ከይሖዋ ጋር ያለህ ተራ ትውውቅ ነው ወይስ ወዳጅነት?
“ዮሐንስ፣ ከወዳጄ ጋር ላስተዋውቅህ? እ . . . ይቅርታ ስምህ ማን ነበር?”
ይህን የመሰለ ቅጥ ያጣ ንግግር ሰምተህ ታውቃለህን? ይህ ንግግር አንዳንድ ሰዎች “ወዳጅ” የሚለውን ቃል እንዴት በተሳሳተ መንገድ እንደሚጠቀሙበት ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ወዳጅ የሚሉት በዓይን ብቻ የሚያውቁትን ሰው ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በዓይን ብቻ የሚታወቅንም ሰው ላያመለክት ይችላል። ከመንገድ ማዶ የሚኖረውን አቶ በቀለን ማወቅና የአቶ በቀለ ወዳጅ መሆን ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
አንድ መዝገበ ቃላት “ትውውቅ” ብለን የተረጎምነውን አክዌንታንስ የተባለ የእንግሊዝኛ ቃል ሲፈታ “ጠንካራ የሆነ ዝምድና ወይም መቀራረብ ሳይኖር በአንድ ማህበራዊ ሁኔታ የተገናኙት ሰው” ይላል። “ከወዳጅ ያነሰ ቅርበት፣ መጠጋጋትና መነፋፈቅ መኖሩን” መኖሩን የሚያመለክት ቃል ነው።
በዓይን ብቻ በምናውቀው ሰው ላይ ስለሚደርሱት ነገሮች ግድየለሾች ስንሆን ወዳጆቻችን ስለሚያጋጥሙአቸው ነገሮች ግን አጥብቀን የምናስበው ይህ ግላዊ የሆነ ዝምድናና መተሳሰር ስላለን ነው። በወዳጆቻችን ደስታም ሆነ ሐዘን እንካፈላለን። ልባችንም በደስታቸውም ሆነ በሐዘናቸው ይነካል። እርግጥ፣ በስሜታችን ብቻ ተገፋፍተን በግል ጉዳዮቻቸው ውስጥ ጣልቃ እንዳንገባ መጠንቀቅ ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 4:15
አብዛኛውን ጊዜ ወዳጆቻችንን ለማስደሰት የምንሞክረውም ጠንካራ መተሳሰር ስላለን ነው። በዓይን ብቻ የምናውቀው ሰው ፀባያችን የማይጥመው ወይም ከሥርዓት ውጭ ሆኖ ቢያገኘው የእርሱ በፀባያችን መከፋት ፀባያችንን እንድንለውጥ አይገፋፋንም። ወዳጃችን የሆነ ሰው ስሜት ግን በአለባበሳችን፣ በፀባያችንም ሆነ በዝንባሌያችን ላይ ኃይለኛ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
ወዳጅነት በእምነት፣ በፍቅር፣ በአክብሮትና በታማኝነት ረገድ ከተራ ትውውቅ ይበልጥ ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት ይጠይቃል። ምንም ዓይነት ኃላፊነት የማያስከትል ወዳጅነት የሚፈልግ ሰው የሚፈልገው ወዳጅነት ሳይሆን ተራ የሆነ ትውውቅ ነው። የቅርብ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች ጠንካራ የሆነው ዝምድናቸው የሚያስከትለውን ኃላፊነት በደስታ ይፈጽማሉ። ይህም ወዳጅነታቸውን ለማሳየት የሚያስችላቸው ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ይገነዘባሉ።
ከአምላክ ጋር ወዳጅ መሆን
ይሖዋ ፈጣሪ በመሆኑ የሰው ልጆች ሰማያዊ አባት ነው። ስለሆነም እርሱን መውደድ፣ ማክበርና መታዘዝ ይገባናል። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች እንዲወዱት፣ እንዲያከብሩትና እንዲታዘዙት የሚፈልገው ግዴታቸው ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር ባላቸው ጠንካራ ዝምድና ተገፋፍተው እንዲሆን ነው። (ማቴዎስ 22:37) በተጨማሪም እንደ ወዳጃቸው አድርገው እንዲወዱት ይፈልጋል።(መዝሙር 18:1) ‘አስቀድሞ የወደደን እርሱ ስለሆነ’ የዚህን ወዳጅነት መሠረት የጣለው እርሱ ራሱ ነው።—1 ዮሐንስ 4:19
የመጀመሪያ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን ከይሖዋ ጋር ትውውቅ ነበራቸው። ጥያቄው ግን “ወዳጆቹ እንዲሆኑ ያቀረበላቸውን ግብዣ ይቀበሉ ይሆንን?” የሚለው ነው። ሳይቀበሉ መቅረታቸው በጣም ያሳዝናል። በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ከአምላክ ተለይተውና ነፃ ሆነው ለመኖር መፈለጋቸው ከእርሱ ጋር ጠንካራ የሆነ ግላዊ ዝምድና ለመመስረት ፍላጎት እንዳልነበራቸው አሳይቷል። አምላክ ያቀረበላቸው የወዳጅነት ግብዣ የሚያመጣውን በረከት ለመቀበል ፈቃደኞች ቢሆኑም ይህ ወዳጅነት የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለማሟላት ግን ፈቃደኞች አልሆኑም። አስደሳች የሆነው ገነታዊ ቤታቸው የሚሰጣቸውን ደስታ፣ ምቾትና ደህንነት እየፈለጉ ኪራዩን ለመክፈል ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ያህል ነው።
ሁላችንም ደረጃው ይለያይ እንጂ ይህንን የምሥጋና ቢስነትና ነፃ የመሆን መንፈስ ወርሰናል። (ዘፍጥረት 8:21) ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ወጣቶች የተፈጥሮ ፍላጎታቸው በሆነው ነፃ የመሆን መንፈስ ወላጆቻቸውን እንዳያደንቁና እንዳያመሰግኑ አድርጎአቸዋል። ይህ ደግሞ በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ በወላጆቻቸውና በእነርሱ መካከል ሊኖር የሚገባውን ውድ ወዳጅነት አበላሽቶባቸዋል። ይህ ራሱ በጣም የሚያሳዝን ነገር ቢሆንም ከሰማያዊ አባታችን ጋር ያለን ወዳጅነት ቢበላሽ ከዚህ የከፋ አሳዛኝ ውጤት ይኖረዋል። እንዲያውም ሞት የሚያስከትል ሊሆን ይችላል!
ከአምላክ ጋር ለመወዳጀት የሚያስፈልጉ ብቃቶች
መተማመን ከሌለ ከሰውም ጋር ይሁን ከአምላክ ጋር የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ዝምድና ዘላቂነት ሊኖረው አይችልም። የእስራኤላውያን አባት የነበረው አብርሃም ይህን ተረድቶ ነበር። በተደጋጋሚ በአምላክ ላይ የሚታመን መሆኑን ያረጋገጠውም በዚህ ምክንያት ነው። በዘፍጥረት 12:1-5 እና 22:1-18 ላይ የሚገኘውን ታሪክ አንብብና አብርሃም በይሖዋ ላይ የሚታመን መሆኑን ያሳየባቸውን ሁለት መንገዶች ልብ በል። አዎ፣ “አብርሃምም [ይሖዋን (አዓት)] አመነ፣ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት።” “የ[ይሖዋ (አዓት)] ወዳጅ” ተብሎ ሊጠራ የቻለውም በዚህ ምክንያት ነው።—ያዕቆብ 2:23
ከአምላክ ጋር ለመወዳጀት አስፈላጊ የሆነው ሌላው ብቃት ደግሞ ይህ ወዳጅነት የሚያስከትላቸውን ግዴታዎች ማሟላት ነው። ከይሖዋ ጋር ስንወዳደር በጣም ያነስን በመሆናችን ምክንያት እነዚህ ግዴታዎች የሰዎች ወዳጅነት ከሚጠይቃቸው ግዴታዎች የበለጡ መሆናቸው ምክንያታዊ ነው። እነዚህ ግዴታዎች ለሰብአዊ ወዳጆቻችን እንደምናደርገው በአንዳንድ ነገሮች ብቻ እርሱን ለማስደሰት ከመፈለግ የበለጡ ነገሮችን ያጠቃልላሉ። በሁሉም ነገር እርሱን ለማስደሰት መፈለግን ይጨምራል። የአምላክ ልጅና የቅርብ ወዳጁ የሆነው ኢየሱስ ስለ ይሖዋ “እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና” ብሎ በተናገረ ጊዜ ይህን አሳይቷል።—ዮሐንስ 8:29
