የሞት ነጋዴዎች—እርስዎስ ደንበኛ ነዎት?
“ማንኛውም አጫሽ ሲጋራ ይገድልሃል የሚለውን ማስጠንቀቂያ ሰምቷል። እኔም ይህን አምናለሁ። ውሎ አድሮ እንደሚገድል አውቃለሁ። ጭስ ወደ ሆዱ የሚያስገባ ማንኛውም ጅል ሰው ችግር ሳያጋጥመው የሚቀር አይመስለኝም። በሕይወቴ አንዲት ሲጋራ እንኳን አጭሼ አላውቅም። ከሲጋራ ንግድ ግን ከፍተኛ ሀብት አግኝቻለሁ። . . . ይህችን አገር ልንገነባ የቻልንበት ብቸኛው መንገድ በዓለም ላሉ ጅሎች ትንባሆ በመሸጥ ነው”—ለበርካታ ዓመታት በኬንታኪ የትንባሆ አምራች የነበሩት ጀምስ ሻርፕ፣ በላሪ ሲ ዋይት በተዘጋጀው “መርቻንትስ ኦቭ ዴዝ—ዘ አሜሪካን ቶባኮ ኢንዳስትሪ ” በተባለው መጽሐፍ
ይህ ግልጽና ሐቀኛ አስተያየት ብዙ የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖርም ብዙ ያልመለሳቸው ጥያቄዎች አሉ። በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ ሰዎች ትንባሆ የሚያጨሱት ለምንድን ነው? ሕይወት እንደሚቀጭ የታወቀውን ይህን ልማድ የሙጥኝ ብለው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው? በመሠረቱ የትንባሆ መዛመት ከአደንዛዥ ዕፅ መዛመት የሚለይ አይደለም። በአቅርቦትና በፍላጎት መጠኖች ላይ የተመካ ነው። ትርፍ የሚያስገኝ ገበያ ካልኖረ አቅርቦቱ እየመነመነ ይሄዳል። ታዲያ ሰዎች የሚያጨሱት ለምንድን ነው?
ዋናው ምክንያት ሱስ ነው። ኒኮቲን በሰዎች አካል ውስጥ ቦታ ካገኘ በኋላ በየቀኑና በየጊዜው ይህን የኒኮቲን ጥም የማርካት ፍላጎት ይፈጠራል። በተጨማሪም ከሱሱ ጋር የሚጣመር ሌላ ልማድ ይኖራል። አንዳንድ የተለመዱ ሁኔታዎች ሲጋራ የማጨስን ፍላጎት ይቀሰቅሳሉ። ከእንቅልፍ መነሳት ወይም የጠዋት ቡና ወይም ከምሳ ቀጥሎ የሚጠጣ መጠጥ፣ በሥራ ቦታ የሚያጋጥም ተጽዕኖ ወይም ማኅበራዊ ጉዳይ ወይም መዝናናት ሊሆን ይችላል። “አጭስ” የሚል ስሜት የሚቀሰቅሱ ከግምት ውስጥ የማይገቡ ብዙ ልማዶች ሊኖሩ ይችላሉ።
ለምን አጨሱ?
ንቁ! ሰዎች ለማጨስ የሚፈልጉበትን ምክንያት ለመረዳት አጫሽ የነበሩ ብዙ ሰዎችን አነጋግሯል። ለምሳሌ ሬይ በ50ዎቹ ዓመታት ዕድሜ የሚገኝ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል ውስጥ የበታች መኮንን የነበረ ሰው ነው። እንዲህ ይላል:- “ማጨስ የጀመርኩት ገና በ9 ዓመት ዕድሜ ቢሆንም ደንበኛ አጫሽ የሆንኩት በ12 ዓመቴ ነበር። አጫሽ በመሆኔ ምክንያት ከቦይ ስካውት እንደተባረርኩ አስታውሳለሁ።”
ንቁ!:- “የማጨስ ፍላጎት እንዲያድርብህ ያደረገው ምክንያት ምን ነበር?”
