ከዓለም አካባቢ
አለ ሐኪም ትእዛዝ ለሚሸጡ መድኃኒቶች ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች
በሰሜን አየርላንድ አለ ሐኪም ትእዛዝ ለሚሸጡ መድኃኒቶች ሱሰኛ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዳለ ዚ አይሪሽ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል። በሌሎች ብዙ አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ በሰሜን አየርላንድም ኮዴይንና ሱስ ሊያሲዙ የሚችሉ ንጥረ ነገሮች ያሏቸው እንደ ሥቃይ ማስታገሻና እንደ ሳል መድኃኒት ያሉትን መድኃኒቶች አለ ሐኪም ትእዛዝ መግዛት ይቻላል። ሳይታወቃቸው ሱሰኛ ከሚሆኑ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሱሳቸውን ማርካት ከባድ ችግር ሆኖባቸዋል። መድኃኒቶቹን ሳይወስዱ በሚቀሩበት ጊዜ እንደ ማቅለሽለሽና ጭንቀት የመሰሉ ስሜቶችን ጨምሮ ብዙ ሥቃይ ይደርስባቸዋል። አንድ ሱሰኛ በሳምንት 70 ብልቃጥ መድኃኒት እንዲወስድ የሚጠይቅበትን ሱስ ለማሸነፍ ሲል በውርስ ያገኘውን ንብረቱን በሙሉ ጨርሶ መኖሪያ ቤቱን ከሸጠ በኋላ 200,000 ብር የሚያክል ዕዳ ውስጥ ገብቷል። ፍራንክ መክጎልድሪክ የተባሉት የቤልፋስት የኬሚካል ሱሰኝነት ምርምር ተቋም ባልደረባ አለ ሐኪም ትእዛዝ የሚሰጡ መድኃኒቶችን አለ አግባብ ከሚወስዱ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ሱሰኛ መሆናቸውንም ሆነ በራሳቸው ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆናቸውን አይቀበሉም ብለዋል። “የሚጥሱት ምንም ሕግ የለም። እንዲያውም አብዛኞቹ መድኃኒቶቹን መውሰዳቸው አግባብ አለመሆኑን አይገነዘቡም” በማለት መክጎልድሪክ ገልጸዋል።
በረዥም ዕድሜ ከዓለም አንደኛ የሆኑት ሴት አረፉ
በጊነስ ቡክ ኦቭ ወርልድ ሪከርድስ መሠረት በረዥም ዕድሜ ከዓለም አንደኛ የሆኑት ዣን ሉዊዝ ካልማ በ122 ዓመታቸው ነሐሴ 4 ቀን 1997 እንዳረፉ ለ ፊጋሮ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። ዣን በደቡባዊ ምሥራቅ ፈረንሳይ በአርል ከተማ የተወለዱት የካቲት 21 ቀን 1875 ሲሆን በዚያ ጊዜ አምፖል፣ የሸክላ ማጫወቻና መኪና ገና አልተፈለሰፉም ነበር። በ1896 ትዳር መስርተው 63 ዓመት ቀድመዋቸው የሞቱትን ሴት ልጃቸውንና በ1963 የሞቱትን የልጅ ልጃቸውን አፍርተዋል። ቪንሰንት ቫን ጎግ ከተባሉት ዝነኛ ሠዓሊ ጋር በ1888 ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳሉ ተገናኝተው እንደነበረና በ1904 የኖቤልን ሽልማት ያሸነፉት ፍሬድሪክ ሚስትራ የተባሉ ገጣሚ ጓደኛቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ዣን ዕድሜ ስለሚያራዝሙ ነገሮች ሲናገሩ ሳቅ፣ ሥራና ያገኙትን ሁሉ መብላት ነው በማለት እየሳቁ ገልጸዋል።
ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ እንዲደረግላት ተማጸነች
