ከሲጋራ ትርቃለህን?
ትንባሆን ለዓለም ያስተዋወቀ አገር የትንባሆን አደገኛነት በማስጠንቀቅ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፏል።
አንድ ታሪክ ጸሐፊ “ትንባሆ፣ አሜሪካ ከመገኘትዋ በፊት ይኸ ነው የሚባል ታሪክ አልነበረውም” ሲሉ ጽፈዋል። በካሪቢያን ደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች ለኮሎምበስ ሰጡት። በሰሜን አሜሪካ የመጀመሪያዋ የብሪታንያ ሠፈር ለሆነችው ለጀምስታውን ሕልውና ምክንያት የሆነው ትንባሆ ወደ ሌሎች አገሮች መላኩ ነው። የአሜሪካ አብዮት የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው ከትንባሆ ሽያጭ ነው። የቀድሞዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንቶች ጆርጅ ዋሽንግተንና ቶማስ ጀፈርሰን የትንባሆ ተክል አምራቾች ነበሩ።
በቅርብ ዓመታት ደግሞ ሆሊውድ ሲጋራን የፍቅር፣ የቁንጅናና የወንድነት ምልክት አድርጎ ተጠቅሟል። የአሜሪካ ወታደሮች በተዋጉባቸው አገሮች በሙሉ ላገኟቸው ሰዎች ትንባሆ ያድሉ ነበር። እንዲያውም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ሲጋራ “ከፓሪስ እስከ ፔኪንግ” ባሉት አገሮች እንደ መገበያያ ገንዘብ አገልግሏል ይባላል።
አሁን ግን ሁኔታው ተለውጧል። የዩናይትድ ስቴትስ ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ኃላፊ ጥር 11 ቀን 1964 ማጨስ ኤምፊዚማ ከተባለው በሽታ፣ ከሳንባ ካንሰርና ከሌሎች ከባድ በሽታዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የሚገልጽ ባለ 387 ገጽ ሪፖርት አውጥተው ነበር። ወዲያው በዩናይትድ ስቴትስ በሚሸጡ ሲጋራዎች ፓኬት ላይ “ማስጠንቀቂያ፣ ሲጋራ ማጨስ ለጤና አደገኛ ሊሆን ይችላል” የሚል ጽሑፍ እንዲወጣ የሚያስገድድ ፌዴራላዊ ሕግ ወጣ። በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየዓመቱ 434,000 የሚያክሉ ሰዎች በማጨስ ምክንያት እንደሚሞቱ ይገመታል። ይህ ቁጥር ባለፈው መቶ ዘመን በጦርነት ምክንያት ከሞቱት አሜሪካውያን ቁጥር ይበልጣል!
እገዳ ተደረገ
ከአሥር ዓመት በፊት በኮሎራዶ የምትገኘው አስፐን የተባለች የክረምት እረፍት ማሳለፊያ ከተማ በምግብ ቤቶች በሙሉ ሲጋራ እንዳይጨስ አገደች። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በምግብ ቤቶች፣ በሥራ ቦታዎችና በሌሎች የሕዝብ ማዘውተሪያ ቦታዎች ትንባሆ የማይጨስባቸውን ቦታዎች መወሰን የተለመደ ነገር ሆኗል። ከበርካታ ዓመታት በፊት አንድ የካሊፎርኒያ ሰው ሴት ልጁን በአንድ የቨርጅንያ ምግብ ቤት ውስጥ ትንባሆ የማይጨስበት ቦታ የት እንደሆነ ጠየቃት። ልጅቷም “አባዬ፣ ይህ የትንባሆ አገር ነው!” ስትል መለሰችለት። ይህ ሰው ዳግመኛ ወደዚያች ከተማ ሲሄድ የምግብ ቤቱ ግማሽ ትንባሆ ለማያጨሱ ሰዎች ብቻ ተመድቦ አገኘ። በቅርቡ ደግሞ አንድም የሚያጨስ ሰው እንዳላገኘ ተናግሯል።
