የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 17:- ከ1530 እዘአ ወዲህ የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ በእርግጥ ተሐድሶ ነበርን?
“አዲስ ነገር መፍጠር ተሐድሶ ሊባል አይችልም።”—የ18ኛው መቶ ዘመን የብሪታኒያ ፓርላማ አባል የነበሩት ኤድመንድ በርክ በብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት ፈቃድ
የፕሮቴስታንት ታሪክ ጸሐፊዎች የፕሮቴስታንት ተሐድሶ እውነተኛ ክርስትናን ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመለስ አድርጓል ብለው ያምናሉ። በአንፃሩ ደግሞ የካቶሊክ ምሁራን የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ለተሳሳተ ሃይማኖታዊ ትምህርት መፈጠር ምክንያት ሆኗል ይላሉ። ሆኖም ከበስተኋላ የሚገኘው ሃይማኖታዊ ታሪክ የሚገልጸው ምንድን ነው? የፕሮቴስታንት ተሐድሶ በእርግጥ ተሐድሶ ነበርን? ወይስ አንዱ ዓይነት የተሳሳተ አምልኮ በሌላ የተሳሳተ አምልኮ የተተካበት አዲስ ነገር ነበር?
የአምላክ ቃል ልዩ ቦታ ተሰጠው
የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች የቅዱሳን ጽሑፎችን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው ገልጸው ነበር። ወጎችን አይቀበሉም ነበር። ሆኖም ዘ ክርስቺያን ሴንቸሪ የተባለው መጽሔት ዋነኛ አዘጋጅ የሆኑት ማርቲን ማርቲ ባለፈው መቶ ዘመን “ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ፕሮቴስታንቶች በመጽሐፍ ቅዱስና በወግ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማየት ፈቃደኞች ሆነዋል” ብለዋል። የእነሱ “የእምነት አባቶች” ግን እንዲህ አላደረጉም ነበር። ለእነሱ “መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ቦታ የነበረው ከመሆኑም በተጨማሪ ወግና የሊቀ ጳጳሳት ሥልጣን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ፈጽሞ ሊመጣጠን አይችልም ነበር።”
ይህ አመለካከት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ ስርጭትና ጥናት በከፍተኛ ደረጃ እንዲካሄድ አስችሏል። የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በ15ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ የሉተር ጓደኛ የነበረው ጀርመናዊው ዮሃንስ ጉተንበርግ ለመጪው የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ የሚያገለግል ጠቃሚ መሣሪያ አበርክቷል። ጉተንበርግ ተንቀሳቃሽ የጽሕፈት መሣሪያ በመሥራት የመጀመሪያውን የታተመ መጽሐፍ ቅዱስ አዘጋጅቷል። ሉተር ይህ ፈጠራ ወደፊት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በመገንዘብ ኅትመት “እውነተኛውን ሃይማኖት በመላው ዓለም ለማሰራጨት የሚያስችል የአምላክ ዘመናዊና ምርጥ ሥራ” እንደሆነ ተናግሯል።
አሁን ብዙ ሰዎች የራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖራቸው ይችላል፤ ሆኖም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህን ሁኔታ አልደገፈችም። በ1559 ሊቀ ጳጳስ ጳውሎስ አራተኛ ያለ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስ በአገሩ ቋንቋ እንዳይታተም የሚያዝ ድንጋጌ አውጥተው ነበር፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ለመስጠት አልፈለገችም። እንዲያውም በ1564 ሊቀ ጳጳስ ፓየስ አራተኛ “ልዩነት ሳያደርጉ መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ እንዲነበብ መፍቀድ . . . ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ከተሞክሮ ታይቷል” በማለት ገልጸዋል።
