የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 20:- ከ19ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ የሚቋቋምበት ጊዜ ተቃረበ!
“መለኮታዊውን ብርሃን ለማየት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጧፋችሁን ማጥፋት ነው።”—ቶማስ ፉለር፣ እንግሊዛዊ ሐኪምና ደራሲ (1654-1734)
አሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን በክርስትና ታሪክ ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናትም ሆነ ከተኃድሶው ዘመን ጋር የሚወዳደር ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተደረገበት ዘመን እንደሆነ ተነግሮለታል። በዚህ ዘመን ሃይማኖታዊ ግንዛቤውም ሆነ እንቅስቃሴው ይህን ያህል የሰፋባቸው ምክንያቶች እጅግ በርካታና የተለያዩ ናቸው።
ደራሲው ኬኔት ኤስ ላቶሬት ምክንያት ይሆናሉ ያሏቸውን 13 ነገሮች የዘረዘሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከአሁን ቀደም በወጣው የዚህ መጽሔት እትም ላይ ተጠቅሰዋል። ኬኔት “የሰው ዘር በዚህን ያክል አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ በስፋቱም ሆነ በዓይነቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ለውጥ ያደረገበት ዘመን ታይቶ አይታወቅም” ብለዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሃይማኖት ማንሠራራቱ በግልጽ ይታይ ነበር። ለምሳሌ ያህል በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከሕዝቡ ብዛቱ 10 በመቶ ብቻ የነበረው የቤተ ክርስቲያን አባላት ቁጥር በዘመኑ ማብቂያ ላይ ወደ 40 በመቶ ከፍ ብሏል። በ1780 በእንግሊዝ የተጀመረው የሰንበት ትምህርት ቤት በሰፊው እየተዘወተረ ሄዶ ነበር። ለዚህ አንዱ ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከአውሮፓ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እንዲነጣጠሉ በመደረጉ በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርት ለመስጠት አለመቻሉ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በደርዘን የሚቆጠሩ የሃይማኖታዊ ቡድን ኮሌጆችና እነዚሁኑ ቡድኖች ያቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት የተቋቋሙ ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዚህ መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ቢያንስ 25 ሃይማኖታዊ የትምህርት ማዕከሎች ተቋቁመው ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕሮቴስታንት እምነት በምድር ዙሪያ ለሚስዮናዊነቱ ሥራ ከፍተኛ ግምት መስጠት ጀምሮ ነበር። እንግሊዛዊው ጫማ ሠሪና አስተማሪ ዊልያም ኬሪ በ1792 ክርስቲያኖች አረመኔዎችን ለመለወጥ በመጣር ረገድ ያሉባቸውን ግዴታዎች መመርመር (An Enquiry Into the Obligations of Christians to Use Means for the Conversion of the Heathens) የተባለውን መጽሐፍ በማዘጋጀት ቀዳሚ ሆኖ ተገኝቷል። ኬሪና ተባባሪዎቹ በሕንድ ውስጥ ሚስዮናውያን ሆነው ሲያገለግሉ መጽሐፍ ቅዱስን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ከ40 ወደሚበልጡ የሕንድና የእስያ ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ተርጉመዋል። ከእነዚህ የጥንት ሚስዮናውያን መካከል አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ በማሠራጨት ረገድ ያከናወኑት ተግባር የሚያስመሰግን ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ የተመረኮዘ የአርኪኦሎጂ ሳይንስም በመጨረሻው መቶ ዘመን ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል። በ1799 የፈረንሳይ ወታደሮች በግብጽ ውስጥ ዛሬ ሮሴታ ድንጋይ በመባል የሚታወቀውን ጥቁር ድንጋይ አገኙ። በዚህ ድንጋይ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ የተጻፈ ሲሆን ሁለት ጊዜ የተጻፈው በሁለት የተለያዩ የግብጻውያን ሥዕላዊ የአጻጻፍ ዘዴዎች አንድ ጊዜ ደግሞ በግሪክኛ ነው። በመሆኑም የግብጻውያኑን ሥዕላዊ ጽሕፈት ትርጓሜ ማወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አረጋግጧል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የአሦራውያን የኪዩኒፎርም ጽሑፎችም ትርጉም ታወቀ። በመሆኑም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአሦርና በግብጽ የመሬት ቁፋሮዎች ሲጀመሩ የተገኙት የእጅ ሥራዎች አዲስ ትርጉም ነበራቸው። የብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ጥቃቅን ዝርዝሮች እንኳ ሳይቀሩ ማረጋገጫ ተገኝቶላቸዋል።
የራሳቸውን ጧፍ አብርተዋል
እንደ ሃይማኖታዊ ዝንባሌው ሁሉ የተኃድሶ አራማጆች ነን ባዮችም ቁጥር ያን ያህል ጨምሯል። ይሁን እንጂ በቅን ልቦና የተነሣሱት ሁሉም እንዳልነበሩ አይካድም። ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ደራሲ ኬኔት ኤስ ላቶሬት ከአዳዲሶቹ ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ “ቅንዓት፣ የእርስ በርስ ሽኩቻ እና የሥልጣን ጥማት የወለዳቸው” መሆናቸውን ምንም ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ አምላክ እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም የሥልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ የየራሳቸውን ጧፍ በሚያበሩ ተኃድሶ አራማጆች ይጠቀማል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።
ሁሉም የየራሱን ጧፍ ብልጭ ድርግም በሚያደርግበት በዚህ ግርግር መሃል ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ውዥንብር ውስጥ ገብቶ ነበር። በአመዛኙ ከጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች የፈለቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች “ወደፊት ተራመደ” ባሉት ሳይንሳዊ እውቀት ብርሃን ለቅዱሳን ጽሑፎች እንደገና አዲስ ትርጉም ሰጥተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስን የአይሁዳውያኑን ሃይማኖታዊ ገጠመኝ ከሚተርክ መጽሐፍ እምብዛም አስበልጠው አያዩትም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተንጸባረቀው የሥነ ምግባር አቋም ጥበብ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንደገባቸው ሁሉ መጽሐፉ የመዳንን መንገድ በማመላከት ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚናም አጠያያቂ አድርገውታል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትችቱ በተለይ በፕሮቴስታንት ቀሳውስት ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል። አንድ ሪፖርት እንደጠቆመው ከሆነ በ1897 በጀርመን ከሚገኙት 20 የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የፔንታቱችን ወይም የኢሳይያስን ጸሐፊ በሚመለከት ቀደም ሲል የነበረውን አመለካከት ያልቀየረ አንድም የፋካልቲ አባል አልነበረም።