ስለዚህ ከይሖዋ ወይም ከልጁ ጋር ወዳጅ መሆን ምንም ዓይነት ግዴታ የማያስከትል ነገር አይደለም። ይሖዋና ልጁ ካወጡአቸው የወዳጅነት ብቃቶች ጋር ተስማምቶ በመኖር ላይ የተመካ ወዳጅነት ነው። (መዝሙር 15:1-5 ተመልከት) ይህንንም ኢየሱስ በተሰቀለበት ዕለት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተነጋገሩ ጊዜ በግልጽ አመልክቶአል። “እናንተም እኔ የማዝዛችሁን ብታደርጉ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሎአቸዋል።—ዮሐንስ 15:14
ሌላው ለወዳጅነት አስፈላጊ የሆነ ብቃት ክፍት እና ግልጽ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ ነው። ኢየሱስ በሞተበት ምሽት ለታማኝ ሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸዋል። “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና። ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።” (ዮሐንስ 15:15) ኢየሱስ ሐሳቡን ለወዳጆቹ ያካፈለው በአሞጽ 3:7 ላይ “በእውነት ጌታ [ይሖዋ (አዓት)] ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” የተባለለትን የሰማያዊ አባቱን አርአያ በመከተል ነው።
ወዳጆች የሆኑ ሰዎች ሐሳብ ለሐሳብ መገላለጻቸው የተለመደ ነገር አይደለምን? ከመንገድ ማዶ እንደሚኖር ብቻ ለምናውቀው ለአቶ በቀለ ስላጋጠሙን ሁኔታዎች ለመናገር የሚገፋፋ ፍላጎት አይኖረንም። በዓይን ብቻ የምናውቀው ሰው ነው። ለወዳጆቻችን ግን ስላጋጠሙን ሁኔታዎች ለመናገር እንጣደፋለን።
ከአምላክ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲህ መሆን ይገባዋል። ፍላጎታችንን፣ ምኞታችንን እና ውስጣዊ ስሜታችንን በጸሎት ለእርሱ ቀርበን ለመንገር አንዘገይም። እርግጥ ነው የሐሳብ ልውውጣችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ከሆነ ወዳጅነታችን ብዙም ሳይቆይ ይሞታል። ስለዚህ አምላክም እኛን እንዲያነጋግረን ፈቃደኞች መሆን አለብን። ይህንንም የምናደርገው የተጻፈውን ቃሉን በጥንቃቄ በማዳመጥ፣ ምክሮቹን በማሰላሰልና በተቻለን ሁሉ በሥራ ላይ በማዋል ነው።
የይሖዋ ወዳጅነት ለአንተ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እንዲረዳህ ስለ አንድ ልዩ የሆነ የሰዎች ወዳጅነት እንመልከት። ወጣት ከሆንክ ምናልባት ወደ ጋብቻ የሚመራ ወዳጅነት ለመመስረት ትፈልግ ይሆናል። ተራ የዓይን ትውውቅ ብቻ ለጋብቻ ጥሩ መሠረት እንደማይሆን እንደምትገነዘብ የታወቀ ነው። በመጀመሪያ ትውውቃችሁ ወደ ወዳጅነት ማደግ ይኖርበታል። ይህ ወዳጅነታችሁ እያደገ ይሄድና ውሎ አድሮ ለደስተኛ ጋብቻ መሠረት የሚሆነውን የተቀራረበ ዝምድና ያስገኛል።
ብዙ ሰዎች ይህን ዓይነቱን ወዳጅነት ለማሳደግና ለማዳበር ምን ያህል ጥረት እንደሚያደርጉ አስብ። ይህን ወዳጅነት ለመመሥረትና ከተመሠረተም በኋላ ጠብቆ ለማቆየት ምን ያህል ጊዜና ገንዘብ ያጠፋሉ? ይህን ወዳጅነት ለማሻሻልና እንደጠነከረ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችላቸውን እቅድ ለማውጣት ወይም ቀደም ሲል ያወጡትን እቅድ ለመለወጥ ምን ያህል ጥረት ያደርጋሉ?
