በማረጥ ምክንያት የሚመጡትን ችግሮች መቋቋም
ና ቹራል ሜኖፖዝ—ዘ ኮምፕሊት ጋይድ ቱ ኤ ውመንስ ሞስት ሚስአንደርስቱድ ፓሴጅ የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች ማረጥ “ከሴት ወደ ሴት የሚለያይና የበለጠ ነጻነት የሚያስገኝ የአዲስ ሕይወት ምዕራፍ መክፈቻ” መሆኑን ተናግረዋል። ስለ ራስሽና ስለ ሕይወትሽ፣ ማለትም ስለ ማንነትሽና ስለ ጠቃሚነትሽ ጥሩ አመለካከት ካለሽ ይህ የሽግግር ወቅት ይበልጥ ቀላል እንደሚሆንልሽ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ይህ የሽግግር ወቅት አንዷ ሴት ከሌላዋ ይበልጥ ከባድ እንደሚሆንባት መካድ አይቻልም። በጣም አስቸጋሪ ከሆነብሽ ማንነትሽ፣ አእምሮሽ፣ ሴትነትሽ፣ አስተዋይነትሽ ወይም ወሲባዊ ፍላጎትሽ ተቃውሷል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ ባዮሎጂያዊ ነው።
“በሚያርጡበት ጊዜ ከፍተኛ ችግር የደረሰባቸው ሴቶች እንኳን ችግራቸውን ተቋቁመው በማሳለፍ አዲስ የሕይወት ዓላማና ብርታት እንዳገኙ” ኒውስዊክ ሪፖርት አድርጓል። አንዲት የ42 ዓመት ሴት እንደተናገረችው “በየጊዜው የሚመጣብኝ የስሜት መለዋወጥ አክትሞ ተረጋግቼ የምኖርበትን ጊዜ በናፍቆት እጠብቃለሁ” ብላለች።
ሴቶች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም የሚችሉት መቼ ነው?
በዕድሜ ለገፉ ሴቶች የሚሰጠው ግምት ሴቶች ማረጥ የሚያስከትለውን ነገር በመቋቋም ረገድ ባላቸው ችሎታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከትላል። በዕድሜ የገፉ ሴቶች ላላቸው ብስለት፣ ጥበብና ተሞክሮ ከፍተኛ ግምት በሚሰጥባቸው አገሮች በማረጥ ምክንያት የሚመጡ አካላዊና ስሜታዊ ችግሮች በጣም ጥቂት ሆነው ተገኝተዋል።
ለምሳሌ ያህል “ማረጥ በደስታ የሚጠበቅ የዕድሜ ሽግግር ተደርጎ በሚወሰድባቸውና ያረጡ ሴቶች ባገኙት ተሞክሮና ጥበብ ምክንያት ከበሬታ በሚያገኙባቸው የአፍሪካ ጎሣዎች ከማረጥ ጋር የሚመጡ ችግሮች እምብዛም አያጋጥሙም” በማለት ዘ ውመንስ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ኸልዝ ኤንድ ናቹራል ሂሊንግ ሪፖርት አድርጓል። ዘ ሳይለንት ፓሴጅ—ሜኖፖዝ የተባለውም መጽሐፍ በተመሳሳይ “የራጅፑት መደብ አባላት የሆኑ ሕንዳውያን ሴቶች በሚያርጡበት ጊዜ የጭንቀት ስሜት ወይም ሌሎች የሥነ ልቡና ችግሮች አያጋጥሟቸውም” ይላል።
በተጨማሪም በዕድሜ ለበሰሉ ሴቶች ከፍተኛ አክብሮት በሚሰጥበት በጃፓን አገር ላረጡ ሴቶች የሆርሞን ሕክምና መስጠት ፈጽሞ አይታወቅም። ከዚህም በላይ የእስያ ሴቶች በማረጥ ምክንያት የሚደርሱባቸው ችግሮች በምዕራብ አገሮች ከሚኖሩ ሴቶች በጣም ያነሰ ነው። አመጋገባቸው አስተዋጽኦ ያደረገላቸው ይመስላል።
አንድ አንትሮፖሎጂስት ባደረጉት ጥናት የማያ ሴቶች የሚያርጡበትን ጊዜ በናፍቆት እንደሚጠባበቁ አረጋግጠዋል። ለእነዚህ ሴቶች ማረጣቸው በተከታታይ ከመውለድ ይገላግላቸዋል። በተጨማሪም በሕይወታቸው ሌሎች የሚመኟቸውን ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል ነጻነት እንደሚያመጣላቸው ጥርጥር የለውም።
ከማረጥ ጋር የሚመጡትን ስጋቶች እንደ ቀላል ነገር ቆጥረን ማለፍ አይገባንም። ወጣትነትንና የወጣትነትን ውበት በሚያደንቅ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ማረጣቸው ከሩቅ ያስፈራቸዋል። እንደነዚህ ያሉት ሴቶች ይህ የሽግግር ጊዜ የሚያስከትልባቸውን ችግር ለማቃለል ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
ሴቶች የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው?
