የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት
አንዲት ማረጥ የሚያስከተለውን ለውጥ የቀመሰች ሴት “ለአንዲት ሴት በጣም አስደሳች የሆነ የሕይወት ክፍል ነው ለማለት አልችልም። ቢሆንም ትምህርት ሊገኝበት የሚችል ይመስለኛል። አቅሜን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ተምሬአለሁ። ሰውነቴ ተጨማሪ እንክብካቤ ወይም ዕረፍት እንደሚያስፈልገው ከተሰማኝ እታዘዘውና የሚያስፈልገውን ዕረፍት እሰጠዋለሁ” ብላለች።
ካናዲያን ፋምሊ ፊዚሽያን በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ በሴቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው በማረጥ ረገድ ከሁሉ የሚከፋው ችግር “ምን ሊያስከትል እንደሚችል በቅድሚያ አለማወቅ” ነው። ማረጥ ተፈጥሯዊ የሆነ ሽግግር መሆኑን የተገነዘቡ ሴቶች ግን “ስለ ወደፊቱ ሕይወታቸው ይበልጥ ብሩሕ የሆነ ተስፋ ሲኖራቸው ብዙ የጭንቀት፣ የመረበሽና የመበሳጨት ስሜት አልታየባቸውም።”
ምንድን ነው?
ዌብስተር ናይንዝ ኒው ኮሊጂየት ዲክሽነሪ ማረጥ (menopause) የሚለውን ቃል “ከ45 እስከ 50 ባለው ዕድሜ ውስጥ የሚከሰት የወር አበባ ዑደት ተፈጥሯዊ መቋረጥ” በማለት ይፈታዋል። በተጨማሪም ማረጥ ሲባል በደፈናው የወር አበባ ዑደት ለዘለቄታው መቋረጥ እንደሆነ ይታሰባል።
የአንዳንድ ሴቶች የወር አበባ ዑደት የሚቋረጠው በድንገት ነው። ወቅቱን ጠብቆ የመጣው የወር አበባ ታይቶ ሲያቆም ድጋሚ ሳይታይ በዚያው ይቀራል። የሌሎቹ ደግሞ ከሦስት ሳምንት እስከ በርካታ ወራት ድረስ እያሰለሰ ሲመጣ ይቆይና ይቆማል። አንዲት ሴት የወር አበባዋን ሳታይ ሙሉ ዓመት ካለፋት የመጨረሻውን የወር አበባ ካየችበት ጊዜ ጀምሮ እንዳረጠች እርግጠኛ ልትሆን ትችላለች።
የሚከሰተው መቼና ለምንድን ነው?
ከዘር የሚወረሱ ሁኔታዎች፣ በሽታ፣ ውጥረት፣ መድኃኒትና ቀዶ ሕክምና የወር አበባ ዑደት የሚቋረጥበትን ጊዜ በተመለከተ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። በሰሜን አሜሪካ ሴቶች የሚያርጡበት አማካኝ ዕድሜ 51 ዓመት ነው። ከ40ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ እስከ 50ዎቹ ዓመታት አጋማሽ በሚደርሱ የተለያዩ ዕደሜዎች ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም ከእነዚህ ዕድሜዎች የሚቀድምበትም ሆነ የሚዘገይበት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው። የሚያጨሱ ሴቶች ቀደም ብለው እንደሚያርጡና ክብደታቸው ከፍ ያለ ሴቶች ደግሞ ዘግይተው እንደሚያርጡ ስታትስቲካዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አንዲት ሴት በሕይወትዋ ሙሉ የሚኖሯትን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ እንቁላሎች በሙሉ ይዛ ትወለዳለች። በእያንዳንዱ የወር አበባ ዑደት ከ20 እስከ 1,000 የሚደርሱ እንቁላሎች ያኮርታሉ። ከዚያም አንዱ ወይም አንዳንድ ጊዜ ከአንድ የሚበልጡ እንቁላሎች ጽንስ ለመሆን ተዘጋጅተው ከእንቁልጢ (ovary) ይለቀቃሉ። ሌሎቹ ያኮረቱ እንቁላሎች ሟሽሸው ይጠፋሉ። በተጨማሪም ከእንቁላል ማኩረት ሂደት በተጓዳኝ ኤስትሮጂንና ፕሮጀስትሮን የሚባሉት ሆርሞኖች መጠን ከፍና ዝቅ ይላል።
አንዲት ሴት በ30ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ስትደርስ የኤስትሮጂንና የፕሮጀስትሮን መጠን ቀስ በቀስ አለዚያም በድንገት መቀነስ ስለሚጀምር በእያንዳንዱ የወር አበባ ዑደት እንቁላል መለቀቁ እየቀረ ይሄዳል። የወር አበባ የሚመጣበት ጊዜ መዛባትና አብዛኛውን ጊዜ መዘግየት ይጀምራል። የወር አበባ ፍሰት ከቀድሞው የተለየ በመሆን ያንሳል ወይም ይበዛል። በመጨረሻም እንቁላሎች መለቀቃቸው ሲያቆም የወር አበባ መምጣቱን ያቆማል።
እስከ አሥር ዓመት ሊደርስ የሚችለው የሆርሞን መጠንና የእንቁልጢ አሠራር ለውጥ ሂደት በወር አበባ መቋረጥ ይደመደማል። ይሁን እንጂ ከማረጥ በኋላም ቢሆን ከ10 እስከ 20 ለሚደርሱ ዓመታት እንቁልጢዎች መጠኑ አነስተኛ የሆነ ኤስትሮጂን ማመንጨታቸውን ይቀጥላሉ። በተጨማሪም የአድሬናሊን እጢዎችና የስብ ሴሎች ኤስትሮጂን ያመነጫሉ።
ጎላ ያሉ የሕይወት ለውጦች
የኤስትሮጂን መጠን በሚቀንስበት ጊዜ ለሕልውናቸው ኤስትሮጂንን በሚፈልጉ ወይም በዚህ ሆርሞን ለውጥ በሚነኩ ሕዋሳት ላይ ለውጥ ይታያል። የትኩሳትና የላብ መፈራረቅ የሚፈጠረው ሆርሞኖች የሰውነትን የሙቀት መጠን በሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ላይ በሚያስከትሉት ለውጥ ምክንያት እንደሆነ ይታሰባል። ትክክለኛው ሂደት በሚገባ የማይታወቅ ቢሆንም የሰውነት ሙቀት ማስተካከያ (thermostat) ዝቅ ስለሚል ከዚህ በፊት የማያስጨንቅ የነበረው ሙቀት አሁን በድንገት በጣም ሞቃት ሆኖ ስለሚሰማ ሰውነት ትኩሳትና ላብ በማምጣት ራሱን ያቀዘቅዛል።
ጌል ሺ ዘ ሳይለንት ፓሴጅ—ሜኖፖዝ በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለዋል:- “የትኩሳትና የላብ መፈራረቅ ከሚደርስባቸው ሴቶች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት ይህ ችግር የሚጀምራቸው ገና የወር አበባቸው ከመቋረጡ በፊትና በ40 ዓመት ዕድሜያቸው አካባቢ ነው። አብዛኞቹ ሴቶች ትኩሳትና ላብ የሚፈራረቅባቸው ለሁለት ዓመት ያህል ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። አንድ አራተኛ የሚሆኑት ደግሞ ለአምስት ዓመት ያህል ሲቆይባቸው 10 በመቶ የሚሆኑት በቀረው የሕይወታቸው ክፍል በሙሉ ይቆይባቸዋል።”
አንዲት ሴት በዚህ የሕይወትዋ ዘመን የኤስትሮጂንዋ መጠን እየቀነሰ በሄደ መጠን የብልትዋ ህብረ ሕዋሳት (tissues) ይሳሳሉ፣ እርጥበታቸውም ይቀንሳል። ሴቶች በማረጥ ምክንያት ከሚያጋጥሟቸው ሌሎች ለውጦች መካከል “የሌሊት ላብ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ሽንት የመቋጠር ችግር፣ ድንገተኛ የሆነ የሆድ መነፋት፣ የልብ ምት መጨመር፣ አለምክንያት ማልቀስ፣ በቁጣ መገንፈል፣ ከባድ ራስ ምታት፣ የቆዳ ማሳከክና መሻከር፣ መርሳት” እንደሚገኙበት ጌል ሺ ይናገራሉ።
የጭንቀት ስሜት የሚሰማባቸው ጊዜያት
የኤስትሮጂን መቀነስ የጭንቀት ስሜት ያስከትላልን? ይህ ብዙ ክርክር ያስነሳ ጥያቄ ነው። መልሱ ከወር አበባቸው በፊት የስሜት መለዋወጥ እንደሚያጋጥማቸውና ሌሊት ስለሚያልባቸው እንቅልፍ የማጣት ችግር እንዳለባቸው ባሉ አንዳንድ ሴቶች ላይ የጭንቀት ስሜት ያስከትላል ወደሚለው ያዘነብላል። በዚህ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ሴቶች የሆርሞን መጠን መለዋወጥ ለሚያስከትለው የስሜት መለዋወጥ በቀላሉ የመሸነፍ አዝማሚያ ያላቸው ይመስላል። እንደነዚህ ያሉት ሴቶች፣ ጌል ሺ እንደሚሉት ከሆነ “የመሸጋገሪያውን ወቅት ሲያልፉ የእፎይታ ስሜት ይሰማቸዋል።” ይህም የሚሆነው የሆርሞናቸው መጠን መለዋወጡን ስለሚያቆምና አንድ ዓይነት ስለሚሆን ነው።
በጨረር ሕክምና ወይም በመድኃኒት ምክንያት ወይም ሁለቱም እንቁልጢዎች በቀዶ ሕክምና በመውጣታቸው ምክንያት በድንገት የወር አበባቸው የሚቋረጥባቸው ሴቶች ከማረጥ ጋር የሚመጡ ይበልጥ ከበድ ያሉ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። እነዚህ ሕክምናዎች የኤስትሮጂን መጠን በድንገት እንዲያሽቆለቁል ስለሚያደርጉ ወዲያው የማረጥ ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ። እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች የሴቲቱ የጤንነት ሁኔታ የሚፈቅድ ከሆነ የኤስትሮጂን መተኪያ ሕክምና ሊታዘዝ ይችላል።
በማረጥ ምክንያት የሚመጡ ችግሮች ከሴት ወደ ሴት፣ የሥጋ ዝምድና ባላቸው ሴቶች መካከል እንኳን ይለያያሉ። እንዲህ የሚሆነው የሁሉም ሴቶች የሆርሞን መጠን አንድ ዓይነት ስላልሆነና የሚቀንሰውም በአንድ ዓይነት ፍጥነት ስላልሆነ ነው። በተጨማሪም ሴቶች ወደ ማረጥ ዕድሜ በሚጠጉበት ጊዜ የሚኖራቸው ስሜታዊ ሁኔታ፣ ውጥረት፣ ተስፋና ችግሮችን የመቋቋም ችሎታ የተለያየ ይሆናል።
አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች በሚያርጡበት ወቅት ሌሎች ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎችም አብረው ይመጣሉ። በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መጦርን፣ የሥራ ጫና፣ ልጆች አድገው ጎጆ ሲወጡ መመልከትን የመሰሉና ሌሎች በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚመጡ ለውጦች ተጨማሪ ውጥረት ይፈጥሩባቸዋል። እነዚህ ውጥረቶች እንደ መርሳት፣ ትኩረት ማጣት፣ ፍርሃት፣ ግልፍተኝነትና ጭንቀት የመሰሉትን አካላዊና ስሜታዊ ቀውሶች ሊያስከትሉ ይችላሉ።
አንድ የዕድሜ ደረጃ
አንዲት ሴት ስታርጥ የሚያከትመው የመውለጃ ዕድሜዋ እንጂ ፍሬያማ ሥራ ልትሠራ የምትችልበት ዕድሜ አይደለም። የወር አበባዋ ከተቋረጠ በኋላ የሆርሞንዋ መጠን በየወሩ መለዋወጡን ስለሚያቆም አብዛኛውን ጊዜ የተረጋጋ ባሕርይ ይኖራታል።
በጣም ግልጽ የሆነ ለውጥ በመሆኑ በወር አበባ መቋረጥ ላይ አተኮርን እንጂ ይህ ለውጥ አንዲት ሴት የመውለጃ ዕድሜዋን ጨርሳ ወደሚቀጥለው የዕድሜ ደረጃ መሸጋገሯን የሚያመለክት ከመሆን የበለጠ ትርጉም የለውም። ጉርምስና፣ እርግዝናም ሆነ መውለድ የሆርሞን፣ የአካልና የስሜት መለዋወጥ የሚያስከትሉ የሽግግር ወቅቶች ናቸው። ስለዚህ ማረጥም በአንዲት ሴት ሕይወት ውስጥ በሆርሞን ለውጥ ምክንያት ከሚደርሱት ለውጦች መካከል የመጨረሻው እንጂ ብቸኛው ለውጥ አይደለም ማለት ነው።
እንግዲያው ማረጥ አንድ የዕድሜ ደረጃ ነው። የጆርናል ኦቭ አሜሪካን ሜዲካል ውመንስ አሶስዬሽን የቀድሞ አዘጋጅ “ምናልባት ሰዎች ማረጥን እንደ ችግር ወይም እንደ ትልቅ ለውጥ አድርገው መመልከታቸውን ትተው ‘ከብዙ የሕይወት ለውጦች አንዱ ብቻ’ እንደሆነ የመመልከት ትክክለኛ ዝንባሌ ላይ ይደርሱ ይሆናል” በማለት ጽፈዋል።
ውመን ካሚንግ ኦቭ ኤጅ የተባለው መጽሐፍ “ለአንዲት ሴት የወላድነት ዕድሜዋ ማክተም እንደ ወላድነት ዕድሜዋ መጀመር ሊቀር የማይችልና ተፈጥሯዊ ነው። ማረጧ የሰውነቷ ውስጣዊ የጊዜ መቆጣጠሪያ በትክክል በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የሚያረጋግጥ የጤናማነት ምልክት ነው” ይላል።
ይሁን እንጂ የሽግግሩን ጊዜ በተቻለ መጠን ለማቅለል ምን ማድረግ ይቻላል? በዚህ የሽግግር ወቅት የትዳር ጓደኛና የቤተሰብ አባሎች ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጉዳዮች ይመረምራል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች በሚያርጡበት ወቅት በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መጦርን ጨምሮ ሌሎች ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች አብረው ይመጣሉ