የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 5/8 ገጽ 4-10
  • ከጡት ካንሰር ለመዳን የሚያስችሉ ቁልፎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከጡት ካንሰር ለመዳን የሚያስችሉ ቁልፎች
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መከላከያና አመጋገብ
  • ቀደም ብሎ ማወቅ
  • ሕክምና
  • ውጥረትና የጡት ካንሰር
  • ሴቶች ስለ ጡት ካንሰር ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮች
    ንቁ!—1998
  • የጡት ካንሰር ፈውስ ይገኝለት ይሆን? እንዴትስ መቋቋም ይቻላል?
    ንቁ!—2011
  • እጅግ አስፈላጊ የሆነ ድጋፍ
    ንቁ!—1998
  • የእናት ጡት ወተት የሚመረጥበት ምክንያት
    ንቁ!—1994
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 5/8 ገጽ 4-10

ከጡት ካንሰር ለመዳን የሚያስችሉ ቁልፎች

በአካባቢያችሁ እያደፈጠ ሰው የሚገድል አንድ ሽፍታ እንዳለ ብትሰሙ ራሳችሁንና ቤተሰባችሁን ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ አትወስዱም? ማንም ሰው ወደ ቤታችሁ ዘው ብሎ እንዳይገባ በሮቻችሁን ደህና አድርጋችሁ መቆለፋችሁ አይቀርም። በተጨማሪም ጥርጣሬ የሚፈጥር ዓይነት እንግዳ ሰው ስታዩ ወዲያው ለፖሊስ ታስታውቃላችሁ።

ታዲያ ሴቶች ቀሳፊ በሆነው የጡት ካንሰር ረገድ ከዚህ ያነሰ ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል? ራሳቸውን ከበሽታው ለመጠበቅና ቢያዙም የመዳን ዕድላቸውን ለማስፋት ምን ዓይነት እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ?

መከላከያና አመጋገብ

በዩናይትድ ስቴትስ ከ3 የካንሰር በሽታዎች መካከል የአንዱ መንስዔ ከአመጋገብ ጋር ግንኙነት ያለው ነው። የሰውነትን በሽታ የመከላከል ኃይል የሚያጠናክር አመጋገብ መከተል ዋነኛ መከላከያ ነው። ካንሰር ያድናል የሚባል ምግብ እስካሁን ያልተገኘ ቢሆንም አንዳንድ ምግቦችን መብላትና አንዳንዶቹን ደግሞ መቀነስ በሽታውን ሊከላከል ይችላል። በኒው ዮርክ ቫልሃላ የአሜሪካ ጤና ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሊዎናርድ ኮኸን “ትክክለኛውን ዓይነት አመጋገብ መከተል በጡት ካንሰር የመያዝን አጋጣሚ እስከ ሃምሳ በመቶ ድረስ ሊቀንስ ይችላል” ብለዋል።

ካልተፈተጉ የእህል ዝርያዎች እንደሚዘጋጅ ዳቦና እንደ ጥራጥሬ ያሉ አሰር የሚበዛባቸው ምግቦች የፕሮላክቲንንና የኤስትሮጂንን መጠን ለመቀነስ ይረዳሉ። ይህን የሚያደርጉት እነዚህን ሆርሞኖች እንዲዋሃዷቸው ካደረጉ በኋላ ከሰውነት እንዲወገዱ በማድረግ ሳይሆን አይቀርም። ኒውትሪሽን ኤንድ ካንሰር የተባለው መጽሔት እንደሚለው “ይህ መሆኑ የካንሰር ህዋሳትን መስፋፋት ሊያግድ ይችላል።”

ከእንስሳት የሚገኙ ቅባቶችን መቀነስም በጡት ካንሰር የመያዝን አጋጣሚ ሊቀንስ ይችላል። ፕሪቨንሽን የተባለው መጽሔት እንደሚለው ቅቤው የወጣለት ወተት መጠጣት፣ ቅቤ መቀነስ፣ ጮማ የሌለው ሥጋ መብላትና የዶሮ ቆዳ ገፍፎ መጣል ወደ ሰውነት የሚገባውን የሚረጋ ቅባት መጠን በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል።