ተሐድሶው አዲስ ዓይነት “ክርስትና” እንዲፈጠር አድርጓል። የሊቀ ጳጳሱን ሥልጣን በግለሰቦች ነፃ ምርጫ ተክቷል። የካቶሊክ የቅዳሴ ሥርዓት በፕሮቴስታንት የአምልኮ ሥርዓት እንዲሁም እፁብ ድንቅ የሆኑት የካቶሊክ ካቴድራሎች ተራ በሆኑት የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ተተክተዋል።
ያልተጠበቁ ጥቅሞች
በመጀመሪያ ሃይማኖታዊ መልክ የነበራቸው እንቅስቃሴዎች ብዙውን ጊዜ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቅርጽ እንደሚይዙ ታሪክ ያስተምረናል። ይህ በፕሮቴስታንት ተሐድሶ ላይ ተፈጽሟል። የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ኡዤን ኤፍ ራይስ ጄአር ስለዚህ ሁኔታ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል:- “በመካከለኛው ዘመን ምዕራባዊቷ ቤተ ክርስቲያን በአንድ የአውሮፓውያን ድርጅት ሥር ነበረች። በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ወቅት ቤተ ክርስቲያኗ ዓለማዊ ባለ ሥልጣናት በበላይነት በሚቆጣጠሯቸው . . . በበርካታ ክልላዊ አብያተ ክርስቲያናት ተከፋፈለች።” ይህም “በመካከለኛው ዘመን በዓለማዊና በቀሳውስት ሥልጣን መካከል የነበረው ለረጅም ጊዜ የቆየ ሽኩቻ ወደ ፍጻሜው እንዲደርስ አድርጓል። . . . የሥልጣን ሚዛን ሲዋዥቅ ቆይቶ በመጨረሻ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ፖለቲካዊ መንግሥትና ከቀሳውስት ወደ ተራው ሕዝብ ተሻገረ።”
ሃይማኖተኛ ለሆነውም ሆነ ላልሆነው ግለሰብ ይህ ትልቅ ነፃነት ያስገኝ ነበር። ከካቶሊክ እምነት በተለየ ሁኔታ መሠረተ ትምህርትን ወይም ልማድን የሚቆጣጠር ማዕከላዊ አካል ስላልነበረው የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ ብዙ ዓይነት ሃይማኖታዊ አመለካከቶች እንዲንጸባረቁ መንገድ ከፍቷል። ይህም የተሐድሶ ጉዳይ ፈጽሞ በማይታሰብበት ወቅት ቀስ በቀስ መቻቻልና ነፃ የሆነ አስተሳሰብ እንዲስፋፋ አድርጓል።
በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ ነፃነት ቀደም ሲል ታምቀው የነበሩ ችሎታዎች እንዲወጡ አድርጓል። አንዳንዶች ወደ ዘመናዊው ዓለም የሚመሩን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና የቴክኖሎጂ እድገቶች እንዲፈጠሩ የሚያስፈልገው የሚገፋፋ ነገር ሆኖ ነበር ይላሉ። ዘመናዊ ደራሲ የሆኑት ቴዎዶር ዋይት የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ ግብረ ገብነት “በመንግሥትም ሆነ በዕለታዊ ኑሮ ውስጥ እንዲተረጎም አድርጓል” ሲሉ ጽፈዋል። ይህን ሲያብራሩም እንዲህ ብለዋል:- “ሰው ለሕሊናውና ለሚያደርጋቸው ነገሮች ያለ ቀሳውስት ጣልቃ ገብነት ወይም አማላጅነት በአምላክ ፊት በቀጥታ ተጠያቂ ነው የሚለው እምነት ነው። . . . አንድ ግለሰብ ጠንክሮ ከሠራ፣ በሚገባ ካረሰ፣ ቸልተኛ ካልሆነና ካልሰነፈ እንዲሁም ሚስቱንና ልጆቹን ከተንከባከበ እድል ወይም አምላክ ዋጋውን ይከፍለዋል።”
እነዚህ ጥሩ የሚመስሉ የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ ገጽታዎች ጉድለቶቹን እንዳናይ ዓይናችንን ሊያሳውሩብን ይገባልን? ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን ኤንድ ኤቲክስ እንዲህ ይላል:- የፕሮቴስታንት ተሐድሶ “ይህ ነው የማይባል ክፋት የተከሰተበት ወቅት ነው። የጀስዊቶችና የኢንኩዊዝሽን ዘመን ቢያከትምም . . . ከዚህ ትንሽ መለስ ያለ ነገር ተካትቷል። በመካከለኛው ዘመን ብዙ ድንቁርና ነበረ ካልን አሁን ሐሰትን ለማስፋፋት በደንብ የተደራጀ መዋቅር ተፈጥሯል ማለት ነው።”
“ሐሰትን ለማስፋፋት በደንብ የተደራጀ መዋቅር” በምን ረገድ?
የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ የመሠረተ ትምህርት ተሐድሶ አመጣለሁ የሚል ተስፋ ቢሰጥም ይህን ሳያደርግ በመቅረቱ “የተቀናጀ ውሸት” ሆኖ ነበር። ብዙውን ጊዜ የተሐድሶ አራማጆችን ቁጣ ያነሣሣው የቤተ ክርስቲያን ደንብ እንጂ የመሠረተ ትምህርት ስሕተት አይደለም። በአብዛኛው የፕሮቴስታንት እምነት በአረማውያን የተበከሉትን የካቶሊክ እምነት ሃይማኖታዊ ሐሳቦችና ድርጊቶች ይዟል። እንዴት? ለዚህ ጉልህ ምሳሌ የሚሆነን የዓለም የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር አባል ለመሆን ዋነኛ መስፈርት የሆነው የሥላሴ እምነት ነው። ምንም እንኳ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን ‘በዛሬው ጊዜ ያሉት ተንታኞችና የሃይማኖት ምሁራን ይህ መሠረተ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ቦታ በግልጽ ተብራርቶ አይገኝም በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ’ ቢልም ይህ መሠረተ ትምህርት ብዙ ደጋፊዎች አሉት።
የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ የተበላሸውን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አሻሽሏልን? አላሻሻለም። ከዚህ ይልቅ ማርቲን ማርቲ እንዳሉት “በመካከለኛው ዘመን የነበረውን የካቶሊክ እምነት የሥልጣን መዋቅር ተቀብሎ የፕሮቴስታንት ለውጦችን ለማምጣት ከሮማን ካቶሊክ ተቋም ተገነጠለ።”
በተጨማሪም የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ “የእምነት አንድነት” ለመመለስ ቃል ገብቶ ነበር። ሆኖም የተከፋፈሉ ብዙ የፕሮቴስታንት ቡድኖች ሲፈጠሩ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋ ሳይፈጸም ቀረ።— ኤፌሶን 4:13 አዓት
ድርጅታዊ ዝብርቅ የተፈጠረው ለምንድን ነው?
የፕሮቴስታንት እምነት በጣም ብዙ በሆኑ ኑፋቄዎችና ሃይማኖታዊ ቡድኖች የተከፋፈለ ስለሆነ አጠቃላዩን ቁጥር ማወቅ የማይቻል ነገር ነው። አንድ ሰው ያሉትን ቆጥሮ ሳይጨርስ አዳዲስ ቡድኖች ሊቋቋሙ ወይም ካሉት መካከል አንዳንዶቹ ሊጠፉ ይችላሉ።
ሆኖም (በ1980) ወርልድ ክሪስቺያን ኢንሳይክሎፔድያ ሕዝበ ክርስትናን “በ20,780 የተለያዩ ክርስቲያናዊ ቡድኖች” በመከፋፈል “የማይቻለውን ነገር” አድርጓል። ከዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት ቡድኖች ናቸው።a እነዚህም 7,889 ዓይነተኛ የፕሮቴስታንት ቡድኖችን፣ 10,065 በአብዛኛው በጥቁሮች መካከል የተፈጠሩ ሃይማኖቶችንና 1,345 አነስተኛ የፕሮቴስታንት ቡድኖችን የሚያካትቱ ናቸው።
ፕሮቴስታንት ክሪስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ ይህ ግራ የሚያጋባ ልዩነት ለምን እንደተፈጠረ ሲያብራራ “የጤናና የበሽታ ምልክት” ብሎ የጠራው ሲሆን “ይህ ከሰብዓዊ የፈጠራ ችሎታና የአቅም ውስንነት የተነሣ ሊሆን ይችላል፤ እንዲያውም ስለ ሕይወት ያላቸውን አመለካከት ከልክ በላይ ከፍ አድርገው በሚመለከቱ ኩሩ ሰዎች ምክንያት ሊሆን ይችላል” ሲል ገልጿል።
ይህ ምንኛ እውነት ነው! ኩሩ ሰዎች መለኮታዊ እውነትን በሚገባ ሳይመረምሩ ደኅንነት፣ ነፃነት ወይም እርካታ የሚገኝባቸውን አዳዲስ አማራጮች ያቀርባሉ። ሃይማኖትን ማብዛት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለውም።
የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ ሃይማኖት እንዲበዛ በማድረጉ አምላክ የሚመለክበት መመሪያ የለውም የሚል ይመስላል። እንዲህ ዓይነቱ የተደራጀ ክፍፍል መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ከሚለው የእውነት አምላክ ጋር የሚስማማ ነውን? ወደ መረጥከው ቤተ ክርስቲያን ሂድ የሚለው የፕሮቴስታንት አስተሳሰብ አዳምና ሔዋንን ወደ ተሳሳተ እምነትና ችግር ከመራቸው በራስ የመመራት አስተሳሰብ የተለየ ነውን?— 1 ቆሮንቶስ 14:33፤ ዘፍጥረት 2:9፤ 3:17-19ን ተመልከት።
ለመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠውን ልዩ ግምት ችላ ማለት
የመጀመሪያዎቹ የተሐድሶ አራማጆች ለመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ግምት ቢሰጡትም ከጊዜ በኋላ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች እንዲነሡና ማርቲ እንዳሉት “መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጽሑፍ እንደሌሎች ሥነ ጽሑፎች እንዲታይ አድርገዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመንፈስ አነሣሽነት ለመጻፋቸው ልዩ ቦታ” አልሰጡትም።
የፕሮቴስታንት ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት መጻፉን ጥያቄ ውስጥ በማስገባታቸው የተሐድሶው አራማጆች ዋነኛ መሠረት አድርገው በሚመለከቱት ነገር ላይ የነበረው እምነት እንዲቀንስ አድርገዋል። ይህም ለጥርጣሬ፣ በራስ አስተሳሰብ ለመመራትና በስሜት ወይም በሃይማኖት ላይ ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሠረተ እምነት ነው ለሚባለው ለራሽናሊዝም ጥርጊያ መንገድ ከፍቷል። ብዙ ምሁራን ተሐድሶውን ለዘመናችን ዓለማዊነት ዋነኛ መንስኤ አድርገው የሚመለከቱት አለ ምክንያት አይደለም።
በፖለቲካ ውስጥ መጠላለፍ
ምንም እንኳ ተሐድሶ አራማጆችና ተከታዮቻቸው ጥሩ ዝንባሌ የነበራቸው ቢሆንም ከላይ የተገለጸው ፍሬ የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ እውነተኛ ክርስትናን ወደ ቦታው እንዳልመለሰ በግልጽ የሚያሳይ ነው። የፕሮቴስታንት እምነት ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን በመጠበቅ ሰላምን ከማራመድ ይልቅ በአገራዊ ስሜት ተጠላልፏል።
ሕዝበ ክርስትና በካቶሊክና በፕሮቴስታት አገሮች ስትከፋፈል ይህ ሁኔታ በግልጽ ታይቷል። የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ኃይሎች በአውሮፓ አህጉር በተካሄዱት ደርዘን ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ጦርነቶች ብዙ ደም አፍስሰዋል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እነዚህን ጦርነቶች “የጀርመንና የስዊዘርላንድ ተሐድሶ በ1520ዎቹ ያቀጣጠላቸው የሃይማኖት ጦርነቶች” በማለት ጠርቷቸዋል። ከእነዚህ ጦርነቶች ውስጥ በይበልጥ የሚታወቀው በጀርመናውያን ፕሮቴስታንቶችና ካቶሊኮች መካከል በነበረው ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ልዩነት ምክንያት የተደረገው የሠላሳ ዓመት (1618-48) ጦርነት ነው።
በእንግሊዝ ውስጥም ብዙ ደም ፈሷል። ንጉሥ ቀዳማዊ ቻርለስ ከ1642 እስከ 1649 ባሉት ዓመታት በፓርላማው ላይ ጦርነት አውጆ ነበር። አብዛኞቹ የንጉሡ ጠላቶች የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የፒዩሪቲያን ክንፍ ከመሆናቸውም በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ ጦርነቱ የፒዩሪቲያን አብዮት ተብሎ ይጠራል። ንጉሡ ከተገደለ በኋላ በኦሊቨር ክሮምዌል የሚመራ ለጥቂት ጊዜ የቆየ የፒዩሪቲያን ሬፑብሊክ ሲቋቋም ጦርነቱ አቆመ። ምንም እንኳ የዚህ የእንግሊዝ የእርስ በርስ ጦርነት ዋነኛ ዓላማ ሃይማኖታዊ ተጋድሎ ማድረግ ባይሆንም የታሪክ ጸሐፊዎች ተፋላሚ ጎራዎችን ለመምረጥ ሃይማኖት ወሳኝ ሚና ተጫውቶ እንደነበር ይስማማሉ።