ማረጥን የሚመለከት ትምህርት በማስፋፋት ረገድ ግንባር ቀደም የሆኑትና ደራሲዋ ጃኒን ኦሊሪ ኮብ “ብዙ ሴቶች የሚያስፈልጋቸው የሚሰማቸው ስሜት ጤናማ መሆኑንና እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማቸው እነርሱ ብቻ አለመሆናቸውን ማወቅ ነው” ይላሉ።
ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘትና ደስተኛ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። አንዲት በማረጥ ዕድሜ ላይ የምትገኝ የ51 ዓመት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ማረጥ ከሚያስከትለው ችግር መርቶ የሚያወጣሽ ስለ ሕይወት ያለሽ አጠቃላይ አመለካከት እንደሆነ ከልቤ አምናለሁ። . . . እርጅና የማይቀር ነገር መሆኑን አውቃለሁ። ወደድንም ጠላን፣ መድረሱ አይቀርም። . . . ይህ [ማረጥ] በሽታ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። የሕይወቴ ክፍል ነው።”
ስለዚህ ሕይወትሽ አዲስ ምዕራፍ የሚጀምርበት ይህ ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ ስለምታደርጊያቸው አዳዲስና አስደሳች ነገሮች በጥልቅ ማሰብ ጀምሪ። ማረጥ የሚያስከትለው አካላዊ ለውጥም መዘንጋት የለበትም። ዶክተሮችና ሌሎች ሊቃውንት ለዚህ የሽግግር ወቅት ለመዘጋጀት ገንቢ ምግቦች በመመገብ፣ በቂ ዕረፍት በመውሰድና መጠነኛ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ለጤንነት እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ።
አመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ
አንዲት ሴት በዕድሜ በምትገፋበት ጊዜ የሚቀንሰው የካሎሪ ፍጆታዋ እንጂ የተመጣጠነ ምግብ (የፕሮቲን፣ የካርቦሃይድሬት፣ የስብ፣ የቪታሚንና የማዕድናት) ፍጆታዋ አይደለም። ስለዚህ የተመጣጠኑ ምግቦች መመገብና “ባዶ ካሎሪ” ብቻ የሆኑትን ስኳርና ቅባት የሚበዛባቸው ምግቦች ማስወገድ አስፈላጊ ነው።
አዘውትሮ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ውጥረትና ጭንቀት የመቋቋም ችሎታን ያዳብራል፤ ጉልበት ከመጨመሩም በላይ ውፍረት ይቀንሳል። ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ሰውነት ምግብን ወደ ኃይል የመለወጥ አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ስለሚሄድ በአካላዊ እንቅስቃሴ ካልተነቃቃ እየወፈሩ መሄድ ይመጣል።
ሴቶች አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግና ተጨማሪ ካልስየም መውሰድ የአጥንትን መዳከምና መቦርቦር እንደሚቀንስ ማወቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ውመን ካሚንግ ኦቭ ኤጅ የተባለው መጽሐፍ “በተገቢ ሁኔታ የሚደረግ አይሮቢክ እንቅስቃሴ፣ በእግር መሄድ፣ መሮጥ፣ ብስክሌት መንዳትና ክብደት ማንሳት” በጣም ጠቃሚ እንደሆኑ ይታሰባል። ሰዎች በጣም በሚያረጁበት ጊዜ እንኳን የጉልበት ሥራ በሚሠሩባቸው ኋላ ቀር ማኅበረሰቦች የአጥንት መቦርቦር (osteoporosis) ፈጽሞ አይታወቅም። እንደነዚህ ባሉት አካባቢዎች የሴቶች ዕድሜ እስከ 80 እና 90 ይደርሳል። ሆኖም ማንኛውንም የአካል እንቅስቃሴ ፕሮግራም ከመጀመር በፊት ሐኪም ማማከር ጥሩ ነው።
የትኩሳትና የላብን መፈራረቅ መቋቋም
ለብዙ ሴቶች የትኩሳትና የላብ መፈራረቅ በጣም ከባድ ችግር አይሆንም። ለአንዳንዶች ግን ቶሎ ቶሎ የሚመላለስባቸው ወይም እንቅልፋቸውን የሚያፋልስባቸው ችግር በመሆኑ ይከብድባቸዋል። ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል?