ይሁን እንጂ ለአጫሾች የተለየ ስፍራ መመደብ መፍትሔ አልሆነም። በዋና ዋናዎቹ የካሊፎርኒያ ጎዳናዎች በንግድ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ “የሲጋራ ጭስ ማጨስ በሚፈቀድባቸው ቦታዎች ብቻ ተወስኖ የሚቀር ይመስላችኋልን?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል።
የኒው ዮርክ ክፍለ ሐገር በትላልቅ ምግብ ቤቶች ትንባሆ እንዳይጨስ የሚከለክል ሕግ ባወጣ ጊዜ የምግብ ቤቶቹ ባለቤቶች ሕጉ ትንባሆ ማጨስን የሚቆጣጠር ሕግ ከሌለባቸው የአውሮፓ አገሮች የሚመጡትን ቱሪስቶች ያርቃል ብለው ተቃውመው ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የተደረገ ጥናት ትንባሆ ወደ ማይጨስበት ምግብ ቤት ለመሄድ የሚመርጡ አሜሪካውያን ቁጥር 56 በመቶ ሲሆን ለመሄድ የማይመርጡ አሜሪካውያን ቁጥር 26 በመቶ ብቻ እንደሆነ አረጋግጧል።
በኒው ዮርክ ከተማ የምድር በታች ባቡሮች ላይ የተጻፈ ማስታወቂያ እንዲህ ይላል:- “በማንኛውም ቋንቋ መልእክቱ ያው አንድ ነው:- በጣቢያዎቻችንም ሆነ በባቡሮቻችን ላይ በማንኛውም ጊዜ፣ በማንኛውም ቦታ ማጨስ ክልክል ነው። እናመሰግናለን።” ማስታወቂያው የተጻፈው በእንግሊዝኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች 15 ቋንቋዎች ጭምር ነው።
ጉዳዩ ይህን ያህል አሳሳቢ ነውን? አዎን፣ አሳሳቢ ነው። 300 ሰዎች በአንድ ዓይነት አደጋ ቢሞቱ ለበርካታ ቀናት፣ እንዲያውም ለሳምንታት ዋነኛ ዜና ሆኖ ይሰነብታል። ይሁን እንጂ ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን ላይ የወጣ ጽሑፍ ሌሎች ሰዎች ያጨሱትን የሲጋራ ጭስ ለረጅም ጊዜ በመተንፈሳቸው ምክንያት በሚደርስባቸው ጉዳት በየዓመቱ 53,000 የሚያክሉ አሜሪካውያን እንደሚሞቱ ይገመታል ብሏል። በዚህ መሠረት “ሊወገዱ ከሚችሉ የሞት ምክንያቶች መካከል ሲጋራ በቀጥታ ከማጨስና ብዙ አልኮል ከመጠጣት ቀጥሎ በሦስተኛነት የሚጠቀሰው በሲጋራ የተበከለ አየር መተንፈስ ነው ማለት ነው።”
ሕፃናት፣ ሊከላከሉ የማይችሉ ተጠቂዎች
