ሃይማኖታዊ አክራሪነት ምንድን ነው?
የሃይማኖታዊ አክራሪነት መነሻው ምንድን ነው? ለዘብተኛ የሃይማኖት ምሁራን እምነታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎችን አስተያየትና እንደ ዝግመተ ለውጥ ያሉትን ሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳቦች እንዲያቅፍ ለማድረግ ሲሉ ባለፈው ምዕተ ዓመት መጨረሻ ላይ ለውጥ ማድረግ ጀምረው ነበር። በዚህ ምክንያት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የነበራቸው እምነት ተናጋ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ወግ አጥባቂ ሃይማኖታዊ መሪዎች የእምነት መሠረት ናቸው ያሏቸውን ነገሮች በመደንገግ ለዚህ እንቅስቃሴ የአጸፋ መልስ ሰጥተዋል።a በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እነዚህን የእምነት መሠረቶች የሚያብራራ ዘ ፋንዳሜንታልስ— ኤ ቴስቲሞኒ ቱ ዘ ትሩዝ የተባለ ተከታታይ ጥራዞች ያሉት ጽሑፍ አሳትመው አወጡ። “ፋንዳሜንታሊዝም” የሚለው መጠሪያ ከዚህ መጽሐፍ ርዕስ የተወሰደ ነው።
በ20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሃይማኖታዊ አክራሪነት የዜና አምዶችን ትኩረት የሚስብ ወሬ እየሆነ መጣ። ለምሳሌ ያህል በ1925 ሃይማኖታዊ አክራሪዎች በቴኔስ ዩ ኤስ ኤ የሚኖረውን ጆን ስኮፕ የተባለ አንድ የትምህርት ቤት መምህር ፍርድ ቤት አቁመውት ነበር፤ ይህ ጉዳይ የስኮፕ ክስ በመባል ይታወቃል። ጥፋቱ ምን ነበር? ከግዛቲቱ ሕግ ጋር ይጻረር የነበረውን የዝግመተ ለውጥ ትምህርት ሲያስተምር በመገኘቱ ነው። በወቅቱ አንዳንዶች ይህ የሃይማኖታዊ አክራሪነት እንቅስቃሴ እንደማይዘልቅ ተሰምቷቸው ነበር። በ1926 ክርስቺያን ሴንቸሪ የተባለ አንድ የፕሮቴስታንቶች መጽሔት “ለፍሬ ለመብቃትም ሆነ በትግሉ ለመግፋት የሚያስችል ብቃት የሌለው” “ባዶና ለይምሰል የሚደረግ” እንቅስቃሴ ነው ሲል ተናግሮ ነበር። ይህ ግምት ምንኛ ስህተት ነበር!
ከ1970 ወዲህ ሃይማኖታዊ አክራሪነት ከዜና አምዶች ጠፍቶ አያውቅም። በካሊፎርኒያ ዩ ኤስ ኤ የሚገኘው የፉለር ሃይማኖታዊ ትምህርት ማሠልጠኛ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚሮስላቭ ቮልፍ “ሃይማኖታዊ አክራሪነት ሕልውናውን ከማቆየትም አልፎ እያበበ ሄዷል” ሲሉ ተናግረዋል። ዛሬ “ሃይማኖታዊ አክራሪነት” የሚለው ቃል የሚሠራበት የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴዎችን ብቻ ሳይሆን እንደ ካቶሊክ፣ እስልምና፣ የአይሁድና የሂንዱ እምነት ባሉት ሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙትን እንቅስቃሴዎችም ለማመልከት ነው።
ዘመናችን ያስከተለው እንቅስቃሴ
ሃይማኖታዊ አክራሪነት የተስፋፋው ለምንድን ነው? ስለ ሃይማኖታዊ አክራሪነት የሚያጠኑ ሰዎች የዘመናችን ሥነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ ግራ መጋባቶች ለዚህ እንቅስቃሴ መስፋፋት ቢያንስ በከፊል ድርሻ እንዳበረከቱ ይናገራሉ። ቀደም ባሉት ዘመናት አብዛኛዎቹ ማኅበረሰቦች በባሕላዊ እምነት ላይ የተመሠረተ የሥነ ምግባር መረጋጋት ይታይባቸው ነበር። ዛሬ እነዚያ እምነቶች ጥያቄ ላይ ወድቀዋል አለዚያም ወደጎን ገሸሽ ተደርገዋል። ብዙ ምሁራን አምላክ የለም፤ የሰው ልጅ የሚኖረው ጽድቅና ኩነኔ በሌለበት ጽንፈ ዓለም ውስጥ ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ብዙ ሳይንቲስቶች ሰው አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ የእጅ ሥራ ሳይሆን በአጋጣሚ የተገኘ የዝግመተ ለውጥ ውጤት ነው ብለው ያስተምራሉ። ልቅ የሆነ አስተሳሰብ ሰፍኗል። ዓለም በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሥነ ምግባር ችጋር ቀስፎ ይዞታል።— 2 ጢሞቴዎስ 3:4, 5, 13