በመጀመሪያ ደረጃ አትሸበሩ። በችግሩ ላይ ጭንቀትና ፍርሃት መጨመር ችግሩን ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። አዘውትሮ ጠንከር ያለ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ሰውነት ከፍተኛ ሙቀት የመቋቋምና በቀላሉ ራሱን የማቀዝቀዝ ችሎታ እንዲያዳብር ስለሚያስችል በጣም ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውኃ መጠጣት ወይም እጅን ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ መንከር ቀላል ነገር መስሎ ቢታይም በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
በተጨማሪም በቀላሉ ሊወልቁ ወይም ሊደረቡ የሚችሉ ሰፋ ያሉ ልብሶችን ደራርቦ የመልበስ ልማድ ይኑራችሁ። ከጥጥ ወይም ከሊኖ የተሠሩ ልብሶች ከሰው ሠራሽ ጨርቆች ከተዘጋጁ ልብሶች የበለጠ ላብ የማትነን ችሎታ አላቸው። ስትተኙ ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ ሊጨመሩና ሊቀነሱ የሚችሉ ስስ ብርድ ልብሶች ደራርባችሁ ልበሱ። ቅያሪ የሚሆን የማታ ልብስ በአጠገባችሁ አስቀምጡ።
ትኩሳትና ላብ የሚያመጣባችሁ ነገር ምን እንደሆነ ለይታችሁ ለማወቅ ሞክሩ። አልኮል፣ ካፊን፣ ስኳር፣ የሚፋጅና ቅመም የበዛበት ምግብ፣ እንዲሁም ትንባሆ ማጨስ ሊያባብስ ይችላል። ትኩሳትና ላብ የሚመጣባችሁ መቼና የት እንደሆነ በማስታወሻ እየመዘገባችሁ ብትከታተሉ ለችግሩ መንስዔ የሆኑትን ምግቦችና እንቅስቃሴዎች ለይታችሁ ለማወቅ ትችላላችሁ። ከዚያ በኋላ ጠንቀኛ የሆኑትን ምግቦችና እንቅስቃሴዎች አስወግዱ።
ሥርዓተ ምግብን በተመለከተ ልዩ ጥናት ያካሄዱ ሐኪሞች ትኩሳትና ላብ ይቀንሳሉ የሚሏቸው ምግቦችና መድኃኒቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል ቪታሚን ኢ፣ የኢቭኒንግ ፕሪምሮዝ ዘይት፣ እንዲሁም ጊንሰንግ፣ ዶንግ ኩዌይ፣ ብላክ ኮሆሽ የሚባሉት ዕፀዋት ይገኛሉ። አንዳንድ ዶክተሮች እንደሚሉት በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚወሰዱት ቤሌርጋልና ክሎኒዲን የተባሉት መድኃኒቶች ፋታ የሚያስገኙ ቢሆኑም ይበልጥ ውጤታማ የሆነው የኤስትሮጂን እንክብል መውሰድ ነው።
የአዝርዕት ወይም የፍራፍሬ ዘይት ወይም የቪታሚን ኢ ዘይትና ሌሎች የማለስለሻ ቅባቶችን በመጠቀም የብልት መድረቅ የሚያስከትለውን ችግር መቋቋም ይቻላል። እነዚህ ሁሉ በቂ ውጤት ካላስገኙ የኤስትሮጂን ቅባት የብልት ግድግዳዎችን ሊያደነድንና ሊያረጥብ ይችላል። የትኛውንም ዘዴ ከመጀመር በፊት ሐኪም ማማከር ጥበብ ይሆናል።
ውጥረትስ?