በፈረንሳይ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጦርነቱ ዘመን የነበረው ፈረንሳዊው የቪሺ መንግሥት በአይሁዳውያን ላይ ለፈጸመው ግፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ “ደንታ ቢስ” በመሆን ለፈጸመችው ኃጢአት አምላክና አይሁዳውያን ይቅርታ እንዲያደርጉላት በመጠየቅ “የንሥሐ መግለጫ” አውጥታለች። ከ1940 እስከ 1944 በነበሩት ዓመታት 75,000 የሚያክሉ አይሁዶች ከፈረንሳይ ወደ ናዚ መግደያ ካምፖች ታስረው ተወስደዋል። ሊቀ ጳጳሳት ኦሊቭየ ደ ቤራንዤ ባነበቡት መግለጫ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሷን ጥቅም በማስቀደሟ ምክንያት “በአምላክ አምሳል ለተፈጠረ ለማንኛውም ሰው አክብሮት እንዲሰጥ የሚያዘውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግዴታ ችላ ብላለች” ሲል ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። አይሁዶችን የደገፉ በጣት የሚቆጠሩ ፈረንሳውያን ቀሳውስት ቢኖሩም አብዛኞቹ ቀሳውስት የቪሺን መንግሥትና መንግሥቱ ይከተል የነበረውን መርሕ ደግፈዋል። መግለጫው በከፊል እንደሚከተለው ይላል:- “በአይሁዳውያን ላይ በደረሰው ስደትና በተለይም የቪሺ ባለሥልጣናት ባወጁዋቸው ፀረ ሴማዊ እርምጃዎች ረገድ ከቁጣ ይልቅ ግድ የለሽነት አይሎ እንደነበረ ቤተ ክርስቲያንዋ መቀበል ይኖርባታል። ይፈጸም ስለነበረው ግፍ ከመናገር ይልቅ በዝምታ መመልከት ሰፍኖ ነበር። . . . ዛሬ ይህ ዝምታ ስህተት እንደነበረ እንናዘዛለን። በተጨማሪም የፈረንሳይ ቤተ ክርስቲያን የሕዝቦችን ሕሊና የማስተካከል ተልእኮዋን እንዳልተወጣች እንገነዘባለን።”
ሁለት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሕፃናት
አንድ ሕፃን የአፍ መፍቻ ቋንቋውን በሚማርበት ጊዜ ንግግር የማቀናበር ችሎታው በአብዛኛው የሚቀመጠው ብሮካስ ኤርያ በሚባለው የአንጎል ክፍል ነው። በቅርቡ ኒው ዮርክ በሚገኘው ሚሞርያል ስሎዋን—ኬተሪንግ ካንሰር ማዕከል የሚሠሩ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት ፈንክሽናል ማግኔቲክ ሬሶናንስ ኢሜጅንግ ቴክኒክ በመጠቀም ሁለት ቋንቋ የሚችሉ ሰዎች አንደኛውን ቋንቋ በሚናገሩበት ጊዜ የሚጠቀሙት በየትኛው የአንጎል ክፍል እንደሆነ ለይተው ለማወቅ ጥረት አድርገዋል። አንድ ሰው ሕፃን እያለ ሁለት ቋንቋዎችን በአንድ ጊዜ በሚማርበት ጊዜ ሁለቱም ቋንቋዎች በብሮካስ ኤርያ በአንድ ክፍል ውስጥ ይቀመጣሉ። ሙሉ ሰው ከሆነ በኋላ ሁለተኛ ቋንቋ በሚማርበት ጊዜ ግን ከመጀመሪያው ቋንቋ ጋር ከመደባለቅ ይልቅ ከጎኑ የሚቀመጥ ይመስላል። ዘ ታይምስ የተባለው የለንደን ጋዜጣ “የመጀመሪያው ቋንቋ በብሮካስ ኤርያ ውስጥ ያለውን የመልእክት ዝውውር ሙሉ በሙሉ ስለሚይዘው ሁለተኛው ቋንቋ ሌላ ቦታ መፈለግ የሚኖርበት ይመስላል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። ተመራማሪዎቹ ዕድሜ ከገፋ በኋላ ሌላ ቋንቋ መማር አስቸጋሪ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ከሁሉ የከፋው የሻርክ ጠላት?