ሬይ:- “ማጨስ እንደ ጀግንነት ይቆጠር ስለነበረ ነው። ማጨስ እንደ ወንድነት ይቆጠር ነበር። በዚያ ዘመን ይወጡ የነበሩት ማስታወቂያዎች የእሳት አደጋ ተከላካዮችና ፖሊሶች ሲጋራ ሲያጨሱ ያሳዩ ነበር። በኋላም በባሕር ኃይል ውስጥ ሳለሁ በባሕር ላይ ጉዞ ከፍተኛ ውጥረት የሚያስከትል ሥራ እሠራ ስለነበረ ማጨስ ውጥረቱን የሚቀንስልኝ ይመስለኝ ነበር።”
“በቀን አንድ ፓኮ ተኩል ሲጋራ [30 ሲጋራ] አጨስ ነበር። ሲጋራ ሳላጨስ የዕለት ተግባሬን ለመጀመር አልችልም ነበር። ጭሱን ወደ ሳንባዬ አስገባ ነበር። ጭሱን ወደ ውስጥ ካላስገባህ ማጨስ ምንም ትርጉም የለውም።”
ቢል የተባለ የኒው ዮርክ አርቲስት ደግሞ በ50ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ ይነግረናል:-
“የጀመርኩት ገና የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። እንደ ትልልቅ ሰዎች ለመሆን ፍላጎት ነበረኝ። በሱሱ መዳፍ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ግን ማቆም አልቻልኩም። ሲጋራ መያዝ ጓደኛ እንደ መያዝ ነበረ። እንዲያውም ልተኛ ስል በቤት ውስጥ ሲጋራ እንደሌለኝ ካስታወስኩ ምንም ዓይነት የአየር ሁኔታ ቢኖር ልብሴን እንደገና ለብሼ እወጣና ለሚቀጥለው ቀን የሚያስፈልገኝን ሲጋራ እገዛ ነበር። በየቀኑ ከአንድ እስከ ሁለት ፓኮ አጨስ ነበር። ሱስ ይዞኝ እንደነበረ አልክድም። በተጨማሪም ኃይለኛ ጠጪ ነበርኩ። በተለይ ብዙ ጊዜ በማሳልፍባቸው መጠጥ ቤቶች ሁለቱ ልማዶች የማይነጣጠሉ ይመስላል።”
ወጣትና ከሰዎች ጋር ተግባቢ የሆነችው አሚ ማጨስ የጀመረችው በ12 ዓመት ዕድሜዋ ነበር። “ማጨስ የጀመርኩት በጓደኞቼ ግፊት ነበር። ከዚያም 15 ዓመት ሲሆነኝ አባቴ ስለሞተ በዚህ ምክንያት ያጋጠመኝ ውጥረት በልማዱ ይበልጥ እንድገፋ አደረገኝ። ይሁን እንጂ በዕድሜ እየገፋሁ ስሄድ ይበልጥ ተጽዕኖ ያደርጉብኝ የነበሩት የሲጋራ ማስታወቂያዎች፣ በተለይም ‘ቆንጂት፣ ከብዙ ጉዞ በኋላ እዚህ ደርሰሻል’ የሚለው ማስታወቂያ ነበር። የቀዶ ሕክምና ነርስ ባለሞያ ለመሆን አጠና ነበር። ብዙ ሳይቆይ በቀን ሦስት ፓኮ እስከ ማጨስ ደረስኩ። ማጨስ በጣም ደስ የሚለኝ ከምግብ በኋላና ስልክ በማነጋግርበት ጊዜ ነበር። ስልክ በማነጋገር የማሳልፈው ጊዜ ደግሞ በጣም ብዙ ነበር።” መጥፎ ውጤት እንዳስከተለባት ተገንዝባ ነበርን? “በየጠዋቱ ያስለኝና ራሴን ያመኝ ነበር። ፈጽሞ አቅመ ቢስ ሆንኩ። ወደምኖርበት አፓርታማ የሚያደርሱኝን ደረጃዎች መውጣት እንኳ በጣም ያደክመኝና ትንፋሼን ያሳጣኝ ነበር። ዕድሜዬ ግን ገና 19 ዓመት ነበር!”
