ከዓለም አካባቢ
በስደተኞች ላይ በር መዝጋት
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሳዳኮ ኦጋታ ባለፉት ሃያ ዓመታት የስደተኞች ቁጥር በመላው ዓለም በስምንት እጥፍ ያደገ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት “የባዕድ አገር ሰዎችን የመጥላትና የመፍራት አዝማሚያ አስደንጋጭ በሆነ መጠን ተስፋፍቷል።” እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ 19.7 ሚልዮን የሚያክሉ ስደተኞች ከራሳቸው አገር ውጭ የሚኖሩ ሲሆን 24 ሚልዮን የሚያክሉ ስደተኞች ደግሞ በገዛ አገራቸው ውስጥ ከመኖሪያ ስፍራቸው ተፈናቅለው ይኖራሉ። በመላው ዓለም ከ125 ሰዎች መካከል አንዱ በዓመፅ፣ በእርስ በርስ ጦርነት ወይም በስደት ምክንያት ከተለመደው መኖሪያ አካባቢው ተፈናቅሎ ለመኖር ተገድዷል። በዚህ ምክንያት “የዓለም ለችግሩ ምላሽ የመስጠት አቅም” እንዲሁም “መጠጊያ የመስጠት ሰብአዊ ወግና ልማድ” ተሸንፏል በማለት ዘ ዋሽንግተን ፖስት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ስደተኞች ስለተደረገው ጥናት በሰጠው ትችት ገልጿል። በርካታ አገሮች የራሳቸው አገር የኢኮኖሚ ድቀት ስለተጫናቸውና መፍትሔ የሌለው በሚመስለው የእርስ በርስ ግጭት ስለ ተሰላቹ በራቸውን መዝጋት ጀምረዋል። ጥናቱ እንዳመለከተው “በ1993 በመላው ዓለም ለስደተኞች መፈጠር ምክንያት ከሆኑት ግጭቶች መካከል አብዛኞቹ በተለያዩ አገሮች መካከል የተደረጉ ሳይሆኑ በአንድ አገር ውስጥ የተደረጉ የእርስ በርስ ግጭቶች ናቸው” ካለ በኋላ የእርስ በርስ ጦርነቶችን ለማጥፋት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ፖሊሲ እንዲቀረጽ ጠይቋል። ስደተኞች ግን አሁንም ለጥላቻ እንደተጋለጡ ናቸው።
የዓለም ሕዝብ ብዛት በኤድስ በሽታ ይቀንሳል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ ሕዝብ ክፍል የሚያሳትመው ፖፑሊ የተባለ መጽሔት “የኤች አይ ቪ መጠን በጣም በተስፋፋባቸው 15 አገሮች ኤድስ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል” ብሏል። ይህ መጽሔት ወርልድ ፖፑሌሽን ፕሮስፔክትስ፣ ዘ 1992 ሪቪዥን የተባለውን ሪፖርት በመመርኮዝ ከአሥር ዓመት በኋላ “በእነዚህ አገሮች የሚኖረው የሕዝብ ብዛት በኤድስ ምክንያት በ12 ሚልዮን ይቀንሳል። 9 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በኤድስ ምክንያት ሲሞቱ ልጅ በመውለጃ ዕድሜያቸው የሚሞቱ ሴቶች በመኖራቸው ምክንያት ደግሞ የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር ይቀንሳል” በማለት ተንብዮአል።
የአበባ ኃይል