አንዲት ሴት ማረጥ ያስከተለባትን የሆርሞንና የአካል ለውጥ ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ እያለች በቀደመው ርዕስ ላይ የተዘረዘሩትን ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ ትገደዳለች። በአንጻሩ ግን የልጅ ልጅ እንደማግኘትና ልጆች ራሳቸውን ከቻሉ በኋላ ነጻ ሆኖ አዲስ ሥራ እንደመጀመር ያሉ ጥሩ ለውጦች እነዚህን ውጥረት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ለመቋቋም ያስችላሉ።
ሱዛን ፔሪ እና ዶክተር ካተሪን ኤ ኦሃንላን ናቹራል ሜኖፖዝ በተባለው መጽሐፋቸው ውጥረት የሚያመጡ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራዊ ዘዴዎችን ይጠቅሳሉ። የውጥረቱ ምንጭ ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅና በየጊዜው ከዚህ ሁኔታ እረፍት ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ። አንድን የቤተሰብ አባል ማስታመም ከሆነ በዚህ ረገድ የሚረዳ ሰው ማግኘት ሊሆን ይችላል። “ሩጫ አታብዢ” በማለት ይመክራሉ። “ጊዜሽን ከመጠን በላይ ላለማጣበብ ሞክሪ። . . . ሰውነትሽን አዳምጪ።” በማከልም “ሌሎችን ማገልገል . . . በጣም ትልቅ የውጥረት መቀነሻ ነው። . . . አዘውትረሽ የሰውነት እንቅስቃሴ አድርጊ . . . ያለብሽ ውጥረት ከቁጥጥርሽ ውጭ ከሆነብሽ የባለሞያ እርዳታ አግኚ” ይላሉ።
የቤተሰብ አባላት እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ
በማረጥ ላይ የምትገኝ ሴት ስሜትዋን የሚረዳላትና ተግባራዊ ድጋፍ የሚሰጣት ሰው ያስፈልጋታል። አንዲት ሚስት የሚያስጨንቃትና የሚያበሳጫት ሁኔታ ሲገጥማት ምን እንደምታደርግ ስትገልጽ “ጉዳዩን ለባለቤቴ እነግረውና በሐዘኔታ ካዳመጠኝ በኋላ ችግሬ የአእምሮዬ ጭንቀት የፈጠረውን ያህል ከባድ እንዳልሆነ እገነዘባለሁ” ብላለች።
በተጨማሪም የሚስቱን ስሜት የሚከታተል ባል ሚስቱ በምታርጥበት ጊዜ የዕለት ተለት ተግባሯን እንደ ቀድሞዋ ልታከናውን እንደማትችል ይገነዘባል። ስለዚህ በራሱ ተነሳስቶ ልብስ እንደ ማጠብ፣ ገበያ እንደመሄድና የመሳሰሉትን ሥራዎች በመሥራት ያግዛታል። በሐዘኔታ ከራሱ ፍላጎት ይልቅ የሚስቱን ያስቀድማል። (ፊልጵስዩስ 2:4) አልፎ አልፎ ውጭ ወጥተው እንዲበሉ ሊጋብዛት ወይም ከዕለታዊ ተግባሮችዋ ፋታ የሚያስገኝላት አንድ ነገር ለማድረግ ሊጋብዛት ይችላል። በተቻለው መጠን ጭቅጭቅ ከሚፈጥሩ ነገሮች ይሸሻል፣ እንዲሁም ጤናማ የሆነ አመጋገብ ለመከተል የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ አንድ ባል ሚስቱን የሚወዳት መሆኑን በተደጋጋሚ ሊያረጋግጥላት ይገባል። አስተዋይ በመሆን ይህ ጊዜ በሚስቱ ላይ የሚቀልድበት ጊዜ እንዳልሆነ ይገነዘባል። ሚስቱን በፍቅር የሚይዝ ባል “ለተሰባሪ ዕቃ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ሚስቶቻችሁን በክብር በመያዝ ከእነርሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይከተላል።—1 ጴጥሮስ 3:7 NW
ልጆችም በተመሳሳይ የእናታቸው ስሜት የሚለዋወጥበትን ምክንያት ለመረዳት ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ብቻዋን የምትሆንበት ጊዜ እንደሚያስፈልጋት ይገነዘባሉ። የእናታቸውን የስሜት መለዋወጥ እንደሚከታተሉ ማሳየታቸው ከልብ እንደሚያስቡላት እንድትገነዘብ ያስችላታል። በአንጻሩ ግን ስለ ጠባይዋ መለዋወጥና አስቸጋሪነት መቀለድ ቢጀምሩ ሁኔታዎች ይባባሳሉ። ምን እየደረሰባት እንዳለ ለመረዳት ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎች ጠይቁ። ሳትጠየቁ በራሳችሁ ተነሳስታችሁ በቤት ውስጥ ሥራዎች እርዱ። እናታችሁን በዚህ አስቸጋሪ በሆነው የዕድሜዋ ክፍል ልትረዱ ከምትችሉባቸው በርካታ መንገዶች ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው።
