የአንባብያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ አጥማቂው ዮሐንስ ከእርሱ በፊት እንደሚሞት አስቀድሞ ያውቅ እንደነበር ከማቴዎስ 11:11 መገንዘብ እንችላለንን?
አዎን፣ ዮሐንስ ቅቡዕ ክርስቲያን መሆን እስከሚችልበት ጊዜ ድረስ በሕይወት እንደማይቆይ ኢየሱስ አውቆ ነበር። ምክንያቱም ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል” በማለት ተናግሮአል።—ማቴዎስ 11:11
መልአኩ ገብርኤል ስለ ዮሐንስ መወለድ ሲያበስር “የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ . . . በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል” በማለት ተንብዮአል። ዮሐንስ ሕዝቡን ለይሖዋ መሲሕ የሚያዘጋጅ መንገድ ጠራጊ ነበር። በዚህ መለኮታዊ ማስታወቂያ ላይ ግን ዮሐንስ ራሱ የመጪው መሲሕ ደቀመዝሙር እንደሚሆን የሚያመለክት ፍንጭ የለም። የዮሐንስ አባት ዘካርያስ በተናገረው ትንቢታዊ ቃል ውስጥም ቢሆን ዮሐንስ የመጪው መሲሕ ደቀመዝሙር እንደሚሆን የሚገልጽ ነገር አልተገለጸም።—ሉቃስ 1:17, 67-79
በመሆኑም ዮሐንስ ኢየሱስን ካጠመቀው በኋላም ሕዝቡን እንዲያዘጋጅ በተሰጠው ምድብ ሥራ ላይ በመጽናት መስበኩንና ማጥመቁን ቀጥሎበታል። ዮሐንስ በተአምራዊ መንገድ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ አውቆ ነበር። እሱ ራሱ ግን መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበልና ቅቡዕ ክርስቲያን እንደሚሆን አልተናገረም። (ማቴዎስ 3:11) ዮሐንስ ኢየሱስ እየበዛ ሲሄድ እሱ ግን እያነሰ እንደሚሄድ ተገንዝቦአል።—ዮሐንስ 3:22-30
ኢየሱስ በማቴዎስ 11:11 ላይ የምናነበውን በተናገረ ጊዜ ዮሐንስ ታሥሮ ነበር። ኢየሱስ ይህ የታሠረ ነቢይ ወደፊት በሰማይ ንጉሥና ካህን ሆኖ ከሚያገለግል ከሁሉ ታናሽ ከሆነ ደቀመዝሙር እንኳ ያነሰ እንደሚሆን በቅድሚያ አስታውቆአል። ኢየሱስ ዮሐንስ ወዲያው እንደሚሞትና ለሰማያዊ ሕይወት “አዲሱ” መንገድ ከመከፈቱ በፊት ከምድራዊው መድረክ እንደሚያልፍ ያወቀ ይመስላል። (ዕብራውያን 10:19, 20) ይህም ማለት ዮሐንስ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ መቀባት እስከጀመሩበት በ33 እዘአ እስከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ድረስ አይቆይም ማለት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በማቴዎስ 11:11 ላይ የተናገረው ቃል ዮሐንስ ወደ ሰማይ የማይሄድ መሆኑን ኢየሱስ እንደሚያውቅ ፍንጭ እንደሚሰጥ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።