የእምነት ፈውስ የአምላክ ድጋፍ አለውን?
“ዛሬ እንግዳ ነገር ተመልክተናል!” አዎ፣ ተመልካቾቹ ባዩት ነገር በጣም ተደነቁ። አንድ ሽባ የነበረ ሰው ሲፈወስ ተመለከቱ። ሰውዬውን የፈወሰው ሰው፦ “ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። የተፈወሰውም ሰው እንደተባለው አደረገ! ከዚያ በኋላ ሽባ አልሆነም። በዚያ የተገኙት ሁሉ አምላክን ማመስገን መጀመራቸው አያስደንቅም! (ሉቃስ 5:18-26) ይህ ከ2,000 ዓመታት በፊት በኢየሱስ ክርስቶስ የተከናወነ ፈውስ የአምላክ ድጋፍ እንደነበረው በጣም ግልጽ ነው።
ዛሬስ? በሕክምና ከበሽታቸው ለመዳን ያልቻሉ ሰዎች በተአምር ሊፈወሱ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላልን? ኢየሱስ በሽተኞችን በተአምር ፈውሶአል። የዘመናችን የእምነት ፈዋሾችም ኢየሱስ እንዳደረገው እያደረግን ነው ይላሉ። ይህን አባባላቸውን እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
የእምነት ፈውስ “በአምላክ ላይ በማመንና በመጸለይ በሽታን የማዳን ዘዴ ነው” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚከተለው በማለት ያረጋግጣል፦ “በክርስትና ውስጥ የእምነት ፈውስ ታሪክ የጀመረው ኢየሱስና ሐዋርያቱ በፈጸሙት አስደናቂ የግል አገልግሎት ነው።” አዎ፣ ኢየሱስ በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ ሰዎችን ፈውሶአል። የዘመናችን የእምነት ፈዋሾች ኢየሱስ የፈጸማቸውን ዓይነት ተአምራት ይፈጽማሉን?
ለመፈወስ እምነት የግድ ያስፈልጋልን?
የብላክስ ባይብል ዲክሽነሪ “ተአምራዊ ፈውስ ለማግኘት በቅድሚያ [ማመን] አስፈላጊ መሆኑን ኢየሱስ ገልጾአል” ይላል። ይሁን እንጂ ይህ አባባሉ እውነት ነውን? ኢየሱስ አንድን በሽተኛ ከመፈወሱ በፊት በእርሱ እንዲያምን ጠይቋልን? መልሱ አልጠየቀም ነው። እምነት እንዲኖረው የሚፈለግበት ፈዋሹ ነው እንጂ የሚፈወሰው በሽተኛ አልነበረም። በአንድ ወቅት የኢየሱስ ደቀመዛሙርት አንድ የሚጥል በሽታ ያለበትን ልጅ መፈወስ አቃታቸው። ኢየሱስ ልጁን ከፈወሰው በኋላ ደቀመዛሙርቱ ለምን ሊፈውሱት እንዳልቻሉ ነገራቸው። “ኢየሱስም ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው” አላቸው።—ማቴዎስ 17:14-20
ማቴዎስ 8:16, 17 ኢየሱስ “የታመሙትን ሁሉ” እንደ ፈወሰ ይናገራል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች ወደ ኢየሱስ የመጡት መጠነኛ እምነት ስለ ነበራቸው ነው። (ማቴዎስ 8:13፤ 9:22, 29) አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸው እንዲፈውሳቸው መጠየቅ ነበረባቸው። ይሁን እንጂ ተአምራቱ እንዲደረግላቸው የግድ እምነት እንዳላቸው ማረጋገጥ አላስፈለጋቸውም ነበር። አንድ ጊዜ ኢየሱስ እሱ ማን እንደሆነ እንኳን የማያውቅ ሽባ ሰው ፈውሶአል። (ዮሐንስ 5:5-9, 13) ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ጆሮው የተቆረጠበትን የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ሊይዙት ከመጡት ጠላቶቹ አንዱ ቢሆንም ፈውሶታል። (ሉቃስ 22:50, 51) እንዲያውም ኢየሱስ የሞተን ሰው እንኳን ያስነሳበት ጊዜ ነበር።—ሉቃስ 8:54, 55፤ ዮሐንስ 11:43, 44
ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉትን ተአምራት ሊፈጽም የቻለው እንዴት ነበር? በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ይተማመን ስለነበረ ነው። ለፈውሱ ምክንያት የሆነው ይህ ኃይል ነበር እንጂ የበሽተኛው ግለሰብ እምነት አልነበረም። በወንጌሎች ውስጥ የተመዘገቡትን ታሪኮች ብታነቡ ኢየሱስ ሰዎችን የፈወሰው ብዙ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ እንዳልነበረ ትገነዘባላችሁ። የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ወይም ስሜታቸውን ለማነሳሳት ያደረገው ነገር አልነበረም። በተጨማሪም ኢየሱስ ለመፈወስ ያቃተው ምንም ዓይነት በሽታ አልነበረም። ሁል ጊዜ በተሳካ ሁኔታ ይፈውስ ነበር፣ ዋጋም አስከፍሎአቸው አያውቅም።—ማቴዎስ 15:30, 31
በዘመናችን ይደረጋሉ የሚባሉት ፈውሶች ኢየሱስ ካደረጋቸው ፈውሶች ጋር ይመሳሰላሉን?