ከማረጥ በኋላ ያለው ሕይወት
ይህ የሽግግር ምዕራፍ ካበቃ በኋላ ብዙውን ጊዜ የበርካታ ዓመታት ሕይወት ከፊትዋ ይጠብቃታል። ያገኘችው ጥበብና ተሞክሮ በዋጋ ሊተመን አይችልም። የደራሲዋ የጌል ሺ ጥናት እንደሚያመለክተው “በሃምሳዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች፣ ራሳቸው እንደተናገሩት፣ ከየትኛውም የዕድሜያቸው ክፍል የበለጠ መረጋጋትና የደህንነት ስሜት እንዳገኙ ስልሳ ሺህ አሜሪካውያን አረጋግጠዋል።”
አዎን፣ እነዚህን የሽግግር ዓመታት ያሳለፉ በርካታ ሴቶች የመንፈስ መታደስ አግኝተዋል። የፈጠራ ችሎታቸው ተቀስቅሷል። ራሳቸውን ምርታማ በሆኑ እንቅስቃሴዎች በማስጠመድ በኑሯቸው ቀጥለዋል። አንዲት ያረጠች ሴት “አእምሮዬን ሥራ አላስፈታም። አዳዲስ ነገሮችን እፈልጋለሁ፣ ሁልጊዜም አጠናለሁ። ቅልጥፍናዬ ከቀድሞው እንደቀነሰ ይሰማኛል። ቢሆንም የሕይወቴ ፍጻሜ እንደ ደረሰ አይሰማኝም። ወደፊት ለበርካታ ዓመታት ለመኖር እጓጓለሁ” ብላለች።
ሺ ለበርካታ ሴቶች ቃለ መጠይቅ ባደረጉበት ጊዜ “በማረጥ ዕድሜ ላይ በመድረሳቸው ጥሩ ስሜትና ክብር የሚሰማቸው ሴቶች የአእምሮ ችሎታ፣ ጥሩ ማመዛዘን፣ የፈጠራ ችሎታ ወይም የመንፈስ ጥንካሬ የሚጠይቁ ሥራዎች የሚሠሩ” እንደሆኑ ተገንዝበዋል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን እውቀትና ማስተዋል ማሳደግንና ይህንንም ለሌሎች ማስተማርን እንደ ዋነኛ ተግባራቸው የቆጠሩ ደስተኛ የሴቶች ሠራዊት አሉ።—መዝሙር 68:11
በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች ስለ ሕይወት አዎንታዊ የሆነ አመለካከት ከመያዝና ትርጉም ያለው ሥራ ከመሥራት በተጨማሪ አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን ስሜታችንን እንደሚያውቅልንና ከልብ እንደሚያስብልን ማስታወሳቸው በጣም ይጠቅማቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:7) በእርግጥ ይሖዋ አምላክ እርሱን ያገለገሉ ሁሉ በሽታ፣ ሥቃይ ወይም ሞት በሌለበት አዲስ የጽድቅ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የሚኖሩበትን ዝግጅት አድርጓል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4
ስለዚህ በማረጥ ዕድሜ ላይ የምትገኙ ሁሉ ይህ ወቅት በሕይወታችሁ ውስጥ አንድ ደረጃ ላይ የደረሳችሁ መሆናችሁን እንደሚያመለክት ተገንዘቡ። ማለፉ አይቀርም። ካለፈ በኋላ ግን አፍቃሪ የሆነውን ፈጣሪያችንን ለማገልገል ብትጠቀሙበት ብዙ ዋጋ የምታገኙበት የበርካታ ዓመታት ዕድሜ ይጠብቃችኋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
ንቁ! ከዚህ ይልቅ ይኸኛው የሕክምና ዓይነት ይሻላል የሚል ምክር አይሰጥም።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤተሰብ አባላት ሊያበረክቱ የሚችሏቸው እርዳታዎች:- ፍቅር ማሳየት፣ በቤት ውስጥ ሥራ መርዳት፣ ጥሩ አዳማጭ መሆን፣ አልፎ አልፎ ለየት ያለ ነገር ማድረግ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የኤስትሮጂን መተኪያ ሕክምና ቢሰጥስ?
ኤስትሮጂን ላረጡ ሴቶች ዋነኛ የሕመም ምክንያት ከሆኑት የልብ በሽታና የአጥንት መቦርቦር ይከላከላል። የኤስትሮጂን መጠን እየቀነሰ በሄደ ከአምስት ወይም ከአሥር ዓመታት በኋላ እነዚህ በሽታዎች መታየት ይጀምራሉ። የኤስትሮጂን መተኪያ ወይም የሆርሞን (ኤስትሮጂንና ፕሮጀስትሮን) መተኪያ ሕክምና መውሰድ ከእነዚህ በሽታዎች እንደሚከላከል ይነገራል።
የኤስትሮጂን መተኪያ መውሰድ የአጥንት መቦርቦርን ፍጥነት ሊቀንስና የልብ በሽታን ሊያስወግድ ይችላል። ፕሮጀስትሮንን ጨምሮ መውሰድ ከጡትና ከማሕጸን ካንሰር ይከላከላል። ቢሆንም ኤስትሮጂን በልብ በሽታ ላይ የሚኖረውን ጠቃሚ ውጤት ያረክሳል።
የሆርሞን መተኪያ ሕክምና ለመውሰድ ወይም ላለመውሰድ ከመወሰን በፊት እያንዳንዷ ሴት ያላት ሁኔታ፣ ጤንነትና የቤተሰብ ታሪክ በጥንቃቄ መጤን ይኖርበታል።
መስከረም 22, 1991 (የእንግሊዝኛ) ንቁ! ገጽ 14-16 ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጥሩ አመጋገብ የትኛው ነው?
የሚከተለው ምክር በሱዛን ፔሪ እና በዶክተር ካተሪን ኤ ኦሃንላን ከተዘጋጀው ናቹራል ሜኖፖዝ—ዘ ኮምፕሊት ጋይድ ቱ ኤ ውመንስ ሞስት ሚስአንደርስቱድ ፓሴጅ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ ነው።
ፕሮቲን
• የምትመገቡት የፕሮቲን መጠን ከምትመገቡት ጠቅላላ ካሎሪ ከ15 በመቶ ያልበለጠ ይሁን።
• የምታገኙት ፕሮቲን በአብዛኛው ከአትክልቶችና ከአዝርዕት ይሁን። ከእንስሳት የሚገኙ ምግቦችን ቀንሱ።
ካርቦሃይድሬት
• እንዳልተፈተጉ እህሎች፣ ዳቦና ፓስታ፣ ባቄላ፣ ኦቾሎኒ፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የመሰሉትን ካርቦሃይድሬቶች ተመገቡ።
• ስኳርና ስኳር በብዛት ያለባቸውን ምግቦች በጣም ቀንሱ።
• ብዙ አሰር ያላቸውን ምግቦች ተመገቡ።
ስብ
• ጠቅላላ የስብ ፍጆታችሁ ከጠቅላላው የካሎሪ ፍጆታችሁ ከ25 እስከ 30 በመቶ የማይበልጥ ይሁን።
• የስብ ፍጆታችሁን በመቀነስ ላይ እንዳላችሁ ‘የጥሩዎቹን ስቦች’ (polyunsaturated) ድርሻ ለመጨመርና ‘የመጥፎዎቹን ስቦች’ (saturated) ለመቀነስ ሞክሩ።
ውኃ
• በየቀኑ ከስድስት እስከ ስምንት ብርጭቆ ውኃ ጠጡ።
ቪታሚኖችና ማዕድናት
• በየቀኑ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ተመገቡ።
• ወተት፣ የወተት ተዋጽኦዎች፣ ብሮኮሊና አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎች ጥሩ የካልስየም ምንጮች ናቸው።