ሙዚቃ ያለው ኃይል
“ሙዚቃ ድንገት በመማረክ የተረበሸን ስሜትና የባከነን አእምሮ ሊያረጋጋ ይችላል።”
ይህ አባባል ዊልያም ኮንግሪቭ የዛሬ 300 ዓመት ገደማ ሂም ቱ ሃርመኒ በሚል ርዕስ ካዘጋጀው መጣጥፍ ላይ የተወሰደ ነው። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የጥንቶቹ ግሪካውያን መጣጥፎች “የኖታዎች ቅንብርና ምት ነፍስ ውስጥ ዘልቀው የመግባት ኃይል ስላላቸው የሙዚቃ ትምህርት ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሣሪያ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በዛሬው ጊዜ ሄቪ ሜታል የተባለውን ሙዚቃ አዘውትረው የሚሰሙ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ልጆቻቸው ፊታቸውን እንደ ሐምሌ ዳመና የሚያጨፈግጉና ሌሎችን ለመርዳት አሻፈረኝ የሚሉ መሆናቸውን የተመለከቱ አንዳንድ ወላጆች ይህን ሐቅ ተገንዝበዋል። በተጨማሪም በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት ጀርመን ውስጥ ናዚዎች ሕዝቡ የሰዎችን ስሜት የመቆጣጠር ኃይል የነበራቸውን የአዶልፍ ሂትለር ንግግሮች እንዲሰማ ለማነሳሳት ቀስቃሽ የሙዚቃ ማርሽ ያሰሙ በነበረበት ወቅትም ይኸው እውነታ በግልጽ ታይቷል።
ሙዚቃ በአእምሮና በልብ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል ከመሆኑም በላይ ልብንም ሆነ አእምሮን ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር ለመገፋፋት መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል ሕፃናት አንዳንድ ሙዚቃዎችን እንዲሰሙ ማድረጉ አእምሯዊና ስሜታዊ ዕድገታቸውን ያፋጥነዋል የሚል እምነት አለ። የሚንተባተቡ ሰዎች እንኳ አንዳንድ ጊዜ ሲናገሩ የሚያደነቃቅፏቸውን ዐረፍተ ነገሮች በትክክል ሊያዜሟቸው ይችላሉ።
አንቶኒ ስቶር ሚውዚክ ኤንድ ዘ ማይንድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት ከሆነ ሙዚቃ በሥርዓተ ነርቭ መዛባት ምክንያት የመንቀሳቀስ እክል በሚገጥማቸው ሕሙማን ላይ አንዳንድ ጊዜ የሚያመጣው ለውጥ በጣም የሚያስደንቅ ነው። ስቶር የአንዲት ሕመምተኛን ምሳሌ ጠቅሰዋል:- “በወጣትነት ዕድሜዋ ታውቃቸው የነበሩ ዜማዎችን ማስታወስ እስከቻለችበት ጊዜ ድረስ [በፓርኪንሰንዝ] በሽታ ሳቢያ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኗት ነበር። እነዚህ ዜማዎች በድንገት የመንቀሳቀስ ችሎታዋን መልሳ እንድታገኝ ረድተዋታል።”
የሚያሳስብ ሁኔታ
ሙዚቃ ያለው ኃይል ጥሩ ጎኖች እንዳሉት ማየት ችለናል። ይሁን እንጂ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ወይም ስግብግብ የሆኑ ሰዎች ሙዚቃ ያለውን ኃይል አጥፊ መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ፀረ ማኅበራዊ በሆነ ምግባርና በአንዳንድ የሙዚቃ ዓይነቶች መካከል ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለ አንዳንድ ጥናቶች አመልክተዋል።
ከዚህ አባባል ጋር በሚስማማ መንገድ ሳይኮሎጂ ኦቭ ዊሜን ኳርተርሊ እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “ዓመፅን የሚያበረታቱ የሮክ ሙዚቃ የቪዲዮ ክሮችን የሚመለከቱ ወንዶች ዓመፅን የማያበረታቱ የሮክ ሙዚቃ የቪዲዮ ክሮችን ከሚመለከቱ ወንዶች ይበልጥ ለሴቶች አሳቢነት የጎደለው የጥላቻ አመለካከት የሚንጸባረቅባቸው በመሆኑ የሮክ ሙዚቃ የቪዲዮ ክሮችን መመልከት ወሲባዊ ጽሑፎችንና ሥዕሎችን የመመልከት ያህል ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል።”
ይህ ተጽዕኖ በወንዶች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ሴቶችንም ሊነካ ይችላል። ይኸው ዘገባ እንዲህ ሲል አክሎ ገልጿል:- “ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እነዚህ ዘፈኖች ሴቶች ዋጋ ቢስ እንደሆኑ አድርገው የሚያስተላልፉትን አፍራሽ መልእክት መቀበል ሊጀምሩ ይችላሉ።”
ሴክስ ሮልስ የተባለው መጽሔት ከዚህ መደምደሚያ ጋር በመስማማት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት ... ጥሩ መንፈስ በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉና የሙዚቃ ቪዲዮዎችን የሚያሳድዱ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች ልቅ የሆነ ወሲባዊ ምግባርና አመለካከት በእጅጉ ይንጸባረቅባቸዋል።” በአንዳንድ የራፕ ሙዚቃዎች ውስጥ በግልጽ የሚንጸባረቁት ዓመፅን የሚያበረታቱ መልእክቶችና የብልግና ግጥሞች አንድ የአሜሪካ የአውራጃ ፍርድ ቤት ዳኛ አንድን የራፕ ሙዚቃ አልበም በተመለከተ “ከማኅበረሰቡ የሥነ ምግባር መስፈርት አንጻር ሲታይ እጅግ ጸያፍ” የሚል ብያኔ እንዲያስተላልፉ አስገድደዋቸዋል።
ዳኛው ይህን ብያኔ ያስተላለፉት አክራሪ ስለሆኑ ይሆን? በፍጹም! አዶለሰንስ የተባለው መጽሔት “ሄቪ ሜታልና ራፕ የሚያደምጡ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ሕይወታቸው ይበልጥ የተመሰቃቀለ እንደሆነ ወጣቶቹም ሆኑ ወላጆቻቸው ይናገራሉ” ሲል ደምድሟል። በዚህ መንገድ የሚፈጠረው ምስቅልቅል ደግሞ “ከጠበኝነትና ከአጥፊነት ጠባይ” እንዲሁም ከዝቅተኛ የትምህርት ውጤት ጋር ዝምድና ያለው ነው።
በተወሰኑ የሙዚቃ ዓይነቶችና በጾታ ስሜት፣ ራስን በመግደልና በፀረ ማኅበራዊ ጠባይ መካከል ያለው ዝምድና በሚገባ በማስረጃ የተረጋገጠ ነው። ይህ ማለት ግን ሁሉም ዓይነት ሙዚቃ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል ማለት ነውን? የሚቀጥሉት ርዕሶች ይህን ጉዳይ አስመልክተው የሚሰጡትን ሐሳብ ተመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሙዚቃ በልብና በአእምሮ ላይ በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል