የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwhf ርዕስ 35
  • ፍቺ በስተርጅና—መከላከያው ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፍቺ በስተርጅና—መከላከያው ምንድን ነው?
  • ለቤተሰብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በስተርጅና የሚፋቱት ለምንድን ነው?
  • ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
  • ዕርቅ ሊወርድ ይችላልን?
    ንቁ!—1999
  • ምርጫችሁ ፍቺ በሚሆንበት ጊዜ
    ንቁ!—1999
  • ጓደኝነት ገደቡን ሲያልፍ
    ንቁ!—2013
  • ለሁለት የተከፈለ ቤት—መፋታት በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ችግር
    ንቁ!—2009
ለተጨማሪ መረጃ
ለቤተሰብ
ijwhf ርዕስ 35
ደስታ የራቃቸው በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት ተራርቀው ተቀምጠዋል። ሁለቱም በሐሳብ ሄደዋል።

ለቤተሰብ | ትዳር

ፍቺ በስተርጅና—መከላከያው ምንድን ነው?

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ1990 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት በተወሰደ አኃዛዊ መረጃ ዕድሜያቸው ከ50 በላይ በሆኑ ባለትዳሮች ዘንድ የፍቺ ብዛት በእጥፍ የጨመረ ሲሆን ከ65 ዓመት በላይ በሆኑት ዘንድ ደግሞ በሦስት እጥፍ ጨምሯል። ሰዎች በስተርጅና የሚፋቱት ለምንድን ነው? የእናንተም ትዳር ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥመው መከላከል የምትችሉት እንዴት ነው?

በዚህ ርዕስ ውስጥ

  • በስተርጅና የሚፋቱት ለምንድን ነው?

  • ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • መወያያ ሐሳብ

በስተርጅና የሚፋቱት ለምንድን ነው?

  • ብዙውን ጊዜ በዕድሜ የገፉ ባለትዳሮች ለፍቺ የሚደርሱት በጊዜ ሂደት እየተራራቁ በመምጣታቸው ነው። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ምንም የጋራ ነገር የሌላቸው እስኪመስል ድረስ የሚያስደስቷቸው ነገሮች ለየቅል እየሆኑ ይሄዳሉ። ወይም ደግሞ ልጆቻቸው አድገው ከቤት ሲወጡ ለረጅም ጊዜ አባት ወይም እናት ሆነው ከመኖራቸው የተነሳ የባልነት ወይም የሚስትነት ነገር ሊረሳ ይችላል።

  • ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የትዳር አዋቂ ነን ባዮች፣ ባለትዳሮች በራሳቸው ፍላጎት ላይ እንዲያተኩሩ እየመከሩ ነው። ‘ትዳሬ ደስታ አስገኝቶልኛል?’ ‘የተሻልኩ ሰው እንድሆን ረድቶኛል?’ ‘የትዳር አጋሬ ስሜታዊ ፍላጎቴን ያሟላልኛል?’ ይሁንና እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉስ? የዘመኑ አስተሳሰብ የሚለው እንዲህ ነው፦ ‘ለአንተ የተሻለውን ነገር ለማግኘት እርምጃ ውሰድ፤ ካስፈለገም ትዳርህን አፍርሰህ ሕይወትን እንደ አዲስ ጀምር።’

  • ፍቺ ከባድ ነገር ተደርጎ መታየቱ ቀርቷል። የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ኤሪክ ክሊነንበርግ እንዲህ ብለዋል፦ “ከተወሰነ ጊዜ በፊት፣ በትዳሩ ደስታ ያጣ ሰው መፋታት ቢፈልግ ትዳሩን ለማፍረስ አሳማኝ ምክንያት ማግኘት ይጠበቅበት ነበር። አሁን አሁን ግን፣ አሳማኝ ምክንያት የሚያስፈልገው በትዳር ለመቀጠል ነው፤ ምክንያቱም ለራስ ብቻ የመኖር ባሕል ብዙዎችን እየተጠናወተ ነው።”a

እርግጥ ነው፣ ፍቺ በአብዛኛው አንድን ችግር ሸኝቶ ሌላ ችግር መሸመት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጥናት እንደጠቆመው “በስተርጅና መፋታት ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ይዳርጋል፤ በተለይ ለሴቶች።”

ልታስቡበት የሚገባ ሌላም ነገር አለ። ፍቺ ይቅርብህ (ዶንት ዲቮርስ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ሕይወትን እንደ አዲስ ጀመርኩ ትል ይሆናል፤ አንተ ግን ያው የድሮው አንተ ነህ። ከባለቤትህ ጋር መግባባት ከባድ እንዲሆንብህ ያደረገህን የአነጋገር ልማድ ለማስተካከል ሞክረሃል? አለመግባባት ሲያጋጥም ሁኔታውን የምትይዝበትን መንገድ ለማሻሻል ያደረግከው ነገር አለ?”b

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ለውጥ እንደሚኖር አምናችሁ ተቀበሉ። ባለበት የሚቀጥል ወዳጅነት የለም። ከትዳር አጋራችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነትም መልኩን ሊቀይር ይችላል፤ ለምሳሌ፣ ልጆቻችሁ ከቤት ሲወጡ ወይም በጊዜ ሂደት የሚያስደስቷችሁ ነገሮች እየተራራቁ ሲሄዱ። የቀድሞውን ጊዜ እየናፈቁ ከመብሰልሰል ይልቅ አሁን ያላችሁበትን ሁኔታ ማሻሻል ስለምትችሉበት መንገድ አስቡ።

    በዕድሜ ተለቅ ያሉ ባልና ሚስት በመመገቢያ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል። ሚስትየው ከልጃቸው ጋር የተነሱትን የቤተሰብ ፎቶ አሻግራ ትመለከታለች፤ ባልየው ደግሞ አጠገባቸው ባለው ባዶ ወንበር ላይ አተኩሮ ተክዟል።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “‘የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?’ አትበል፤ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጥበብ አይደለምና።”​—መክብብ 7:10

  • ጓደኝነታችሁን አጠናክሩ። የትዳር አጋራችሁ በሚወደው ነገር ለመደሰት ጥረት ማድረግ ወይም ደግሞ እናንተን የሚያስደስታችሁን ነገር ለትዳር ጓደኛችሁ ማጋራት ትችሉ ይሆን? ሁለታችሁንም የሚያስደስታችሁ አዲስ ነገር መፈለግስ ትችላላችሁ? ዋናው ዓላማችሁ ከትዳር አጋራችሁ ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ነው፤ ይህም እንደ ደባል ሳይሆን እንደ ትዳር አጋር እንድትተያዩ ይረዳችኋል።

    በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት በደስታ አትክልት ሲንከባከቡ።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”​—1 ቆሮንቶስ 10:24

  • መልካም ባሕርይ ማሳየታችሁን ቀጥሉ። መላመድ፣ ቀላል ተደርገው የሚታዩ የመልካም ባሕርይ መገለጫዎችን እንዳታሳዩ እንቅፋት አይሁንባችሁ። የትዳር አጋራችሁን በአክብሮት አነጋግሩ፤ ያኔ ስትጠናኑ አንዳችሁ ለሌላው ታሳዩ የነበረውን መልካም ምግባር አትተዉ። “እባክህ/ሽ” እና “አመሰግናለሁ” ተባባሉ። አዘውትራችሁ ፍቅራችሁን ግለጹ፤ የትዳር አጋራችሁ ለሚያደርግላችሁ ነገር አድናቆታችሁን አሳዩ።

    በዕድሜ ተለቅ ያለ አንድ ሰው ለሚስቱ ጃንጥላ ይዞላታል፤ የመኪና በር እየከፈተላት ነው።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ።”​—ኤፌሶን 4:32

  • ያሳለፋችኋቸውን ጥሩ ጊዜያት አስታውሱ። የሠርጋችሁን አልበም ወይም በሌሎች ፕሮግራሞች ወቅት አንድ ላይ የተነሳችኋቸውን ፎቶዎች አብራችሁ ተመልከቱ። እንዲህ ማድረጋችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ፍቅርና አክብሮት መልሶ እንዲያብብ ይረዳችኋል።

    በዕድሜ የገፉ ደስተኛ ባልና ሚስት የፎቶ አልበም አብረው እየተመለከቱ ነው።

    የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።”​—ኤፌሶን 5:33

a ጎይንግ ሶሎ—ዚ ኤክስትራኦርዲነሪ ራይዝ ኤንድ ሰርፕራይዚንግ አፒል ኦቭ ሊቪንግ አሎን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

b በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ለፍቺ ምክንያት ተደርጎ ሊቀርብ የሚችለው የፆታ ብልግና ብቻ ነው። (ማቴዎስ 19:5, 6, 9) “መጽሐፍ ቅዱስ ፍቺን ይፈቅዳል?” የሚለውን ርዕስ አንብብ።

መወያያ ሐሳብ

በመጀመሪያ፣ ጥያቄዎቹን ለየብቻችሁ አስቡባቸው። ከዚያም በመልሶቻችሁ ላይ ተወያዩ።

  • ይህን ሰው ያገባችሁት የትኛው ባሕሪው ማርኳችሁ ነው?

  • ውሎ ሲያድር በግንኙነታችሁ ላይ ምን ለውጦች ተከስተዋል?

  • ትዳራችሁን በተመለከተ ምን እንዲሻሻል ትፈልጋላችሁ?

  • ከትዳር አጋራችሁ ጋር ያላችሁን ጓደኝነት ለማጠናከር እናንተ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ጓደኝነታችሁ እንዲጠናከር የትዳር አጋራችሁ ምን ቢያደርግ ደስ ይላችኋል?

  • የትዳር አጋራችሁ የትኞቹን የደግነትና የአክብሮት መገለጫዎች እንዲያሳያችሁ ትፈልጋላችሁ?

  • ሁለታችሁንም የሚያሳትፉ ምን እንቅስቃሴዎች አሉ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