እንደ ካሮት፣ ዙኪኒ ወይም ዱባ፣ ስኳር ድንች ያሉ ቪታሚን ኤ በብዛት የሚገኝባቸውን አትክልቶች እንዲሁም እንደ ስፒናችና ጎመን ያሉትን አረንጓዴ ቅጠሎች መመገብ በጣም ሊረዳ ይችላል። ቪታሚን ኤ የካንሰርነት ባሕርይ ያላቸው ህዋሳት እንዳይፈጠሩ ይከላከላል ተብሎ ይታሰባል። በተጨማሪም እንደ ብሮኮሊ፣ ብራሰልስ ስፕራውት፣ አበባ ጎመን፣ ጥቅል ጎመንና ባሮ ሽንኩርት የመሰሉት አትክልቶች ተከላካይ ኤንዛይሞችን የሚፈጥሩ ኬሚካሎች አሏቸው።

ዶክተር ፖል ሮደሪጌዝ ብሬስት ካንሰር—ዋት ኤቭሪ ውመን ሹድ ኖው በተባለው መጽሐፋቸው ጤነኛ ያልሆኑ ህዋሳትን ለይቶ የሚያውቀውና የሚያጠፋው በሽታ የመከላከል አቅማችን በአመጋገብ ሊጠናከር ይችላል ብለዋል። እንደ ቀይ ሥጋ፣ አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠሎችና ሼልፊሽ የመሰሉትን በብረት የበለጸጉ ምግቦች፣ አንዲሁም ቪታሚን ሲ በብዛት የሚገኝባቸውን ፍራፍሬዎችና አትክልቶች መመገብ ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ። ብዙ ቪታሚን ሲ የሚገኝባቸው ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በጡት ካንሰር የመያዝን አጋጣሚ በጣም እንደሚቀንሱ ጆርናል ኦቭ ናሽናል ካንሰር ኢንስቲትዩት ሪፖርት አድርጓል። የእብጠቱ እድገት እንዳይጨምር እንደሚከላከል በቤተ ሙከራዎች የተረጋገጠለት ጀንስተን በአኩሪ አተርና ከአኩሪ አተር በሚሠሩ ያልቦኩ ምግቦች ውስጥ ይገኛል። ይሁን እንጂ የዚህ ንጥረ ነገር ውጤታማነት በሰዎች ላይ ተሞክሮ ገና አልተረጋገጠም።

ቀደም ብሎ ማወቅ

ሬዲዮሎጂክ ክሊኒክስ ኦቭ ኖርዝ አሜሪካ የተባለው ጽሑፍ “አሁንም የጡት ካንሰርን ሂደት ለመቀየር የሚያስችለው በጣም አስፈላጊ እርምጃ በሽታው መኖሩን ቀደም ብሎ ማወቅ ነው” ይላል። በዚህ ረገድ ቁልፍ የሆኑት ሦስት እርምጃዎች በየወሩ የራስን ጡት በራስ መመርመር፣ በዶክተር የሚደረግ ዓመታዊ ምርመራና ማሞግራፊ ናቸው።

አንዲት ሴት እንደ ማበጥ ወይም መጠጠር የመሳሰሉ በጡቷ ላይ የሚታዩ አጠራጣሪ ነገሮችንና ስሜቶችን በንቃት መከታተል ስለሚኖርባት በየወሩ የራሷን ጡት በራሷ መመርመር ይኖርባታል። ያገኘችው ነገር ምንም ያህል አነስተኛ ቢሆን ወዲያው ሐኪሟን ማማከር ይኖርባታል። እብጠቱ ቀደም ብሎ መታወቁ የወደፊት ሕይወቷን ይበልጥ በተሻለ ሁኔታ መቆጣጠር እንድትችል ይረዳታል። ከስዊድን የተገኘ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ገና ያልተሰራጨ የጡት ካንሰር መጠኑ ከ15 ሚሊ ሜትር ያልበለጠ ከሆነና በቀዶ ሕክምና ከወጣ ሴቲቱ 12 ዓመት በሕይወት የመኖሯ ዕድል 94 በመቶ ይሆናል።

ዶክተር ፓትሪሽያ ኬሊ “የጡት ካንሰር የመመለስ አዝማሚያ ሳያሳይ ለ12 ዓመት ተኩል ከቆየ ዳግመኛ አይመለስም ለማለት ይቻላል። . . . ሴቶች በጣቶቻቸው ብቻ በመጠቀም ከአንድ ሴንቲ ሜትር ያነሰ መጠን ያላቸውን የካንሰር እበጦችን ፈልገው እንዲያገኙ ማስተማር ይቻላል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

