የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 11/8 ገጽ 18-20
  • ቁጣህን መቆጣጠር ያለብህ ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቁጣህን መቆጣጠር ያለብህ ለምንድን ነው?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሲቆጡ
  • ክርስቲያኖች ኃላፊነት አለባቸው
  • መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን በተመለከተ ምን ይላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ቁጣ የሚያስከትለው ጉዳት
    ንቁ!—2012
  • ቁጣ እንዳያሰናክልህ ተጠንቀቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 11/8 ገጽ 18-20

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ቁጣህን መቆጣጠር ያለብህ ለምንድን ነው?

ገና ከጅምሩ አላማረም ነበር። “ከእንግዲህ የቤቱ ራስ እኔ ነኝ፤ በአንቺ የተነሳ እየዘገየሁ የምሸማቀቅበት ምክንያት የለም” በማለት ጆን አዲስ ሙሽራ በሆነችው ሚስቱ ላይ አንባረቀባት።a ሶፋ ላይ እንድትቀመጥ ካዘዛት በኋላ ከ45 ደቂቃ በላይ ጮኸባት። የዘለፋ ንግግር የትዳራቸው ክፍል ሆነ። የሚያሳዝነው ደግሞ የጆን የቁጠኝነት ባሕርይ ይበልጥ እየከፋ መሄዱ ነው። በሩን በኃይል ይዘጋል፣ የወጥ ቤቱን ጠረጴዛ ደጋግሞ ይደበድባል፣ የሌሎች ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል መንገድ የመኪናውን መሪ እየደበደበ በቁጣ መኪናውን ይነዳል።

እናንተም እንደምታውቁት እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በስፋት የሚፈጸም የተለመደ ነገር መሆኑ የሚያሳዝን ነው። ይህ ሰው የተቆጣው በቂ ምክንያት ኖሮት ነው ወይስ ራሱን መቆጣጠር ተስኖት? ሁሉም ዓይነት ቁጣ ስህተት ነውን? ቁጣ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል የሚባለው መቼ ነው? ከልክ አልፏል የሚባለውስ መቼ ነው?

ከቁጥጥር ውጪ ያልሆነ ቁጣ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ብልሹ ሥነ ምግባር በነበራቸው በጥንቶቹ የሰዶምና ገሞራ ከተሞች ላይ የአምላክ ቁጣ ነድዶ ነበር። (ዘፍጥረት 19:24) ለምን? ምክንያቱም በእነዚያ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በኃይል እያስገደዱ በሚፈጽሙት ወራዳ የፆታ ብልግና በአገሩ ሁሉ በሰፊው የታወቁ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል መላእክት ወደ ሎጥ ቤት መልእክት ለማድረስ ሄደው በነበረበት ጊዜ ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ ተሰባስበው በመምጣት የሎጥን እንግዶች በፆታ ለማስነወር ሙከራ አድርገው ነበር። ይሖዋ አምላክ እነዚህ ሰዎች ባሳዩት ጸያፍ ምግባር መቆጣቱ የተገባ ነበር።—ዘፍጥረት 18:20፤ 19:4, 5, 9

ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ አባቱ የተቆጣባቸው ጊዜያት ነበሩ። በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የተገነባው አምላክ ለመረጠው ሕዝብ የአምልኮ ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ነበር። ቤተ መቅደሱ ግለሰቦች ለአምላክ መሥዋዕቶችንና ቁርባኖችን የሚያቀርቡበት እንዲሁም የእርሱን መንገዶች የሚማሩበትና ኃጢአታቸውን ይቅር የሚባሉበት “የጸሎት ቤት” እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነበር። በቤተ መቅደስ ውስጥ ሆነው ከይሖዋ ጋር መነጋገር የሚችሉ ያክል ነበር። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ግን ቤተ መቅደሱን “የንግድ ቤት” እና “የወንበዶች ዋሻ” አድርገውት ነበር። (ማቴዎስ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 2:14–17) ለመሥዋዕት ከሚሸጡት እንስሳት ጥቅም ያገኙ ነበር። ቃል በቃል መንጋውን ማለትም ሕዝቡን ይገፍፉ ነበር ለማለት ይቻላል። ስለዚህም የአምላክ ልጅ እነዚያን አጭበርባሪዎች ከአባቱ ቤት ጠራርጎ ሲያባርር ትክክለኛ እርምጃ መውሰዱ ነበር። ኢየሱስ ተቆጥቶ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም!

ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሲቆጡ

ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችም አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ በሆነ ምክንያት ሊቆጡ ይችላሉ። የሙሴን ሁኔታ እንመልከት። የእስራኤል ብሔር ከግብፅ ምድር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ገና ነፃ መውጣቱ ነበር። ይሖዋ ግብፃውያንን በአሥር መቅሰፍቶች በመምታት ከግብፅ የሐሰት አማልክት የበለጠ ኃይል እንዳለው በሚያስደንቅ መንገድ አሳይቶ ነበር። ከዚያም ቀይ ባሕርን ለሁለት በመክፈል እስራኤላውያን ሸሽተው የሚያመልጡበትን መንገድ አሰናዳላቸው። ከጊዜ በኋላ ወደ ሲና ተራራ ግርጌ ደረሱና እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ተደራጁ። ሙሴ እንደ መካከለኛ ሆኖ በማገልገል የአምላክን ሕግጋት ለመቀበል ወደ ተራራው ወጣ። ይሖዋ ሌሎቹን ሕግጋት ጨምሮ እርሱ ራሱ ከተራራው ጠርቦ ባዘጋጀው የድንጋይ ጽላት ላይ “በአምላክ ጣት” የተጻፉትን አሥርቱን ትእዛዛት ለሙሴ ሰጠው። ይሁን እንጂ ሙሴ ከተራራው ሲወርድ ምን ነገር ገጠመው? ሕዝቡ ከወርቅ የተሠራ የጥጃ ምስል ማምለክ ጀምረው ነበር! በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉን ዘንግተው ነበር! ነፃ ከወጡ ገና ጥቂት ሳምንታቸው ነበር። ወዲያውም “የሙሴ ቁጣ ተቃጠለ።” የድንጋይ ጽላቶቹን ወርውሮ ከከሰከሳቸው በኋላ የጥጃውን ምስል አፈራረሰ።—ዘጸአት 31:18፤ 32:16, 19, 20

በሌላ ጊዜ ደግሞ ሕዝቡ ውኃ በማጣታቸው ምክንያት አማርረው በተናገሩ ጊዜ ሙሴ ቁጣውን መቆጣጠር ተስኖት ነበር። በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ ተለይቶ የሚታወቅበትን ገርነቱን ወይም የዋሕነቱን ለጥቂት ጊዜ አጥቶ ነበር። ይህም ከባድ ስህተት እንዲፈጽም አደረገው። እስራኤላውያን የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ የሚያቀርበው ይሖዋ መሆኑን ጎላ አድርጎ ከማሳየት ይልቅ ሙሴ ሕዝቡን ሻካራ በሆኑ ቃላት በመናገር ትኩረታቸው በወንድሙ በአሮንና በራሱ ላይ እንዲሆን አደረገ። ስለዚህም አምላክ ለሙሴ ተገቢውን ተግሳጽ ሰጥቶታል። ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ አልተፈቀደለትም። ይህ ሁኔታ በመሪባ ከተፈጸመ በኋላ ሙሴ ቁጣውን መቆጣጠር እንደተሳነው የሚገልጽ ሌላ ዘገባ አናገኝም። ከስህተቱ እንደተማረ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል።—ዘኁልቁ 20:1-12፤ ዘዳግም 34:4፤ መዝሙር 106:32, 33

በአምላክና በሰው መካከል ልዩነት መኖሩ እሙን ነው። ይሖዋ ‘ቁጣውን መግታት’ ይችላል። የእርሱ ዋነኛ ባሕርይ ቁጣ ሳይሆን ፍቅር በመሆኑ “ለቁጣ የዘገየ” እንደሆነ ተደርጎ በትክክል ተገልጿል። ቁጣው ሁልጊዜ በጽድቅና በበቂ ምክንያት ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም በላይ ሁልጊዜ ቁጣውን መቆጣጠር ይችላል። (ዘጸአት 34:6፤ ኢሳይያስ 48:9፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስም ቁጣውን ሁልጊዜ ይቆጣጠር ነበር። “የዋህ” እንደሆነም ተገልጿል። (ማቴዎስ 11:29) በሌላ በኩል ግን እንደ ሙሴ ያሉትን የእምነት ሰዎች ጨምሮ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በጠቅላላ ቁጣቸውን የመቆጣጠር ችግር አለባቸው።

በተጨማሪም በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ ቆም ብለው አያስቡም። አንድ ሰው በቁጣ ገንፍሎ የሚፈጽመው ነገር መጥፎ ውጤት ሊያስከትልበት እንደሚችል ማወቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ባል በሚስቱ ላይ ተቆጥቶ ግድግዳውን በቡጢ ቢመታው ምን ነገር ሊከተል ይችላል? ንብረቱ ሊበላሽ እጁም ሊጎዳ ይችላል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በቁጣ መንደዱ ፍቅርና አክብሮት ታሳየው በነበረችው ሚስቱ ላይ ምን ውጤት ያስከትላል? የተበላሸው ንብረት በጥቂት ቀናት ውስጥ ሊጠገን ይችላል፣ እጁም ቢሆን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሊድን ይችላል፤ ይሁን እንጂ የሚስቱን እምነትና አክብሮት እንደገና ለማትረፍ ምን ያህል ጊዜ ይወስድበት ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቅሳቸዋል። ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት። ቃየን ወንድሙን አቤልን ከገደለ በኋላ አካባቢውን ጥሎ ተሰድዷል። ስምዖንና ሌዊ የሴኬምን ሰዎች በመግደላቸው አባታቸው ረግሟቸዋል። ዖዝያን ሊያርሙት በሞከሩት ካህናት ላይ በመቆጣቱ ይሖዋ በለምጽ መትቶታል። ዮናስ በ“ተቆጣ” ጊዜ ይሖዋ ገሥጾታል። ሁሉም ያደረባቸው ቁጣ ተጠያቂነት አስከትሎባቸዋል።—ዘፍጥረት 4:5, 8-16፤ 34:25-30፤ 49:5-7፤ 2 ዜና መዋዕል 26:19፤ ዮናስ 4:1-11

ክርስቲያኖች ኃላፊነት አለባቸው

በተመሳሳይም ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች ለሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ለአምላክም ሆነ በተወሰነ መጠን ለእምነት ባልንጀሮቻቸው መልስ መስጠት አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን ለማመልከት የገቡትን የግሪክኛ ቃላት የተጠቀመበት መንገድ ይህን ግልጽ ያደርገዋል። በተደጋጋሚ ከተሠራባቸው ሁለት ቃላት መካከል አንደኛው ኦርግ የሚለው ነው። ይህ ቃል በጥቅሉ “ቁጣ” ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን ብዙውን ጊዜም በቀል ለመፈጸም በማሰብ በተወሰነ መጠን አውቆና አልፎ ተርፎም ሆን ብሎ አንድ ነገር ማድረግን ያመለክታል። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ በሮም የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል:- “ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው [ኦርግ] ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።” በወንድሞቻቸው ላይ ጥላቻን አምቀው ከሚይዙ ይልቅ “ክፉውን በመልካም [እንዲያሸንፉ]” ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—ሮሜ 12:19, 21

ሌላው በተደጋጋሚ ተጠቅሶ የሚገኘው ቃል ታይሞስ የሚለው ነው። መሠረታዊው ቃል “በመጀመሪያ ይሠራበት የነበረው አየር፣ ውኃ፣ መሬት፣ እንስሳት ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን ኃይለኛ እንቅስቃሴ ለማመልከት ነበር።” በዚህም የተነሳ ቃሉ “ገንፍሎ የወጣን የጥላቻ ስሜት፣” “በንዴት መጦፍን፣” ወይም “በቁጣ ስሜት ገንፍሎ የአእምሮን ሰላም በማናጋት በቤት ውስጥና በውጪ ሽብርና ረብሻ መፍጠርን” ለማመልከት በተለያየ መንገድ ተሠርቶበታል። ቁጣቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ወንዶች ወይም ሴቶች ሳይጠበቅ ድንገት ፈንድቶ አመድ፣ አለትና ገሞራ ትፍ በመትፋት የአካል ጉዳትና ሞት ሊያስከትል እንደሚችል እሳተ ገሞራ ናቸው። ጳውሎስ በገላትያ 5:20 ‘ቁጣን’ ከዝሙት፣ ከመዳራት፣ ከስካርና ከሌሎች ‘የሥጋ ሥራዎች’ (ቁጥር 19) ጋር በጠቀሰበት ላይ ታይሞስ የሚለው ቃል የተሠራበት ብዙ ቁጥርን በሚያመለክት መንገድ ነው። በእርግጥም በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጆን ያሳየው ባሕርይ እዚህ ላይ የተገለጸውን “ቁጣ” በሚገባ የሚያንጸባርቅ ነው ማለት ይቻላል።

