚፈጸሙባቸውን የአምልኮ ቤቶች አስገኝቶላቸዋል።
ዋና ዋናዎቹ የሺንቶ ዓይነቶች እርስ በርሳቸው የተዛመዱ ናቸ ው። የቤተ አምልኮው ሺንቶና ባህላዊው ሺንቶ ጥቂት ግልጽ የሆኑ ልዩነቶች አሏቸው። የኑፋቄ ሺንቶ የሚባሉት ግን በ19ኛው መቶ ዘመን የተመሠረቱትንና ከኮንፊሽያኒዝም፣ ከቡድሂዝምና ከታኦኢዝም በተለያየ መጠን አንዳንድ ነገሮችን የወሰዱትን 13 ኑፋቄዎች ናቸው።
በተለይ የቡድሂስት ሃይማኖት በሺንቶ ላይ ጠንካራ ተጽዕኖ አሳድሯል። ብዙ ጃፓናውያን ቡድሂስቶችም ሺንቶኢስቶችም የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው። ባህላዊ በሆኑ የጃፓናውያን ቤቶች ውስጥ ሁለት መሠዊያዎች ይኖራሉ። አንደኛው ካሚ የሚከበርበት የሺንቶ መሠዊያ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የቀድሞ አባቶች የሚከበሩበት የቡድሂስት መሠዊያ ነው። ኬኢኮ የተባለች አንዲት ጃፓናዊት ልጃገረድ “የቀድሞ አባቶቼን ማክበር ይኖርብኛል። ይህንንም የማሳየው በቡድሂዝም አማካኝነት ነው። . . . ጃፓናዊ እንደመሆኔ ደግሞ የሺንቶ የአምልኮ ሥርዓቶችን በሙሉ እፈጽማለሁ” ብላለች። ቀጥላም “ክርስቲያን ባገባ በጣም ጥሩ እንደሚሆን ተሰማኝ። እርስ በርሱ የሚቃረን ነገር ነው። ግን ምን አለበት?” ብላለች።
ቾንዶግዮ—የኮሪያውያን የሰማያዊ መንገድ ሃይማኖት
ክርስቲያን ያልሆኑ ኮሪያውያን ከሚከተሏቸው ዋነኛ ሃይማኖቶች አንዱ በታኦኢዝምና በኮንፊሽየኒዝም የዳበረ ቡድሂዝም ነው። እነዚህ ሃይማኖቶች ከቻይና እንደገቡ የኮሪያ ባህላዊ ሃይማኖት የሆነው ሻማኒዝም ተጽዕኖ አድርጎባቸዋል። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን እንደሚለው ይህ ሃይማኖት “በኮሪያ ልሳነ ምድር ከነበረው ማኅበረሰባዊና አእምሮአዊ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልክ ተመርጧል፣ ተለውጧል፣ ተሻሽሏል።”a
ሌላው በኮሪያ የሚገኝ ሃይማኖት “የሰማያዊ መንገድ ሃይማኖት” የሚል ትርጉም ያለው ቾንዶግዮ ነው። ይህ ስም የወጣለት በ1905 ነው። በ1860 በቾኤ ሱን (ቼው) የተመሠረተው ይህ ሃይማኖት በመጀመሪያ ቶንግሃክ፣ ማለትም “ምሥራቃዊ ትምህርት” ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህም ስም የወጣለት “ምዕራባዊ ትምህርት” የሚባል ስም ከተሰጠው ክርስትና ለመለየት ነው። ቾንዶግዮ የተመሠረተው በከፊል ይህን ሃይማኖት ለመቋቋም ነው። ጌርሃርድ ቤሊንገር የተባሉት ጀርመናዊ ደራሲ እንዳሉት ቾንዶግዮ “የኮንፊሽየስን ሰብዓዊ ደግነትና ፍትሕ፣ የታኦን አለተቃውሞ የመቀበል ትምህርት፣ የቡድሂስትን ርኅራኄ አንድ ላይ ለማዋሃድ ይሞክራል። የሃይማኖቱም መሥራች ዓላማው ይህ ነበር። በተጨማሪም ቾንዶግዮ ከሻማኒዝምና ከሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት አንዳንድ ነገሮችን ወስዷል። ይህ ሃይማኖት፣ ሃይማኖታዊ አንድነት አመጣለሁ ቢልም እስከ 1935 ድረስ 17 የሚያክሉ ኑፋቄዎች ከውስጡ ተለይተው ወጥተዋል።
“የሰማያዊው መንገድ ሃይማኖት” ዋነኛ እምነት የተመሠረተው የሰው ልጅ መለኮታዊ ባሕርይ ያለው የአምላክ ክፍል ነው በሚለው ትምህርት ላይ ነው። ስለዚህም ዋነኛው የሥነ ምግባር ደንብ ሳዪን ዮች ኦን (“ሰውን እንደ አምላክ ተመልከት”) የተባለው ነው። ይህም ሰዎች ሁሉ “በከፍተኛ አሳቢነት፣ በአክብሮት፣ በቅንነት፣ በእኩልነትና በፍትሕ እንዲያዙ ያዛል” በማለት የሮድ አይላንድ ዩኒቨርስቲው ዮንግ–ቹን ኪም ያብራራሉ።