የማዳጋስካር ደሴት ነዋሪዎች በደሴታቸው የሚበቅሉ ብዙ ዕፀዋት መድኃኒትነት እንዳላቸው ካወቁ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል። አፍሪካ፣ ኢንቫይረመንት ኤንድ ዋይልድ ላይፍ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው ከተለያዩ አበቦች በሚቀመሙ መድኃኒቶች አማካኝነት “ከትኩሳት እስከ ችፌና እስከ እባጭ የሚደርሱ የተለያዩ በሽታዎችን ያክማሉ።” በጣም ቆንጆ መልክ ያላት ኦርቺድ የተባለችው አበባ እንኳን ጥቅም አላት። አንግራኤኩም ኤቡርኒዩም የተባለው የዚህች አበባ ዝርያ ለቫይረሶችና ለውርጃ መከላከያነት በማገልገል ላይ ነው። በቅርቡ ሉኪሚያ የተባለውን በሽታ ለማከም የሚያስችል መድኃኒት ምንጭ በዚህች ደሴት ላይ ተገኝቷል። እርሱም ሮዚ ፐሪዊንክል (ካታራንተስ ሮዚየስ ) የተባለው አበባ ነው። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ከእነዚህ አበቦች ለመጠቀም የሚችሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? ይኸው ዘገባ “ገና ያልታወቁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዕፀዋት ዝርያዎች እንደ ዛፍ ቆረጣ፣ እርሻና ማዕድን ማውጣት በመሰሉት የንግድ ሥራዎች ምክንያት በየቀኑ ስለሚጠፉ በጣም መጣደፍ ያስፈልጋል” ብሏል።
ሊቀ ጳጳሱ ከበር ወደ በር መስበክን ደገፉ
የካቶሊክ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች የሆኑ ብዙ ሰዎች የዳግማዊ ጆን ፖልን የአደራ ቃል በመቀበል ከበር ወደ በርና በሮማ ጎዳናዎች እንዲሁም በኢጣልያ የገጠር ከተሞች ለመስበክ ተስማምተዋል። ላ ሪፑብሊካ በተባለው ጋዜጣ ላይ እንደተዘገበው “እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመፎካከር የተነሡት ወሬኞች የኢየሱስን የሕይወት ታሪክ ይናገራሉ።” በመጀመሪያው ቡድን ውስጥ የተካተቱት 15 ቤተሰቦች ብቻ ነበሩ። ቢሆንም ይህ ፕሮጀክት “በየቦታው በርካታ ፍሬ እንደሚያስገኝ” ተስፋ ያደርጋሉ። ይህ አዲስ እንቅስቃሴ የተጀመረበት ምክንያት ምንድን ነው? የማኅበራዊ ኑሮ ምሁር የሆኑት ማሪያ ማቺዮቲ የካቶሊክ ቤተ ክህነት “ሰዎችን የመያዝ ችሎታውንና ሃይማኖታዊ መስህቡን አጥቷል” ብለዋል። በዚህም ምክንያት በእነዚህ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት ጳጳሱ “የሰዎችን ስሜት በማነሳሳት የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለማሳደግ” ተስፋ ያደርጋሉ። ሰርጊዮ ክዊንሲዮ የተባሉት ካቶሊካዊ ደራሲ እንዲህ በማለት አክለዋል:- “በተስፋ ወይም በቀቢጸ ተስፋ ማንኛውም ነገር መጥቀሙ አይቀርም በሚል አስተሳሰብ ማንኛውም ዓይነት አጋጣሚ እንዲያመልጣቸው ያልፈለጉ ይመስላል።”
በትንባሆ ማጨስ ላይ የሚደረገው ልጓም ጠብቋል