የጉባኤ አባል ሆነው የዚህ ዓይነቱን ባሕርይ በማንጸባረቅ በሰዎች ወይም በሌላ ሰው ንብረት ላይ በተደጋጋሚ የኃይል ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን የክርስቲያን ጉባኤ እንዴት ሊመለከታቸው ይገባል? ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን በቀላሉም ወደ ጥል ይመራል። ኢየሱስ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ [“ሁልጊዜ፣” NW] የሚቈጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነበር። (ማቴዎስ 5:21, 22) ባሎች “ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው” ተብለው ተመክረዋል። በትንሽ በትልቁ ‘የሚቆጣ’ ሰው በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆኖ የማገልገል ብቃት አይኖረውም። ከዚህ የተነሳ ቁጣቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ግለሰቦች ጉባኤው እንደ ምሳሌ አድርጎ አይመለከታቸውም። (ቆላስይስ 3:19፤ ቲቶ 1:7፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:8) እንዲያውም የግለሰቡን ዝንባሌ፣ የጠባዩን ሁኔታና በሌሎች ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት ቁጣውን የመቆጣጠር ችግር ያለበት ግለሰብ ከጉባኤ ሊወገድ ይችላል። በእርግጥም መዘዙ ከባድ ነው።

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆን ስሜቱን መቆጣጠር ችሎ ይሆን? መከራ ውስጥ ዘው ብሎ እንዲገባ የሚያደርገውን ችግር ማሸነፍ ችሎ ይሆን? የሚያሳዝነው ከመጮህም አልፎ መግፋትና መገፍተር ጀመረ። ጣቱን መቀሰር ብቻ ሳይሆን ቃል በቃል መማታትም ጀመረ። ጆን ድርጊቱ ይፋ እንዳይወጣበት ይጠነቀቅ ስለነበር ሚስቱን ሰው በቀላሉ ሊያየው በሚችለው አካሏ ላይ አይመታትም ነበር። ውሎ አድርጎ ግን እርግጫ፣ ቡጢ፣ ጠጉር መሳብና ከእነዚህ የባሱ ድርጊቶችን መፈጸም ጀመረ። አሁን ጂንጀር ከጆን ተለያይታለች።

ይህ መሆን አልነበረበትም። እንዲህ ዓይነት ችግር የነበረባቸው በርካታ ሰዎች የቁጠኝነት ባሕርያቸውን መቆጣጠር ችለዋል። ስለዚህም ፍጹም ምሳሌ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ መከተሉ ምንኛ አስፈላጊ ነው። ቁጣውን መቆጣጠር ተስኖት የታየበት አንድም ጊዜ የለም። ቁጣው ምንጊዜም በጽድቅ ላይ የተመሠረተ ነበር። ቁጣው ከቁጥጥሩ ውጪ የሆነበት አንድም ጊዜ የለም። ጳውሎስ “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” በማለት ለሁላችንም ጥበብ የተሞላበት ምክር ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:26) ሰው እንደመሆናችን መጠን አቅማችን ውስን መሆኑንና የዘራነውን የምናጭድ መሆናችንን አምነን መቀበላችን ቁጣችንን እንድንቆጣጠር ሊያደርገን ይገባል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹን ቀይረናቸዋል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳዖል ዳዊትን ለመግደል ያደረገው ሙከራ/The Doré Bible Illustrations/Dover Publications, Inc.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