ብዙ ሰዎች ሻርክን በጣም ይፈራሉ። ይሁን እንጂ ሻርኮች ሰውን ይበልጥ መፍራት የሚኖርባቸው ይመስላል። ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ሪፖርት እንዳደረገው በየዓመቱ ከሻርኮች በተሰነዘረባቸው ጥቃት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከመቶ ያነሱ ሲሆን ዓሣ አጥማጆች በየዓመቱ የሚገድሏቸው ሻርኮች ቁጥር ግን 100,000,000 ይደርሳል። ይህ ግድያ ከቀጠለ የውቅያኖሶችን የተፈጥሮ ሚዛን ሊያቃውስ ስለሚችል ጉዳዩ በርካታ የውቅያኖስ ባዮሎጂስቶችን አሳስቧቸዋል። ሻርኮች በውቅያኖሶች ውስጥ የሚኖሩትን ፍጥረታት ብዛት በመቆጣጠር ረገድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሚና ይጫወታሉ። ሻርኮች ለርቢ የሚደርሱት ብዙ ዘግይተው በመሆኑና ከረዥም የእርግዝና ጊዜ በኋላ የሚወልዷቸው ግልገሎች ጥቂት ስለሆኑ ብዙ የሻርክ ዝርያዎች በዓሣ አጥማጆች እየተገደሉ ጨርሶ ወደ መጥፋት እየተቃረቡ ነው። የውቅያኖስ ፍጥረታት ጠበብትን በተለይ በጣም የሚያሳዝናቸው ዓሣ አጥማጆች የሻርኮችን አቅጣጫ መቆጣጠሪያ ክንፍ ቆርጠው ለምግብነት ከወሰዱ በኋላ ሻርኮቹን ወደ ባሕር ጥለው እንዲሞቱ ማድረጋቸው ነው።
ሥራ አጥነት የሚያስከትለው ውጥረት
ዙድዶቸ ሳይቱንግ በተባለው የጀርመን ጋዜጣ ላይ የተጠቀሱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሥራ አጥነት የሚያስከትለው ስሜታዊና ማኅበራዊ ጫና በአንድ ሰው ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም እንዲህ ባለው ጫና ሊዳከም እንደሚችል ተነግሯል። በተጨማሪም ሥራ ካላቸው ሰዎች ይበልጥ ሥራ የሌላቸው ለከፍተኛ የደም ግፊትና ለልብ ሕመም ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው። የጀርመን፣ ሀኖቨር ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ቶማስ ኪዝለባኽ “ለረዥም ጊዜ ሥራ የፈታ ሰው የሚቋቋመው ውጥረት ሥራ ካለው ሰው በጣም የሚከፋና ብዙ ጉዳት የሚያስከትል ነው” ብለዋል። “ሁሉም ሥራ አጦች ማለት ይቻላል፣ በአንድ ዓይነት መንገድ ከጭንቀት በሚመጡ ችግሮች ይሠቃያሉ።” በአውሮፓ ኅብረት አገሮች የሚኖሩ ሥራ አጦች ቁጥር የዴንማርክን፣ የፊንላንድንና የስዊድንን ነዋሪዎች ጠቅላላ ድምር ያክላል።
‘በቅልጥፍናው ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጓጓዣ’
በሰዓት ከስምንት ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ በማይቻልባቸው የከተማ መንገዶች ብስክሌት ከመኪና የበለጠ ፍጥነት ሊኖረው እንደሚችል ዚ አይላንድ የተባለው የኮሎምቦ ስሪ ላንካ ጋዜጣ ዘግቧል። ፍሬንድስ ኦቭ ዚ ኧርዝ የተባለው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ብስክሌትን “በቅልጥፍናው ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጓጓዣ በማለት ጠርቶታል። ብስክሌት ከአንድ ሊትር ቤንዚን ከሚገኝ ኃይል ጋር በሚመጣጠን ጉልበት በአካባቢ ላይ ምንም ዓይነት ብክለት ሳያስከትል 2,400 ኪሎ ሜትር ሊጓዝ እንደሚችል ጠቁሟል። በብስክሌት መጠቀም ለጤንነት ጠቃሚ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።
ሁለተኛው ሺህ ዓመት አልቋል?
ምሁራን እንደሚሉት “ሁለተኛው ሺህ ዓመት ካለቀ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። እናዝናለን፣ ሁላችንም ሳናውቀው አልፏል” በማለት ኒውስዊክ መጽሔት ይናገራል። ምክንያቱ ምንድን ነው? የዘመን አቆጣጠራችን የተመሠረተው “በዘፈቀደ በተወሰነ የዘመናት አከፋፈል ላይ ነው።” ይህ አከፋፈል ክርስቶስ በተወለደበት ዓመት ላይ የተመሠረተ ነው ይባላል። ይሁን እንጂ ጽሑፉ እንዳለው ኢየሱስ የተወለደው ከ“ዓመተ ምሕረት” ብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ እንደሆነ ብዙ ምሁራን ያምናሉ። ኒውስዊክ እንደሚለው “ወደ ሦስተኛው ሺህ ዓመት ከገባን ብዙ ቆይተናል” ማለት ነው። ስህተቱ የተፈጸመው ዳኒሲየስ አጭሩ በ525 እዘአ ለቤተ ክርስቲያን አጽዋማትና በዓላት መቁጠሪያ የሚያገለግል የዘመናት አቆጣጠር እንዲያዘጋጅ በሊቀ ጳጳሳት ጆን ቀዳማዊ በታዘዘ ጊዜ ነበር። ዳኒሲየስ ለአቆጣጠሩ መነሻ ያደረገው የኢየሱስን ልደት ቢሆንም ኢየሱስ የተወለደበትን ዓመት ሲያሰላ ተሳስቷል። ኒውስዊክ “የታሪክ ምሁራን ኢየሱስ የተወለደበትን ጊዜ በእርግጠኝነት ፈጽሞ ሊያውቁ አይችሉም” ይላል። “የኢየሱስ ልደት የሚከበርበት ገና የሚውልበት ቀን እንኳን በዘፈቀደ የተመረጠ ነው። ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 25ን የመረጠችው በክረምቱ ወራት የቀንና የሌሊት ርዝመት እኩል ሲሆን ከሚከበረው የአረማውያን በዓል ጋር ለማጋጠምና ይህንንም በዓል ለማስረሳት ስትል ነው።” ኢየሱስ የተወለደው በ2 ከዘአበ እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት አቆጣጠር ያመለክታል።
በዕድሜ የገፉ ሠራተኞች ያላቸው ብልጫ
ከ47 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሠራተኞች በዕድሜ ከሚያንሱ የሥራ ባልደረቦቻቸው ይበልጥ ከሰዓት በፊት ባሉት ሰዓቶች ሥራቸውን በንቃትና በቅልጥፍና እንደሚያከናውኑ የለንደን ዘ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል። ይህ አዝማሚያ ከሰዓት በኋላ ተቀይሮ የተገላቢጦሽ ስለሚሆን የሊቨርፑል ጆን ሙርስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ቶም ራይለ አሠሪዎች ሸምገል ያሉ ሠራተኞችን በጠዋት ፈረቃ፣ ወጣቶቹን ደግሞ በከሰዓት በኋላና በምሽት ፈረቃ ቢመድቡ ጥሩ እንደሚሆን ምክር ሰጥተዋል። በተጨማሪም ስለ እርጅና በተደረገው የብሪታንያ ሕክምና ማህበር ጉባኤ ላይ የቀረቡ ተናጋሪዎች የገበያ አዳራሾችና ራስን በራስ የሚስተናገዱበት ሱቆች ሸምገል ያሉ ሠራተኞችን ለመቅጠር እንደሚመርጡ ገልጸዋል። ለምን? እነዚህ ሰዎች ለደንበኞች የበለጠ አሳቢነት ስለሚያሳዩና የጽሑፍ መመሪያ የሌላቸው መሣሪያዎች እንዴት እንደሚሠሩ በማስረዳት ረገድ የበለጠ እውቀት ስለሚኖራቸው ነው። በተጨማሪም “ኩባንያው ችላ ያላቸውን የሥነምግባር ደንቦች ጠብቀው ይገኛሉ” በማለት ጋዜጣው ዘግቧል።