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1902 በስኮትላንድ በተደረገው የፕሪስቢቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትችቶችን በሚመለከት ውዝግብ ተነስቶ ነበር። ኤዲንበርግ ኢቭኒንግ ኒውስ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎቹ አባባል ከሆነ . . . አንድ ጥሩ የሥነ ምግባር ሰው ከኤስፖስ ፋብሌስ መጽሐፍ ውስጥ ከዚህም ከዚያም ለቃቅሞ ስለ ግብረ ገብ ሊያስተምር እንደሚችል ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም አንድ ሰባኪ ጥቂት ሐሳብ ቀንጭቦ ወስዶ የግብረ ገብ ትምህርት ሊሰጥበት የሚችል ‘አፈ ታሪኮችን’ የያዘ መጽሐፍ ነው።” ይሁን እንጂ ይኸው ጋዜጣ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “የሠራተኛው መደብ ሞኝ አይደለም። ጭጋግ የጋረደው አእምሮ ይዘው የሚመላለሱ ሰዎች የሚናገሩትን ለመስማት ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄድም።”
ከጥቂት ቀናት በኋላ የወጣው ሁለተኛ ርዕስ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ ፍርጥርጥ አድርጎ ገልጾታል:- “ነገር መሸፋፈን ምንም ጥቅም የለውም። የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን የግብዞች ድርጅት ነው፤ መሪዎቹም ሰዎችን ለማሳሳት ቆርጠው የተነሡ ናቸው። ከዚህ አንጻር ሲታይ ‘የምክንያታዊነት ዘመን’ ተብሎ ይጠራ በነበረው ወቅት ይኖር የነበረው ደራሲ ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ክቡር ቶማስ ፔን በግላስኮ የሚገኘው የዩ[ናይትድ] ፍ[ሪ] ኮሌጅ የዕብራይስጥና የብሉይ ኪዳን ጥናት ፕሮፌሰር ብሎ የሚያቆላምጠው እንጂ አረማዊው ቶም ፔን ብሎ በንቀት ሊናገረው የሚደፍር ባልተገኘ ነበር። በፕሮቴስታንቶች መድረክ ላይ ቆሞ ለመስበክ . . . [እና] የሃይማኖታዊ ትምህርት ፕሮፌሰር ተብሎ ወፍራም ደሞዝ ለመዛቅ አይቸገርም ነበር።”
ሃይማኖታዊ ቅዋሜ
የፕሮቴስታንት እምነት ከመጀመሪያው አንስቶ በአብዛኛው በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በመመርኮዝ በግል ሃይማኖት መለወጥንና የክርስትና ገጠመኞችን ከፍ አድርጎ ከመመልከቱም ሌላ የቁርባን ሥነ ሥርዓትን እንዲሁም ልማዳዊ ባሕሎችን ያጣጥል ነበር።
በ1830ዎቹና 1840ዎቹ ውስጥ ብዙ የፕሮቴስታንት ወንጌላውያን ክርስቶስ ዳግም የሚመጣበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነና ያኔ የሺው ዓመት ግዛት እንደሚጀመር ማወጁን ተያያዙት። የኒው ዮርክ ገበሬ የነበረው ዊልያም ሚለር ኢየሱስ በ1843 ገደማ ሁለተኛ ሊመጣ ይችላል ብሎ ለመናገር ደፍሮ ነበር። ይህ የሺው ዓመት አማኞች እንቅስቃሴ ፋንዳሜንታሊዝም በመባል ለሚታወቀው ይበልጥ ገናና እና አክራሪ ለሆነው የወንጌላዊነት እንቅስቃሴ መሠረት ጥሏል።
ፋንዳሜንታሊዝም የተቋቋመበት ትልቁ ምክንያት እጅግም አጥባቂ ያልሆነው የፕሮቴስታንት እምነት ያፈራቸውን እንደ ጥርጣሬ፣ ነፃ አስተሳሰብን እና የሥነ ምግባር ልቅነት ያሉትን ነገሮች ለመቃወም ነው። ከጊዜ በኋላ ከ1909 እስከ 1912 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በሙዲ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቋም ከተዘጋጀው ዘ ፋንዳሜንታልስ ከተባለው በ12 ተከታታይ እትም ከወጣው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ፋንዳሜንታሊዝም የሚለውን ስያሜውን አግኝቷል።
ፋንዳሜንታሊዝም በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሰፊው የታወቀው ውጤታማ በሆነው በራዲዮና በቴሌቪዥን በሚያከናውነው አገልግሎት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ተቋማቱ እንዲሁም ከፍተኛ የማስተዋወቂያ ዘመቻ በሚደረግላቸውና ስሜታዊነት በሚንጸባረቅባቸው ስብሰባዎቹ አማካኝነት ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውስጡ ያሉት አንዳንድ ታላላቅ መሪዎች በሚፈጽሙት የገንዘብና የጾታ ቅሌት ምክንያት ስሙ እየጠፋ መጥቷል። በተለይ ደግሞ በቅርቡ የፈረሰው ሞራል ማጆሪቲ ከተመሠረተበት ከ1979 ወዲህ በፖለቲካ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ጨምሯል የሚል ነቀፋ ሲሰነዘርበት ቆይቷል።
