አመለካከትህን የሚቀርጸው ምንድን ነው?
ከ2,700 ዓመታት ገደማ በፊት አንድ ጸሐፊ በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ የሚከተለውን ስሜት ቀስቃሽ ምሳሌ ጽፎ ነበር:- “ክፉ ነገር ማድረግ [“የብልግና ድርጊት፣” NW] ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው።” (ምሳሌ 10:23) በተለይ የፆታ አብዮት ከፈነዳበት ጊዜ አንስቶ ይህ አባባል እውነት መሆኑ ተረጋግጧል። ኤድስ የማስጠንቀቂያ ደወል ከማሰማቱ በፊት በእጅጉ ተስፋፍቶ የነበረው አመለካከት የፆታ ግንኙነት ‘ለመዝናናት ሲባል የሚፈጸም ድርጊት’ ሲሆን የፆታ ፍላጎት ‘ምንም ያስከትል ምን’ መሟላት አለበት የሚል ነበር። ይህ አመለካከት ተለውጦ ይሆን? አልተለወጠም።
በዛሬው ጊዜም ሰዎች በፆታ ስሜት መቃጠላቸው፣ ሥነ ምግባር የግል ጉዳይ ነው እንዲሁም ከብዙ ሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት ማድረግ ምንም ስህተት የለበትም ብለው ሽንጣቸውን ገትረው በመከራከር “የፆታ ፍቅር ሱሰኞች፣” ‘በአንድ የማይረጉ’ እና “ሴሰኞች” እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። (ገጽ 6 ላይ ያለውን “ፆታዊ የአኗኗር ዘይቤዎች” የሚለውን ሳጥን ተመልከት።) የፆታ ግንኙነቱ የሚፈጸመው ለአካለ መጠን በደረሱ ሰዎች መካከል እስከሆነ ድረስ ማንም ሰው ከፈለገው ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም ‘ምንም የሚደርስበት ጉዳት የለም’ ይላሉ። በ1964 በአየዋ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አይረ ራይስ እንዲህ ዓይነቱን ምግባር “ልቅ ፆታዊ ፍቅር” ሲሉ ገልጸውታል።
በስኮትላንድ፣ ኢድንበርግ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ይህንኑ ስሜት በማንጸባረቅ ሰዎች የተፈጠሩት ብዙ ፍቅረኞች እንዲያፈሩ ተደርገው ነው ሲሉ ተናግረዋል። ፆታንና ክርስትናን አስመልክተው በሰጡት ንግግር ላይ እንዲህ ብለዋል:- “አምላክ የፆታ ፍላጎታችንን ለማርካት የሚገፋፋ የፆታ ስሜት በውስጣችን ተክሎ እንደፈጠረን ያውቃል። የዘማዊነት በራሂዎች (genes) በውስጣችን አስቀምጧል። ቤተ ክርስቲያኒቷ ተፈጥሯዊ ዝንባሌያቸውን የተከተሉ ሰዎችን ማውገዟ ትክክል መስሎ አይታየኝም።”
እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ጤናማ ነውን? ልቅ የፆታ ግንኙነት ያስከተለው ኪሣራ ምንድን ነው? የፆታ ጓደኞችን በየጊዜው መለዋወጡ እርካታና ደስታ አስገኝቷልን?
በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ወረርሽኝ መዛመታቸውና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በተለይም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከጋብቻ ውጪ መጸነሳቸው እንዲህ ዓይነቱ ፍልስፍና ከንቱ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ኒውስዊክ መጽሔት እንደዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በየዓመቱ ሦስት ሚልዮን የሚደርሱ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ያጠቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከእነዚህ “ለአካለ መጠን የደረሱ” ወጣቶች መካከል ብዙዎቹ ለተጸነሰው ሕፃን “ፍቅር የሌላቸው” ወይም ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው በመሆናቸው ብዙውን ጊዜ ውርጃ ለመፈጸም ይጣደፋሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:3) ይህም ሕፃኑ ከእናቱ ማኅፀን ውስጥ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲወጣ በማድረግ ሕይወቱን እንዲያጣ ያደርገዋል። ወጣቷ እናትም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሊያድርባትና በተቀረው የሕይወት ዘመኗ ሁሉ ሲቆረቁራት የሚኖር የጥፋተኝነት ስሜት ሊያድርባት ይችላል።
በዶክተር ፓትሪክ ዲክሰን ስሌት መሠረት በ1990ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ በብሪታንያ ብቻ የፆታ አብዮት ያመጣው ውጤት ያስከተለው ክስረት በየዓመቱ 20 ቢልዮን የአሜሪካን ዶላር ደርሷል። ዶክተር ዲክሰን ዘ ራይዚንግ ፕራይዝ ኦቭ ላቭ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እዚህ አኃዝ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ኤድስን ጨምሮ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ለማከም የወጣውን ወጪ፣ ለረጅም ጊዜ የዘለቁ ጋብቻዎች መፍረሳቸው ያስከተለውን ኪሳራ፣ በነጠላ ወላጆች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች መኖራቸው በማኅበረሰቡ ላይ ያስከተለውን ኪሳራና ለቤተሰብና ለልጆች የሥነ ልቦና ሕክምና የሚወጣውን ወጪ አንድ ላይ በማጠናቀር ነው። የካናዳ ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል እንደዘገበው ዶክተር ዲክሰን እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “ነፃነት ያስገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት በፆታዊ ዝምድናዎች ረገድ የተካሄደው አብዮት ብዙዎች በፆታዊ ዝብርቅ፣ በአሳዛኝ ክስተት፣ በብቸኝነት ስሜት፣ በስሜት ሥቃይ፣ በዓመፅና በግፍ ውጥንቅጡ በወጣ ዓለም ቁጥጥር ሥር እንዲወድቁ አድርጓቸዋል።”
ታዲያ አሁንም ሰዎች ለፆታ ስሜት ተገዢ የሆኑት፣ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ የፆታ ዝምድናዎችን መመሥረት የመረጡትና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ ልቅ የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸውን የቀጠሉት ለምንድን ነው? ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት የተገኙት መጥፎ ፍሬዎች በግልጽ እየታዩ ሳለ ሰዎች አሁንም ለእንዲህ ዓይነቱ ጎጂ የፆታ ስሜት ተገዢ እንዲሆኑ የሚገፋፋቸው ነገር ምንድን ነው?
ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ፆታን በተዛባ መንገድ ያቀርባሉ
ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ሰዎች በፆታ ስሜት እንዲቃጠሉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። የነበረበትን መጥፎ ልማድ በግልጽ የተናገረ አንድ የወሲብ ሱሰኛ ዘ ቶሮንቶ ስታር ለተባለው ጋዜጣ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከአምስት ዓመታት በፊት ሲጋራ አቁሜያለሁ፤ መጠጥ ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት አቁሜያለሁ፤ ሆኖም ከፆታ እንዲሁም ከወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ሱስ እንደ መላቀቅ የከበደኝ ነገር የለም።”
በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን የመከታተል ልማድ ካላቸው የፆታ ስሜትን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እንደሚያድርባቸው ተናግሯል። ፆታዊ ቅዠታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ስለሚሞክሩ በገሃዱ ዓለም ከተቃራኒ ፆታ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት የተወሳሰበና አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ይህም ራሳቸውን እንዲያገልሉ የሚያደርጋቸው ከመሆኑም በላይ ሌሎች ችግሮችም ያስከትልባቸዋል። ከሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ችግሮች አንዱ ዘላቂ የሆነ ፍቅራዊ ዝምድና መመሥረት አለመቻላቸው ነው።
የመዝናኛው ዓለም ፆታን አግባብ ባልሆነ መንገድ ይጠቀምበታል
ሰዎች በሕጋዊ ጋብቻም ይሁን አይሁን የፆታ ጓደኞችን በማፈራረቅ የሚከተሉት ልቅ የአኗኗር ዘይቤ በመዝናኛው ዓለም በእጅጉ የተስፋፋና በይፋ የሚንጸባረቅ ልማድ ነው። በፊልሞች ላይ በግልጽ የሚታየው ፍቅር አልባና በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ፆታዊ ዝምድና ይህ ትውልድ ሰብዓዊውን የፆታ ስሜት በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው በማድረግ ለፆታ ስሜት ይበልጥ ተገዢ እንዲሆን ያደርገዋል። በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርበው መዝናኛ ብዙውን ጊዜ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነት ከፍቅራዊ ዝምድና ጋር አንድ ዓይነት አድርጎ በተሳሳተ መንገድ ያቀርባል። በመዝናኛው ዓለም ውስጥ ያሉትን ዝነኛ ሰዎች የሚያመልኩ የመዝናኛ አፍቃሪያን መረን በለቀቀ የፆታ ፍላጎትና በፍቅር፣ ለአጭር ጊዜ በሚቆይ ፆታዊ ዝምድናና ዘላቂ በሆነ ቃል ኪዳን ወይም ደግሞ በቅዠትና በእውነታ መካከል ያለውን ልዩነት መለየት የተሳናቸው ይመስላል።
እንደዚሁም አብዛኛውን ጊዜ የማስታወቂያው ዓለም ፆታን የንግድ ማካሄጃ መሣሪያ አድርጎ አላግባብ ይጠቀምበታል። ፆታ “ትኩረትን ወደ አንድ ምርት ለመሳብ የሚያገለግል ስብዕና የለሽ ዕቃ” ሆኗል ሲሉ አንድ የፆታ ሕክምና ባለሙያ ተናግረዋል። ማስታወቂያ የሚያሠሩ ሰዎች ፆታን አላግባብ የተጠቀሙበት ከመሆኑም በላይ የፆታ ስሜት መግለጫዎችን ከጥሩ ሕይወት ጋር አያይዘው ለማቅረብ ይሞክራሉ፤ ይህ ደግሞ ፋሚሊ ሪሌሽንስ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ሌላው የ20ኛው መቶ ዘመን “የተዛባ ፆታዊ አመለካከት” ነው።
ፆታዊው ሚና መለወጡ አመለካከትን ያዛባል
ማኅበራዊው ሁኔታ እየተለወጠ መሄዱና በ1960 የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ መዋላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን የፆታ ባሕርይ ለውጠውታል። እንክብሎቹ ሴቶች ቀደም ሲል አግኝተውት በማያውቁት ሁኔታ ፆታዊ እኩልነት፣ ፆታዊ ነፃነት ወይም በራስ የመመራት መብት እንደተጎናጸፉ ሆኖ እንዲሰማቸው አድርገዋቸዋል። ያልተፈለገ እርግዝና ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ሳያድርባቸው ወንዶቹ እንደሚያደርጉት ሁሉ እነርሱም የተለያዩ ወንዶችን ለመለዋወጥ ይችላሉ ማለት ነው። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በፆታዊ ነፃነታቸው እጅግ በመደሰት ተፈጥሯዊውን የቤተሰብና የፆታ ሚና አሽቀንጥረው ጥለዋል።
አንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች “ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ . . . መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ . . . ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ” በማለት ገልጿቸዋል።—2 ጴጥሮስ 2:14, 15
በትምህርት ቤቶች የሚሰጥ የፆታ ትምህርት
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ገና ባላገቡ 10,000 የሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት “በፆታ ትምህርት ኮርሶች ያገኙት እውቀትም ሆነ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴን በተመለከተ አለን የሚሉት እውቀት” ከጋብቻ ውጪ የሚጸንሱትን በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ቁጥር እንዳልቀነሰ አመልክቷል። ሆኖም አንዳንድ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ምንም እንኳ ድርጊቱ ብዙ ያወዛገበ ቢሆንም ወረርሽኙን ለመከላከል በሚል ለተማሪዎቻቸው በነፃ ኮንደሞች አድለዋል።
ካልጋሪ ሄራልድ በተባለ ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ የተደረገላት አንዲት የ17 ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እንዲህ ብላለች:- “በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኙ አብዛኞቹ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች . . . የ12 ዓመት ልጆች እንኳ ሳይቀሩ የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ መሆናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው።”
ፍቅርና ቃል ኪዳን ምንድን ናቸው?
ፍቅር፣ መተማመንና የጠበቀ ወዳጅነት እንዲሁ በድንገት በፆታ ስሜት በመሳሳብ ወይም ደግሞ የፆታ ፍላጎትን በማርካት የሚገኙ ነገሮች አይደሉም። የፆታ ግንኙነት ብቻውን እውነተኛ ፍቅር ሊፈጥር አይችልም። ፍቅርና የጠበቀ ወዳጅነት ዘላቂ ዝምድና ለመገንባት በቆረጡ ሁለት የሚተሳሰቡ ሰዎች ልብ ውስጥ የሚጸነሱ ነገሮች ናቸው።
ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ዝምድናዎች ውሎ አድሮ አንድን ግለሰብ በራሱ እንዳይተማመን፣ ብቸኛ እንዲሆንና ምናልባትም እንደ ኤድስ ባሉ በፆታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች እንዲለከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ። ልቅ የፆታ ግንኙነትን የሚያራምዱ ሰዎች 2 ጴጥሮስ 2:19 ላይ በሚገኙት ቃላት በጥሩ ሁኔታ ተገልጸዋል:- “ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው:- አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና።”
የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የማኅበራዊ ጉዳዮች ቦርድ ሰኔ 1995 ላይ “ሊወደስ የሚገባው ነገር” በሚል ርዕስ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። ቦርዱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ፈጽሞ በሚቃረን መንገድ ቤተ ክርስቲያኒቷ “‘በኃጢአት መኖር’ የሚለውን ሐረግ እንድታጠፋና ሳይጋቡ አንድ ላይ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ያላትን የነቀፋ አመለካከት እንድታስወግድ” አጥብቆ ማሳሰቡን ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ሪፖርቱ “ሳይጋቡ አብረው በሚኖሩ ሰዎች ሕይወት ውስጥ አምላክ እንዳለ ሰዎች ሁሉ ይገነዘቡ ዘንድ . . . ጉባኤዎች እነዚህን ሰዎች ሊቀበሏቸው፣ ሊሰሟቸውና ከእነሱ ሊማሩ ይገባል” ሲል ሐሳብ አቅርቧል።
ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉትን የሃይማኖት መሪዎች ምን ብሎ ይጠራቸው ነበር? ‘ዕውር መሪዎች’ ብሎ ይጠራቸው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህን መሪዎች የሚከተሉ ሰዎችስ? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ።” ይህን ነገር በተመለከተ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፤ ኢየሱስ “ምንዝርነት” እና “ዝሙት” ‘ሰውን ከሚያረክሱት’ ነገሮች መካከል እንደሚገኙበት በግልጽ ተናግሯል።—ማቴዎስ 15:14, 18–20
ፆታን በተዛባ መንገድ የሚተረጉሙና አግባብ ባልሆነ መንገድ የሚጠቀሙ እነዚህን የመሳሰሉ የተለያዩ ነገሮች እያሉ አንድ ሰው በተለይ ደግሞ ወጣቶች ለፆታ ስሜት ተገዢ ከመሆን ሊጠበቁ የሚችሉት እንዴት ነው? አስደሳችና ዘላቂ የሆነ ዝምድና ለመመሥረት ቁልፉ ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ወላጆች ወጣት ልጆቻቸው ለወደፊት ሕይወታቸው ዝግጁ እንዲሆኑ ለመርዳት ምን ማድረግ እንደሚችሉ ይገልጻል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በየዓመቱ ሦስት ሚልዮን የሚያክሉ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በፆታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች ይጠቃሉ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፆታዊ የአኗኗር ዘይቤዎች
የፆታ ፍቅር ሱሰኞች:- በፍቅር መያዝ ያስደስታቸዋል፤ በመሆኑም የወረት ፍቅራቸው በከሰመ ቁጥር ፍቅረኞቻቸውን ይቀያይራሉ። ይህን መጠሪያ ያወጡት በኒው ዮርክ ስቴት በሥነ አእምሮ ኢንስቲትዩት የሚሠሩት ዶክተር ማይክል ሊበዊትስ ናቸው።
በአንድ የማይረጉ:- ሕጋዊ በሆነ መንገድ እያገቡ፣ እየፈቱና እንደገና እያገቡ በየጊዜው ከተለያዩ ሰዎች ጋር ፆታዊ ዝምድና የሚመሠርቱ ሰዎች በማኅበራዊ ጉዳዮች ተመራማሪዎች ዘንድ በዚህ መጠሪያቸው ይታወቃሉ።
ሴሰኞች:- በርካታ ጓደኞች በመያዝ በፆታ ግንኙነት ረገድ ያላቸውን ችሎታ ለማሳየት ይፈልጋሉ ሲሉ በቤተሰብ ጥናቶች ፕሮፌሰርና የፆታ ሐኪም የሆኑት ሉተር ቤከር ገልጸዋል። ይህ መጠሪያ በአሁኑ ጊዜ ልጆችን በፆታ የሚያስነውሩ ሰዎችንም ለማመልከት ይሠራበታል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ሱስ የሚያስይዙ ከመሆናቸውም በላይ የፆታ ስሜትን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት ያስተላልፋሉ