በሽታ በጣም አስከፊ ችግር ነው። ስንታመም ቶሎ ለመዳን እንፈልጋለን። “ሰዎች፣ በተለይም ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች በሕክምና ባለሞያዎች ዘንድ እንደ ሰብአዊ ፍጡር ሳይሆን እንደ ዕቃ በሚታዩበት” አካባቢ ብንኖርስ? አንድ ዶክተር በአንድ የላቲን አሜሪካ አገር የታዘቡት ይህን የመሰለ ሁኔታ ነበር። ከላይ የተገለጸው ዓይነት ሁኔታ በሚፈጸምበትና ‘በሞያቸው የመሥራት ብቃት ያላቸው የሕክምና ዶክተሮች 40 ከመቶ’ ብቻ በሆኑበት ተመሳሳይ አካባቢ ብንኖርስ?
ብዙዎች የሚሄዱበት ስለሚጠፋቸው የእምነት ፈዋሾችን ለመሞከር ይገደዳሉ። ይሁን እንጂ የእምነት ፈዋሾች አደረጉአቸው ስለሚባሉት ተአምራት ብዙ ክርክር ተነስቶአል። ለምሳሌ ያህል በብራዚል ሳኦ ፓውሎ 70,000 የሚገመቱ ሰዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ሁለት ፈዋሾች የማየት ችሎታችሁ ይመለስላችኋል ሲሉ የሰጡትን ተስፋ በማመን ከዓይናቸው እያወለቁ የጣሉላቸውን በመቶ የሚቆጠሩ መነፅሮች ረጋግጠው ሰብረዋል። ከፈዋሾቹ አንዱ ለቀረበለት ቃለ መጠይቅ ሲመልስ እንደሚከተለው በማለት አምኖአል፦ “እንዲፈወሱ የምንጸልይላቸው በሽተኞች ሁሉ ይፈወሳሉ ብዬ መናገር አልችልም። መፈወስ አለመፈወሳቸው ባላቸው እምነት ላይ የተመካ ነው። ግለሰቡ የሚያምን ከሆነ ይፈወሳል።” ፈዋሹ ማንኛውም ሰው የማይፈወሰው በራሱ የእምነት ጉድለት ምክንያት እንደሆነ ተናግሮአል። ይሁን እንጂ ቀደም ብለን እንዳየነው ፈውስ የማድረግ ሙከራ የማይሳካው እፈውሳለሁ በሚለው ሰው እምነት ማነስ ምክንያት ነው ብሎ ኢየሱስ መናገሩን አስታውሱ!
ሌላው ፈዋሽ ደግሞ የካንሰርና የሽባነት በሽታ እፈውሳለሁ ብሎ ነበር። ታዲያ ምን ሆነ? የቬዣ መጽሔት እንደዘገበው “የሰጠውን ተስፋ ሊፈጽም አልቻለም።” ፈዋሹ ምን እንዳደረገ አድምጡ። “[የእምነት ፈዋሹ] ሁለት ሰዓት ለሚያህል ጊዜ በተመልካቾቹ ፊት ሲሰብክ፣ ሲጸልይ፣ ሲጮህ፣ ሲዘምርና በአማኞች ላይ ያደሩት አጋንንት እንዲወጡ ለማድረግ በዱላ ሲማታ ቆየ። በመጨረሻም ክራቫቱንና መሐረቡን በድርጊቱ ወደተመሰጡት ተመልካቾች ወረወረና የገንዘብ እርዳታ እንዲሰጡት ሙዳዬ ምፅዋት ለሕዝቡ ማዞር ጀመረ።” ኢየሱስና ሐዋርያቱ ለፈጸሙአቸው ተአምራታዊ ፈውሶች በፍጹም ገንዘብ ጠይቀው አያውቁም። ይህን የመሰለ ትያትርም ፈጽመው አያውቁም።
ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የዘመናችን የእምነት ፈዋሾች ኢየሱስ የፈጸመውን ዓይነት ነገር እንደማይፈጽሙ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በአምላክ ድጋፍ የሚፈጸም ተአምራታዊ ፈውስ ይኖራልን? እኛም ሆንን የምንወዳቸው ሰዎች በምንታመምበት ጊዜ እምነታችን ሊረዳን የሚችልበት መንገድ ይኖራል?