ፋንዳሜንታሊዝም ለመጽሐፍ ቅዱስ ቆሜያለሁ ይበል እንጂ በአንጻሩ ግን ተቀባይነት እያጣ እንዲሄድ አድርጓል። እንዲህ ያደረገበት አንዱ መንገድ ቀጥታ ሊተረጎሙ እንደማይችሉ ግልጽ የሆኑትን ጥቅሶች ቃል በቃል በመተርጎም ነው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን በዘፍጥረት ዘገባ መሠረት ምድር ቃል በቃል የ24 ሰዓታት ርዝማኔ ብቻ ባሏቸው 6 ቀናት ውስጥ ተፈጥራለች የሚለው አባባል ነው። እነዚህ ቀናት ከዚያ እጅግ የላቀ የጊዜ ርዝማኔ ያላቸው ምሳሌያዊ ቀናት መሆናቸው ግልጽ ነው። (ከዘፍጥረት 2:3, 4 እና ከ2 ጴጥሮስ 3:8 ጋር አወዳድር።) ፋንዳሜንታሊዝም መጽሐፍ ቅዱስ ተቀባይነት እያጣ እንዲሄድ ያደረገባቸው ሌሎች መንገዶች ደግሞ በሲኦል እሳት መሰቃየትን የመሳሰሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ የሌላቸውን መሠረተ ትምህርቶች በማስተማር እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የአልኮል መጠጦችን ወይም ደግሞ ሴቶች እንዳይኳኳሉ መከልከልን የመሳሰሉ በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ የሌሉ የአቋም ደረጃዎችን በማውጣት ነው። በዚህ መንገድ ፋንዳሜንታሊዝም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ቁም ነገር የሌለው፣ ምክንያተ ቢስና ኢሳይንሳዊ እንደሆነ ቆጥረው እንዲተዉት አድርጓል።
የጊዜ ጉዳይ ነው
አዎን፣ አንገብጋቢ የነበረው ነገር የእውነተኛው አምልኮ መልሶ መቋቋም እንደሆነ ግልጽ ነው! ይሁን እንጂ መክብብ 3:1 እንደሚለው “ለሁሉም ጊዜ አለው።”
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ በክርስትና መልክ እውነተኛውን አምልኮ እንደገና አቋቁሞ ነበር። ይሁን እንጂ ክህደት እንደሚነሳ ትንቢት ተናግሯል። እንደ ስንዴ የተመሰሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች እና በእንክርዳድ የተመሰሉት አስመሳይ ክርስቲያኖች ‘እስከ መከር ጊዜ አብረው እንደሚያድጉ’ ተናገረ። ያ ጊዜ ሲደርስ እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክን ሞገስ አግኝተው ሲሰበሰቡ መላእክት ‘እንክርዳዱን ለቅመው በእሳት ያቃጥሉታል።’ (ማቴዎስ 13:24-30, 37-43) በ19ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ የሚቋቋምበት ይህ ጊዜ ቀርቦ ነበር።
ቻርልስ ቴዝ ራስል የተወለደው በ1852 በፔንሲልቫኒያ ፒትስበርግ ሲሆን ልጅ እያለም መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። በ20ዎቹ ዕድሜው መጀመሪያ ላይ የቤተሰቡን የንግድ ሥራ ትቶ ሙሉ ጊዜውን ለስብከቱ ሥራ አዋለ። በ1916 በ64 ዓመት ዕድሜው እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ከ30,000 በላይ ንግግሮችን ሰጥቶና ከ50,000 ገጾች በላይ ያሏቸው መጻሕፍትን ጽፎ ነበር።
ራስል ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማሠራጨት ያደረጉትን የሚያስመሰግን እንቅስቃሴ ቢገነዘብም መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም፣ ማሳተምና ማሠራጨት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ያምን ነበር። በመሆኑም ዛሬ መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀውን መጽሔት በ1879 ማሳተም ጀመረ። የመጀመሪያው እትም እንደሚከተለው ይል ነበር:- “ስለ ማንኛውም ጥያቄ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ ከማለት ይልቅ የእኔ ቤተ ክርስቲያን ምን ይላል? ማለት ይቀናናል። ሃይማኖታዊ ትምህርት ስናሳድድ መጽሐፍ ቅዱስን ረስተነዋል። እንግዲያውስ ‘ቅዱሳን ጽሑፎች ጥበብ ሊሰጡን እንደሚችሉና የጌታ ምሥክርነት አላዋቂዎችን ጠቢብ እንደሚያደርግ’ በማመን መጽሐፍ ቅዱስን እንመርምር።”
ያለ አንዳች መስተጓጎል ሲታተም የቆየውና ዛሬ 118ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት (በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዱ እትም በ125 ቋንቋዎች ከ20 ሚልዮን በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች ተዘጋጅቶ ይሠራጫሉ) የአምላክን ቃል መመርመሩን ቀጥሏል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሔቱ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በማጥናት፣ በመረዳት እንዲሁም ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሚያበረክተውን እርዳታ ተገንዝበዋል።
ራስል በዘመኑ ከነበሩት የተኃድሶ አራማጆች የተለየ ነበር። ልዩ በሆነ መንገድ ወደ አምላክ ስለመቅረብ አልሰበከም፣ መለኮታዊ ራእይ አያለሁ አላለም፣ ሥውር በሆነ መጽሐፍ ወይም በሌላ መንገድ ለብቻዬ የተገለጠልኝ መልእክት አለ አላለም እንዲሁም አካላዊ ፈውስ የማድረግ ችሎታ አለኝ ብሎ አያውቅም። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መተንተን እችላለሁ ብሎ ተናግሮ አያውቅም። “የእርሱ ጧፍ” ከመለኮታዊው ብርሃን አሸንፎ እንዲታይ ላለማድረግ ፈታኝ ሁኔታዎችን ሁሉ በመዋጋት በመለኮታዊ እጅ እንዳለ የጽሕፈት መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል።
ራስል በ1900 “ሊከብርና ሊታወጅ የሚገባው እውነት እንጂ የእውነት አገልጋይ አይደለም” ሲል ጽፏል። በመጨመርም “ሁሉም እውነት እርሱ እንደፈለገ አንዱን ወይም ሌላውን አገልጋዩን ተጠቅሞ እንዲታወጅ ሊያደርግ ከሚችለው አምላክ የመነጨ መሆኑን በመዘንጋት እውነትን ከሰባኪው የመነጨ እንደሆነ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ይታያል” ብሏል። የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጽሑፎች ጸሐፊዎችም ሆኑ ተርጓሚዎች እንዲሁም የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ ስማቸውን የማያሳውቁበት ዋነኛው ምክንያት ይኸው ነው።
የአምላክ ንጉሥ በዙፋኑ ተቀምጧል!
አጥማቂው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ በአምላክ የተሰየመ ንጉሥ ሆኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚገለጥ አውጆ ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመንም ንጉሡ በሰማያዊ ሥልጣኑ የሚገለጥበት ጊዜ እንደ ቀረበ የሚታወጅበት ጊዜ ደርሶ ነበር። በዚህ መሠረት የጽዮን መጠበቂያ ግንብ በመጋቢት 1880 እትሙ ላይ “‘የአሕዛብ ዘመናት’ እስከ 1914 የሚዘልቁ ሲሆን እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሰማያዊው መንግሥት ሙሉ በሙሉ መግዛት አይጀምርም” ሲል አስታውቋል።
በመሆኑም ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቀው ቡድን 1914 የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምርበትን ጊዜ የሚያመለክት መሆኑን ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት ሲያሳውቅ ቆይቷል። የአምላክ ንጉሥ ሥልጣኑን መጨበጡ ብልጭ ድርግም የሚለው የሐሰት ሃይማኖት ጧፍ ዳግም መለኮታዊውን ብርሃን እንዳይጋርድ ለማጥፋት ሲባል የሚወሰደው የመጨረሻው እርምጃ መቅድም ነው።
አሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ወደ ማብቂያው እየተቃረበ ሲመጣ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የአምላክ አገልጋይ መሆናቸውን የሚያሳውቅ መጎናጸፊያ አልነበራቸውም። በአምላክ ፊት የተጣሉ መሆናቸው ተገቢ ነበር። ፍርዳቸውን የሚቀበሉበት ጊዜ ቀርቦ ነበር። ይህንን በሚመለከት በሚቀጥለው ጊዜ በሚወጣው ርዕስ ላይ ተጨማሪ ነገር ትማራለህ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንድ “ዘግይተው የመጡ”