በዚህ ጦርነት ወቅት ፍሬንድስ ወይም ኩዌከርስ የተባለው ሃይማኖታዊ ቡድን ተፈጠረ። ይህ ቡድን ከፕሮቴስታንት “ወንድሞቹ” ጠንካራ ተቃውሞ አጋጥሞታል። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ አባላት በእስር ቤት የሞቱ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ውርደት ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ እንቅስቃሴ በአሜሪካ በሚገኙ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ውስጥ እንኳ ሳይቀር ተሰራጭቷል፤ እዚያም በ1681 ዳግማዊ ቻርለስ የኩዌከር ቅኝ ግዛትን ለመመሥረት ከዊልያም ፔን ጋር ተፈራረመ፤ ቆየት ብሎ ይህ ቦታ የፔንሲልቫኒያ ግዛት ሆኗል።
ቀደም ሲል ሌሎች ሃይማኖቶችም እንደዚህ ያደርጉ ስለ ነበር ኩዌከሮች ውጭ አገር ሄደው እምነታቸውን በማስፋፋት ረገድ የመጀመሪያዎቹ አልነበሩም። አሁን ግን ከፕሮቴስታንት “አዲስ ነገር” በኋላ ካቶሊኮች በጣም ብዙ ከሆኑ የፕሮቴስታንት ቡድኖች ጋር ሆነው የክርስቶስን የእውነትና የሰላም መልእክት “ለማያምኑ ሰዎች” ለማሰራጨት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ምንኛ የሚያስገርም ነው! ምክንያቱም “አማኞቹ” ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ለመለኮታዊ እውነት የጋራ ፍቺ በመስጠት ረገድ ሊስማሙ አልቻሉም። በተጨማሪም ወንድማማቻዊ ሰላምና አንድነት ማሳየት እንደተሳናቸው የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ሁኔታ አንፃር ሲታይ “‘ክርስቲያኖች’ እና ‘መናፍቃን’ ሲገናኙ” ምን ሊጠበቅ ይችላል? በሚቀጥለው እትማችን ላይ የሚወጣውን ክፍል 18 እንዲያነቡ ተጋብዘዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ በ1982 ታትሞ የወጣ መጽሐፍ “በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ 270 (በየሳምንቱ 5) አዳዲስ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ይጨምራሉ” በማለት በ1985 22,190 ቡድኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጾ ነበር።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የተሐድሶው የመጀመሪያ ልጆች
የአንግሊካን ኅብረት:- 25 ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች 6 ቡድኖች ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድ ዓይነት የሆነ መሠረተ ትምህርት፣ መስተዳድርና የአምልኮ ሥርዓት ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ለስም ብቻ የሆነውን የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ አመራር ይቀበላሉ። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን የአንግሊካን እምነት “ስለ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ተተኪነት የሚገልጸውን እምነት የሚጠብቅ ሲሆን ከተሐድሶ በፊት የነበሩትን ብዙ ልማዶች ይዟል” ብሏል። በአምልኮው ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራ የያዘውና “ከተሐድሶ ዘመን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ የሚሠራበት ብቸኛው መጽሐፍ” ዘ ቡክ ኦቭ ኮመን ፕረየር የተባለው መጽሐፍ ነው። ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ተገንጥለው ወጥተው በ1789 የፕሮቴስታንት ኤፒስኮፓል ቤተ ክርስቲያንን ያቋቋሙት በዮናይትድ ስቴትስ የሚገኙት የአንግሊካን እምነት ተከታዮች በየካቲት 1989 በአንግሊካን ታሪክ የመጀመሪያዋ የሆነችውን ሴት ጳጳስ በመሾም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ልማድ ትተዋል።
