እጅግ አስፈላጊ የሆነ ድጋፍ
ቨርጅንያ በአርጀንቲና የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ስትሆን “ከሚሰማኝ የሞት ፍርሃትና የመንፈስ ጭንቀት ጋር ሁልጊዜ እየታገልኩ ለመኖር ተገድጃለሁ” ትላለች። ከጡት ካንሰር ጋር በምታደርገው ትግል ምክንያት ጡቶችዋና ሁለቱም እንቁልጢዎቿ ተቆርጠው ወጥተዋል።a
በየትኛውም ዓለም የሚገኙ የጡት ካንሰር በሽተኞች በሽታው ይገድለኛል የሚል ፍርሃት ያድርባቸዋል። ይህ ፍርሃትና በሽታውን ተከትሎ የሚመጣው የሴትነት ባሕርይና ወልዶ የማጥባት ችሎታ ማጣት በአንዲት ሴት ሕይወት ላይ ከፍተኛ የስሜት መቃወስ ሊያስከትል ይችላል። የብቸኝነት ስሜት ስለሚጫናት በተስፋ ቢስነት ስሜት ትዋጣለች። ይህን የመሰለውን የስሜት ቁስል እንዴት መቋቋም ትችላለች?
ድጋፍ የማግኘት አስፈላጊነት
የዩናይትድ ስቴትስ ኗሪ የሆነችው ጆአን “ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋታል!” ትላለች። የዚህች ሴት እናትና አያት የሞቱት በጡት ካንሰር ሲሆን እሷም በተራዋ ከዚህ በሽታ ጋር የመዋጋት እጣ ተደቅኖባታል። ታማኝ የቤተሰብ አባሎችና ወዳጆች የሚሰጡት የሚያጽናና እርዳታና ድጋፍ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ነው። የጆአን ባለቤት ቴሪ ጥሩ ድጋፍ ሆኖላታል። ቴሪ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ለኔ እንደሚታየኝ ከሆነ ድርሻዬ እርሷን ማረጋጋት ነው። በራሷ እንድትተማመንና በሽታዋን ለመዋጋት የሚያስችላትን ብርታት የሚያስገኝላትን እንጂ ተስፋ እንድትቆርጥ የሚያደርጋትን የሕክምና ውሳኔ እንዳታደርግ መርዳት ነበረብኝ። ለካንሰር ቀዶ ሕክምና ያላትን ፍርሃት ማሸነፍ ነበረብን። ከሐኪሞቹ ጋር ባደረግነው ውይይት ጥያቄዎችዋና ሥጋቶችዋ በሙሉ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ሞክሬያለሁ።” ቴሪ በማከል “ይህ ለቤተሰቦቻችንና የቤተሰብ ድጋፍ ለማያገኙ ክርስቲያን ባልደረቦቻችን በሙሉ ልናደርገው የምንችለው ነገር ነው። ከሕክምና ባለሞያዎች ጋር በሚያደርጉት ውይይት ዓይን፣ ጆሮና ድምፅ ልንሆንላቸው እንችላለን” ብሏል።
በተለይ ነጠላ ለሆኑ ወይም ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል። አውስትራሊያዊቷ ዳያና እንዲህ ትላላች:- “ከአምስት ዓመት በፊት ባለቤቴ የካንሰር ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ቢሞትም ልጆቼ በሱ መሞት ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ሞልተውልኛል። ስሜታዊ ሳይሆኑ የደግነት መንፈስ አሳይተውኛል። ይህም ብርታት እንዳገኝ አስችሎኛል። የሚያስፈልገኝን ሁሉ ያለምንም ችግር ወዲያውኑ አሟልተውልኛል።”
የጡት ካንሰር በመላው ቤተሰብ ላይ የሚያሳድረው ስሜታዊ ጫና አለ። ስለዚህ ሁሉም የቤተሰብ አባላት የሌሎችን (በተለይ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ የመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን) ፍቅራዊ አሳቢነትና ድጋፍ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።
እናቷ በጡት ካንሰር ትሰቃይባት የነበረችው በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ረቤካ እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “ጉባኤ ትልቁ ቤተሰባችን በመሆኑ የጉባኤው አባላት የሚያደርጉት ነገር ከፍተኛ የሆነ ስሜታዊ ተጽእኖ አለው። ብዙዎቹ እናቴ የምትወስደውን ያልተለመደ ሕክምና የማይደግፉት ቢሆንም ስልክ በመደወልና እየመጡ በመጠየቅ አበረታተውናል። እንዲያውም አንዳንዶቹ እየመጡ ለየት ያለውን ምግቧን በማዘጋጀት ይረዱን ነበር። ሽማግሌዎች ስብሰባዎች እንዳያመልጡን በስልክ አማካኝነት እንድንከታተል አድርገዋል። ጉባኤው የገንዘብ ስጦታ የያዘ ፖስት ካርድ ልኮልናል።”
ጆአን እንደሚከተለው ብላለች:- “አሁንም እንኳ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ያሳዩኝን ፍቅር ሳስብ እንባ ይተናነቀኛል! ለሰባት ሳምንታት በየሳምንቱ ለአምስት ቀናት አፍቃሪ እህቶቼ ተራ ገብተው ከቤቴ ወደ ሆስፒታል ለሕክምና አመላልሰውኛል። ይህ ጉዞ በደርሶ መልስ 150 ኪሎ ሜትር የሚያክል ነበር! ለዚህ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ይሖዋን ከልብ አመሰግነዋለሁ!”