በተለይ አንዲት ሴት 40 ዓመት ካለፋት በኋላ በየዓመቱ ሐኪም ዘንድ እየሄደች የጤና ምርመራ ብታደርግ ጥሩ ይሆናል። እብጠት እንዳለ ከታወቀ የጡት ስፔሻሊስት ወይም ቀዶ ሐኪም እንዲያየው ማድረግ ይበጃል።

የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ካንሰር ተቋም የጡት ካንሰርን ለመዋጋት ከሚያስችሉ ጥሩ መሣሪያዎች አንዱ ማሞግራም መነሳት ነው ይላል። ይህ ዓይነቱ የራጅ ምርመራ አንድ እብጠት አድጎ ሊታወቅ ወደሚችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ ከሁለት ዓመት በፊት እንዲታወቅ ይረዳል። ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ይህን ምርመራ ቢወስዱ ጥሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ “ምርመራው ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ አይደለም” ይላሉ ዶክተር ዳንኤል ኮፓንስ። ሁሉንም ዓይነት የጡት ካንሰሮች መርምሮ ማግኘት አይችልም።

በኒው ዮርክ የሚገኝ የአንድ የጡት ክሊኒክ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዌንዲ ሎገን ያንግ አንዲት ሴት ወይም ሐኪሟ የሚያጠራጥር ሁኔታ ቢመለከቱና ማሞግራሙ ግን ምንም ዓይነት ምልክት ባያሳይ በጡቱ ላይ የታየውን ምልክት ችላ ብሎ የራጁን ውጤት የማመን አዝማሚያ እንዳለ ለንቁ! ተናግረዋል። “በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ትልቅ ስህተት ይህ ነው” ይላሉ። ሴቶች የማሞግራፊን ካንሰርን የመመርመር ችሎታ በጥርጣሬ እንዲመለከቱና በጡት ላይ የሚታዩ ምልክቶችን በይበልጥ እንዲያምኑ መክረዋል።

ማሞግራፊ እብጠት መኖሩን ሊመረምር ቢችልም እብጠቱ ገር (የካንሰርነት ጠባይ የሌለው) ወይም ቂመኛ (የካንሰርነት ጠባይ ያለው) መሆንና አለመሆኑን ሊመረምር አይችልም። ይህ ሊታወቅ የሚችለው ከእብጠቱ በተወሰደ ቁራጭ ናሙና ላይ በሚደረግ ምርመራ ነው። የማሞግራም ምርመራ ለማድረግ የሄደችው አይሪን የገጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ሐኪሟ የራጁን ፊልም ተመልክቶ ያላት እብጠት የካንሰርነት ባሕርይ እንደሌለው በመግለጽ “ካንሰር እንደሌለብሽ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ” ይላታል። ማሞግራሙን ያነሳችው ነርስ ሁኔታው ደስ እንዳላላት ብትናገርም አይሪን ግን “ዶክተሩ ይህን ያህል እርግጠኛ ከሆነ የራሴ ፍርሃት የፈጠረው ችግር ብቻ ነው ብዬ አሰብኩ” በማለት ተናግራለች። ወዲያው ብዙ ሳይቆይ እብጠቱ በማደጉ አይሪን ሌላ ሐኪም አማከረች። ከእብጠቱ በተወሰደ ቁራጭ ናሙና ላይ የተደረገው ምርመራ በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ካንሰር እንደያዛት አረጋገጠ። አንድ እብጠት የካንሰርነት ባሕርይ ያለውና የሌለው መሆኑን ለማረጋገጥ (ከአሥሩ ስምንቱ የካንሰርነት ባሕርይ የላቸውም) ከእብጠቱ በተወሰደ ቁራጭ ናሙና ላይ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። አንድ እብጠት አጠራጣሪ ምልክቶች ካሳየ ወይም እያደገ ከሄደ ከእብጠቱ ላይ የተወሰደውን ቁራጭ ናሙና መመርመር አስፈላጊ ነው።

ሕክምና

በአሁኑ ጊዜ የተለመደውና ሙሉ ተቀባይነት ያገኘው የጡት ካንሰር ሕክምና ቀዶ ሕክምና፣ በጨረር ማስመታትና መድኃኒት መውሰድ ነው። ስለ እብጠቱ ዓይነት፣ መጠን፣ የመዛመት ባሕርይና ወደ ፍርንትቶች የተዛመተ ስለመሆኑና ስላለመሆኑ በቂ መረጃ ማግኘት እንዲሁም ሴቲቱ ያረጠች ወይም ያላረጠች መሆኗን ማወቅ ሐኪሙንም ሆነ በሽተኛዋን ምን ዓይነት ሕክምና ብትወስድ እንደሚሻል ለመወሰን ይረዳል።

ቀዶ ሕክምና። ጡቱንና በጡቱ አካባቢ የሚገኙትን ጡንቻዎችና ፍርንትቶች በሙሉ ቆርጦ ማውጣት ለበርካታ ዓመታት ሲሠራበት የቆየ ቀዶ ሕክምና ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እብጠቱንና ፍርንትቶቹን ብቻ ቆርጦ በማውጣትና ጨረር በማስመታት የሚሰጠው ሕክምና ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ ቆርጦ በማውጣት ከሚሰጠው ሕክምና ያላነሰ ውጤት አስገኝቷል። ይህ ዓይነቱ ሕክምና በሰውነት ቅርጽ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አነስተኛ በመሆኑ ለአንዳንድ ሴቶች ተመራጭነት ያለው ሕክምና ሆኗል። ይሁን እንጂ ብሪትሽ ጆርናል ኦቭ ሰርጀሪ ዕድሜያቸው አነስተኛ የሆኑና በአንድ ጡት ውስጥ በበርካታ ቦታዎች ካንሰር ያለባቸው ወይም ከሦስት ሳንቲ ሜትር የሚበልጥ መጠን ያለው እብጠት ያላቸው ሴቶች አጠቃላይ ቀዶ ሕክምና ካልተደረገላቸው የበሽታው እንደገና የመመለስ ዕድል በጣም ከፍተኛ እንደሚሆን ይናገራል።

በሽታው እንዳይመለስ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር በክሌቭላንድ ክሊኒክ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን ተገልጾአል:- “ደም መውሰድ . . . በደረት አካባቢ የሚገኙ ትላልቅ ጡንቻዎች ያልተወገዱበት ቀዶ ሕክምና ከተደረገ በኋላ ከበሽታው በመዳንም ሆነ ዳግመኛ እንዳይመለስ በማድረግ ረገድ አሉታዊ ተጽእኖ አለው።” ሪፖርቱ እንዳመለከተው በቀዶ ሕክምናው ወቅት ደም ከወሰዱት መካከል የአምስት ዓመት ዕድሜ ያገኙት 53 በመቶ የሚሆኑት ሲሆኑ ደም ካልወሰዱት መካከል ደግሞ ይህንን የሚያክል ዕድሜ ያገኙት 93 በመቶ ሆነዋል።

ዕድሜ በማርዘም ረገድ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘ ሌላ ነገር ደግሞ ዘ ላንሰት በተባለ መጽሔት ላይ ዶክተር አር ኤ ባድዊ የገለጹት ነው:- “የጡት ካንሰር በያዛቸው ያላረጡ ሴቶች ረገድ ቀዶ ሕክምናው የሚደረግበት የወር አበባ ዑደት ወቅት ሕክምናው በሚያስገኘው የረዥም ጊዜ ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል።” ሪፖርቱ እንዳመለከተው ኤስትሮጂን ባየለበት ወቅት ቀዶ ሕክምና ያደረጉ ሴቶች ያገኙት ውጤት የኤስትሮጂን መጠን በሚቀንስበት ወቅት ካደረጉት ሴቶች የከፋ ሆኖ ተገኝቷል። ከመጀመሪያዎቹ ክፍሎች የአሥር ዓመት ዕድሜ ያገኙት 54 በመቶ የሚሆኑት ሲሆኑ ከሁለተኞቹ ክፍሎች ግን 84 በመቶ የሚሆኑት ናቸው። ገና ላላረጡ የጡት ካንሰር ሕመምተኞች ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በጣም የተሻለ ሆኖ የተገኘው የወር አበባ ካበቃ ከ12 ቀን በኋላ ያለው ጊዜ ነው።