የቀድሞ የባሕር ኃይል አብራሪና በአሁኑ ጊዜ በ60ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ሃርሊ ማጨስ የጀመረው ታላቁ የኢኮኖሚ ውድቀት ደርሶ በነበረበት ዘመን ገና በአምስት ዓመት ዕድሜው ነበር! ማጨስ የጀመረው ለምን ነበር? “በተወለድኩበት በደቡብ ዳኮታ፣ በአበርዲን ከተማ ይኖሩ የነበሩ ልጆች በሙሉ ያጨሱ ነበር። የሚያጨስ ሁሉ ጎበዝ እንደሆነ ይቆጠር ነበር።”
ሀርሊ ማጨስ የፈለገበትን ምክንያት አልሸሸገም። “ለእኔ ማጨስ ምንም ጉዳት የሌለው ጨዋታ ነበር። ጭሱን በረዥሙ ወደ ውስጥ ስቤ ወደ ሳንባዬ ካስገባሁት በኋላ እዚያው ይዤ አቆየዋለሁ። ከዚያም የቀለበት ቅርጽ ያለው ጭስ ማውጣት በጣም ያስደስተኝ ነበር። አለ ሲጋራ ልኖር ወደማልችልበት ደረጃ ደረስኩ። እያንዳንዱን ቀን የምጀምረውና የምጨርሰው በሲጋራ ሆነ። በባሕር ኃይል ውስጥ ሳለሁ በቀን ከሁለት እስከ ሦስት ፓኮ ሲጋራና በወር አንድ ሣጥን ሲጋር አጨስ ነበር።”
ቢል፣ ሬይ፣ አሚ እና ሃርሊ ማጨስ አቁመዋል። ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ማጨስ አቁመዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከ43 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ማጨስ ትተዋል። ይሁን እንጂ የትንባሆ ነጋዴዎች ተስፋ ቆርጠው ሥራቸውን አላቆሙም። ሁልጊዜ አዳዲስ ገበያ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
እርስዎስ ከዒላማዎቻቸው አንዱ ነዎትን?
በኢንዱስትሪ በገፉት አገሮች የሚኖሩ ብዙ ወንድ አጫሾች ማጨስ በማቆማቸውና ብዙ ደንበኞቻቸው በተፈጥሮ ምክንያቶችም ሆነ ትንባሆ በማጨስ ምክንያት በመሞታቸው የትንባሆ ኩባንያዎች አዳዲስ ገበያዎች ለመፈለግ ተገደዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች የሽያጫቸውን መጠን ከፍ ለማድረግ ሲሉ የማስታወቂያ ዘዴዎቻቸውን ቀይረዋል። እንደ ቴኒስና ጎልፍ የመሳሰሉ የስፖርት ውድድሮችን ማዘጋጀት ማጨስ ጥሩ መልክ ያለው መስሎ እንዲታይ ከሚያደርጉት ጥረቶች አንዱ ነው። ሌላው ያደረጉት ለውጥ ደግሞ ዒላማ የሚያደርጓቸውን ገበያዎች ይመለከታል። እርስዎስ ለደንበኝነት ከሚታሰቡት ሰዎች መካከል ይሆኑ ይሆን?
