የሰዎች አመለካከት መለወጡ አዳዲስ ጥያቄዎች ያስነሳል?
“የፆታ አብዮት፣” “በፆታ ስሜት መቃጠል፣” “የሥነ ምግባር አብዮት።” እነዚህ ቃላት ሰዎች በተለይ ከ1960ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ወዲህ ለፆታ ስሜት ያላቸው አመለካከት እየተለወጠ መሄዱን በስፋት ያሳወቁ ናቸው። ብዙዎች “ልቅ የፆታ ግንኙነት” የሚለውን መፈክር በማንገብ ጋብቻንና ድንግልናን ይቃወማሉ።
“ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ የሚያደርግ ነገር ሁሉ ትክክለኛ ሥነ ምግባር ሲሆን መጥፎ ስሜት እንዲሰማህ የሚያደርግ ነገር ሁሉ ደግሞ ብልሹ ሥነ ምግባር ነው” የሚለው የደራሲው የኧርነስት ሄሚንግዌይ መግለጫ ፆታዊ ነፃነትና እርካታ እናገኛለን በሚለው ተስፋ የተማረኩ ሰዎችን አመለካከት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ይህ ፍልስፍና ተቀባይነት ማግኘቱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የየራሳቸውን የፆታ ስሜት የሚፈትሹበት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ፆታዊ ዝምድና ከበርካታ ግለሰቦች ጋር መመሥረታቸው ትክክል እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ አድርጓል። የፆታ ስሜትን “የማርካቱ” ፍላጎት ምንም ገደብ አልነበረውም። በዚያው አሥርተ ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ሰዎች ይበልጥ ልቅ በሆነ መንገድ የፆታ ግንኙነት ሙከራ እንዲያካሂዱ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ልቅ የአኗኗር ዘይቤ ያተረፈው ቅርስ ቢኖር ኤድስና ሌሎች በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ነው። ሥነ ምግባሩ የተበላሸው ትውልድ ፆታን በተመለከተ የነበሩት አመለካከቶች ከሥረ መሠረታቸው ተናጉ። በርከት ካሉ ዓመታት በፊት ታይም መጽሔት “ፆታ በ1980ዎቹ ዓመታት—አብዮቱ አከተመ” የሚል ርዕሰ ዜና ይዞ ወጥቶ ነበር። ይህ መግለጫ እጅግ የተስፋፉትንና በርካታ አሜሪካውያንን ያጠቁትን በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን በዋነኛነት መሠረት በማድረግ የወጣ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ላይ በኤድስ የተለከፉ ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ በመጨመር 30 ሚልዮን ገደማ ደርሷል!
በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች የፈጠሩት ስጋት ብዙዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ፆታዊ ዝምድናዎችን በተመለከተ የነበራቸውን አመለካከት እንዲለውጡ አድርጓቸዋል። ዩ ኤስ የተባለ አንድ አዝናኝ መጽሔት በ1992 እትሙ ላይ ያወጣው አንድ የመንግሥት ጥናት እንዲህ ይላል:- “ኤድስንና ሌሎች በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን በመፍራት 6.8 ሚልዮን የሚሆኑ ነጠላ ሴቶች በፆታዊ ባሕርያቸው ላይ ለውጥ አድርገዋል።” ጽሑፉ በሚለው መሠረት መልእክቱ ግልጽ ነው:- “የፆታ ግንኙነት እንደ ዋዛ የሚታይ ነገር አይደለም። አውቃችሁ ግቡበት።”
እነዚህ ቀውጢ አሥርተ ዓመታት ሰዎች ለፆታዊ ዝምድና ያላቸውን አመለካከት የነኩት እንዴት ነው? በቅርብ አሥርተ ዓመታት ልቅ የፆታ ግንኙነት የሚል መፈክር በማንገብ በግዴለሽነት መንፈስ ለስሜት ተገዥ በመሆን ከተፈጸመው ድርጊትና በ80ዎቹ ዓመታት ከተከሰቱት አሳሳቢ የሆኑ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ትምህርት መቅሰም ተችሏል? በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የፆታ ትምህርት መሰጠት መጀመሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች የፆታ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዲችሉ ረድቷቸዋል? በዛሬው ጊዜ የፆታ ስሜትን በተመለከተ ሰዎች ያላቸው አመለካከት መለወጡ የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ምንድን ነው?