በአውስትራሊያ ዋና ከተማ ክልል ሲጋራ ማጨስ አደገኛ መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ እንዲሰፍር የሚያስገድዱ አዳዲስ ሕጎች ወጥተዋል። ከሚያዝያ 1, 1994 ጀምሮ በማንኛውም የሲጋራ ፓኮ ላይ “ማጨስ ይገድላል”፣ “የአንተ ማጨስ በሌሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል”፣ “ማጨስ ሱሰኛ ያደርጋል”፣ “በነፍሰ ጡርነት ጊዜ ማጨስ በሕፃኑ ላይ ጉዳት ያደርሳል” እንደሚሉ ያሉ ማስጠንቀቂያዎች በግልጽ ሊታዩ በሚያስችላቸው መጠን መስፈር አለባቸው። ዘ ካንቤራ ታይምስ እንደገለጸው ማስጠንቀቂያዎቹ ከ25 በመቶ ያላነሰውን የፓኮ የፊት ለፊት ሽፋን መሙላት አለባቸው። በፓኮው ጀርባ ደግሞ ከአንድ ሦስተኛ ባላነሰ ቦታ ላይ የሚከተለው ቃል መስፈር ይኖርበታል። “በትንባሆ ጭስ ውስጥ ለካንሰር ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ኬሚካሎች አሉ። ጭሱ ወደ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ እነዚህ ኬሚካሎች በሳንባ ላይ ጉዳት ሊያደርሱና ካንሰር ሊያመጡ ይችላሉ። በማጨስ ምክንያት ከሚመጡት የካንሰር ዓይነቶች በጣም የተለመደው የሳንባ ካንሰር ነው። የሳንባ ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ምንም ዓይነት ምልክት ሳይሰጥና ሳይታወቅ አድጎ ይስፋፋል። አብዛኛውን ጊዜም አጣድፎ ይገድላል። በማጨስ ምክንያት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በአልኮልና በአደንዛዥ ዕፆች ምክንያት ከሚሞቱት ሰዎች በሦስት እጥፍ ይበልጣል። በማጨስ ምክንያት በሚመጡ ጠንቆች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመኪና አደጋ ከሚሞቱት በስድስት እጥፍ ይበልጣል።”
ከሕፃን ልጅ ጋር አብሮ መተኛት
“እናቶች አንድ ነገር ቢያደርጉ፣ ማለትም ልጆቻቸውን አንድ ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ብቻቸውን ሌላ አልጋ ላይ ከማስተኛት ይልቅ አብረዋቸው ቢተኙ ኖሮ ሲድስ የተባለውን ሕፃናትን በድንገት የሚደል በሽታ ለመቀነስ ከመቻላችን በላይ ይበልጥ ጤናማና ደስተኛ የሆኑ ልጆች ለማሳደግ እንችል ነበር።” ይህን የተናገሩት በካሊፎርኒያ የፖሞና ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ጀምስ ማክኬና ናቸው። ዘ ዳላስ ሞርኒንግ “አንድ ሕፃን ገላው ከወላጁ ገላ ጋር ተነካክቶ ሲተኛ ሌሊቱን በሙሉ የሰውነቱ አሠራር ሲስተካከል ያድራል” ብሏል። በተለያዩ ሙከራዎች አማካኝነት አንድ ሕፃን ከእናቱ ጎን ሲተኛ “አተነፋፈሱ፣ የልቡ ትርታና የእንቅልፉ መጠን የእናቱን መምሰል እንደሚጀምር ተረጋግጧል።” በተጨማሪም እናትና ልጅ ፊት ለፊት ስለሚሆኑ ሕፃኑ በፈለገበት ጊዜ ጡት ለመጥባት ይችላል። ሚስተር ሚክካና “ብቻቸውን በራሳቸው አልጋ ላይ የሚተኙ ሕፃናት የስሜት ረሀብ ይደርስባቸዋል። ይህም አእምሮአቸው በሚፈልገው መጠን እንዳይዳብርና ለሲድስ አደጋ ለሚዳርጉ ሁኔታዎች ይበልጥ እንዲጋለጡ እንደሚያደርግ እናምናለን” ብለዋል። ሕፃናት በተለምዶ ከእናቶቻቸው ጋር በሚተኙባቸው አገሮች የሲድስ መጠን በጣም አነስተኛ መሆኑን የሚያመለክቱ የስታትስቲክስ መረጃዎች አሉ።
ከቆሻሻ የሚሠሩ ሕንፃዎች
ቻይና ልዩ የሆነ ቆሻሻ የማስወገጃ ዘዴ አግኝታለች። የቤጅንግ የአካባቢና የሐይጂን ምርምር ተቋም ቆሻሻ ከሸክላ ጋር በመደባለቅ ጡብ ለመሥራት የሚያስችል ዘዴ ፈልስፏል። ቻይና ቱደይ የተባለው መጽሔት በዚህ መንገድ የሚሠራው ጡብ ምን ዓይነት ጥራት እንዳለው ሲገልጽ “ለሕንፃ ኢንዱስትሪ ሊያገለግሉ የሚችሉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ሸክላዎች” ብሏል። አንድ ፋብሪካ በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ “46, 884 ቶን ጥራጊ ቆሻሻ በመፍጀት” 54 ሚልዮን የሚያክሉ ጡቦች አምርቷል። ጡቦቹ 1, 800 እስከ 3, 600 ዲግሪ ፋራንሃይት በሚደርስ ሙቀት ከተቃጠሉ በኋላ “የንጽሕና ደረጃቸው ከማንኛውም ተራ ጡብ ያልተለየ ይሆናል።”
ሕፃናት በጦርነት ጊዜ
ዘ ስቴት ኦቭ ወርልድስ ችልድረን 1994 የተባለው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዘገባ እንዳመለከተው ባለፉት አሥር ዓመታት 1.5 ሚልዮን ሕፃናት በጦርነት ተገድለዋል። አራት ሚልዮን የሚያክሉ ተጨማሪ ሕፃናት ደግሞ አካለ ስንኩላን፣ ዓይነ ስውራን፣ ደንቆሮዎች ሆነዋል ወይም የአእምሮ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ስደተኛ የሆኑት ሕፃናት ቁጥር እጅግ ቢያንስ አምስት ሚልዮን እንደሚደርስ ተገምቷል። እንዲያውም ሕፃናት ለውጊያ የተመለመሉበት ሁኔታ አለ። በብዙ አገሮች በሕፃናት ላይ ሥቃይ ደርሷል ወይም የጭካኔ ድርጊቶችን እንዲመለከቱ ወይም በድርጊቶቹ እንዲካፈሉ ተገድደዋል። በአንድ አካባቢ ልጃገረዶችን አስገድዶ መድፈር “ከጦርነት መሣሪያዎች አንዱ” ሆኗል። ዘገባው እንደሚለው “የሥልጣኔ ውጪያዊ ሽፋን የአሁኑን ያህል ሳስቶ አያውቅም” ብሏል።
ውጤት ለማሻሻል ወይስ ለጤንነት?
የአጥንት ሐኪም የሆኑት ቪክቶር ማትሱዶ “በአጠቃላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚጠይቁ ስፖርቶች የአትሌቶችን ውጤት ለማሻሻል እንጂ ጤንነታቸውን ለማሻሻል አይጠቅሙም” እንዳሉ በቬጃ መጽሔት ላይ ተጠቅሷል። “ማንም ሰው ጤንነቱን ለማሻሻል አትሌት መሆን አያስፈልገውም። እንዲያውም ዶክተር ማትሱዶ እንደሚሉት “ከመጠን በላይ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሰው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ከማያደርግ ሰው ቀድሞ ይሞታል።” በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል:- “ብዙ ሰዎች አሁንም ትክክለኛ የሆነው አካላዊ እንቅስቃሴ በጣም ከባድ፣ ላብ የሚያመጣና ሰውነት የሚያስጨንቅ መሆን የሚገባው ይመስላቸዋል። ይህ ግን እውነት አይደለም። ትክክለኛ አካላዊ እንቅስቃሴ መጠኑ ልከኛ የሆነ፣ የማያሳምም ወይም ሰውነት የማያስጨንቅና የማያቆስል መሆን ይኖርበታል። . . . ብዙ እንቅስቃሴ ሳያደርግ ኖሮ ጥሩ አካላዊ ብቃት ቀስ በቀስ ለማዳበር ለሚፈልግ ሰው ከሁሉ የሚሻለው አካላዊ እንቅስቃሴ በእግር መሄድ ነው። በሳምንት ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ለግማሽ ሰዓት ያህል በእግሩ የሚሄድ ሰው የመሞት አጋጣሚው ምንም አይነት እንቅስቃሴ ከማያደርግ ሰው በ15 በመቶ ያነሰ ነው። ዶክተር ማትሱዶ በእግር የሚኬድበት ቦታ ደልዳላ መሬት እንዲሆንና የአካሄዱም ፍጥነት በቀላሉ ለመተንፈስና ከሰው ጋር ለማውራት የሚያስችል መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።
