የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 10/8 ገጽ 8-10
  • የተፈጠረውን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የተፈጠረውን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ወላጆች
  • ፈታኙን ሁኔታ በተሳካ መንገድ መወጣት
  • ይሖዋ ለሕይወት ያደረገውን ዝግጅት ተቀበል
  • አመለካከትህን የሚቀርጸው ምንድን ነው?
    ንቁ!—1998
  • የሰዎች አመለካከት መለወጡ አዳዲስ ጥያቄዎች ያስነሳል?
    ንቁ!—1998
  • ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም
    ንቁ!—2013
  • ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርኩ ለመጫወት ደርሻለሁን?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 10/8 ገጽ 8-10

የተፈጠረውን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም

የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ መጽሐፎች፣ መጽሔቶች፣ ፊልሞችና ሙዚቃዎች በፆታ ሥነ ምግባር ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚጀምሩት ከለጋ ዕድሜ አንስቶ ነው። ወጣቶች ስሜታዊ ጥንካሬው ሳይኖራቸው የዐዋቂዎች ዓይነት ፆታዊ ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ግፊት ይደረግባቸዋል። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በአፍላ ዕድሜያቸው ከተቃራኒ ፆታ ጋር እየተቀጣጠሩ እንዲጫወቱ በመፍቀድ ፆታዊ ግፊቱ እንዲያይልባቸው ያደርጋሉ። የእኩዮች ተጽዕኖ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወትን ያበረታታል፤ ቋሚ የወንድ ጓደኛ ወይም የሴት ጓደኛ ያላቸው ብዙ ወጣቶች ብዙም ሳይቆይ ይዘናጉና የፆታ ግንኙነት ይፈጽማሉ። “የወላጆቿ ፍቅር እንደተነፈጋት የሚሰማት በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጅ . . . ፍቅርና የተቀራረበ ዝምድና ያስገኝልኛል በሚል የተሳሳተ እምነት ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸሟ . . . የተለመደ ነገር ነው” ሲሉ በቤተሰብ ጥናቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ሉተር ቤከር ተናግረዋል።

ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የጉርምስና ዕድሜያቸውን ለቀሪው ሕይወታቸው የሚዘጋጁበት ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥ የመጨረሻውን የደስታ ጊዜ የሚያሳልፉበት እንደሆነ አድርገው ሲመለከቱት ይታያሉ። “የፆታ ግንኙነት መፈጸም መቻላቸው ስለሚያስደስታቸውና የፆታ ግንኙነት መፈጸም የወንድነት መለኪያ ነው የሚለውን የእኩዮቻቸው ቃል ማመናቸው ብዙ ወጣቶች” በጉርምስና ዕድሜያቸው “ሴት አሳዳጆች” እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ሲሉ ፕሮፌሰር ቤከር ተናግረዋል። ከ30 ዓመታት ገደማ በፊት ታሪክ ጸሐፊው አርኖልድ ቶይንቤ በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊው የምዕራቡ ዓለም ያለው የረቀቀ የፈጠራ ችሎታ በከፊል ሊገኝ የቻለው በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች እውቀት በመሰብሰብ ላይ ማተኮር እንዲችሉ ‘የፆታ ግንኙነት መፈጸም’ የሚጀምሩበትን ጊዜ ማዘግየት በመቻሉ እንደሆነ ታሪክ አስተምሮናል የሚል እምነት ስላላቸው በወጣትነት ዘመን የሚያጋጥመውን ይህን አታላይ ነገር ነቅፈዋል።

በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ወላጆች

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ልጆቻቸው ለመዝናናት ብለው ከተቃራኒ ፆታ ጋር እየተቀጣጠሩ እንዲጫወቱ የማይፈቅዱ ወላጆች ለልጆቻቸው የወደፊት ጤናና ደስታ ከልብ እንደሚያስቡ ያሳያሉ። ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎች በማውጣትና ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት በመፍጠር በልጆቻቸው ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። በወጣቶች ፆታዊ ባሕርይ ላይ የተደረገው ጥናት “ይህ ተጽዕኖ ልጆቹ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚጀምሩበትን ጊዜ ሊያዘገየው እንደሚችል” ማመልከቱን ጆርናል ኦቭ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ ዘግቧል።

ልጆቻቸው ራስን በራስ የመገሰጽ ዝንባሌ በውስጣቸው እንዲሰርጽና ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማድረግ የቻሉ ወላጆች የተሻሉ ውጤቶች ያገኛሉ። “በጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችም ሆኑ ወላጆቻቸው ኃላፊነት መሸከምን ጎላ አድርገው የሚገልጹ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ሲኖሯቸው ወጣቶቹ ከጋብቻ ውጪ ልጅ የመውለድ ዕድላቸው በእጅጉ እንደሚቀንስ” አንድ ጥናት አረጋግጧል። ይህም ልጆቻቸው የቤት ሥራቸውን በሚገባ የሚሠሩ መሆናቸውን በማረጋገጥ፣ የትና ከማን ጋር እንደሚውሉ በመከታተል፣ ሊጨበጡ የሚችሉ የትምህርት ግቦችን በማውጣትና መንፈሳዊ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በማካፈል በልጆቻቸው እንቅስቃሴ ውስጥ አሳቢነት የተሞላበት ተሳትፎ ማድረግ ይጠይቅባቸዋል። ከወላጆቻቸው ጋር እንዲህ ዓይነት የተቀራረበ ግንኙነት ያላቸው ልጆች ስለ ራሳቸው የተሻለ አመለካከት የሚኖራቸው ከመሆኑም በላይ የፆታ ስሜታቸውን በተመለከተ የመረበሽ ስሜት አይሰማቸውም።

ለወላጆችም ሆነ ለልጆች ከሁሉ የላቀው መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ነው። በእስራኤል የነበሩ ወላጆች ትክክለኛ የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ታዝዘው ነበር። ይሖዋ “በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው?” ሲል ጠይቋቸዋል። ልጆቻቸውን ሞቅ ያለ ፍቅርና የጠበቀ ዝምድና ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ይህን ‘የጽድቅ ሥርዓት’ ማስተማር ነበረባቸው። “ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” ልጆች የሚከተለው ምክር ተሰጥቷቸዋል:- “የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው።” አባትም ሆነ እናት እንዲህ ያለ ወዳጃዊና ፍቅራዊ ትምህርት ለልጆቻቸው መስጠታቸው ልጆቻቸው ለሕይወትም ሆነ ለፆታ ስሜት ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ አንድን ወጣት በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ‘ይጠብቀዋል።’—ዘዳግም 4:8፤ 6:7፤ ምሳሌ 6:20, 22

ወጣቶች፣ ለፆታ ስሜታችሁ በመሸነፍ የወደፊቱን ሕይወታችሁን ለምን ታበላሻላችሁ? አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ተብለው የሚጠሩት ዓመታት ሰባት ናቸው። በእነዚህ ዓመታት በአእምሮ፣ በስሜትና በመንፈሳዊ በማደግና ስለ ፆታ ስሜት ሚዛናዊ አመለካከት በማዳበር ለቀሪዎቹ 50 ወይም 60 ዓመታት መዘጋጀት ይኖርባችኋል። ወላጆች፣ አምላክ የሰጣችሁን ኃላፊነት አክብዳችሁ ተመልከቱ፤ እንዲሁም ልጆቻችሁን በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችና ያልተፈለገ እርግዝና ከሚያስከትሉት የልብ ሐዘን ጠብቋቸው። (መክብብ 11:10) ልጆቻችሁ ለሌሎች ፍቅርና አሳቢነት ማሳየት እንዴት ዘላቂ ዝምድና ሊመሠርት እንደሚችል በዕለታዊ ሕይወታችሁ እንዲመለከቱ አድርጉ።