የመጥምቃውያን አብያተ ክርስቲያናት:- በ16ኛው መቶ ዘመን ከነበሩት አናባፕቲስቶች የመጡና (በ1970) 369 ሃይማኖታዊ ቡድኖች የነበሯቸው ሲሆን ውኃ ውስጥ በማጥለቅ የሚደረገውን የአዋቂዎች ጥምቀት ጉልህ ስፍራ ይሰጡታል። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን መጥምቃውያን “ድርጅታዊ ወይም ሃይማኖታዊ አንድነት መያዝ አስቸግሯቸዋል” ካለ በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ አክሎ ሲናገር “በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት የመጥምቃውያን ቤተሰቦች ብዙ ናቸው፤ . . . ሆኖም እንደ ሌሎቹ ብዙ ትላልቅ ቤተሰቦች ሁሉ አንዳንድ አባላት ከሌሎች አባላት ጋር አይነጋገሩም” ብሏል።
የሉተራን አብያተ ክርስቲያናት:- (በ1970) 240 ሃይማኖታዊ ቡድኖች የነበሯቸው ሲሆን ከማንኛውም የፕሮቴስታንት ቡድን የበለጠ ብዙ አባላት እንዳላቸው በኩራት ይናገራሉ። ዘ ወርልድ አልማናክ ኤንድ ቡክ ኦቭ ፋክትስ 1988 “አሁንም ቢሆን በመጠኑ በጎሣ (ጀርመናዊ፣ ስዊድናዊ፣ ወዘተ . . . ተብለው) የተከፋፈሉ ናቸው” ሲል የተናገረ ቢሆንም “በዋነኝነት ግን ፈንዳሜንታሊስቶችና ሊበራሎች ተብለው በሁለት ይከፈላሉ” በማለት አክሏል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሉተራውያን በአገር ደረጃ እንደተከፋፈሉ በግልጽ የታየ ሲሆን በአሜሪካ የሉተራን ሃይማኖታዊ ሴሚናር አባል የሆኑት ኢ ደብልዩ ግሪትስች በዚህ ጊዜ “[በጀርመን ውስጥ] ሂትለርን የተቃወሙት የሉተራን ፓስተሮችና ጉባኤዎች አነስተኛ ቢሆኑም አብዛኞቹ ሉተራውያን ዝም ብለው ነበር ወይም ከናዚ አገዛዝ ጋር በሙሉ ልብ ተባብረው ነበር” ብለዋል።
የሜቶዲስት አብያተ ክርስቲያናት:- ጆን ዌስሊ በ1738 ባቋቋመው በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከነበረ አንድ ንቅናቄ የተነሡ ሲሆን (በ1970) 188 ሃይማኖታዊ ቡድኖች ነበሯቸው። እርሱ ከሞተ በኋላ አንድ የተለየ ቡድን ሆኖ ተገነጠለ፤ ዌስሊ የሜቶዲስት እምነትን “በመጽሐፍ ቅዱስ በተደነገገው መንገድ የሚሄድ” የሚል ፍቺ ሰጥቶት ነበር።
ሪፎርምድና ፕሪስባይተርያን አብያተ ክርስቲያናት:- ሪፎርምድ አብያተ ክርስቲያናት (በ1970 354 ሃይማኖታዊ ቡድኖች ነበሯቸው) በመሠረተ ትምህርት ከሉተራን ይልቅ የካልቪንን ሐሳብ የሚደግፉ ሲሆን “የተሻሻለ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን” ተከታዮች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። “ፕሪስባይተርያን” የሚለው አጠራር በሽማግሌዎች (ፕሪስባይተርስ) የሚመራ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርን ያመለክታል፤ የፕሪስባይተርያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ሪፎርምድ አብያተ ክርስቲያናት ቢሆኑም ሪፎርምድ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የፕሪስባይተርያን ዓይነት አስተዳደር የላቸውም።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውብ በሆነ መንገድ የታተመው የጉተንበርግ የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ ገጽ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጉተንበርግ እና ተንቀሳቃሽ የጽሕፈት መኪናው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን መሥራች የሆነው ጆን ዌስሊ (1738)