የጨረር ሕክምና። የጨረር ሕክምና የካንሰር ህዋሳትን ይገድላል። ጡትና በአካባቢው የሚገኙ የሰውነት ክፍሎች በማይወገዱበት ቀዶ ሕክምና ቀዶ ሐኪሙ ጡቱን ለማስቀረት ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ጥቃቅን የካንሰር ርዝራዦች ሊያመልጡት ይችላሉ። የጨረር ሕክምና እነዚህን ያመለጡ ህዋሳት ሊያስወግድ ይችላል። ይሁን እንጂ የጨረር ሕክምና በሚሰጥበት ጊዜ በመጠኑም ቢሆን በተቃራኒ ጎን በሚገኘው ጡት ውስጥ ካንሰር እንዲፈጠር የሚያደርግ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። ዶክተር በነዲክ ፍራስ በተቻለ መጠን በተቃራኒ ጎን የሚገኘው ጡት ለጨረር እንዳይጋለጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። “ካንሰር የተያዘ ጡት በጨረር በሚመታበት ጊዜ ቀላል የሆኑ ጥቂት ጥንቃቄዎች ቢደረጉ ወደ ተቃራኒው ጡት የሚደርሰውን ጨረር በእጅጉ መቀነስ ይቻላል” ብለዋል። በተቃራኒው ጎን በሚገኘው ጡት ላይ የ2.5 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያለው የእርሳስ ሽፋን ማድረግ ጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የመድኃኒት ሕክምና። የካንሰር ህዋሳትን በቀዶ ሕክምና ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም የጡት ካንሰር ከተገኘባቸው ሴቶች መካከል ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት በመጀመሪያ ላይ ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት የማያሳዩና ወደ ሌሎቹ የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጩ የሚችሉ ድብቅ የካንሰርነት ባሕርይ ያላቸው ሕዋሶች ይኖሯቸዋል። እነዚህን ሌሎቹን የሰውነት ክፍሎች የሚያጠቁ ህዋሳትን ለመግደል ኬሚካላዊ መድኃኒቶች በመጠቀም የሚሰጥ ኬሞቴራፒ የሚባል ሕክምና አለ።

በካንሰር እብጠቶች ውስጥ የተለያየ የመድኃኒት መቋቋም ችሎታ ያላቸው የተለያዩ ሴሎች ስለሚኖሩ ኬሞቴራፒ የሚያስገኘው ውጤት በጣም ውስን ነው። ከመድኃኒት ሕክምና የተረፉት ህዋሳት መድኃኒት ለማይደፍራቸው ለሌሎች አዳዲስ እብጠቶች ጥንስስ ይሆናሉ። ቢሆንም ዘ ላንሰት በጥር ወር 1992 እትሙ ኬሞቴራፒ አንዲት ሴት የአሥር ዓመት ተጨማሪ ዕድሜ የማግኘት ዕድሏን እንደ ዕድሜዋ ሁኔታ ከ5 እስከ 10 በመቶ እንደሚጨምር የሚያሳይ ማስረጃ አቅርቧል።

ኬሞቴራፒ ከሚያስከትላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች (side effects) መካከል ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ የፀጉር መርገፍ፣ መድማት፣ የልብ ሕመም፣ መካንነት፣ በሽታ የመከላከል አቅም ማጣትና ሉኪሚያ ይገኙበታል። ጆን ካርንዝ በሳይንቲፊክ አሜሪካን ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “እነዚህ ጉዳቶች ብዙ ሥር የሰደደና በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ካንሰር ለያዛት ሴት ከግምት ውስጥ የማይገቡ ቢሆኑም ገና ያልተሰራጨና በጣም አነስተኛ የሆነ [1 ሴንቲ ሜትር] የጡት ካንሰር ላላት ሴት ግን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ናቸው። ከቀዶ ሕክምና በኋላ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ሕክምና ባይሰጣት እንኳን በአምስት ዓመት ጊዜ በካንሰርዋ ምክንያት የመሞት ዕድሏ 10 በመቶ ያህል ብቻ ነው።”