የትንባሆ ኩባንያዎች አንደኛ ዒላማ የሚያደርጉት ሴቶችን ነው። ባለፉት አሥርተ ዓመታት ገና የ18 ዓመት ወጣት ከነበረችበት ከ1917 ጀምሮ ታጨስ የነበረችውን ግሎሪያ ስዋንሰንን የመሰሉትን የፊልም ተዋንያን እየተመለከቱ ጥቂት ሴቶች ትንባሆ ማጨስ ጀምረው ነበር። እንዲያውም ይህች የፊልም ተዋናይ ለሠራቻቸው የመጀመሪያ ፊልሞች የተመረጠችበትን ምክንያት የፊልሙ ዳይሬክተር ሲገልጹ “ፀጉርሽ፣ ፊትሽ፣ አቀማመጥሽ፣ ሲጋራ አያያዝሽና አጫጫስሽ . . . ልክ የምፈልጋት ዓይነት ሴት ነሽ” ብለዋል።
በ1940ዎቹ ዓመታት ከባድ አጫሽ ከሆነው ባልዋ ከሀምፍሪ ቦጋርት ጋር ኮከብ ተዋናይ ሆና ትሠራ የነበረችው ሎረን ባካል ለትንባሆ አጫሽነት ጥሩ ምሳሌ ሆና ትታይ ነበር። ይሁን እንጂ ሴቶች በሲጋራ ገበያ የነበራቸው ድርሻ ከወንዶቹ በጣም ያነሰ ነበር። በዚህም ምክንያት በካንሰር የሚሞቱት ሴቶች ቁጥር ያነሰ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በማጨሱም ሆነ የሳንባ ካንሰር ሰለባዎች በመሆን ረገድ በወንዶቹ ላይ ለመድረስ በመገስገስ ላይ ይገኛሉ።
በቅርብ ዓመታት ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው የፉክክር ድርሻ እየጨመረ በመምጣቱና ስለ ትንባሆ የሚነገሩ ማስታወቂያዎችም ስውር የሆነ ተጽዕኖ እያሳደሩ በመምጣታቸው አዲስ ዓይነት የማስታወቂያ አዝማሚያ እየተፈጠረ መጥቷል። ለሴቶች እንዲደርስ የሚፈለገው መልእክት ምንድን ነው? በተለያዩ የንግድ ስሞች የሚጠሩ ሲጋራዎችን የሚያመርተው የፊሊፕ ሞሪስ ኩባንያ በተለይ ለዘመናዊ ሴቶች የተዘጋጀ “ቨርጂንያ ስሊምስ” የተባለ ሲጋራ ያመርታል። አሚን የሳባት ማስታወቂያ “ቆንጂት፣ ከብዙ ጉዞ በኋላ እዚህ ደርሰሻል” የሚለው የዚህ ኩባንያ መፈክር ነው። በማስታወቂያው ላይ በጣቶችዋ መካከል ሲጋራ የያዘች ዘመናዊ ሴት ሥዕል ይታያል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሴቶች የት ነው የደረስነው ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በጡት ካንሰር ከሚሞቱት ሴቶች ቁጥር በሳንባ ካንሰር የሚሞቱት ሴቶች ቁጥር በልጧል።
ሌላው የሲጋራ ዓይነት ደግሞ “አንድ ፓኮ ለሚገዙ 5 ሲጋራ በነፃ!” “አንድ ካርቶን ለሚገዙ 50 ሲጋራ በነፃ!” የሚሰጥ መሆኑን ለሴቶች አስታውቋል። እንዲያውም አንዳንድ የሴቶች መጽሔቶች ነጻ ሲጋራ የሚያሰጥ ኩፖን ከመጽሔታቸው ጋር መስጠት ጀምረዋል!
ሲጋራ ማራኪ ሆኖ እንዲታይ ከሚገለገሉባቸው ዘዴዎች አንዱ የጾታ ስሜት ነው። አንድ የሲጋራ ዓይነት “የበለጠ ደስታ አግኝ” የሚል ግብዣ አቅርቧል። ከዚህ ግብዣ ጋር የሚከተለው ማስታወቂያ ወጥቷል:- “ይፈለጋል— ረዥም ጥቁርና እንግዳ የሆነ ሰው፣ ዘላቂነት ላለው ግንኙነት። ጥሩ ቁመናና ጥሩ ጣዕም ያለው መሆን ይኖርበታል። ፊርማ፣ የማጨስ እርካታ ለማግኘት በናፍቆት በመጠባበቅ።” ማስታወቂያ የተነገረለት ሲጋራ “ረዥም” ሆኖ በጥቁር ወረቀት ተጠቅልሎ ቀርቧል። ወሲባዊ ስሜትን ከሲጋራ ጋር ለማዛመድ የተደረገ መሰሪ ዘዴ አይደለምን?
