ሴቶች ስለ ጡት ካንሰር ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮች
በሁሉም አህጉሮች የጡት ካንሰር ሕመምተኞች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው። አንዳንዶች እንደሚገምቱት ከሆነ በመላው ዓለም እስከ 2000 ባሉት ዓመታት በየዓመቱ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሴቶች በጡት ካንሰር ይያዛሉ።
ይህ በሽታ የማያሰጋት ሴት ትኖር ይሆን? በሽታውን በቅድሚያ ለመከላከል ምን ማድረግ ይቻላል? ከዚህ ባላጋራ ጋር በመታገል ላይ የሚገኙ ሴቶችስ ምን ዓይነት ማጽናኛና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል?
ለቆዳ ካንሰር በአብዛኛው ምክንያት የሚሆነው ከፀሐይ የሚመጣው ልዕለሃምራዊ ጨረር ነው። የሳንባ ካንሰር በአብዛኛው የሚመጣው ትንባሆ በማጨስ ምክንያት ነው። የጡት ካንሰር ግን የሚመጣው በዚህ ምክንያት ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።
ይሁን እንጂ የዘር ውርሻ፣ የመኖሪያ አካባቢ ሁኔታና ከሆርሞኖች ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች በጡት ካንሰር ለመያዝ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለእነዚህ ሁኔታዎች የተጋለጡ ሴቶች በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
የቤተሰብ ሁኔታ
በጡት ካንሰር የተያዘች እናት፣ እህት፣ የእናቷ ወገን የሆነች አክስት ወይም ሴት አያት ወይም ደግሞ የቅርብ ዘመድ ያላት ሴት በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልዋ ከፍተኛ ይሆናል። በርካታ ዘመዶቿ በጡት ካንሰር የተያዙ ከሆኑ ደግሞ በዚህ በሽታ የመያዝ ዕድልዋ የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ይሆናል።
ዶክተር ፓትሪሽያ ኬሊ የተባሉት አሜሪካዊት ጀነቲስስት ለንቁ! እንደገለጹት በዘር ውርሻ ምክንያት በበሽታው የሚያዙ ሴቶች ቢኖሩም በዚህ ሳቢያ ለጡት ካንሰር የሚጋለጡት ሴቶች ከ5 እስከ 10 በመቶ ብቻ ናቸው። “የዘር ውርሻን ያህል ጠንካራ ያልሆኑ ምክንያቶች ከመኖሪያ አካባቢ ሁኔታዎች ጋር ተጣምረው በሚያሳድሩት ተጽእኖ ምክንያት በጡት ካንሰር የሚያዙ ሴቶች ቁጥር በርካታና በውል የማይታወቅ ነው” ሲሉ አብራርተዋል። በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ አንድ ዓይነት ጅን ያላቸው የቤተሰብ አባላት በአንድ አካባቢ እንደሚኖሩ የታወቀ ነው።
የመኖሪያ አካባቢ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
ዴቭራ ደቪስ የተባሉት ምሁር ሳይንስ በተባለው መጽሔት ላይ ባቀረቡት አስተያየት “ተጽእኖ የሚያሳድሩ በርካታ የመኖሪያ አካባቢ ሁኔታዎች እንዳሉ ግልጽ ነው” ብለዋል። ጡት በጨረር በቀላሉ ሊጎዱ ከሚችሉ የሰውነት ክፍሎች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ለጨረር የሚጋለጡ ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል። መርዛም ለሆኑ ኬሚካሎች የሚጋለጡም በዚሁ ዓይነት በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል።
ሌላው ከአካባቢ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ለጡት ካንሰር አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሁኔታ አመጋገብ ነው። አንዳንዶች የጡት ካንሰር በቪታሚን ዲ ጉድለት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው ይላሉ። ይህ ቪታሚን ሰውነት ካልስየም የተባለውን ማዕድን እንዲያዋህድ ሲረዳ ካልስየም ደግሞ የሴሎች እድገት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ይቆጣጠራል።
ሌሎች ጥናቶች ደግሞ በምግብ ውስጥ የሚኖረው ቅባት ራሱ ምክንያት ባይሆንም ለጡት ካንሰር አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል ያመለክታሉ። ኤፍ ዲ ኤ ኮንስዩመር የተባለው መጽሔት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ የቅባትና ከእንስሳት ተዋጽኦ የሚገኙ ፕሮቲኖች ፍጆታ ከፍተኛ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ በጡት ካንሰር ምክንያት የሚሞቱ ሴቶች ቁጥር በጣም ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል። “ጃፓናውያን ሴቶች የጡት ካንሰር በብዛት እንደማይዛቸው የታወቀ ሲሆን የአመጋገብ ልማዳቸው ከምዕራባውያኑ አመጋገብ ጋር እየተመሳሰለና የቅባት ፍጆታቸው እየጨመረ በሄደ መጠን በጡት ካንሰር የሚያዙ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
አንድ በቅርብ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ቅባት የበዛበት ምግብ የሚኖረው ከፍተኛ ካሎሪ መጠን ይበልጥ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ሳይንስ ኒውስ “እያንዳንዱ ትርፍ ካሎሪ በጡት ካንሰር የመያዝን ዕድል ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ከቅባት የተገኘ ካሎሪ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከሌሎች ምግቦች የሚገኘው ካሎሪ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ 67 በመቶ ይበልጣል” ብሏል። ትርፍ ካሎሪዎች ለውፍረት መጨመር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሲሆን በጣም ወፍራም የሆኑ ሴቶች፣ በተለይም ያረጡ ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዛቸው ዕድል በሦስት እጥፍ ይበልጣል። የሰውነት ስብ ኤስትሮጂን የተባለውን የሴቶች ሆርሞን ሲያመነጭ ይህ ሆርሞን ደግሞ በጡት ህብረህዋስ ላይ ጎጂ ለውጥ ሊያመጣና ካንሰር ሊያስከትል ይችላል።
የግል ታሪክና ሆርሞኖች
በጡት ውስጥ በሴቲቱ የሕይወት ዘመን በሙሉ በጡት ሕዋሳት ላይ የተለያየ ለውጥ የሚያስከትሉ ሆርሞኖች ይኖራሉ። ኦንኮሎጂስት የሆኑት ፖል ክሬ በአውስትራሊያን ዶክተር ዊክሊ ላይ “ይሁን እንጂ የጡት ህብረህዋስ በሆርሞን መነቃቃት ለሚከሰቱ ለውጦች ለረዥም ጊዜ መጋለጡ በአንዳንድ ሴቶች ላይ . . . ውሎ አድሮ ወደ ካንሰርነት ደረጃ የሚደርስ የሴሎች ለውጥ ያስከትላል” ሲሉ ጽፈዋል። በዚህ ምክንያት ቀደም ብለው ማለትም ከ12 ዓመት ዕድሜ በፊት የወር አበባ ማየት የጀመሩ ወይም ዘግይተው ያረጡ፣ ማለትም እስከ 50ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ቆይተው ያረጡ ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ይታሰባል።
በሕክምና አማካኝነት ተጨማሪ ኤስትሮጂን መውሰድ ከጡት ካንሰር ጋር ዝምድና ይኖረው ይሆን የሚለው ጥያቄ ብዙ ውዝግብ አስከትሏል። አንዳንድ ጥናቶች ተጨማሪ ኤስትሮጂን መውሰድ ለጡት ካንሰር እንደማያጋልጥ ቢያመለክቱም ለረዥም ጊዜ በወሰዱ ሴቶች ላይ በቀላሉ የማይገመት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። በ1992 የወጣው ብሪትሽ ሜዲካል ቡለቲን ጥናቶቹን ከመረመረ በኋላ “ለወሊድ መቆጣጠሪያነት ሳይሆን ለሕክምና ኤስትሮጂንን ለረዥም ጊዜ መውሰድ በጡት ካንሰር የመያዝን ዕድል ከ30-50 በመቶ ከፍ ሳያደርግ አይቀርም” ብሏል።
ለወሊድ መቆጣጠሪያነት በሚዋጡ መድኃኒቶችና በጡት ካንሰር መካከል ስላለው ዝምድና የቀረቡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት እነዚህን መድኃኒቶች መጠቀም በጡት ካንሰር የመያዝን አደጋ እምብዛም አይጨምርም። ይሁን እንጂ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ሆነው የተገኙ ቡድኖችም አሉ። ወጣት ሴቶች፣ ልጅ ወልደው የማያውቁ ሴቶችና የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን ለረዥም ጊዜ የወሰዱ ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከሌሎች ሴቶች 20 በመቶ ከፍ ብሎ ተገኝቷል።
ይሁን እንጂ በጡት ካንሰር ከተያዙ 4 ሴቶች መካከል ሦስቱ በምን ምክንያት በሽታው እንደያዛቸው በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። ስለዚህ የጡት ካንሰር አያሰጋኝም ልትል የምትችል ሴት ትኖራለች? የሚል ጥያቄ ይነሳል። ኤፍ ዲ ኤ ኮንስዩመር “ሐኪሙ ሁሉም ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድል እንዳላቸው አድርጎ ማየት አለበት” ሲል ሪፖርት አድርጓል።
ስለዚህ ሁሉም ሴቶች፣ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሴቶች በዚህ በሽታ የመያዝ አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ዶክተር ኬሊ የጡት ካንሰር የተለያዩ መንስዔዎች ያሉት ቢሆንም ‘እርጅናና ህዋሳት በትክክል መራባት አለመቻላቸው አንዳንድ ጊዜ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ’ ብለዋል።
በካንሰር የሚጠቃው ለምንድን ነው?
የሴቶችን ጡት አፈጣጠር ብንመረምር ለምን በቀላሉ በካንሰር እንደሚጠቃ ለመረዳት እንችላለን። በጡት ውስጥ ወተት የሚያመነጩ ጥቃቅን ከረጢቶችን ከጡቱ ጫፍ ጋር የሚያገናኙ ጥቃቅን ቱቦዎች አሉ። በእነዚህ ቱቦዎች ግድግዳ ዙሪያ ያሉት ህዋሳት የሴቲቱን ወርሐዊ ኡደት ተከትለው በመራባትና በመለዋወጥ ለእርግዝና፣ ወተት ለማዘጋጀትና ለማጥባት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ያደርጋሉ። አብዛኞቹ የጡት ካንሰሮች ማደግ የሚጀምሩት በእነዚህ ቱቦዎች ውስጥ ነው።
ሮዝ ኩሽነር የተባሉት ተመራማሪ ኦልተርኔቲቭስ፤ ኒው ደቨሎፕመንትስ ኢን ዘ ዋር ኦን ብረስት ካንሰር በተባለው መጽሐፋቸው የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል:- “ሁልጊዜ በተለያዩ ጣልቃ ገብ ለውጦች የሚጨናገፍ ልማዳዊ አሠራር፣ ምንም ያህል ተፈጥሮአዊ ቢሆን . . . ስህተት ላይ የመውደቁ ዕድል በጣም ከፍተኛ ነው።” አክለውም “በሥራ የተዳከመው የጡት ህዋስ ሁልጊዜ ‘ይህን ማድረግህን አቁም፣ ይህን ማድረግ ጀምር’ የሚል ትእዛዝ በሚያስተላልፍለት አንድ ዓይነት ሆርሞን ይጥለቀለቃል። አዲስ ከሚወለዱት ህዋሳት ብዙዎቹ ከቁጥጥር ውጭ መሆናቸው አያስገርምም” ሲሉ ገልጸዋል።
የጡት ካንሰር የሚጀምረው አንድ ጤነኛ ያልሆነ ህዋስ መራባት ሲጀምርና አስተዳደጉን መቆጣጠር ተስኖት ከመጠን በላይ መብዛት ሲጀምር ነው። እንዲህ ያሉት ህዋሳት መራባታቸውን ስለማያቆሙ ከጊዜ በኋላ በዙሪያቸው ያለውን ጤነኛ ህብረህዋስ በማጥቃት ጤነኛውን የአካል ክፍል በሽተኛ ያደርጋሉ።
የካንሰር ህዋሳት መዛመት
ካንሰሩ በጡት ውስጥ ብቻ የተወሰነ ከሆነ በቀዶ ሕክምና ሊወገድ ይችላል። የጡት ካንሰር ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሲዛመት ግን ሜታስታቲክ የጡት ካንሰር ይባላል። በጡት ካንሰር በሽተኞች ላይ ሞት የሚያስከትለው ዋነኛ ምክንያት ይህ ነው። የካንሰር ህዋሳት በጡት ውስጥ በብዛት ሲራቡና የእብጠቱ መጠን እየጨመረ ሲሄድ የካንሰር ህዋሳት ምንም ሳያስታውቁ ቀስ በቀስ ከነበሩበት እበጥ አፈትልከው ወደ ደም ሥርና ወደ ፍርንትቶች (lymph nodes) ይገባሉ።
የካንሰር ህዋሳት እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሩቅ ወደ ሆኑ የሰውነት ክፍሎች መጓዝ ይችላሉ። በደምና በፍርንትት ፈሳሽ ውስጥ የሚገኙትን ፀረ እንግዳ አካል ህዋሳት ጨምሮ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ማጥቃት ከጀመሩ እነዚህ የካንሰር ህዋሳት እንደ ጉበት፣ ሳንባና አንጎል ያሉትን ዋነኛ ብልቶች ሊወርሩ ይችላሉ። እነዚህንም ብልቶች ካንሰር ካስያዙ በኋላ ተራብተው እንደገና ሊሰራጩ ይችላሉ። ካንሰር መዛመት ከጀመረ የሴቲቱ ሕይወት ትልቅ አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው።
ስለዚህ ከጡት ካንሰር ለመዳን ዋነኛው ቁልፍ ሥር ከመስደዱና የመሰራጨት አጋጣሚ ከማግኘቱ በፊት በሽታው መኖሩን ማወቅ ነው። አንዲት ሴት በሽታው ሥር ከመስደዱ በፊት መኖሩን ልታውቅ የምትችለው እንዴት ነው? የጡት ካንሰር እንዳይዝ መከላከል የሚቻልበት መንገድ ይኖራል?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጡት ካንሰር ከተያዙ 4 ሴቶች መካከል ሦስቱ በምን ምክንያት በሽታው እንደያዛቸው በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም