ለይሖዋ ያለን ፍቅር እሱን እያገለገልን እንድናመልከው ይቀሰቅሰናል
“ትዕዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና።”—1 ዮሐንስ 5:3
1, 2. ይሖዋን እንድናገለግል የሚያነሳሳን ምን መሆን ይኖርበታል?
ከጃፓን የመጡ 80 አገር ጐብኚዎች በካሊፎርኒያ ዩ.ኤስ.ኤ. የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ እየዞሩ ይጎበኙ ነበር። ልዩ ልዩ በቀለማት ያሸበረቁ የሚያማምሩ ወፎችና ርግቦች የሚገኙበት ደስ የሚያሰኝ አካባቢ ወደ ታላቁ ፈጣሪያቸው ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንደቀረቡ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። እያዞረ የሚያስጐበኛቸው ወንድም እንግዶቹ በሙሉ አቅኚዎች በመሆን በሙሉ ጊዜ እያገለገሉ ያሉ መሆናቸውን ተገነዘበ። ስለዚህ አንድ አዘውትሮ የሚጠየቅ ጥያቄ ለእንግዶቹ ቀረበላቸው፦ “በጃፓን ብዙ አቅኚዎች ያሉት ለምንድን ነው?” ለጥቂት ጊዜ ዝምታ ከሰፈነ በኋላ አንዲት ወጣት ሴት መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነችና “ይሖዋን ስለምንወድ ነው” አለች።
2 ለይሖዋ ያለን ፍቅር፦ በአገልግሎቱ ቀናተኞች እንድንሆን ይገፋፋናል። እውነት ነው ሁሉም ሰው አቅኚ ለመሆን አይችልም። እውነትም ከአራት ሚሊዮን የመንግሥት አስፋፊዎቻችን መካከል አብዛኞቹ ይህን መብት ሊቀበሉ አልቻሉም። ቢሆንም ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ሁሉ ለዚህ መብት በቅተዋል። የተቀረነውም ደቀመዝሙር በማድረጉ ሥራ መጠነኛ ድርሻ በማበርከት ፍቅራችንን እያሳየን “በይሖዋ ልንታመንና መልካምንም ልናደርግ” እንችላለን። (መዝሙር 37:3, 4) የይሖዋ ውስን አምላኪዎች ሁሉ አቅኚዎች ለሆኑት ፍቅራዊ ድጋፍ በመስጠት የአቅኚነትን መንፈስ በማበረታታት ሥራ ሊካፈሉ ይችላሉ።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19
3. በአብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮችና በይሖዋ ምሥክሮች መሃል ምን ልዩነት ይስተዋላል?
3 የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖትን ተራ እንደሆነ የኑሮ ቅጥያ አድርገው ብቻ ከሚመለከቱት ክርስቲያን ነን ባዮች በተለየ መንገድ “አስቀድመው መንግሥቱንና ጽድቁን በመፈለግ” እንዲቀጥሉ የሚያነሣሣቸው ኃይለኛ የአምላክ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያሉ። ይህም መሥዋዕት ማድረግን ጠይቆባቸዋል። ቢሆንም ይህ መሥዋዕት አስፈላጊ የሆነና ምንም ያህል ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባ ነው። (ማቴዎስ 6:33፤ 16:24) ይህም መጀመሪያ በሙሴ ከተነገረውና በኋላም በኢየሱስ ክርስቶስ ከተደገመው “ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው። አንተም ይሖዋ አምላክህን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አሳብህ፣ በሙሉ ኃይልህም ውደድ” ከሚለው ከመጀመሪያው ትልቅ ትዕዛዝ ጋር የሚስማማ ነው።—ማርቆስ 12:29, 30፤ ዘዳግም 6:4, 5