የሆርሞን ሕክምና። ፀረ ኤስትሮጂን ሕክምና መስጠት ኤስትሮጂን ያለውን እድገት የማፋጠን ኃይል ያመክናል። ይህ የሚደረገው ገና ያላረጡ ሴቶች ከሆኑ እንቁልጢያቸውን በቀዶ ሕክምና በማውጣት ወይም መድኃኒት በመስጠት የኤስትሮጂን መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ነው። ከሁለቱ አንደኛው ሕክምና ከተሰጣቸው 100 ሴቶች መካከል የአሥር ዓመት ዕድሜ ሊያገኙ የቻሉት ከ8 እስከ 12 የሚሆኑ ሴቶች እንደሆኑ ዘ ላንሰት ሪፖርት አድርጓል።

የጡት ካንሰር ለያዛት ሴት የሚደረገው የሕክምና ክትትል በቀሪ የሕይወት ዘመኗ በሙሉ የሚቀጥል ነው። አንዱ ዓይነት ሕክምና ከከሸፈና በሽታው ካገረሸ ሌሎች ዓይነት ሕክምናዎች ውጤት ሊያስገኙ ስለሚችሉ ዘወትር የቅርብ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

ካኬክሲያ በተባለው የሕመም ሁኔታ ላይ የሚያነጣጥር ለየት ያለ የካንሰር ሕክምናም አለ። ካንሰር ሪሰርች የተባለው መጽሔት እንደሚያብራራው ከሆነ በካንሰር ከሚሞቱት ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የሚሞቱት በካኬክሲያ ምክንያት ነው። ካኬክሲያ ለብዙ ጊዜ በቆየ ሕመም ሳቢያ የጡንቻዎችንና የሌሎች ህብረ ህዋሳትን መመናመን የሚያመለክት ቃል ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሲራከስ ካንሰር ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ጆሴፍ ጎልድ “ለካኬክሲያ መንገድ ጠራጊ የሆኑት ባዮኬሚካላዊ ሁኔታዎች ካልኖሩ በስተቀር እብጠቶቹ በሰውነት ውስጥ ለማደግና ረዥም ዕድሜ ለማግኘት የሚችሉ አይመስለንም” በማለት ለንቁ! ገልጸዋል። ሃይድራዚን ሰልፌት የተባለውን መርዝነት የሌለው መድኃኒት በመጠቀም የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከእነዚህ መንገድ ጠራጊ ሁኔታዎች አንዳንዶቹን ማገድ ይቻላል። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሥር የሰደደ የጡት ካንሰር የያዛቸው በሽተኞች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑትን ባሉበት ሁኔታ ማቆየት ተችሏል።

አንዳንድ ሴቶች ቀዶ ሕክምና ከማድረግ ወይም መርዝነት ያላቸውን መድኃኒቶች ከመውሰድ ይልቅ አማራጭ በሚባሉት ወይም ባሕላዊ በሆኑ ሕክምናዎች መጠቀም መርጠዋል። በዚህ ክፍል የሚመደቡት የሕክምና ዓይነቶች በርካታ ሲሆኑ አንዳንዶቹ መድኃኒትነት ባላቸው እፀዋትና በምግቦች ይጠቀማሉ። የሆክሲ ሕክምና ከእነዚህ አንዱ ነው። ይሁን እንጂ የእነዚህን ሕክምናዎች ውጤታማነት ለማመዛዘን የሚያስችሉ ታትመው የወጡ ጥናቶች እምብዛም አይገኙም።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ከጡት ካንሰር መዳን የሚቻልባቸውን መንገዶች መጠቆም ቢሆንም ንቁ! የትኛውንም ዓይነት ሕክምና ከሌላው የተሻለ ነው አይልም። ማንኛውም ሰው የተለያዩትን የሕክምና ዓይነቶች በጥንቃቄ እንዲመረምር እናበረታታለን።—ምሳሌ 14:15

ውጥረትና የጡት ካንሰር

ዶክተር ኤች ባልትሩሽ አክታ ኒውሮሎጂካ በተባለው መጽሔት ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ወይም ለረዥም ጊዜ የቆየ ውጥረት የእብጠትን መፈጠር የሚያግደውን የሰውነት በሽታ የመከላከል ኃይል ሊያዳክም እንደሚችል ገልጸዋል። ድካም የሚበዛባቸው፣ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወይም የስሜት ድጋፍ የማያገኙ ሴቶች በሽታ የመከላከል አቅማቸው እስከ 50 በመቶ በሚደርስ መጠን ይቀንሳል።