የተኃድሶ እርምጃው ልጆች
የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ ሳይንቲስት:- ይህ ሃይማኖታዊ ንቅናቄ በአብዛኛው የሚታወቀው ክርስቲያን ሳይንስ በሚል መጠሪያ ነው። ንቅናቄው የተመሠረተው በ1879 ስለ ጤንነት አጥብቃ ታስብ በነበረችው በሜሪ ቤከር ኤዲ ነው። በ1866 ከደረሰባት ከባድ አደጋ በቅጽበት ማገገሟ የሚነገርላት ሜሪ ኢየሱስ የታመሙትን ለመፈወስና የሞቱትን ለማስነሳት የቻለበትን ምሥጢር እንዳገኘች ታምን ነበር። በ1875 ያሳተመችው ሳይንስ ኤንድ ሄልዝ ዊዝ ኪ ቱ ዘ ስክሪፕቸርስ የተባለው መጽሐፏ እንደሚያስተምረው መንፈሳዊ ነገር ከሥጋዊ ነገር ያይላል፤ በመሆኑም ኃጢአት፣ በሽታ፣ ሞትና ሌሎችም አሉታዊ ነገሮች በእውነት እውቀት እንዲሁም ከአምላክ ጋር የሚስማማ አዎንታዊ አስተሳሰብ በመያዝ ድል ሊነሱ የሚችሉ አጉል እምነቶች ናቸው።
የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት:- ይህ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተው በ1832 ሲሆን መሥራቾቹ የተኃድሶ አራማጆች የሆኑት የአሜሪካ ፕሪስቢቴራውያን ናቸው። “ቅዱስ ጽሑፉ በሚናገርበት ቦታ ላይ እንናገራለን፤ ዝም ሲል ዝም እንላለን” የሚል መርሆ ነበራቸው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “በመሠረተ ትምህርታዊና ሃይማኖታዊ ነገሮች ረገድ የመጣውን ሁሉ ያስተናግዳሉ” ሲል ገልጿቸዋል። አባላቱ በዩናይትድ ስቴትስ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በፖለቲካ እርስ በርስ ተከፋፍለው ነበር። በ1906 የተመሠረቱትን የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ጨምሮ በ1970 በአጠቃላይ 118 የሚያክሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ተፈጥረው ነበር።
አዳኝ ሠራዊት:- ይህንን ወታደራዊ አደረጃጀት ያለውን ቡድን ያቋቋመው ዊልያም ቡዝ ነው። ቡዝ ወደ ሜቶዲስት አገልግሎት የተቀላቀለው በ20ዎቹ ዕድሜው መጀመሪያ ላይ ሲሆን በ1861 ብቻውን የሚንቀሳቀስ ወንጌላዊ ሆኗል። እርሱና ሚስቱ በለንደን ምሥራቃዊ ዳርቻ ለሚገኙ ድሆች መስበክ ጀመሩ። ከዚያም በ1878 ክርስቲያን ሚሽን የነበረው የቡድኑ ስም አዳኝ ሠራዊት ተብሎ ተለወጠ። ይህ አዳኝ ሠራዊት መጠለያ ለሌላቸው፣ ለተራቡት፣ ግፍ ለሚፈጸምባቸውና ለተናቁት ወገኖች ማኅበራዊ እርዳታ በማቅረብ “ነፍሳትን የማዳን” ተግባር ለማከናወን ይጥራል።
ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት:- ይህ 200 ከሚያክሉት የአድቬንቲስት ቡድኖች ሁሉ ትልቁ ነው። ስማቸው የተመሠረተው ክርስቶስ ሁለተኛ ይመጣል በሚለው እምነት ላይ ነው [በእንግሊዝኛ አድቨንት ማለት መምጣት ማለት ነው]። የአድቬንቲስቶች ቡድን የተመሠረተው ባፕቲስት የነበረው ዊልያም ሚለር በ1840ዎቹ መጀመሪያ ላይ ባካሄደው ንቅናቄ ነው። ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ሰዎች አሁንም በአሥርቱ ትእዛዛት ሥር ናቸው ብለው ስለሚያስተምሩ ቅዳሜን ጠብቀው ሰንበት ያከብራሉ። አንዳንዶቹ የቡድኑ አባላት በተከታታይ መለኮታዊ ራእይ በማየት ብዙ ነገር ተገልጦልኛል የምትለውና ከፍተኛ ተደማጭነት ከነበራቸው የቡድኑ መሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ኤለን ጎልድ ዋይት የጻፈችውን መጽሐፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ እንደሆነ አድርገው ያዩታል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሮሴታ ድንጋይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኛነት ለማረጋገጥ እገዛ አድርጓል
[ምንጭ]
Courtesy of the Trustees of the British Museum