4, 5. እንደ ታማኞች መቆጠር ያለባቸው እነማን ናቸው? ታማኝነትስ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
4 በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆነ አንድ ወንድም የ98 ዓመት ዕድሜ አረጋዊ ለሆነውና ከ70 ዓመት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላሳለፈው የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዘዳንት ለኤፍ ደብልዩ ፍራንዝ “ወንድም ፍራንዝ ጥሩ የታማኝነት ምሳሌ ሆነሃል” አለው። ወንድም ፍራንዝም መልሶ “አዎ ታማኝ መሆን ያስፈልጋል” አለው። ይህ አነጋገር ነገሩን በሙሉ ያጠቃልለዋል። በየትኛውም የመንግሥቱ ሥራ መስክ ብናገለግል ታማኞች ልንሆን እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 4:2፤ ገላትያ 3:9
5 እውነት ነው፣ ብዙዎች በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ መሥራት ቢችሉ ይወዱ ነበር። ነገር ግን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች ወይም የጤና ችግሮች ሊሠሩ የሚፈልጉትን መጠን ወስኖባቸዋል። ይሁን እንጂ አቅኚዎች መሆን የማይችሉት ታማኝነት እንደጐደላቸው ተደርገው አይታዩም። አንዳንዶቹ፣ አብዛኛውን ጊዜ ለብዙ ዓመታት በጣም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ታማኝነታቸውን ጠብቀው ኖረዋል። አዎን ታማኞች ሆነዋል! ለይሖዋ ፍቅር አሳይተዋል። ቲኦክራቲካዊ ዝግጅቶቹን በሙሉ ልብ በመደገፍ በትጋት አገልግለዋል። የአቅኚዎችን አገልግሎት በትጋት ከመከታተላቸውም በላይ አቅኚዎች ለመሆን የሚችሉ ሁሉ አብዛኛውን ጊዜም የራሳቸው ልጆች ከሌሎች ሥራዎች ሁሉ የሚበልጠውን አቅኚነት የሕይወታቸው ቋሚ ሥራ ለማድረግ እንዲጥሩ ማበረታቻ ሰጥተዋል።—ከዘዳግም 30:19, 20 ጋር አወዳድሩ።
6, 7. በ1 ሳሙኤል 30:16-25 ላይ የተመለከተው ምሳሌ ዛሬም የሚሠራው እንዴት ነው?
6 በዛሬው ጊዜም በሁሉም የአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚታየው ፍቅራዊ የተግባር አንድነት በ1 ሳሙኤል 30:16-25 ላይ ባለው ታሪክ ሊገለጽ ይችላል። በአማሌቃውያን ላይ በተደረገው ጦርነት “ዳዊትም ከማታ ጀምሮ እስከ ማግስቱ ማታ ድረስ መታቸው”ና ብዙ ምርኮ ወሰደ። ወደሠፈር ሲመለስ ከዳዊት ጋር የተዋጉ አንዳንድ ሰዎች ምርኮው ከእነሱ ጋር ወደተፋፋመው ውጊያ ገፍተው ላልገቡት ሰዎች እንዳይሰጥ ጠየቁ። ዳዊት ግን “ይህን ነገር ማን ይሰማችኋል? ነገር ግን የተዋጉትና ዕቃውን የጠበቁት ዕድል ፈንታ እኩል ይሆናል። አንድነት ይካፈላሉ” በማለት መለሰላቸው።
7 ዛሬም ይህ ሥርዓት ይሠራል። አቅኚዎች በመንፈሳዊ ውጊያችን ግንባር ቀደም ሆነዋል። ይሁን እንጂ በጉባኤው ውስጥ ያሉት ሁሉ ለዚህ ሥራ የሙሉ ልብና የታማኝነት ድጋፍ ይሰጣሉ። በ1991 በቅንጅት የፈጸሙት ሥራ ያስገኘው ከፍተኛ ውጤት በሚቀጥለው ሠንጠረዥ ላይ ተገልጿል።
አስደናቂ ሪፖርት
8. (ሀ) የዓለም አቀፉ ሪፖርት ጠቅላላ አስፋፊዎችንና በይሖዋ አገልግሎት የሚያሳልፉትን ሰዓት በተመለከተ ምን ያሳያል? (ለ) በሪፖርቱ ላይ ገና አዲስ ነፃነት በተገኘባቸው አገሮች ረገድ ምን ስሜት የሚስብ ነገር ትመለከታላችሁ?