በዚህም ምክንያት ዶክተር ባዚል ስቶል ማይንድ ኤንድ ካንሰር ፕሮግኖሲስ በተባለው ጽሑፍ ላይ “በሕክምናው ወቅትም ሆነ ከሕክምናው በኋላ በካንሰር በሽተኞች ላይ የሚደርሰውን አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ቁስል ለመቀነስ የተቻለው ጥረት ሁሉ መደረግ ይኖርበታል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ምን ዓይነት ድጋፍ ነው የሚያስፈልገው?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ካንሰር ያድናል የሚባል ምግብ እስካሁን ያልተገኘ ቢሆንም አንዳንድ ምግቦችን መብላትና አንዳንዶቹን ደግሞ መቀነስ በሽታውን ሊከላከል ይችላል። ዶክተር ሊዎናርድ ኮኸን ‘ትክክለኛውን ዓይነት አመጋገብ መከተል በጡት ካንሰር የመያዝን አጋጣሚ እስከ ሃምሳ በመቶ ድረስ ሊቀንስ ይችላል’ ብለዋል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሬዲዮሎጂክ ክሊኒክስ ኦቭ ኖርዝ አሜሪካ” የተባለው ጽሑፍ “አሁንም የጡት ካንሰርን ሂደት ለመቀየር የሚያስችለው በጣም አስፈላጊ እርምጃ በሽታው መኖሩን ቀደም ብሎ ማወቅ ነው” ይላል። በዚህ ረገድ ቁልፍ የሆኑት ሦስት እርምጃዎች:- ዘወትር የራስን ጡት በራስ መመርመር፣ በዶክተር የሚደረግ ዓመታዊ ምርመራና ማሞግራፊ ናቸው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ድካም የሚበዛባቸው፣ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወይም የስሜት ድጋፍ የማያገኙ ሴቶች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ይቀንሳል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ራስን በራስ መመርመር—በየወሩ የሚደረግ ምርመራ

አንዲት ሴት ጡቷን ራስዋ በራሷ መመርመር ያለባት የወር አበባዋ ካበቃ ከአራት እስከ ሰባት ቀን በኋላ ነው። ያረጡ ሴቶችም በየወሩ በተወሰነ ቀን መመርመር ይኖርባቸዋል።

በየወሩ በተወሰነ ቀን ልትመረምሪያቸው የሚገቡ ምልክቶች

• እብጠት ወይም ጠጠር ያለ ነገር (ትንሽም ሆነ ትልቅ መጠን ያለው) መኖሩን።

• የጡት ቆዳ መጨማደድ፣ መጎድጎድ ወይም ቀለም መቀየር።

• የጡት ጫፍ መጎድጎድ ወይም መጣመም።

• ሽፍታ ወይም የጡት ጫፍ ቆዳ መላጥ ወይም ፈሳሽ ማውጣት።

• የብብት ውስጥ እጢዎች ማበጥ።

• በጡት ቆዳ ላይ የሚገኙ መስመሮች ወይም ሽታ የሚባሉ ምልክቶች ሁኔታ መቀየር።

• የሁለቱ ጡቶች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ መበላለጥ።

ራስን በራስ የመመርመር ዘዴ

ቆመሽ ግራ እጅሽን ወደላይ አንሺ። ከጡትሽ ውጨኛ ጠርዝ ጀምረሽ በቀኝ እጅሽ ጣቶች መዳፍ ጫን እያልሽ እስከ ጡትሽ ጫፍ ድረስ ዙሪያውን ፈትሺ። በተጨማሪም በብብትሽና በጡትሽ መካከል ያለውን ሥፍራ ፈትሺ።

በጀርባሽ ከተኛሽ በኋላ ከግራ ትከሻሽ ሥር ትራስ አድርገሽ የግራ ክንድሽን ራስሽ ላይ ወይም ከማጅራትሽ በታች አድርጊ። ከላይ በተገለጸው ዓይነት ዙሪያውን ፈትሺ። ቀኙን ጡት በዚሁ ዓይነት ፈትሺ።

የጡትሽን ጫፍ በቀስታ ጫን በማድረግ ፈሳሽ ይወጣው እንደሆነ ተመልከቺ። የቀኝ ጡትሽንም በዚሁ ዓይነት ፈትሺ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