የዚህ ሃይማኖት መሥራች የሆነው ሱን እነዚህን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋል ማኅበራዊውን ሥርዓት ለመለወጥ ያደረገው ጥረት ከመንግሥት ጋር አጋጭቶታል። በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባቱ ምክንያት እርሱም ሆነ ወራሹ ተገድለዋል። በተጨማሪም በ1894 በቻይናና በጃፓን መካከል የተደረገውን ጦርነት ከቀሰቀሱት ምክንያቶች መካከል አንደኛው ምክንያት ይህ ሃይማኖት ነበር። እንዲያውም በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባት የአዳዲሶቹ የኮሪያ ሃይማኖቶች ዋነኛ ባሕርይ ሆኗል። የቶንግሃክ እንቅስቃሴ ደግሞ ከእነዚህ አዳዲስ ሃይማኖቶች የመጀመሪያው ነው። የእነዚህ ሃይማኖቶች ዋነኛ መልእክት ብሔራዊ ስሜትን መቀስቀስ ነው። ኮሪያ ወደፊት በመላው ዓለም ላይ የበላይነት እንደሚኖራት ያስተምራሉ።
ወደ ሕይወት የሚመራው የትኛው “መንገድ” ነው?
ብዙዎቹ እስያውያን አንድ ሰው የትኛውንም “መንገድ” ቢከተል ምንም ለውጥ አይኖረውም ብለው እንደሚያምኑ ግልጽ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን “መንገድ” ተብሎ ይጠራ የነበረ ሃይማኖት የመሠረተው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አምላክ ሁሉንም ሃይማኖታዊ “መንገዶች” ይቀበላል የሚለውን አመለካከት አልተቀበለም። እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል:- “ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ . . . ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” — ሥራ 9:2፤ ማቴዎስ 7:13, 14 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት፤ ከምሳሌ 16:25 ጋር አወዳድር።
እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዶች ቃሉን አልተቀበሉም። ኢየሱስ እውነተኛ መሲሕ፣ ያስተማረው ሃይማኖት ደግሞ እውነተኛው “መንገድ” መስሎ አልታያቸውም። ዛሬ ከ19 መቶ ዘመናት በኋላ እንኳን የእነዚህ አይሁዳውያን ተወላጆች መሲሕ ይመጣል ብለው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የሚቀጥለው እትማችን ለምን እንዲህ እንደሚሉ ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሻማኒዝም የተመሠረተው በጥንቆላ ኃይል የመፈወስና ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር የመነጋገር ኃይል አለው ተብሎ በሚታመንበት ሻማን የተባለ ሃይማኖታዊ ሰው ላይ ነው።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጀኔራል ጉዋን ዩ፣ በቻይናዎች ባሕላዊ ሃይማኖት የጦርነት አምላክ፣ እንዲሁም የወታደርና የነጋዴ መደቦች ጠባቂ ነው
ከግራ ወደ ቀኝ፣ ሃን ሲያንግዚ፣ ሉዶንግቢን እና ሊ ቲጉዋይ እነዚህ የማይሞቱ ናቸው ከሚባሉት ከስምንቱ ታኦሲስት ሦስቱ ናቸው፤ እንዲሁም የረዥም ዕድሜ አምላክ የሆነው አስቴላር
[ምንጭ]
Courtesy of the British Museum
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሺንቶ ጸሎት ቤት ግቢ ውስጥ የተለያዩ ሐውልቶች ይገኛሉ። በግራ በኩል ያለው ጠባቂ ውሻ አጋንንትን ያባርራል ተብሎ ይታመናል
ተማሪዎችና ወላጆች ቶኩዮ በሚገኘው የዩሺማ ቴንጂን የሺንቶ ጸሎት ቤት ፈተና ለማለፍ እንዲችሉ ይጸልያሉ