8 አዎን ያለፉት የዚህ መጽሔት አራት ገጾች የሁሉም የይሖዋ ቀናተኛ አምላኪዎች የተባበረ ጥረት በ1991 ለተደረገው አስደሳች የሆነ ዓለም አቀፍ መስፋፋት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ያመለክታሉ። 4,278,820 ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ተገኝቷል። ይህም ካለፈው ዓመት 6.5 በመቶ ጭማሪ መሆኑ ነው። እነዚህም አስፋፊዎች 951,870,021 ሰዓት (ከአንድ ቢልዮን ሰዓት ምንም ያህል አያንስም) ለአገልግሎቱ አውለዋል። ቀደም ሲል ታግደው የነበሩና አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፉ ሪፖርት ላይ መውጣት በጀመሩት አገሮች ለምሳሌ በቡልጋሪያ፣ በካሜሩን፣ በቸኮዝሎቫኪያ፣ በኢትዮጵያ፣ በሞዛምቢክ፣ በኒካራጉዋ፣ በሩዋንዳና በዩ.ኤስ.ኤስ.አር የሚኖሩ ወንድሞቻችን ያደረጉትን ብርቱ ጥረት ተመልከቱ።
9, 10. (ሀ) አቅኚዎች በአሁኑ ጊዜ የሚገኘውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዴት ተቀብለውታል? (ለ) ወደ አቅኚነት አገልግሎት ለመግባት ምን ማበረታቻ ቀርቧል?
9 በቅርብ ዓመታት የአቅኚነት መንፈስ በዓለም በሙሉ ተዛምቷል። በቅርቡ የአምልኮ ነፃነት በተሰጠባቸው አገሮችም እንኳን ሳይቀር የአቅኚዎች ቁጥር እያደገ ነው። በእነዚህ አገሮች የሚገኘው አስከፊ የኢኮኖሚ ሁኔታ እንኳን እነዚህ ቆራጥ ምሥክሮች ያላቸውን ሁሉ ለይሖዋ አምልኮ እንዳያውሉ አላገዳቸውም። (ከ2 ቆሮንቶስ 11:23, 27, ጋር አወዳድሩ) በየወሩ በአማካይ ከመንግሥት አስፋፊዎቹ ውስጥ 14 በመቶ የሚያክሉት በአቅኚነት ያገለግሉ ነበር። ከፍተኛው የአቅኚዎች ቁጥር የጠቅላላ አስፋፊዎቹ ሁሉ 18 በመቶ ሲሆን 780,202 አቅኚዎች ነበሩ።
10 ሌሎችም አቅኚዎቹ የሚያገኙትን ደስታ በመመልከት ይህን አገልግሎት ለመጀመር እየተበረታቱ ነው። እስከአሁን ድረስ በአቅኚነት አላገለገልክ ከሆነ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር በኢሳይያስ 6:8 ላይ እንደምናነበው “እነሆኝ! እኔን ላከኝ” እንድትል ይገፋፋሃልን? ወይም ደግሞ የአምላክ ቃል በትጋት በምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አማካኝነት ወደ አቅኚነት አገልግሎት ለመግባት የሚያስችልህን ተጨማሪ እርምጃ እንድትወስድ የሚገፋፋ ፍላጎት በልብህ ውስጥ አይቀሰቅስብህምን? የይሖዋ ቃል ኤርምያስን በችግር ጊዜም እንኳን ሳይቀር ወደኋላ እንዳይል አነቃቅቶታል።—ኤርምያስ 20:9
ለሰው ልጆች የተሰጠ ፍቅራዊ አገልግሎት
11. የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሥራ ምን ያህል ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶበታል?
11 ከዓመቱ ሪፖርት አስደናቂ ገጽታዎች አንዱ የነፃ የቤት መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በቁጥር ማደግ ነበር። በዓለም ዙሪያ በየወሩ 3,947,261 የዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል። ይህም የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲሰብኩ የሚያገኙአቸው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ፍላጎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዱበት ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረውን አይነት ትጋት በማሳየት ከተለያዩ ሕዝቦችና ነገዶች ለተውጣጡ ሰዎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት በጣም ያስደስታል። ጳውሎስ ‘ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች በትጋት መመስከሩ’ እውነትን ለማስተማር ሥራ ብዙ ሰዓቶችን ማሳለፍ ጠይቆበት እንደነበረ አያጠራጥርም። (ሥራ 20:20, 21) ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ” እንዲችሉ እየረዱአቸው ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:4
12-14. ከአውሮፓ ምን አስደሳች ሪፖርቶች እየመጡ ነው?
12 በምሥራቅ አውሮፓ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሥራ በጣም እንደጨመረ የሚያሳየው ሪፖርት በጣም የሚያስደስት ነው! ለብዙ አሥር ዓመታት ወንድሞቻችን የሚሰበሰቡት በትናንሽ ቡድኖች ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን የሚኖረው አንድ ያረጀና በእጅ የተባዛ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ብቻ ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወደ እነዚህ አገሮች በብዛት እየጐረፉ ነው። ይህም በመኃልየ መኃልይ 2:4 ላይ እንደ ኪንግ ጀምስ ቨርሽን “[ኢየሱስ ክርስቶስ] ወደ [መንፈሳዊ] ግብዣው ቤት አገባኝ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው” የሚለውን የሰለሞን መዝሙር ያስታውሰናል። አሁን የየራሳቸው የግል ቅጂዎች ስላሏቸው ብዙዎቹ “የእውነትን ቃል በቅንነት (በትክክል) የሚናገሩ” ለመሆን በሚገባ የታጠቁ እየሆኑ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
13 በሩሲያ 103 አስፋፊዎች ያሉበት፣ በቅዱስ ፒተርስበርግ የሚገኝ አንድ ጉባኤ 300 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዳሉት በቅርቡ ሪፖርት አድርጓል። የዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጥረት ፍሬ የሆኑ 53 አዳዲስ ምሥክሮች በ8 ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ተጠምቀዋል። በጉባኤው ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በእውነት ውስጥ ያሳለፉት ጊዜ ከስምንት ወር አይበልጥም። በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የሚረዳ ሽማግሌ የላቸውም። በጉባኤው ውስጥ ያለው አንድ ዲያቆን ብቻ ነው።
14 በኢስቶኒያ የምትኖር አንዲት የመንግሥት አስፋፊ ከጓደኞቿ አንዳንዶቹን ጥናት ላይ እንዲገኙ ልትጋብዛቸው ትችል እንደሆነ ጠየቀቻት። በሚቀጥለው ጊዜ አስጠኚዋ እህት እቤት ስትመጣ ከ30 ሰዎች በላይ ተሰብስበው አገኘች! በእርግጥ ለእነዚህ ሰዎች ሁሉ ተገቢውን መንፈሳዊ እንክብካቤ ለማድረግ ልዩ ዝግጅት ማድረግ አስፈልጎ ነበር።
15. በመታሰቢያው ላይ ስለተገኙት ሰዎችና ስለ ጥምቀት ምን ተብሏል?
15 በአሁኑ ጊዜ ከሚያጠኑት ሰዎች ብዙዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስቲያኖች ጋር የሚሰበሰቡት በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ በመገኘት ነው። ባለፈው ዓመት በዚህ አስደሳች ወቅት በዓለም ዙሪያ በሚገኙት 66,207 ጉባኤዎች የተሰበሰቡት ሰዎች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከ10,000,000 በላይ ሲሆን 10,650,158 ሰዎች ተገኝተው ነበር። በብዙ የላቲን አሜሪካ፣ የአፍሪካና የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር የመንግሥት አስፋፊዎቹን ቁጥር ሦስት ወይም አራት ጊዜ የሚያጥፍ ነበር። አሁን ደግሞ በዚህ ዓመት ሚያዝያ 17 ቀን ዓርብ ዕለት ለሚውለው የመታሰቢያ በዓል እየተዘጋጀን ነው። በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ብዙዎቹ ለመጠመቅ የሚያበቃ መሻሻል ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ ተብሎ ተስፋ ይደረጋል። ጥምቀትን በተመለከተ በ1991 ቁጥራቸው ከሶስት መቶ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውሃ ጥምቀት አሳይተዋል። ይህም በ1990 ከተጠመቁት ሰዎች በ10 በመቶ ይበልጣል።
የአምላካዊ ነፃነት አፍቃሪዎች
16. ከ“ነፃነት አፍቃሪዎች” የወረዳ ስብሰባዎች ምን የሚያነቃቃ ሪፖርቶች እየመጡ ነው?