ሁላችንም ልናበረታታና ድጋፍ ልንሰጥ የምንችልበት ሌላው መንገድ የሚያንጹ አስተያየቶችን መስጠት ነው። አፍራሽ የሆኑ ነገሮችን በመናገር ሳይታወቀን ጭንቀታቸውን እንዳናባብስባቸው መጠንቀቅ ያስፈልገናል። በደቡብ አፍሪካ የምትኖረው ጁን “ካንሰር ተይዞ የማያውቅ ሰው ትክክለኛውን ነገር ይናገራል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። በእኔ ሁኔታ ሌሎች ሰዎች አዎንታዊ በሆነ መልኩ ካልሆነ በስተቀር ስለ ካንሰር ጨርሶ ባያነሱ ይሻለኛል” ብላለች። ጃፓናዊቷ ኖሪኮ ከዚሁ ሐሳብ ጋር በመስማማት “ሰዎች ካንሰር አሟት ስለ ዳነችና በሽታዋ ስላልተመለሰባት ሴት ሲነግሩኝ እኔም እንደዚች ሴት እሆን ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች።
አንዳንድ ሴቶች አሥሬ ስለ በሽታቸው ማውራት እንደማያስደስታቸው አትዘንጉ። ሌሎች ግን ስለ ሕመማቸው፣ በተለይ ቅርባቸው ለሆኑ ሰዎች መናገር ያሽላቸዋል። ታዲያ ለበሽተኛዋ የሚበጃት የትኛው እንደሆነ እንዴት ማወቅ ይቻላል? የዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪ የሆነችው ሄለን “ሕመምተኛዋ ራስዋ ስለ በሽታው መናገር ትፈልግ እንደሆነ ጠይቋትና እንድትናገር ፍቀዱላት” የሚል ሐሳብ ሰጥታለች። የዴንማርክ ተወላጅ የሆነችው ኢንግሊስም “ለማዳመጥ ዝግጁ ሁኑ፣ ብቻዋን ሆና እንዳትተክዝ አትለይዋት” ትላለች።
አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት ማድረግ
የጡት ካንሰር ሕክምና በሽተኛዋን ለሳምንታት፣ ለወራት ወይም ለዓመታት ደካማና አቅመቢስ ሊያደርጋት ይችላል። የጡት ካንሰር የያዛት ሴት ከሚያጋጥሟት ትላልቅ ፈተናዎች አንዱ የቀድሞውን ያህል መሥራት አለመቻሏ ሊሆን ይችላል። ሁኔታዋን ተረድታ አቅሟ የሚፈቅድላትን ያህል ብቻ መሥራትና በቀኑ ውስጥ የተወሰነ እረፍት መውሰድ ይኖርባታል።
የመንፈስ ጭንቀት ሲሰማት አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርባታል። ኖሪኮ የራሷን ተሞክሮ ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “የምወስደው የሆርሞን ሕክምና የመንፈስ ጭንቀት ያመጣብኛል። በዚህ ሁኔታዬ የምፈልጋቸውን ነገሮች ማድረግ ስለማልችል በይሖዋ ዘንድና በጉባኤው ውስጥ ምንም ዋጋ የሌለኝ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል። አስተሳሰቤ ይበልጥ አሉታዊ እየሆነ ሲሄድ በካንሰር የሞቱ ዘመዶቼ ያሳለፉትን የመጨረሻ ሥቃይ አስታውሳለሁ። ‘እኔስ እንደነሱ ያን ሁሉ ሥቃይ መቋቋም እችል ይሆን?’ ብዬ ሳስብ ፍርሃት ይውጠኛል።”
ኖሪኮ በመቀጠል እንዲህ ትላለች:- “በይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች አማካኝነት ይሖዋ ስለ ሕልውናችን ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ማሰብና አስተሳሰቤን ለማስተካከል ጥረት ማድረግ የጀመርኩት በዚህ ወቅት ነበር። ለአምላክ የማደር ባሕርይ የሚገለጸው በምናከናውነው ሥራ መጠን ሳይሆን ትክክለኛውን ዝንባሌ ይዞ በመሥራት እንደሆነ ለማወቅ ቻልኩ። ይሖዋ በልቤ ሁኔታና በአስተሳሰቤ እንዲደሰት ስለፈለግኩ በክርስቲያን አገልግሎት ልሠራ የምችለው ምንም ያህል አነስተኛ ቢሆን እርሱን በደስታና በሙሉ ነፍስ ለማገልገል ወሰንኩ።”
የጡት ካንሰር የያዛቸው ሴቶች ስለሚያጋጥማቸው ዕጣ እርግጠኛ ሳይሆኑ ረዥም ጊዜ ስለሚያሳልፉ የነበራቸው አዎንታዊ አመለካከት ተሟጥጦ ሊያልቅ ይችላል። ዳያና ከሁሉ ይበልጥ የረዳት ልቧና አእምሮዋ ይሖዋ አምላክ የሰጣትን ግሩም ነገሮች በማሰብ እንዲያዝ ማድረግዋ እንደሆነ ትናገራለች:- “ቤተሰቤ፣ ወዳጆቼ፣ ቆንጆ ሙዚቃ፣ ኃይለኛውን የባሕር ሞገድና የሚያምረውን የፀሐይ ጥልቀት መመልከት ደስ የሚያሰኙኝ የይሖዋ ስጦታዎች ናቸው።” በተለይ ደግሞ እንዲህ ስትል ታበረታታለች:- “ስለ አምላክ መንግሥት ለሰዎች ተናገሩ። በዚህች መንግሥት በምትተዳደረውና በሽታ የሚባል ነገር በማይኖርባት ምድር ላይ ለሚኖሩት ሁኔታዎች ከፍተኛ ናፍቆት እንዲያድርባችሁ አድርጉ!”—ማቴዎስ 6:9, 10
ቨርጅንያም በሕይወት የምትኖርበትን ዓላማ ማሰላሰሏ የሚሰማትን የመንፈስ ጭንቀት ለመዋጋት የሚያስችል ኃይል ሰጥቷታል። “ልሠራው የሚገባኝ በጣም ውድ የሆነ ሥራ ስላለኝ ከፍተኛ የመኖር ፍላጎት አለኝ” ትላለች። ፍርሃትዋ አይሎ ከፍተኛ ጭንቀት ሲሰማት “ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወኝ በማወቅ ሙሉ ትምክህቴን በእርሱ ላይ እጥላለሁ። ‘በሕያዋን አገር በእግዚአብሔር ፊት እሄዳለሁ’ የሚለውን መዝሙር 116:9 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስባለሁ።”
እነዚህ ሁሉ ተስፋቸውን በመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ በይሖዋ ላይ የጣሉ ሴቶች ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የ2ኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍ በምዕራፍ 1 ቁጥር 3 እና 4 ላይ ይሖዋን “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ካለ በኋላ “እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል” ይላል። ይሖዋ በእርግጥ መጽናናት የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እጁን ዘርግቶ ይደግፋል?
ጃፓናዊቷ ሚኤኮ “በእርሱ አገልግሎት በመጽናቴ ብርቱ የሆነውን የይሖዋ ማጽናኛና እርዳታ እንዳገኘሁ እርግጠኛ ነኝ” በማለት ትመልሳለች። ዮሺኮም “የተሸከምኩትን ሥቃይ ሰዎች ሊረዱልኝ ባይችሉ እንኳ ይሖዋ ሁሉንም ያውቃል። በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንደረዳኝም እርግጠኛ ነኝ” ብላለች።
ጆአን እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ጸሎት ተስፋ ከመቁረጥ አዘቅት ጎትቶ የማውጣትና ቀጥ አድርጎ በሁለት እግር የማቆም ኃይል አለው። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የፈጸማቸውን አስደናቂ ፈውሶችና ወደፊት በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚፈጽማቸውን ፍጹም የሆኑ ፈውሶች ሳስብ በጣም እጽናናለሁ!”—ማቴዎስ 4:23, 24፤ 11:5፤ 15:30, 31
የጡት ካንሰርም ሆነ ሌላ ዓይነት በሽታ የማይኖርበት ዓለም ይመጣል ብላችሁ ታስባላችሁ? የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው ይሖዋ ይህ እንደሚሆን ቃል ገብቶልናል። ኢሳይያስ 33:24 በምድር ላይ የሚኖር ማንም ሰው ታምሜአለሁ ስለማይልበት ጊዜ ይናገራል። ይህ ተስፋ በቅርቡ በልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ ሲገዛና የበሽታን፣ የሐዘንንና የሞትን መንስኤዎች ጠራርጎ ሲያጠፋ ፍጻሜውን ያገኛል! ስለዚህ አስደናቂ ተስፋ ራእይ 21:3 እስከ 5 የሚናገረውን ለምን አታነቡም? አይዟችሁ። ከእውነተኛ መጽናናት በምታገኙት ድጋፍ የወደፊቱን ጊዜ መቋቋም ትችላላችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እንቁልጢዎች ላላረጡ ሴቶች ዋነኛ የኤስትሮጂን ምንጭ ናቸው።