ሴቶችን ለማጥማድ ከሚሠራባቸው ዘዴዎች አንዱ ሲጋራን ከፋሽን ጋር ለማገናኘት መሞከር ነው። አንድ የሲጋራ ዓይነት “በኢቭ ሳን ሎረን [የፋሽን ዲዛይነር ነው] የተደነቀ ስታይልና ጥሩ ጣዕም” በመባል በአድናቆት ተገልጿል። ስለ ውፍረታቸው ለሚጨነቁ ሴቶች ደግሞ ሌላ ማጥመጃ ቀርቧል። በማስታወቂያው ላይ በጣም ቀጭን የሆነች ሴት ፎቶግራፍ የወጣ ሲሆን ሲጋራው ደግሞ “በጣም ቀጭን ለሆኑ— በጣም ቀጭን ስታይል” ተብሏል።
የሲጋራ አምራቾች የዓለምን ሴቶች ዒላማቸው ያደረጉት ለምንድን ነው? የዓለም ጤና ድርጅት “በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የወንድ አጫሾች ቁጥር 50 በመቶ ሲሆን የሴት አጫሾች ብዛት ግን አምስት በመቶ ብቻ መሆኑንና በአንጻሩ ግን በበለጸጉ አገሮች የወንዶችም ሆነ የሴት አጫሾች ቁጥር 30 በመቶ” እንደሆነ በመግለጽ ምክንያታቸውን እንድናውቅ የሚያስችለን ፍንጭ ይሰጠናል። በጤንነት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ቢያደርስ ገና ያልተበላ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ የትንባሆ ገበያ አለ ብለው ያምናሉ። ትንባሆ ሻጮቹ በዚህ ረገድ የተሳካ ውጤት በማግኘት ላይ ናቸው። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ጥበቃ ኃላፊ ባወጡት የ1989 ሪፖርት ‘በአነስተኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች፣ በተለይም በአነስተኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴት ልጆች ማጨስ እንደ ጀመሩና’ ይህም የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን እንደሚጨምር ገልጸዋል። በተጨማሪም በቅርብ ዓመታት በአሥራዎቹ ዓመታት የሚገኙ ሴት አጫሾች ቁጥር 40 በመቶ እንደጨመረ በሌላ ምንጭ ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ የሞትና የበሽታ ነጋዴዎች ዒላማቸው ያደረጉት ሴቶችን ብቻ አይደለም።
ልዩ ዒላማ የተደረጉ ዘሮች
ላሪ ሲ ዋይት መርቻንትስ ኦቭ ዴዝ—ዘ አሜሪካን ቶባኮ ኢንዳስትሪ በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለዋል:- “ጥቁሮች ለሲጋራ አምራቾች ጥሩ ደንበኞች ሆነዋል። የብሔራዊ ጤና ስታትስቲክስ ማዕከል እስከ 1986 ድረስ በዩናይትድ ስቴትስ ከአጫሽ ነጮች የአጫሽ ጥቁሮች ብዛት በእጅጉ እንደሚበልጥ አመልክቷል። . . . የጥቁር አጫሾች ቁጥር ከነጮች መብለጡ የሚያስደንቅ አይደለም። ምክንያቱም ጥቁሮች ለሲጋራ ማስታወቂያዎች ልዩ ዒላማ ሆነዋል።” ይሁን እንጂ ልዩ ዒላማ የሆኑት ለምንድን ነው? ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደሚለው “ይህን ልማድ አሽቀንጥሮ በመጣል ረገድ ከመላው ሕዝብ መካከል ወደኋላ የሚያዘግሙት ጥቁሮች ናቸው።” ስለዚህ አንድ ጥቁር ደንበኛ ‘ሞት እስኪለየው ድረስ’ የሚቆይ “ታማኝ” ደንበኛ ነው።
