ስለ ሃይማኖት ብዙ ግድ የሌለው ለምንድን ነው?
“ሃይማኖት የሌለው ሰው መስኮት እንደሌለው ቤት ነው።” ይህ አንድ ጃፓናዊ ሰው ለልጁ ለሚትሱኦ ስለሃይማኖት አስፈላጊነት ሲገልጽለት የተናገረው ቃል ነው። ሚትሱኦ ግን የአባቱን ቃል አላጤነም። በጃፓንም ሆነ በሌሎች አገሮች ቁጥራቸው እየበዛ የሚሄዱ ብዙ ሰዎች እንደ ሚትሱኦ እየተሰማቸው ሄዶአል። ሃይማኖታዊ ብርሃን በሕይወታቸው ውስጥ እንዲያበራ ስለማይፈልጉ መስኮት የሌላቸው ቤቶች ሆነው በመኖር ረክተዋል።
በዚህም ምክንያት ጃፓን ብሔራዊ የምግባር ጥናት ስታደርግ ከዜጎችዋ መካከል 69 በመቶ የሚያክሉት ራሳቸውን ሃይማኖተኞች እንደሆኑ አድርገው እንደማይቆጥሩ ተናግረዋል። በወጣቶች መካከል መጠኑ ከዚህ የበለጠ ነው። በተመሳሳይም በጣም ሃይማኖተኛ በነበረችው በታይላንድ አገር በከተሞች ከሚኖሩት ሰዎች 75 በመቶ የሚያክሉት ወደ ቡድሂስት ቤተመቅደሶች መሄዳቸውን አቁመዋል። በእንግሊዝ አገር ባለፉት 30 ዓመታት አንድ ስምንተኛ የሚያክሉት የአንግሊካን አብያተ ክርስቲያናት ተገልጋይ በማጣታቸው ምክንያት ተዘግተዋል።
በጃፓን ግን አሁንም ቢሆን የሃይማኖተኛነት መንፈስ አልጠፋም። ይሁን እንጂ ሃይማኖታቸው ብቅ የሚለው እንደውድ የሸክላ ዕቃ በሠርግና በቀብር ጊዜ ብቻ ነው። ሃይማኖት ተፈላጊ የሆነው በመንፈሳዊ ብርሃን ሰጪነቱ ሳይሆን የአካባቢውን ባሕልና የቤተሰብን ወግ ጠባቂ በመሆኑ ነው። ብዙዎች ሃይማኖትን የሚመለከቱት ለደካሞችና ለተጨነቁ ሰዎች ማታለያ እንደሆነ አድርገው ነው። ከሃይማኖት ሌላ ተጨባጭ ጥቅም ይገኛል ብለው አያስቡም። አንዳንዶች ‘ጊዜ ከኖረህና የሚያስፈልግህ ሆኖ ከተሰማህ ሃይማኖት ጥሩ ነው። ኑሮህን ለማሸነፍና ወጪህን ለመሸፈን ግን በራስህ መተማመን ይኖርብሃል’ ይላሉ።
ይህን የመሰለ ግድየለሽነት የኖረው ለምንድን ነው? ብዙ ምክንያት መስጠት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ የአካባቢ ተጽእኖ አለ። ብዙ ወጣቶች ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ማሠልጠኛ አልተሰጣቸውም፣ ቢሰጣቸውም በጣም አነስተኛ ነው። ስለዚህ ቁሳዊ ሀብት ለማሳደድ ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጥ ኅብረተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች ትልቅ ሰው ሲሆኑ በፍቅረ ነዋይ የተመረዙ መሆናቸው አያስደንቅም።
በአንዳንድ አገሮች የቴሌቪዥን ወንጌላውያንና ሌሎች ታዋቂ የሃይማኖት መሪዎች አሳፋሪ የስግብግብነትና የብልግና ባሕርይ ማሳየታቸው ሰዎችን ከሃይማኖት አርቆአቸዋል። በተጨማሪም ሃይማኖት በፖለቲካና በጦርነት ጉዳዮች ጣልቃ መግባቱ ሰዎች ከሃይማኖት እንዲርቁ አድርጎአቸዋል። ይህንንም በጃፓን አገር በሺንቶ ሃይማኖት ላይ ከደረሰው ለመረዳት እንችላለን። የጃፓን ሃይማኖቶች ኢንሳይክሎፒድያ እንዳለው “ጦርነቱ [ሁለተኛው የዓለም ጦርነት] በ1945 በሽንፈት ሲፈጸም የሺንቶ ቤተ ጸሎቶች ከባድ ችግር ተደቀነባቸው።” የጦርነቱን እሳት ሲያርገበግብና ድል የእኛ ነው ሲል የቆየው የሺንቶ ሃይማኖት የተናገረው ሁሉ ስላልተፈጸመ አማኞቹን አሳፈረ። አምላክም ሆነ ቡድሃ የሚባል ነገር የለም የሚለው ፍልስፍና በፍጥነት ተዛመተ።”
ይሁን እንጂ ጠባብና ራስ ወዳድ በሆነ አስተሳሰብ ተጠምደን አሁንና እዚህ በምናየው ብቻ በቃኝ ብለን መኖር ይገባናልን? አብዛኞቹ የሰው ልጆች ተመራማሪ አእምሮ አላቸው። ከየት እንደመጡ፣ ወዴት እንደሚሄዱ፣ ለምንና እንዴት እንደሚኖሩ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ተስፋ ያለመልማቸዋል። ስለ ሕይወት የሚነሱትን ጥያቄዎች ገሸሽ አድርጎ ማለፍ፤ ወይም “ስለእነዚህ ጉዳዮች ማወቅ አይቻልም” ብሎ ጥያቄዎቹን ማዳፈን አያረካቸውም። በአምላክ የማያምነው በርትራንድ ራሰል እንኳን “እንግዳ የሆነ ኃይለኛ ስቃይ፣ በዓለም ውስጥ ካሉት ነገሮች ባሻገር ያሉትን ነገሮች የመመርመር ፍላጎት” እንዳለው ተናግሮአል። እውነተኛው ሃይማኖት ይህንን ፍላጎት ለማርካት ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ይህን ያህል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሃይማኖት ስለመኖሩ ምን ማስረጃ አለን?