በመኖሪያ ቤት ውስጥ ሲጋራ ማጨስስ? ኸልዚ ፒፕል፣ 2000 የተባለ “አለ ዕድሜ መቀጨትን፣ ሊወገዱ የሚችሉ አላስፈላጊ የሆኑ በሽታዎችንና አካለ ስንኩልነትን” ለመቀነስ የሚቻልባቸውን ዘዴዎች የሚመክር የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታዊ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል:- “በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአማካይ ከስድስት ሰዎች መካከል አንዱ የሚሞተው በትንባሆ ምክንያት ሲሆን በኅብረተሰባችን ውስጥ ዋነኛው ሊወገድ የሚችል የሞትና የበሽታ መንስዔ ሲጋራ ነው።”
ጽሑፉ በማከል “ዝቅተኛ ክብደት ኖሯቸው ከሚወለዱ ሕፃናት መካከል ከ20 እስከ 30 በመቶ ለሚሆኑት፣ አለጊዜያቸው ከሚወለዱ ሕፃናት መካከል 14 በመቶ ለሚሆኑት፣ እንዲሁም በጨቅላነታቸው ከሚሞቱ ሕፃናት መካከል 10 በመቶ ለሚሆኑት ሕፃናት ምክንያቱ በእርግዝና ወቅት ማጨስ ነው” ብሏል። የሚያጨሱ እናቶች የትንባሆውን ጭስ ቅመሞች ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉት ጡት በማጥባት ወይም በአካባቢያቸው በማጨስ ብቻ ሳይሆን “ሕፃኑን በተጨሰበት ቤት ውስጥ በመተው ጭምር ነው” ይላል።
አባቶችም ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይኸው ጽሑፍ “ከልጆች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ማጨስ ከኖረባቸው ጭሱ ወደ ልጁ ክፍል ሊገባ በማይችልባቸው አካባቢዎች ወይም ከቤት ውጭ ማጨስ ይኖርባቸዋል” ብሏል። በትንባሆ አማካኝነት የሚደርሰው ጉዳት በአንድ ክፍል ውስጥ እንደሚያጨሱት ሰዎች ቁጥርና እንደሚጨሰው ሲጋራ ብዛት ይጨምራል። በመሆኑም የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ የጤና አጠባበቅ ኃላፊ የሆኑት ጀስሊን ኤልደርስ “ልጆቻችሁ የሱሳችሁ ንጹሐን ተጠቂዎች ናቸው” ብለዋል።
በሌሎች ሰዎችም ላይ ጉዳት ይደርሳል። አንድ መንግሥት የሚያስተላልፈው የካሊፎርኒያ ቴሌቪዥን ማስታወቂያ አንድ ሽማግሌ ሰው ብቻውን ተቀምጦ ያሳያል። ‘ሚስቴ ሁልጊዜ ሲጋራ እንድተው ትጨቀጭቀኝ ነበር’ ሲል ይናገራል። “እንዲያውም ማጨስ ካልተውክ ሁለተኛ አልስምህም ብላ አስፈራርታኝ ነበር። በራሴ ሳንባና በራሴ ሕይወት ምን አገባሽ አልኳት። ግን ተሳስቻለሁ። ማጨሴን አልተውኩም። ባለቤቴን እንደማጣ አልተገነዘብኩም ነበር። . . . ያጣሁት የሚስቴን ሕይወት ሆነ።” ሽማግሌው ፎቶዋን በሐዘኔታ እየተመለከተ “ሚስቴ ሕይወቴ ነበረች” ይላል።
የአመለካከት ለውጥ
እንደነዚህ ባሉት ማስጠንቀቂያዎች ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ የአጫሾች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። ሲጋራ ያጨሱ ከነበሩ መካከል 49.6 በመቶ የሆኑ 46 ሚልዮን የሚገመቱ አሜሪካውያን ማጨስ ማቆማቸው የሚያስደንቅ ነው!
ይሁን እንጂ የትንባሆ ኩባንያዎች ለማስታወቂያ ሥራ ከፍተኛ ባጀት ከመመደባቸውም በላይ እንዳይሸነፉ መራራ ትግል በማድረግ ላይ ናቸው። በዚህ ምክንያት የአጫሾች ቁጥር መቀነስ እያዘገመ መጥቷል። በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሱስና አለአግባብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ነገሮች ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ጆሴፍ ኤ ካሊፋኖ ጁንየር እንዲህ ብለዋል:- “የትንባሆ ኢንዱስትሪዎች በሕዝብ ጤና ላይ እያደረሱ ያሉት ትልቅ ጥቃት ሕፃናትና አፍላ ጎረምሶች፣ ማለትም አዲሱ ትውልድ የገዳይ ምርታቸው ሱሰኛ እንዲሆን የሚያስተላልፉት የማስታወቂያዎችና የመሸጫ ዘዴዎች ውርጅብኝ ነው።”
ዘ ጆርናል ኦቭ ዘ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን እንዲህ ብሏል:- “በየቀኑ 3000 ወጣቶችና አፍላ ጎረምሶች አዘውታሪ አጫሾች ይሆናሉ። በየዓመቱ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ አዳዲስ አጫሾች ይገኛሉ ማለት ነው። እነዚህም በየዓመቱ ማጨስ ለሚያቆሙት ወይም ለሚሞቱት 2 ሚልዮን የሚያክሉ አጫሾች ምትክ ይሆናሉ።”
ከዩናይትድ ስቴትስ አጫሾች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት ማጨስ የሚጀምሩት በ14 ዓመታቸው ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ኮሚሽነር የሆኑት ዴቪድ ከስለር በየቀኑ ማጨስ ከሚጀምሩት 3000 ልጆች መካከል 1000 የሚያክሉት ከማጨስ ጋር በተያያዙ በሽታዎች ምክንያት ይሞታሉ ብለዋል።
እነዚህ የአኃዝ መረጃዎች የሚያሳስቡህ ከሆነ ልጆቻችን የእኛን ምሳሌ እንደሚከተሉ አስታውስ። እንዳያጨሱ ከፈለግን እኛም ማጨስ አይኖርብንም።
የባሕር ማዶ ሽያጭ
የዩናይትድ ስቴትስ የሲጋራ ፍጆታ እየቀነሰ ቢሄድም የባሕር ማዶው ገበያ እያደገ መጥቷል። ሎስ አንጀለስ ታይምስ እንደዘገበው “ወደ ውጭ የሚላከው የትንባሆ መጠን በሦስት እጥፍ ያደገ ሲሆን ከዩናይትድ ስቴትስ ትንባሆ ፋብሪካዎች የሚወጡት ምርቶች ገበያ በውጭ አገሮች እያሻቀበ ሄዷል።” ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን በታዳጊ አገሮች “ማጨስ ለሚያስከትለው አደጋ ምንም ያህል ትኩረት ስለማይደረግ” የትንባሆ ኩባንያዎች “የባሕር ማዶውን ገበያ በቀላሉ ሊቆጣጠሩ ችለዋል።”
ይሁን እንጂ ካሜል እና ዊንስተን የተባሉትን ሲጋራዎች የሚያመርተው ኩባንያ መስራች የሆኑት የአር ጄ ሬይኖልድስ ጁንየር ልጅ ፓትሪክ ሬይኖልድስ በዩናይትድ ስቴትስ ከ5 ሰዎች መካከል አንዱ የሚሞተው በማጨስ እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም በየዓመቱ በኮኬይን፣ በአልኮል፣ በሄሮይን፣ በእሳት አደጋ፣ ራሳቸውን በመግደል፣ በነፍስ ግድያ፣ በኤድስና በመኪና አደጋ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር አንድ ላይ ቢደመር በየዓመቱ በማጨስ ምክንያት ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እንደሚያንስና በዘመናችን በቀላሉ ሊወገዱ ከሚችሉት የሞት፣ የበሽታና የሱስ ምክንያቶች ዋነኛው ነው ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል።
ዓለምን ማጨስ ያስለመደ አገር የትንባሆ ዋነኛ ተቃዋሚ ሆኖ መቆሙ እንግዳ ነገር ይመስላልን? እንግዲያው ‘የዚህን መፍትሔ ማግኘት የሚኖርበት ማን ነው?’ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ ጥሩ ነው።
ሞደርን ማቹሪቲ የተባለው መጽሔት ከ50 ዓመት በላይ ስላጨሰች ሴት ተናግሯል። “አንዴ በሱስ ከተያዝክ ተጠመድክ ማለት ነው” ብላለች። ይሁን እንጂ የምታጨስባቸውን ምክንያቶች ከመረመረች በኋላ ማጨስ እንድትጀምር ምክንያት የሆናትን አመለካከት ከአእምሮዋ አውጥታ ሲጋራ አቆመች።
“ሞክሩት፣ በጣም ትደሰቱበታላችሁ” ስትል ጽፋለች።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የካንሰር ማስጠንቀቂያዎች
የሚከተሉት ማስጠንቀቂያዎች ፋክትስ ኦን ላንግ ካንሰር እና ካንሰር ፋክትስ ኤንድ ፊገርስ—1995 ከተባለው የአሜሪካ ካንሰር ማኅበር ብሮሹር የተወሰዱ ናቸው:-
• “የማያጨሱ ሴቶች ባሎቻቸው አጫሾች ከሆኑ በሳንባ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው በ35 በመቶ ከፍ ይላል።”
• “በሳንባ ካንሰር ከሚያዙ ወንዶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ከሴቶች ደግሞ 79 በመቶ የሚሆኑት በሳንባ ካንሰር የሚያዙት ሲጋራ በማጨስ ምክንያት እንደሆነ ይገመታል።”
• “በቀን 2 ፓኮ ሲጋራ ከ40 ዓመት በላይ ያጨሰ ሰው በሳንባ ካንሰር የመሞት ዕድሉ ከማያጨስ ሰው 22 እጥፍ ይበልጣል።”
• “ከሁሉ የሚሻለው የሳንባ ካንሰር መከላከያ ማጨስ አለመጀመር አለበለዚያም በተቻለ ፍጥነት ማቆም ነው።”
• “ጉዳት የሌለው ሲጋራ የሚባል ነገር የለም።”
• “ትንባሆ በጉንጭ ይዞ ማላመጥ ወይም በሱረት መልክ መውሰድ በአፍ፣ በጉሮሮና በላንቃ ካንሰር የመያዝን ዕድል ከፍ ከማድረጉም በላይ በጣም ከባድ የሆነ ሱስ ያስይዛል።”
• “ለረዥም ጊዜ ትንባሆ በሱረት መልክ የወሰዱ ሰዎች በጉንጭና በድድ ካንሰር የመያዛቸው ዕድል እስከ 50 እጥፍ ከፍ ሊል ይችላል።”
• “ማጨስ የሚያቆሙ ሰዎች በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ቢሆኑ ማጨስ ከማያቆሙት የበለጠ ዕድሜ ይኖራቸዋል። 50 ዓመት ዕድሜ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ማጨስ ያቆሙ ሰዎች በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ የመሞት ዕድላቸው በማጨስ ከሚቀጥሉት በግማሽ ያንሳል።”
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ገበሬዎች ያጋጠማቸው ችግር
ሌላ ምርት ቢያመርቱ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸው መሬት የሌላቸው ገበሬዎች ለብዙ ዓመታት ኑሯቸውን ሲያሸንፉ የኖሩት ትንባሆ በመትከል ነበር። ይህም ብዙ ሰዎችን የሚያስጨንቅ ነገር ሆኗል። አንድ የትንባሆ ቱጃር በመሠረቱት ዱክ ዩኒቨርሲቲ የተባለ ትምህርት ቤት የሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር ፕሮፌሰር የሆኑት ስታንሊ ሐወርዋስ እንዲህ ብለዋል:- “ትንባሆ አምራቾች ያጋጠማቸው ትልቅ ችግር . . . ትንባሆ መትከል በጀመሩበት ጊዜ ምርታቸው ማንንም ሰው እንደሚገድል አለማወቃቸው ነው።”
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ባደጉ አገሮች ውስጥ በ1990ዎቹ ከ35 እስከ 69 ዓመት የዕድሜ ክልላቸው ከሞቱት መካከል 30 በመቶዎቹ የሞቱት በትንባሆ ምክንያት እንደሆነ ይገመታል፤ ይህም ባደጉ አገሮች ውስጥ ብዙ ሰዎች ያለዕድሜያቸው በመቀጨት የመጀመሪያውን ስፍራ እንዲይዙ ያደርገዋል።”—ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትንባሆ ጭስ ለአጫሾች በተመደበ ቦታ ብቻ ተወስኖ አይቀርም
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእርግዝና ወቅት ማጨስ በጨቅላነታቸው ከሚሞቱት ሕፃናት መካከል 10 በመቶ ለሚሆኑት ሞት ምክንያት ነው