የትንባሆ ኩባንያዎች ጥረታቸው በጥቁሮች ላይ እንዲያተኩር የሚያደርጉት እንዴት ነው? ደራሲ ዋይት “እንደ ኤቦኒ፣ ጀት እና ኢሰንስ ባሉት የጥቁሮች መጽሔቶች ላይ በርካታ የሲጋራ ማስታወቂያዎች ይወጣሉ። በ1985 የሲጋራ ኩባንያዎች በኤቦኒ መጽሔት ላይ ብቻ ላወጡት ማስታወቂያ 3.3 ሚልዮን ዶላር ወጪ አድርገዋል።” በተጨማሪም አንድ የትንባሆ ኩባንያ በየዓመቱ ለጥቁር ሴት ሸማቾች የሚቀርብ የፋሽን ትርዒት ያቀርባል። በዚህ ጊዜ ሲጋራ በነጻ ይሰጣል። ሌላ ኩባንያ ደግሞ በአንድ ወቅት በጥቁሮች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ የጃዝ ሙዚቃ ድግስ ሲያቀርብ ከመቆየቱም በላይ በአሁኑ ጊዜ በጥቁሮች ዘንድ ተወዳጅ ለሆኑ የሙዚቃ ዝግጅቶች ድጋፍ ይሰጣል። ጥቁሩ ሕዝብ ምን ያህል በልዩ ግምት የሚታይ የኅብረተሰብ ክፍል ነው? የፊሊፕ ሞሪስ ቃል አቀባይ “የጥቁሮቹ ገበያ በጣም አስፈላጊያችን ነው። በጣም የደራ ገበያ ነው” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ትላልቆቹ የትንባሆ ኩባንያዎች ከተለዩ ዘሮችና ቡድኖች የበለጠ ግምት የሚሰጧቸው ገበያዎች አሉ። እነርሱም አንዳንድ ብሔራት ናቸው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ሲጋራ መያዝ ጓደኛ እንደ መያዝ ነው”
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማጨስ እና የበርገርስ በሽታ
በቅርቡ በካናዳ አገር በማክሊንስ መጽሔት ሪፖርት የተደረገ አንድ ሁኔታ በማጨስ ምክንያት የሚመጣ ሌላ በሽታ መኖሩን ይጠቁማል። ሮዤ ፔሮ ማጨስ የጀመረው በ13 ዓመት ዕድሜው ነበር። በ27 ዓመቱ የበርገርስ በሽታ ስለያዘው አንደኛውን እግሩን ከጉልበቱ በታች ለማስቆረጥ ተገደደ። ማጨሱን ካላቆመ በሽታው ወደፊትም መከሰቱ እንደማይቀር ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር። ማክሊንስ እንዲህ በማለት ይዘግባል:- “ፔሮ ግን ማስጠንቀቂያውን አልሰማም። በ1983 ዶክተሮች ሁለተኛ እግሩን ለመቁረጥ ተገደዱ። ከዚያ በኋላ . . . ፔሮ ማጨሱን አቆመ።” በአሁኑ ጊዜ አንዱን የትንባሆ ኩባንያ ካሣ እንዲሰጠው በመክሰስ ላይ ነው።
የበርገር በሽታ ምንድን ነው? “አብዛኛውን ጊዜ በሚያጨሱ ወንዶች ላይ የሚደርስ በሽታ ነው። የደም ቅዳና የደም መልስ ደም ቧንቧዎችን እንዲሁም ነርቮችን የሚያስቆጣና በዚህም ምክንያት የደም ሥር ግድግዳዎች በነጭ ሴሎች ተወርረው እንዲያብጡ የሚያደርግ በሽታ ነው። የበሽታው የመጀመሪያ ምልክት በእጅ ወይም በእግር ጣት ላይ የሚታይ ሰማያዊ ቀለም ያለው ምልክት ሲሆን በተጨማሪም በበሽታው የተጠቃው የእጅ ወይም የእግር ክፍል ይደነዝዛል ወይም የቅዝቃዜ ስሜት ይሰማዋል። ከዚህም በላይ ነርቮቹ ስለሚቆጡ ነርቮቹ የሚቆጣጠሯቸው ትናንሽ የደም ቧንቧዎች በመጨማደዳቸው ምክንያት ከባድ የሕመም ስሜት ሊሰማ ይችላል። በተጨማሪም ሲምፓተቲክ ነርቮች ከመጠን በላይ ስለሚሠሩ እግሮች ቅዝቃዜ ቢሰማቸውም እንኳን በጣም ብዙ ላብ እንዲያልባቸው ሊያደርግ ይችላል። . . . የበርገር በሽታ ሥር እየሰደደ ሲሄድ በአብዛኛው በደም ዝውውር መታገድ ምክንያት የሚደርስ ቁስልና ጋንግሪን የተባለ የሕዋሳት መሞት ያስከትላል።”
