እምነት አንድን የታመመ ሰው ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ተአምራታዊ ፈውሶች አምላክ ስለ ደህንነታችን እንደሚያስብና እኛንም ለመፈወስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ያረጋግጡልናል። እነዚያ ተአምራታዊ ፈውሶች አምላክን ስለ አስከበሩና ብዙ ደስታም ስላመጡ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የመፈወስ ስጦታ በአሁኑ ጊዜ ይሠራልን? ብሎ መጠየቅ ምክንያታዊ ነው።
ለዚህ ጥያቄ መልሱ አይደለም ነው። እንደዚህ የተባለበት ምክንያት አንዳንዶችን ሊያስገርም ይችል ይሆናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸሙ ተአምራታዊ ፈውሶች ዓላማቸውን አከናውነዋል። ዘ ኢላስተሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ በትክክል እንደገለጸው “ተአምራዊ ፈውስ ይደረግ የነበረው ለሃይማኖታዊ ምክንያት እንጂ ለሕክምና አልነበረም።” እነዚህ ተአምራት ካከናወኗቸው ሃይማኖታዊ ዓላማዎች አንዳንዶቹ ምን ነበሩ?
አንደኛ ነገር፣ ኢየሱስ ያደረጋቸው የፈውስ ተአምራት እርሱ መሲሕ መሆኑን አሳውቀው ነበር። እሱ ከሞተም በኋላ ቢሆን የአምላክ በረከት በክርስቲያን ጉባኤ ላይ እንዳለ አረጋግጠዋል። (ማቴዎስ 11:2-6፤ ዕብራውያን 2:3, 4) በተጨማሪም አምላክ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሰውን ዘር ለመፈወስ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም አረጋግጠዋል። “በዚያም የሚቀመጥ፦ ታምሜአለሁ አይልም፣ በእርሷም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል” የሚባልበት ጊዜ እንደሚመጣ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። (ኢሳይያስ 33:24) እነዚህ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓላማዎች ከተፈጸሙ በኋላ የተአምራት አስፈላጊነት ቆሞአል።
የመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ተአምራታዊ ፈውስ ያላገኙባቸው በሽታዎች ነበሩአቸው። በዚህም ምክንያት በተለያዩ አካላዊ ሕመሞች ይሰቃዩ እንደ ነበር ማስተዋል ይገባል። ይህም ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ በተአምር ይፈውሱ የነበረው አስፈላጊ እውነቶችን ለማስተማር እንጂ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንዳልነበረ የሚያረጋግጥልን ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ስለ ነበረበት ሕመም ማድረግ ስለሚገባው ሕክምና በመከረው ጊዜ ወይን ጥሩ መድኃኒት እንደሆነ ነገረው እንጂ በእምነት እንዲፈወስ አልነገረውም። ሰዎችን በተአምር ይፈውስ የነበረው ጳውሎስ ‘ከሚጎስመው የሥጋ መውጊያ’ በተአምር አልተፈወሰም።—2 ቆሮንቶስ 12:7፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23
ሐዋርያት ሞተው ሲያልቁ የመፈወስ ስጦታም አቆመ። ጳውሎስም እንዲህ እንደሚሆን አስቀድሞ አመልክቶአል። የክርስቲያን ጉባኤን ከአንድ ሕፃን ጋር በማመሳሰል እንደሚከተለው ብሏል፦ “ሕፃን በነበርሁ ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር ነበር፤ እንደ ሕፃን አስብ ነበር፤ እንደ ሕፃን እመራመር ነበር፤ ሙሉ ሰው በሆንሁ ጊዜ ግን የሕፃንነቴን ጠባይ ተውሁ።” በምሳሌው ሊያስገነዝብ የፈለገው ሐሳብ ተአምራዊ የመንፈስ ስጦታዎች የክርስቲያን ጉባኤ ገና ሕፃን መሆኑን ከሚያሳውቁት ነገሮች አንዱ መሆኑን ነበር። የሕፃንነት ጠባዮች ነበሩ። ከዚህም በኋላ እንዲህ ሲል ገለጸ፦ ‘እነሱ [ተአምራታዊ ስጦታዎች]ይቀራሉ።’—1 ቆሮንቶስ 13:8-11(የ1980 አማርኛ ትርጉም)
በምንታመምበት ጊዜ እምነት ሊረዳን ይችላልን?
ምንም እንኳን በእምነት ፈውስ ባናምንም በምንታመምበት ጊዜ አምላክ እንዲረዳን መጸለይ ተገቢ ነው። ሌሎችም ስለኛ ቢጸልዩ ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም ጸሎታችን ምክንያታዊና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። (1 ዮሐንስ 5:14, 15) መጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ ላይ የእምነት ፈውስ እንዲሰጠን እንድንጸልይ አያዘንም።a ከዚህ ይልቅ በሕመም ምክንያት ችግር ሲደርስብን የይሖዋን ፍቅራዊ እርዳታ ለማግኘት እንጸልያለን።
መጽሐፍ ቅዱስ “[ይሖዋ (አዓት)] ራሱ በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል” በማለት የእምነት ሰዎች በሚታመሙበት ጊዜ ምን ብለው መጸለይ እንደሚችሉ ያመለክታል። (መዝሙር 41:3) በተጨማሪም የስሜት ቀውስ ደርሶባቸው የታመሙ ሰዎች የሚያገኙት እርዳታ አለ። መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ጽፎአል። “ለመውደቅ ተቃርቤአለሁ ብዬ ነበር። [ይሖዋ (አዓት)] ሆይ ዘላለማዊ ፍቅርህ ግን ደግፎ አቆመኝ። አሳብና ጭንቀት በያዘኝ ጊዜ አንተ ታጽናናኛለህ፣ ደስም ታሰኘኛለህ።”—መዝሙር 94:18, 19 (የ1980 የአማርኛ ትርጉም)፤ በተጨማሪም 63:6-8ን ተመልከት።
በተጨማሪም ለጤንነታችን ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስም ይህን በሚመለከት ምክር ይሰጠናል። የዕፅ ሱሰኛ በመሆን፣ በማጨስ፣ ያለልክ በመጠጣት ወይም ከመጠን በላይ በመብላት በሽታ ላይ ወድቀን ተስፋ በመቁረጥ የእምነት ፈውስ ከማግኘት ይልቅ መጀመሪያውኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች መመላለስ በጣም ጥሩ ይሆናል። በሽታ ላይ ከወደቁ በኋላ ተአምራዊ ፈውስ ለማግኘት መጸለይ የተመጣጠነ ምግብ በመብላት፣ ወይም የሚቻል ሲሆን ጥሩ ሕክምና በማድረግ በሽታን ለመከላከል ለሚወሰደው የጥበብ አኗኗር ምትክ አይሆንም።
በተጨማሪም የአምላክ ቃል አካላዊ ጤንነታችንን ሊጠቅም የሚችለውን ጤናማ የአዕምሮ ዝንባሌ እንድንኮተኩት ያበረታታናል። የምሳሌ መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት ይመክራል፦ “ትሁት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፤ ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል።” “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች።” (ምሳሌ 14:30፤ 17:22) መንፈስ ቅዱስ ሰላምና ደስታ በውስጣችን እንዲሰፍን እንዲያደርግ መጸለይም በአካላዊ ጤንነታችን ላይ ጠቃሚ ውጤት እንደሚኖረው የታወቀ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ስለ እምነት ፈውስስ ምን ሊባል ይቻላል?
አንድ ሰው ሁኔታዎቹ የፈቀዱለትን ያህል ስለ ጤንነቱ ተጠንቅቆ ቢኖርም ሊታመም ይችላል። ታዲያ ምን ያድርግ? ከበሽታው ለመፈወስ ወደ እምነት ፈዋሾች ቢሄድ ጉዳት አለውን? አዎ፣ ጉዳት አለው። የዘመናችን የእምነት ፈዋሾች አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብ ያስከፍላሉ። የሕክምና እርዳታ ሊያስገኝልን የሚችለውን ገንዘብ ለእምነት ፈዋሽ መስጠት ትልቅ ኪሣራ ሊያስከትልብን ይችላል። በተጨማሪም ሰዎችን አለአግባብ በማታለል ጥቅም ለማግኘት ለሚፈልጉ ግለሰቦች ገንዘባችንን ለምን እንሰጣለን?
አንዳንዶች “ወደ እምነት ፈዋሾች ከሚሄዱት መካከል የሚፈወሱት ጥቂቶቹ ብቻ ቢሆኑም እንኳን የእምነት ፈውስ ጥቅም አለው” ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ የእምነት ፈዋሾች ማንንም ሰው ዘላቂነት ባለው መንገድ መፈወስ መቻላቸው ሊያከራክር የሚችል ጉዳይ ነው። ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፦ “በእምነት ፈውስ ላይ የተደረጉ ሥርዓት ያላቸው ጥናቶች በጣም ጥቂት ናቸው” ብሎአል።
ጥቂት ሰዎች ፈውስ ያገኙ ቢመስልም ይህ ብቻውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑን አያረጋግጥም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፣ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 7:22, 23) በተጨማሪም ኢየሱስ አንዳንዶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ባይኖራቸውም የተለያዩ ምልክቶች በማሳየት የሰውን ትኩረት ወደራሳቸው እንደሚስቡ ሲያስጠነቅቅ፦ “ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፣ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችና ድንቅ ያሳያሉ” ብሏል። (ማቴዎስ 24:24) በእርግጥም እነዚህ ቃላት ተአምራታዊ ፈውስ እናደርጋለን እያሉ ያለማቋረጥ ገንዘብ ለሚጠይቁትና ልዩ ዓይነት ትርዒት በሚያሳዩት የዘመናችን የእምነት ፈዋሾች ላይ ይሠራሉ።
እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የኢየሱስን ፈለግ አይከተሉም። ታዲያ የሚከተሉት የማንን ፈለግ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።” (2 ቆሮንቶስ 11:14, 15) ፈዋሾቹ እንደሚናገሩት በተአምር ለመፈወስ ካልቻሉ ‘ዓለምን ሁሉ የሚያስተውን’ የሰይጣንን መንገድ የሚከተሉ አሳሳቾች መሆናቸው ነው። (ራእይ 12:9) ሆኖም ጥቂት ሰዎችን ለመፈወስ ቢችሉስ? ተአምራት የሚያደርጉት በሰይጣንና በአጋንንቱ ኃይል መሆን አለበት ብለን ማሰብ አይገባንምን? አዎ፣ በሰይጣንና በአጋንንቱ ኃይል መሆን አለበት።
እውነተኛ ፈውስ የሚገኝበት ጊዜ
ኢየሱስ በተአምር ይፈውስ የነበረው በአምላክ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ነው። እነዚህም ተአምራት አምላክ የሰውን ልጅ የጤንነት ችግሮች ለአንዴና ለዘላለም የመፍታት ዓላማ ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል። (ራእይ 22:2) በሽታዎችን በመፈወስ ብቻ ሳይወሰን ሞትንም ጭምር ያስወግዳል። ዮሐንስ ኢየሱስ የመጣው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” ነው በማለት ገልጿል። (ዮሐንስ 3:16) ይህም በጣም ግሩም የሆነ ፈውስ ይሆናል! ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ፈውሶች በጣም ከፍተኛ ስፋት ባለው መጠን በድጋሚ ይፈጽማል። የሞቱትን ሰዎች እንኳ ያስነሳል! (ዮሐንስ 5:28, 29) ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ነዋ! ይህ አዲስ ዓለም በጣም ቅርብ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ይህ የዚህ ሥርዓት ክፋት ለዘላለም ተጠራርጎ ከተወገደ በኋላ የሚመጣው አዲስ ዓለም ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ላላቸው የሰው ዘሮች ሁሉ እውነተኛ በረከት ያስገኝላቸዋል። ከሥቃይ ነፃ የሆነ ዓለም ይሆናል። “[አምላክ] እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት፣ ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።” (ራእይ 21:4) ዛሬ በዙሪያችን ከምናየው ዓለም ምን ያህል የተለየ ዓለም ይሆናል!
ስለዚህ በምትታመምበት ጊዜ አምላክ እንዲያበረታህ ጸልይ። በሽተኛም ሆንክ ጤናማ ከበሽታ ነፃ የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት እንዴት ሊገኝ እንደሚችል ተማር። ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሐሳቦች በማጥናት በዚህ የታመነ የአምላክ ተስፋ ላይ ያለህን እምነት አሳድግ። ይህን በሚመለከት አምላክ ያወጣው ዓላማ በራሱ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዴት ሊፈጸም እንደተቃረበ ተማር። “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ [ይሖዋ (አዓት)] ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” በማለት የአምላክ ቃል ስለሚያረጋግጥልን ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አይኑርህ።—ኢሳይያስ 25:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶች በያዕቆብ 5:14, 15 ላይ ያሉት ቃላት ከእምነት ፈውስ ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ከጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ያዕቆብ የሚናገረው ስለ መንፈሳዊ ሕመም መሆኑን ያሳያሉ። (ያዕቆብ 5:15, 16, 19, 20) ያዕቆብ በእምነት የደከሙ ግለሰቦች ሽማግሌዎች እንዲረዷቸው መጠየቅ እንዳለባቸው ይመክራል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ተአምራታዊ ፈውሶች ዓላማቸውን አከናውነዋል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ወደ ፊት ተአምራታዊ ፈውሶችን በስፋት ይደግማቸዋል