ካፊንና እርግዝና
በ1980 የዩናይትድ ስቴትስ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ነፍሰ ጡር ሴቶች በቡና፣ በሻይና በኮላ መጠጦች ውስጥ የሚገኘውን ካፊን የተባለ ቅመም ፍጆታ በጣም እንዲቀንሱ መክሮ ነበር። ይህ ምክር የተሰጠው በእንስሳት ላይ በተደረገ ሙከራ ላይ በመመሥረት ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ ወዲህ በእርጉዝ ሴቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች በካፊን አጠቃቀም ረገድ ጠንቃቃ መሆን እንደሚያስፈልግ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠዋል። ዘ ጆርናል ኦቭ አሜሪካን ሜዲካል አሶሰሽን አብዛኞቹ ጥናቶች በቀን ከ300 ሚሊ ግራም (ሦስት ስኒ ቡና ያክል) የሚበልጥ ካፊን መውሰድ በጽንሱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ቢያመለክቱም 75 በመቶ የሚያክሉ ነፍሰ ጡር ሴቶች ካፊን ይጠጣሉ። በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት ደግሞ በቀን ከ163 ሚሊ ግራም የሚበልጥ ካፊን መጠጣት እንኳን በአንዳንድ ሴቶች ላይ የውርጃ አደጋ የመድረሱን አጋጣሚ ከፍ እንደሚያደርግ አመልክቷል። የጥናቱ ጸፊዎች “በእርግዝና ወቅት ካፊን የሚገኝባቸውን መጠጦች በእጅጉ መቀነስ ምክንያታዊ የሆነ ምክር ነው” ብለዋል።
እንቅልፍ እንቅልፍ ይልሃልን?
በየምሽቱ በቂ እንቅልፍ ታገኛለህን? አንድ ተመራማሪ እንደሚሉት በቂ እንቅልፍ ማግኘትና አለማግኘትህን ከምታውቅባቸው መንገዶች አንዱ በጣም ጠግበህ በልተህ አሰልቺ ንግግር ወደሚሰጥበት ሙቀት ያለበት ክፍል መግባት ነው። ጥሩ ዕረፍት አግኝተህ ከነበረ ሰልችቶህ ትቁነጠነጣለህ እንጂ እንቅልፍ አይዝህም። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን እንዳለው 100 ሚልዮን የሚያክሉ አሜሪካውያን በቂ እንቅልፍ አያገኙም። አብዛኞቹ ሰዎች ከስምንት እስከ ስምንት ሰዓት ተኩል የሚደርስ የማታ እንቅልፍ ያስፈልጋቸዋል። ከ17 እስከ 25 ዓመት ዕድሜ የሚገኙ ደግሞ ከዚህ የበለጠ እንቅልፍ ያስፈልጋቸዋል። ብዙ ሰዎች ከሚያስፈልጋቸው ያነሰ እንቅልፍ እየተኙ የሚኖሩ ቢሆንም በቂ እንቅልፍ የማያገኙ ሰዎች ስህተት ለመሥራት ያላቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም “የእንቅልፍ ዕዳ” እየተከመረባቸው ይሄዳል። ትሪብዩን “ወላጆች ልጆቻቸው በዕረፍት ቀናት እስከ እኩለ ቀን ድረስ ስለሚተኙ ሰነፎች ናቸው በማለት በጣም ተማረው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ወጣቶች ብዙዎቹ ይህን ያህል የሚተኙት በሳምንቱ ውስጥ የተጠራቀመባቸውን የእንቅልፍ ዕዳ ለመክፈል ነው” ብሏል።