“የበርገርስ በሽታ የሚመጣበት ምክንያት በውል የማይታወቅ ቢሆንም በሽታው የሚይዛቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ትንባሆ የሚያጨሱ ወጣት ወንዶች በመሆናቸው ሲጋራ በሚያስከትለው ጠንቅ ምክንያት የሚመጣ በሽታ እንደሆነ ይታሰባል። ከሁሉ የተሻለው ሕክምና ማጨስ ማቆም ነው።” (በአይታሊክ የጻፍነው እኛ ነን።)—ዘ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኦቭ ፊዚሽያንስ ኤንድ ሰርጅንስ ኮምፕሊት ሆም መዲካል ጋይድ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማጨስ እና ልብ ድካም
“ብዙ ሰዎች ሲጋራ በማጨስ፣ በሳንባ ካንሰርና በሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች መካከል ያለውን ቀጥተኛ ተዛምዶ የሚያውቁ ቢሆንም ማጨስ ልዩ ልዩ የልብ ሕመም በማስከተል የሚያደርሰውን አደጋ ገና የማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ። እንዲያውም የጤና ጥበቃ ኃላፊው ስለ ማጨስና ጤንነት ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በየዓመቱ በልብና በደም ዝውውር በሽታ ከሚሞቱ አሜሪካውያን [ሰሜን አሜሪካውያን] መካከል 225,000 የሚያክሉት ከማጨስ ጋር ግንኙነት ባላቸው ምክንያቶች የሚሞቱ ናቸው። ይህም በማጨስ ምክንያት የሚመጡ ናቸው በሚባሉት የካንሰርና የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ከሚሞቱት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር በጣም ይበልጣል።”
“አጫሾች የታርና የኒኮቲን መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሲጋራዎች በልብና በደም ዝውውር በሽታ ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ይቀንሱ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ያቀርባሉ። መልሱ አይቀንሱም የሚል ይመስላል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ባለ ፊልተር ሲጋራዎች ወደ ሰውነት የሚገባው ካርቦን ሞኖኦክሳይድ መጠን እንዲጨምር ስለሚያደርጉ በልብ ላይ ፊልተር ከሌላቸው ሲጋራዎች የበለጠ ጉዳት ያስከትላሉ።”(በአይታሊክ የጻፍነው እኛ ነን።)—ዘ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኦቭ ፊዚሽያንስ ኤንድ ሰርጅንስ ኮምፕሊት ሆም መዲካል ጋይድ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የትንባሆ ማስታወቂያዎች ሴቶችን ዒላማቸው በማድረግ የተሳካ ውጤት በማግኘት ላይ ናቸው