16 አንደኛው የ1991 አገልግሎት ዓመት የሚደነቅ ገጽታ አሁን በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ የተጠናቀቀውና በደቡባዊው ንፍቀ ክበብ ደግሞ እስከ 1992 የሚቀጥለው የ“ነፃነት አፍቃሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ነው። ሙሉው የስብሰባ ፕሮግራም አዲስ ባገኙት ነፃነት በመጠቀም ይሖዋን በማወደስ ላይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በሚኖሩባቸው በርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርቧል። እስከ ጥቅምት 1919 ድረስ በ54 አገሮች በተደረጉ 705 ስብሰባዎች ላይ 4,774,937 ሰዎች እንደተገኙ ሪፖርት ተደርጓል።
17, 18. (ሀ) የይሖዋ አምላኪዎች ያገኙትና የሚጠብቁት የትኛውን ነፃነት ነው? (ለ) አምላካዊ ነፃነት ከዓለማዊ ነፃነቶች የሚለየው እንዴት ነው?
17 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሎአቸው ነበር። (ዮሐንስ 8:32) ዛሬም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሕዝበ ክርስትና ጨቋኝ ደንቦችና ቀኖናዎች ነፃ አውጥቷቸዋል። እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በኩል ያደረገው ዝግጅት የሰው ልጅ “ከጥፋት ባርነት ነፃ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ” እንደሚያስችል ተምረዋል። (ሮሜ 8:19-22) ይሖዋ በፍቅሩ በሚመድበው ትክክለኛ ድንበር ውስጥ ተወስኖ በምድራዊ ገነት ለዘላለም መኖር እንዴት ዓይነት ትልቅ ነፃነት ይሆናል!—ኢሳይያስ 25:6-8፤ ሥራ 17:24-26
18 የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ ያገኙት ነፃነትና ወደፊት በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለማግኘት የሚጠባበቁት የበለጠ ነፃነት የሚገኙት ከአፍቃሪው አምላካችን ከይሖዋ ነው። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ወደፊት የሚገኙት ነፃነቶች በማንኛውም ፖለቲካዊም ሆነ አብዮታዊ ንቅናቄዎች ላይ የተመኩ አይደሉም። (ያዕቆብ 1:17) በዚህ ረገድ የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳይፈጠር በማሰብ በ1991 በአንዳንድ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የይሖዋ ምሥክሮች በስብሰባዎቻቸው ላይ የለጠፉአቸው አርማዎች “የነፃነት አፍቃሪዎች የወረዳ ስብሰባ” ብቻ ከማለት ይልቅ “የአምላካዊ ነፃነት አፍቃሪዎች የወረዳ ስብሰባ” የሚሉትን ቃላት ይዘው ነበር።
ለይሖዋ የጋለ ፍቅር ማሳደር
19. በጸሎት ከይሖዋ ጋር መቀራረብ የሚያበረታን እንዴት ነው?
19 ለይሖዋ ያለን ፍቅርና በእሱ ላይ ያለን እምነት በጸሎት ከእርሱ ጋር ተቀራርበን እንድንኖር ያደርገናል። ወንድሞቻችንን በብዙ ችግርና ስደት እንዲጸኑ የረዳቸው ይህ ከይሖዋ ጋር ያላቸው መቀራረብ ነው። (መዝሙር 25:14, 15) ኢየሱስ ከፍተኛ ፈተና ባጋጠመው ሰዓት ከአባቱ ጋር ያለውን የቅርብ ግንኙነት የጠበቀው በጸሎት አማካኝነት ነበር። (ሉቃስ 22:39-46) ይህ በጸሎት አማካኝነት የሚደረገው ከይሖዋ ጋር መገናኘት እስጢፋኖስንም በሰማዕታዊ ሞት ጣር ላይ እያለ አበርትቶታል። እንዲሞት በድንጋይ በሚወገርበት ጊዜ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ በመመልከት “እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።—ሥራ 7:56
20-22. አምላክ ጸሎቶችን እንደሚሰማ አንድ ተሞክሮ የሚገልጽልን እንዴት ነው?