አሁን ደግሞ ራስህን እንደዚህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ይህ ሰዎች የሚያደርጉት ጥረት እኔ ከፈጣሪዬ ጋር ያለኝን ዝምድና ለማሳደግ፣ ለማሻሻልና ለማጠናከር ከማደርገው ጥረት ጋር ሲወዳደር እንዴት ነው? ከይሖዋ ጋር ያለኝ ወዳጅነት በየዕለቱ በማስባቸው ነገሮች ውስጥ ምን ያህል ቦታ ይይዛል? ይህን ወዳጅነት ለማሻሻልና ጥንካሬውን ለመጠበቅ የሚያስችሉኝን እቅዶች ለማውጣትና ቀደም ሲል ያወጣኋቸውንም እቅዶች ለመለወጥ ምን ያህል ጥረት አደርጋለሁ?’
ወጣት ክርስቲያኖች ማንኛውም ዓይነት ሰብአዊ ወዳጅነት፣ ወደ ጋብቻ የሚያደርስ ወዳጅነትም ቢሆን ከፈጣሪ ጋር ካላቸው ወዳጅነት ጋር ሲወዳደር በአስፈላጊነቱ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በመክብብ 12:1: ላይ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” ተብለው የተመከሩትም በዚህ ምክንያት ነው። ብዙዎች በሕዝብ ፊት አምላክን በማገልገል ፈጣሪያቸውን እንደሚያስቡ እያሳዩ ነው። የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ወይም አቅኚዎች የሚሆኑ ወጣቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መጥቶአል።
በአካባቢያቸው ተጠራጣሪነትና ሃይማኖት የለሽነት እየተስፋፋ ቢሄድም በይሖዋ ላይ የሚሰነዘሩትን የሐሰት ስድቦችና ክሶች በሚሰሙበት ጊዜ በድፍረት ለይሖዋ ጠበቃ ሆነው ይቆማሉ። ይሖዋስ ወዳጆቹ ሁሉ እንዲህ እንዲያደርጉ መጠበቅ አይገባውምን? እኛስ ብንሆን ከወዳጆቻችን የምንጠብቀው ይህንን አይደለምን? ወዳጆቻችን በቅንዓት እና በእርግጠኝነት ስለ እኛ እንደሚናገሩ ስናውቅ ልባችን ደስ አይለውምን?—ከምሳሌ 27:11 ጋር አወዳድር
አዎ፣ ከሰዎች ጋርም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት ዘለቄታ ያለው እንዲሆን ልናሟላቸው የሚያስፈልጉ ኃላፊነቶች ይኖራሉ። ይህንን ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው ወይም ለአምላክ ራሱን ገና ያልወሰነና ውሳኔውንም ለመፈጸም ያልተዘጋጀ ሰው በእርግጥ ከይሖዋ ጋር ትውውቅ አለኝ ሊል ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ወዳጅ በማድረግ የሚገኘውን ደስታ ገና አልቀመሰም።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብርሃም በአምላክ ይታመን ነበር። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ወዳጅ ተብሎ ተጠርቶአል