ፈታኙን ሁኔታ በተሳካ መንገድ መወጣት

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያለው ለፆታ ስሜት ተገዢ የመሆን መንፈስ ለሕይወት ያላችሁን አመለካከት እንዲያዛባውና አርኪና አስደሳች ሕይወት የመኖር አጋጣሚያችሁን እንዲያበላሽባችሁ አትፍቀዱለት። በሰው ልጆች መካከል የነበሩ ዝምድናዎችን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱት በርካታ ምሳሌዎች ላይ አሰላስሉ። ሕይወትና ፍቅር ከአፍላ የጉርምስና ዕድሜ በኋላም አስደሳችና ትርጉም ያላቸው ሆነው እንደሚቀጥሉ እርግጠኛ ሁኑ። ይህ እውነታ ለክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ከወጣው መለኮታዊ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ በጥሞና ሲታሰብበት ለሁለት ፍቅረኛሞች ወዳጃዊና ዘላቂ ትዳር ጥሩ መሠረት ሊጥል ይችላል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን እንደ ያዕቆብና ራሔል፣ ቦዔዝና ሩት፣ እንዲሁም እረኛውና ሱነማይቱ ልጃገረድ ያሉትን ጥንዶች ስትመለከቱ በዝምድናቸው መካከል ፆታዊ መሳሳብ እንደነበረ ትረዳላችሁ። ይሁን እንጂ ዘፍጥረት ምዕራፍ 28 እና 29⁠ን፣ የሩትን መጽሐፍና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንን በጥሞና ስታነቡ እነዚህን ዝምድናዎች ያጠነከሩ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችም እንደነበሩ ትገነዘባላችሁ።a

ይሖዋ ለሕይወት ያደረገውን ዝግጅት ተቀበል

የሰው ዘር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ የሰውን ልጅ የፆታ ስሜትና ይህ ስሜት የሚያሳድረውን ግፊት አሳምሮ ያውቃል። በፍቅር በመነሳሳት በመልኩ ፈጥሮናል፤ የፈጠረን “የዘማዊነት በራሂዎችን” በውስጣችን ተክሎ ሳይሆን ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ስሜቶቻችንን የመቆጣጠር ችሎታ ሰጥቶን ነው። “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ . . . ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፣ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፣ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤ . . . ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል።”—1 ተሰሎንቄ 4:3–6

ይህ በመላው ዓለም በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ በተግባር ታይቷል። አምላክ ለክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ያወጣቸውን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ያከብራሉ። ሽማግሌዎችን እንደ አባቶች “ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፣ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፣ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና” ይመለከቷቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ወጣት ወንዶችና ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ከተቃራኒ ፆታ ጋር እየተቀጣጠሩ እንዲጫወቱና እንዲያገቡ ከሚያደርግ ተጽዕኖ ወይም ደግሞ በፆታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ነፃ ሆነው ችሎታቸውን ሙሉ በሙሉ መጠቀም ወደሚችሉበት ደረጃ እንዲደርሱ የሚረዳ ጤናማ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል! በክርስቲያን ጉባኤ የተጠናከረ ንቁ የሆነ ክርስቲያን ቤተሰብ በፆታ ስሜት ካበደው ዓለም የሚጠብቅ አስተማማኝ ከለላ ነው።

ክርስቲያን ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሥራ ላይ በማዋል ለፆታ ስሜት ተገዢ ከመሆን መጠበቅ ከመቻላቸውም በላይ ለሚከተለው የአምላክ ቃል ምክር ትኩረት በመስጠት ደስታ ያገኛሉ:- “አንተ ጎበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ፤ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ። ሕፃንነትና ጉብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ኀዘንን አርቅ፣ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ።”—መክብብ 11:9, 10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 247 ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤተሰብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ፆታዊ ዝምድና የመመሥረት ፍላጎት አያድርባቸውም

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለፆታ ስሜት ተገዢ የመሆን መንፈስ የተሟላና አስደሳች ሕይወት የመኖር አጋጣሚህን እንዲያበላሽብህ አትፍቀድለት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