20 የይሖዋ አምላኪዎች በተደጋጋሚ እንዳጋጠማቸው ይሖዋ ከፈቃዱ ጋር የሚስማሙ ጸሎቶችን ይሰማል። ለምሳሌ ያህል የምሥክሮቹ ሥራ በታገደበት አንድ የአፍሪቃ አገር በአውቶብስ ወደ ሰሜን የሚጓዝ አንድ ልዩ አቅኚ የመንግሥቱን ጽሑፎችና ኤንቨሎፖች በአንድ ትልቅ ጆንያ ይዞ ነበር። ጆንያውን የሚጭነው የአውቶብስ ረዳት “ጆንያው ውስጥ ያለው ምንድን ነው” ብሎ ጠየቀው። ወንድምም አፉ እንዳመጣለት በመናገር “ደብዳቤ ነው” ብሎ መለሰ።
21 በመንገድ ላይም አውቶብሱ አንድ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ሳያቆም በኃይል እየነዳ አለፈ። የትራፊክ ፖሊሶች ኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ ይሆናል ብለው በመጠርጠር ተከታትለው አስቆሙት። ሁሉም መንገደኞች እንዲወርዱና ጭነቶቹ በሙሉ እንዲፈተሹ አዘዙ። ይህ አስጊ ሁኔታ ነበር! ወንድም ሌሎቹ መንገደኞች ሲያጉረመርሙ ከእነሱ ለየት ብሎ ትንሽ ራቅ አለና በጉልበቱ ተንበርክኮ ወደ ይሖዋ ጸለየ ተመልሶ ወደ ሰዎቹ ሲመጣ የእያንዳንዱ መንገደኛ ጓዝ እየተከፈተ በጥንቃቄ ይበረበር ነበር። የወንድም ጆንያ ሊከፈት ሲል ወንድም ድምጹን ሳያሰማ ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ።
22 “ይህ የማን ጆንያ ነው? በውስጡስ ያለው ምንድነው?” ብሎ ፖሊሱ ጮኸ። ወንድም አፉን ከመክፈቱ በፊት የአውቶብሱ ረዳት “ከ——ፖስታ ቤት ወደ——ፖስታ ቤት የሚወሰድ ደብዳቤ ነው” ብሎ መለሰ። መኮንኑም “ደህና” አለና ኬሻውን አንስቶ ለረዳቱ ሰጠው። “ምንም አይነት ጉዳት እንዳያገኘው ጥሩ ቦታ አስቀምጠው” ብሎ አዘዘው። ልዩ አቅኚው እንደገና በጉልበቱ ተንበርክኮ ይሖዋን አመሰገነ።—መዝሙር 65:2፤ ምሳሌ 15:29
23. ይሖዋ ምን ለማድረግ የሚችል መሆኑን አሳይቷል? አንዳንዴስ ስደቱ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቀጥል የሚፈቅደው ለምንድነው?
23 ይሁን እንጂ ይህ ማለት የይሖዋ አምላኪዎች ምንም አይነት አስጊ ሁኔታ አይደርስባቸውም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ዘመኖችም ሆነ ዛሬ ይሖዋ ሕዝቡን ማዳን እንደሚችል ያሳየባቸው ሁኔታዎች አሉ። ይሁን እንጂ ፍጹም አቋም ጠባቂ ስለመሆን በተነሳው ክርክር መሠረት ረዘም ላለ ጊዜ ስደት እንዲኖር የሚፈቅድበት ጊዜ አለ። (ከማቴዎስ 26:39 ጋር አወዳድሩ) በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተግባራዊ ጥበብ ማሳየት ጥቅም ያለው ቢሆንም ሕዝቦቹን ሕዝቦቹ ስለሆኑ ብቻ ከአደጋ፣ ከእርስ በርስ ግጭት፣ ወይም ከወንጀል አይጠብቃቸውም። (ምሳሌ 22:3፤ መክብብ 9:11) ይሁን እንጂ ከፈታኝ ሁኔታዎች ቢያድነንም ባያድነንም የታማኝነታችንን ዋጋ አስፈላጊ ከሆነም በትንሣኤ አማካኝነት እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
24. ይሖዋ ምን ፍቅራዊ ስጦታዎችን አቅርቧል? እኛስ ለዚህ ፍቅሩ ምላሽ የምንሰጠው እንዴት ነው?