ሃይማኖታዊ አክራሪዎች የጥንቱን መረጋጋት መልሰው ለማምጣት ይናፍቃሉ፤ አንዳንዶቹም ኀብረተሰባቸውን ወይም አገራቸውን እነርሱ ትክክለኛ የሥነ ምግባርና የሃይማኖታዊ ትምህርት መሠረት ነው ብለው ወደሚያስቡት ሁኔታ ለመመለስ ይጣጣራሉ። ሌሎች ሰዎች “በትክክለኛው” የሥነ ምግባር አቋምና ሃይማኖታዊ ሥርዓተ ትምህርት እንዲመላለሱ ለማስገደድ ባላቸው ኃይል ሁሉ ይጠቀማሉ። አንድ ሃይማኖታዊ አክራሪ እርሱ ትክክል እንደሆነና ሌሎቹ ሰዎች እንደተሳሳቱ አጥብቆ ያምናል። ፕሮፌሰር ጄምስ ባር “ፋንዳሜንታሊዝም” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ሃይማኖታዊ አክራሪነት “ብዙውን ጊዜ ጠባብነትን፣ ጎጠኛነትና ሐቁን ከሕዝብ መሰወርን እንዲሁም ጎራ መለየትን ለማመልከት የሚያገለግል ጥላቻና ንቀት የተንጸባረቀበት ቃል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ማንም ሰው ጠባብ ወይም ጎጠኛ ተብሎ መጠራት ስለማይፈልግ ሃይማኖታዊ አክራሪ የሚባለው ማን ነው በሚለው ሐሳብ የሚስማሙት ሁሉም ወገኖች አይደሉም። ይሁን እንጂ ሃይማኖታዊ አክራሪነት ተለይቶ የሚታወቅባቸው አንዳንድ ዘርፎች አሉ።
አንድን ሃይማኖታዊ አክራሪ ለይቶ ማወቅ
ሃይማኖታዊ አክራሪነት ብዙውን ጊዜ የአንድ ባሕል ጥንታዊ ልማድ ወይም ሃይማኖታዊ እምነት ነው ተብሎ የሚታመንበትን ነገር ጠብቆ ለማቆየትና የዓለም ሥጋዊ አስተሳሰብ እንደሆነ ተደርጎ የሚታየውን ነገር ለመቃወም የሚደረግ ጥረት ነው። ይህ ማለት ግን ሃይማኖታዊ አክራሪዎች ዘመናዊ የሆነውን ነገር ሁሉ ይቃወማሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ አመለካከታቸውን ለማስፋፋት ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎችን አሳምረው ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ሥጋዊ አስተሳሰብ እንዲጠናወተው የሚያደርጉትን ነገሮች ይዋጋሉ።b
አንዳንዶቹ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች ቆርጠው የተነሡት የሃይማኖታዊ ትምህርታቸውን ባሕላዊ ይዘት ወይም የአኗኗር መንገዳቸውን ጠብቀው ለማቆየት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ይህን እንዲከተሉ ለማስገደድና ሁሉም ሰው ከሃይማኖታዊ አክራሪዎቹ እምነት ጋር እንዲስማማ የማኅበረሰቡን መዋቅሮች ለመቀየር ነው። በመሆኑም የካቶሊክ ሃይማኖታዊ አክራሪ የሆነ ሰው ራሱ ውርጃ ከመፈጸም በመቆጠብ ብቻ አያበቃም። የአገሩ ሕግ አውጪ አካላት ውርጃን የሚከለክል ሕግ እንዲደነግጉ ተጽዕኖ ለማሳደርም ይጥር ይሆናል። በፖላንድ የሚታተመው ላ ራፑብሊካ የተባለው ጋዜጣ እንደገለጸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፀረ ውርጃ ሕግ እንዲጸድቅ “ያላትን ኃይልና ተሰሚነት ተጠቅማ ትታገላለች።” የቤተ ክርስቲያኒቷ ባለ ሥልጣኖች በዚህ እርምጃቸው ከሃይማኖታዊ አክራሪዎች ጋር የሚያስመድብ ተግባር ፈጽመዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው ክርስቺያን ኮሊሽን የተባለው የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ ‘ትግል’ ያካሂዳል።
ከሁሉም በላይ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች ተለይተው የሚታወቁት በጽኑ ሃይማኖታዊ እምነታቸው ነው። በመሆኑም አንድ የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ አክራሪ ለመጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ቀጥተኛ ትርጓሜ ይስማማል፤ ይህም ምድር የተፈጠረችው ቃል በቃል በስድስት ቀናት ውስጥ ነው የሚለውንም ሐሳብ ሳይጨምር አይቀርም። አንድ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ አክራሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ፈጽሞ የማይሳሳቱ ሰው ስለመሆናቸው ቅንጣት ታክል አይጠራጠርም።
እንግዲያውስ “ሃይማኖታዊ አክራሪነት” የሚለው ቃል ጭፍን አጥባቂ የሚል መልእክት የሚያስተላልፈውና ሃይማኖታዊ አክራሪ ላልሆኑት ሰዎች ይህ የሃይማኖታዊ አክራሪነት መስፋፋት በጣም የሚያስፈራቸው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። በግለሰብ ደረጃ በሃይማኖታዊ አክራሪነት አንስማማ ይሆናል፤ እንዲሁም የሚያደርጉት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና አንዳንዴ የሚወስዱት የኃይል እርምጃ ያስደነግጠን ይሆናል። እርግጥ የአንዱ ሃይማኖት አክራሪዎችም ሌሎች ሃይማኖታዊ አክራሪዎች በሚፈጽሙት ድርጊት አይደሰቱ ይሆናል! ያም ሆኖ ግን ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ብዙ ሰዎች የሃይማኖታዊ አክራሪዎች እንቅስቃሴ እንዲጀመር መንስኤ የሆኑት ነገሮች ማለትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የሥነ ምግባር ቸልተኝነት፣ እምነት የለሽነት እንዲሁም በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮች ገሸሽ መደረጋቸው ያሳስባቸዋል።
ይህን ዝንባሌ ለመዋጋት ብቸኛው መፍትሔ ሃይማኖታዊ አክራሪነት ነውን? ካልሆነስ ሌላው አማራጭ ምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በ1895 የተደነገጉት የፋንዳሜንታሊዝም መሠረታዊ ሐሳቦች የሚባሉት አምስት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው:- “(1) ቅዱሳን ጽሑፎች ሙሉ በሙሉ በመንፈስ የተጻፉና ፍጹም ትክክል መሆናቸው፤ (2) ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑ፤ (3) ክርስቶስ ከድንግል መወለዱ፤ (4) ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት የከፈለው ምትክ የሚሆን የሥርየት ዋጋ (5) ኢየሱስ ከነአካሉ መነሣቱና ዳግመኛም በአካል ወደ ምድር የሚመጣ መሆኑ።”— ሰታዲ ዲ ቲኦሎጂያ (ሃይማኖታዊ ጥናት)
b “ሥጋዊ አስተሳሰብ የተጠናወተው” ማለት መንፈሳዊ ወይም ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች በሚቃረን መንገድ ሥጋዊ ነገሮች ከፍ አድርጎ የሚመለከት ማለት ነው። ሥጋዊ ነገሮች ከሃይማኖት ወይም ከሃይማኖታዊ እምነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ነገሮች ናቸው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በ1926 አንድ የፕሮቴስታንት መጽሔት ሃይማኖታዊ አክራሪነት “ለፍሬ ለመብቃትም ሆነ በትግሉ ለመቀጠል የሚያስችል ብቃት የሌለው” “ባዶና ለይምሰል የሚደረግ” እንቅስቃሴ ነው ሲል ተናግሮ ነበር