24 የይሖዋ ፍቅራዊ ስጦታዎች በጣም አስደናቂ ናቸው። ይህችን ምድርና በላይዋ ያለውን ነገር ሁሉ ለሰው ልጅ መስጠቱ ጐልቶ የሚታይ የፍቅሩ መግለጫ ነው። (መዝሙር 104:1, 13-16፤ 115:16) የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለመዋጀት ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በርኅራኄ መስጠቱ ካደረገልን ስጦታዎች ሁሉ የበለጠው ፍቅራዊ ስጦታ ነው። “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው። እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተሠሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደወደድነው አይደለም።” (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ለዚህ ፍቅር ምላሽ በመስጠትም “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ ግዛትም ቢሆን ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን ልዩ ፍጥረትም ቢሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል” እርግጠኛ እንሁን።—ሮሜ 8:38, 39
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ ታማኝ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ለይሖዋ ፍቅራችንን ማሳየት ያለብን በምን የሥራ ዘርፎች ነው?
◻ ይበልጥ ትኩረትህን ወይም ስሜትህን የሳበው የትኛው የአገልግሎት ዓመቱ ገጽታ ነው?
◻ ለይሖዋ ፍቅራዊ ስጦታዎች ያለንን አድናቆት እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብዙ አቅኚዎች የኖሩት ለምንድን ነው?
ጃፓናውያን ለ2,600 ዓመታት ንጉሠ ነገሥታቸውን በጋለ ስሜት ሲያመልኩ ቆይተዋል ይባላል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች ብቻ ከ3,000,000 በላይ የሆኑ ጃፓናውያን በውጊያው ላይ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። እንዲህ ያደረጉበትም ምክንያት አምላክ ለሆነው ንጉሠ ነገሥታቸው ከመሞት የበለጠ ክብር የለም ብለው ስላሰቡ ነው። ይሁን እንጂ የቡዲስትና የሽንቶ ሃይማኖቶች ጦረኝነት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተንኮታኩቶ ወደቀ። ከዚያም ወዲህ ንጉሠ ነገሥቱ አምላክ አለመሆናቸውን በይፋ አሳወቁ። አሁን ይህንን ሃይማኖታዊ ባዶነት ምን ሊሞላው ይችላል? ከይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያንና በኋላም የጃፓን ተወላጆች ከሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያደረጉት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንዲያገኙና ሕይወታቸውን ለእሱ እንዲሰዉ ብዙ ሰዎችን ረድቷቸዋል። ይህ ሕይወትን መወሰን ለእነዚህ ጃፓናውያን ከፍ ያለ ትርጉም ነበረው። ከዚህ በፊት ንጉሠ ነገሥታቸውን አምላክ ነው በማለት ሕይወታቸውን ይሰዉ ከነበረ አሁን ጉልበታቸውን ሕያውን አምላክና የጽንፈ ዓለም ፈጣሪ የሆነውን ልዑሉን ጌታ ይሖዋን አቅኚዎች ሆነው በማገልገል ለማምለክ በከፍተኛ ቅንዓት ይጠቀሙበታል።
[ከገጽ 10-13 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]
የ1991 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት
(መጽሔቱን ተመልከት)
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላካዊ ነፃነት አፍቃሪዎች—የይሖዋ አምላኪዎች በፕራግ ውስጥ ከነሐሴ 9-11, 1991 ትልቅ ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት