የብስጭትን ስሜት መቋቋም ይቻላል!
የ23 ዓመት ዕድሜ ያለውን የአንድ ሰው አሳዛኝ ሁኔታ ተመልከት። ትምህርቱ በጣም አነስተኛ ሲሆን በዝቅተኛ ደመወዝ ተቀጥሮ ይሠራል። ትዳር መሥርቶ የሚያረካ ሕይወት መኖር የማይታሰብ ነገር ሆኖበታል። እናቱ ስለ እርሱ ሲናገሩ “በጣም ሐዘንተኛና ብስጩ ነው” ማለታቸው አያስደንቅም። የዚህ ወጣት ሰው ሁኔታ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሌሎች ወጣት ሰዎችም ላይ የሚደርስ የተለመደ ነገር ነው። በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ብስጭት ይደርስባቸዋል።
ብስጭት “በተጨናገፈ ምኞት፣ በውስጣዊ የባሕርይ ግጭት ወይም በሌሎች መፍትሔ ያላገኙ ችግሮች ምክንያት የሚመጣ ሥር የሰደደ የመረጋጋት የመተማመንና የእርግጠኝነትና የእርካታ ስሜትን የማጣት ሁኔታ ነው።” (የዌብስተር ሦስተኛ አዲስ ዓለም አቀፍ መዝገበ ቃላት) አንድን ነገር ለማከናወን በጣም ጥረን ሳይሳካልን ሲቀር እንበሳጫለን። ይሳካልናል ብለን የሞከርነው ሁሉ ከድንጋይ ጋር እንደመጋጨት ስለሚሆንብን በሁሉም አቅጣጫ መንገዳችን እንደታጠረ ሆኖ ይሰማናል። ይህ ዓይነቱን ስሜት ሁላችንም እናውቀዋለን።
የማያረካ መስሎ በሚታይ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች የዋጋ ቢስነት ስሜት ያጋጥማቸው ይሆናል። ከየዕለቱ ጭንቀቶችና አድካሚ ሥራዎች ጋር የሚታገሉ ሚስቶች ወይም እናቶች ሥራቸውን የሚገነዘብላቸው ወይም የሚያመሰግናቸው ሰው ከሌለ ምንም ዓይነት ክብር እንደሌላቸውና አድናቆት እንዳልተሰጣቸው ሊሰማቸው ይችላል። በትምህርት ቤት ችግር የሚገጥማቸው ወጣቶች ትምህርት ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ሊበሳጩ ይችላሉ። አናሳ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ፍትሕ የሌለበት አድልዎ እንደሚደረግባቸው ስለሚሰማቸው በውስጣቸው ሊበሳጩና ሊያዝኑ ይችላሉ። ጥራት ያላቸውን ምርቶች ወይም አገልግሎቶች ለማቅረብ በሐቀኝነት የሚጥር ነጋዴ ይሉኝታ ቢስና አጭበርባሪ በሆኑ ተፎካካሪዎቹ ምክንያት ኪሳራ ሊደርስበት ይችላል። እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ተሞክሮዎች ብስጭትና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የኖረ አንድ ጠቢብ ሰው ያጋጠመውን ብስጭት ሊገልጽልን ችሎአል። እርሱም የእሥራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ሲሆን እንደሚከተለው ብሏል፦ “እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፣ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፣ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። ከፀሐይ በታች የደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው? ዘመኑ ሁሉ ኀዘን፣ ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።” (መክብብ 2:11, 22, 23) የሰሎሞን ቃላት ብዙ ሰዎች አስደሳች ኑሮ የሚያሳጣቸውን ብስጭት ለመቋቋም ሲጥሩ የሚያጋጥማቸውን ምሬት ይገልጻሉ።
የተበሳጩ ሰዎች ተስፋ የመቁረጥ ድርጊት እስከመፈጸም ሊደርሱ ይችላሉ። በጣም ሲጠናባቸውም አንዳንዶች ትግሉን ትተው ከኅብረተሰብ ውጭ የሆነ ኑሮ ለመኖር ይገደዳሉ። አንዳንዶች መብታችን ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ወንጀልና ዓመፅ ይፈጽማሉ። የኑሮ ሸክሞች መብዛት ጋብቻዎችንና የቤተሰብ ማሠሪያዎችን አፈራርሶአል።
ብዙዎቻችን የብስጭት ስሜታችንን የምንቋቋምበትን ዘዴ ለመፈለግ ብዙ ጥረት ማድረግ ይኖርብን ይሆናል። ማንኛውንም ዓይነት ጥረት ብናደርግ ነገሮች እየተባባሱ ሊሄዱ ይችላሉ። ምሳሌ 13:12 “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ይላል። ሥጋዊና መንፈሳዊ ጤንነታችን ሚዛኑን ስቶ በአደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ታዲያ እንዲህ ካለው ሁኔታ ፈጽሞ ልንወጣ አንችልም ማለት ነውን? በችሎታችን ማነስና የምንሳሳት በመሆናችን ምክንያት አለብስጭት ለመኖር አንችልም ማለት ነውን? ብስጭታችንን ተቋቁመን ይበልጥ አርኪ የሆነ ሕይወት ለመኖር እንድንችል ልንወስዳቸው የምንችላቸው አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች አሉን? እስቲ እንመልከት።
ብስጭትን ለመቋቋም የሚረዱ አንዳንድ ዘዴዎች
ችግር ሲያጋጥመንና ምክር ስንፈልግ ብዙውን ጊዜ የምንሄደው ወደምናምነው ዐዋቂና ተሞክሮ ወዳለው ሰው ነው። ምሳሌ 3:5, 6 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” በማለት ይመክራል። ተግባራዊ የሆነ ጠቃሚ ምክር በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊገኝ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጣቸው ማስተዋል ያለባቸው ምክሮች አንዳንዶቹን ተመልከት።
ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት ምክንያት ብስጭት ሊያጋጥም ይችላል። ለምሳሌ ያህል ዓለማዊ ሥራችን አስደሳች ቢሆንም የምናገኘው ደመወዝ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ልናዝን እንችላለን። ቤተሰባችንን ስለምንወድ ማንኛውንም ጥሩ ነገር እንዲያገኙ እንፈልጋለን። ሆኖም ገንዘብ ነክ ግዴታዎቻችንን ለማሟላት ስለመቻላችን የሚያጋጥመን ጭንቀት ፍጻሜ የሌለው ይሆንብናል። በዚህም ምክንያት ትርፍ ሰዓት ለመሥራት ወይም ሁለተኛ ሥራ ለመሥራት እንገደድ ይሆናል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሕይወት በመብላት፣ በመተኛትና በመሥራት ብቻ ይወሰንና አሰልቺ ይሆንብናል። ሆኖም ወጪዎች መደራረባቸው፣ ዕዳዎችና ብስጭቶች መጨመራቸው አያቆምም።
የሥጋዊ ሥራ ዋና ዓላማ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት ነው። ግን የሚያስፈልገን ምን ያህል ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን እርሱ ይበቃናል” በማለት ጽፎአል። እኛ ግን ከዚህ አልፈን ሌሎች ያላቸው እንዲኖረን ወይም ሌሎች ሊያደርጉ የቻሉትን ለማድረግ እየጣርን ነውን? ከሆነ በውጤቱ ብስጭት እናጭዳለን። ጳውሎስ “ባለጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:7-10) ቁሳዊ ነገሮችን የምናሳድድበትን ምክንያት በሐቀኝነት መመርመራችን አንዳንድ አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን እያሳደድን እንዳለን ሊያሳየን ይችላል። በቁጠባና ይበልጥ ልከኛ የሆነ ኑሮ ለመኖር የሚያስችሉ ጥቂት ምክንያታዊ የሆኑ ማስተካከያዎችን ማድረግ ብስጭታችንን ለመቀነስ በጣም ሊረዳን ይችላል።
የታፈኑ ወይም ሊሟሉ ያልቻሉ የተፈጥሮ ፍላጎቶች ብዙ ብስጭት አስከትለዋል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ወጣት ሴት ለማግባትና ከቤተሰብ ኑሮ የሚገኘውን የተረጋጋ ኑሮና የሞቀ ፍቅር ለማግኘት ጠንካራ ምኞት ቢኖራት ፍላጎትዋ ከተፈጥሮ ባሕርይ የወጣ አይደለም። ይበልጥ ማራኪ ሆና ለመታየት ስትል በቅርብ የወጡትን የልብስ ፋሽኖች፣ ጌጣጌጦች፣ ቅባቶች፣ የፀጉር አበጣጠሮችና ለውበት የሚጠቅሙ ነገሮችን በመከታተል ብዙ ጥረት ልታደርግና ፍቅር ለተራቡ ሰዎች ምክር የሚሰጡ መጽሔቶችንና ጋዜጦችን በጉጉት ልታነብ ትችላለች። ሴቲቱ የሚስማማትን ሰው አገኛለሁ በሚል ሰዎች በብዛት በሚገኙበት ማኅበራዊ ስብሰባ ወይም የግብዣ ቦታ በመገኘት ብዙ ብትለፋም ላይሳካላት ይችላል። ዓመታት ያልፋሉ፣ ብስጭትዋም እያየለ ይሄዳል። ተስፋ በመቁረጥ የማይስማማትን አንድ ሰው ለማግባት ልትገፋፋ ትችላለች። ይባስ ብላም ፍቅር ለማግኘት ያላትን ጉጉት ለማርካት ስትል ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ ድርጊት ትጠላለፍ ይሆናል።
እንዲህ ላለችዋ ሴት ትዕግሥትና ጥሩ ማመዛዘን አስፈላጊ ናቸው። ተስማሚ ባሕርይ የሌለው ሰው፣ በተለይም በይሖዋ የማያምን ሰው ማግባት ከባድ ስህተት ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:39፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14, 15) የፆታ ብልግና ደግሞ መሪር ኀዘንና ተስፋ መቁረጥ ከማስከተል በቀር የሚያስገኘው ፋይዳ የለም። (ምሳሌ 6:32, 33) አስተዋይነትና ራስን በሐቀኝነት መመርመር ከፍተኛ ጥቅም ሊኖረው ይችላል። ከቄንጠኛ ልብሶች ወይም እንግዳ ከሆኑ መኳኳያዎች ይልቅ “የዋህና ዝግተኛ መንፈስ” ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊስብ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) ዓለማውያን ጠበብቶች በሚሰጡት አርቆ አስተዋይነት የሌለበት ወይም ቀላል የሆነ ምክር ከመተማመን ይልቅ የጋብቻ ምንጭ ወደሆነው አምላክ ሄዶ የምትወደድና የምትከበር ሚስት ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ መማር በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ ምዕራፍ 31) ያላገቡ ወንዶችና ሴቶች የትዳር ጓደኛቸው አድርገው በሚመርጡት ሰው ላይ ሊያዩት የሚፈልጉትን ባሕርይ ራሳቸው ለማሳየት መጣር ይኖርባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን ሥርዓቶች ከሚያከብሩ ሰዎች ጋር ባልንጀራ መሆን ምንኛ ጥበብ ነው። እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ካዋልን አስደሳች ጋብቻ የማግኘት ተስፋችን በጣም የተሻለ ይሆናል። ወዲያው ጋብቻ መመሥረት ባይቻልም እንኳን ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚስማማ ሥራ መሥራት ደስታ የሚያመጣና የነጠላነትን ሕይወት በጣም አርኪ የሚያደርግ ነው።
ከባድ የኃላፊነት ሸክሞችን መሸከም ወደ ብስጭት ሊያደርሰን ይችላል። ከሁሉም አቅጣጫ ግፊት ሊደርስብን ይችላል። ቤተሰባችን ጊዜ የማይሰጡ ፍላጎቶች ይኖሩታል። አሠሪያችን ደግሞ በፍጹም በቃኝ የማይልና ልናስደስተው የማንችል ሊሆንብን ይችላል። ዘመዶቻችን ችግር ባጋጠማቸው ቁጥር የእርዳታ እጃችንን እንድንዘረጋ ይጠብቁብን ይሆናል። የሚያጋጥሙን ተጽእኖዎች በመብዛታቸው ምክንያት ችላ ያልናቸው ብዙ የግል ጉዳዮች ትኩረታችንን ይጠይቃሉ። ጊዜና ጉልበታችን በአንድ ጊዜ ወደ ብዙ የተለያዩ አቅጣጫዎች መሠራጨት የሚኖርበት ሊመስል ይችላል። ብስጭታችን ተስፋ ወደ መቁረጥ ሊያመራና ሁሉንም ነገር ወደመተው ሊያደርሰን ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡንን ነገሮች መመርመር ጥበብ ሊሆን ይችላል። በአንድ ጊዜ ልንሠራ የምንችለው ነገር የተወሰነ በመሆኑ ሌሎች የሚፈልጉብንን ነገር ሁሉ ለማድረግ አንችልም። ጉዳዮቻችንን ቀንሰን “ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች” ላይ ማተኮር ያስፈልገናል። (ፊልጵስዩስ 1:10) “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና።” (መክብብ 9:4) አንዳንድ ግዴታዎቻችን በጣም አሳሳቢና በይደር የማይተላለፉ ናቸው። እምብዛም አጣዳፊ ያልሆኑት ሌሎቹ ደግሞ ሊቆዩ ይችሉ ይሆናል። በአንዳንድ ሥራዎች ላይ ለሌሎች ልናካፍለው የሚገባ ሙሉ ኃላፊነት ሊኖረን ይችላል። አንዳንድ ኃላፊነቶች በጣም አስፈላጊ ካልሆኑ ጭራሹን ልናስወግዳቸው ይገባን ይሆናል። ይህን ማድረጋችን መጀመሪያ ላይ ለሌሎች ያልተመቻቸ ሁኔታ ሊያስከትል ወይም ቅር ሊያሰኛቸው ቢችልም የራሳችንን የግል አካላዊና ስሜታዊ አቅም ማክበር ያስፈልገናል።
የሚያዳክም ሕመምም አንዳንዴ ለቀናት ወይም ለሳምንታት የአልጋ ቁራኛ እንድንሆን ሊያደርገን ስለሚችል ሊያበሳጨን ይችላል። ኃይለኛ የሕመም ሥቃይም ምሬት እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። ፈውስ ፍለጋም ከአንዱ ሐኪም ወደ ሌላው ሐኪም እንሄድ ይሆናል፣ ወይም ይጠቅሙናል በሚል ተስፋ ብዙ መድኃኒቶችን ወይም ቪታሚኖችን እንወስድ ይሆናል። ሆኖም ሥቃያችን ሊቀጥልና ምናልባትም ሕይወት ይህን ያህል ልንታገልለት የሚገባ ነገር እንዳልሆነ ማሰብ እንጀምር ይሆናል።
ይህ ችግር በአምላክ አዲስ ዓለም ብቻ መፍትሔ የሚያገኝ ሊሆን ይችላል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ከኢሳይያስ 33:24 ጋር አወዳድሩት።) ሰዎች ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት ሐኪሞችና መድኃኒቶች ሊሰጡን የሚችሉት እርዳታ የተወሰነ ብቻ ነው። አንድ ደረጃ ላይ ስንደርስ ሥቃያችንን እንደ ሕይወታችን ክፍል አድርገን ለመቀበል እንገደድ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሥጋ መውጊያ” ነበረው፣ ከሕመሙ እንዲፈወስ ተደጋጋሚ ጸሎት እንዲያቀርብ ያስገደደው ይህ ሕመም ምናልባት የዓይን ሕመም ወይም በሌላ ሰውነቱ ላይ የደረሰ በሽታ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) ይሁን እንጂ አምላክ ጳውሎስን አልፈወሰውም፣ ስለዚህ ሐዋርያው ሥቃዩን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ መቋቋም ሳያስፈልገው አልቀረም። ከሥቃዩ ጋር የኖረ ሲሆን በበሽታው ምክንያት እንዲታዘንለት አልጠየቀም፣ ደስታውንም አላጣም። (2 ቆሮንቶስ 7:4) ጻድቅ ሰው የነበረው ኢዮብ በጣም ከፍተኛ ሥቃይ ቢደርስበትም በይሖዋ የነበረውን እምነቱን ጠብቋል፣ ይህም በጣም ከፍተኛ በረከት አስገኝቶለታል። (ኢዮብ 42:12, 13) እኛም የአምላክ አገልጋዮች ከሆንን በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችንንና ይሖዋ እርዳታ እንዲሰጠን መጸለያችንን በመቀጠል ብርታት ልናገኝ እንችላለን።—መዝሙር 41:1-3
ብስጭት ቢያጋጥምም ጠንክሮ መቆም
የይሖዋ ሕዝቦች ማንኛውም ዓይነት ብስጭት ቢያጋጥማቸው በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ሕመማችንን ችለን ለመኖር ብንገደድም በአምላክ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም “በእምነት ጤናሞች” ሆነን ልንኖር እንችላለን። (ቲቶ 2:1, 2) በቁሳዊ ሀብት ረገድ በሚያበሳጭ ሁኔታ ድሆች ብንሆንም በመንፈሳዊ ግን በሚያስደንቅ መንገድ ሀብታሞች ልንሆን እንችላለን።
አምላክ ጥበብና ብርታት እንዲሰጠን በመታመን በቤት ውስጥ በሚፈጠሩ ሁኔታዎች የተነሳ የሚያጋጥመንን ብስጭት ልንቋቋም እንችላለን። ለምሳሌ ያህል የናባልን ሚስት አቢጋኤልን እንውሰድ። ባልዋ “ባለጌና ግብሩም ክፉ ነበረ።” የስሙ ትርጓሜ ራሱ “የማይረባ፣ ስንፍና የሠፈነበት ሰው” (የ1980 ትርጉም) ማለት ነው። ከእንዲህ ዓይነቱ ሰው ጋር መኖር ምን ያህል የሚያበሳጭ መሆን አለበት! ሆኖም አቢጋኤል “በመልካም አእምሮ” የኖረችና ተስፋ መቁረጥ ያላጠቃት ሴት ነበረች። በእርግጥም በአንድ አስጊ ሁኔታ ዳዊት የናባልን ስድብና ምስጋና ቢስነት ደም በማፍሰስ እንዳይበቀልና በይሖዋ ሳይተማመን እንዳይቀር ስለ አሳመነችው በቃልዋም ሆነ በድርጊቷ በጣም አስተዋይ መሆኗን አስመስክራለች።—1 ሳሙኤል 25:2-38
ብስጭት ያስከተለብን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ግለሰብ ባሕርይ ቢሆን እንኳን ይሖዋ በሚሰጠን ብርታት ልንታገሠው እንችላለን። ይህም ሊያበሳጭ በሚችለው በዲዮጥራጥስ አድራጎት ጥሩ ከማድረግና ከጥሩ አድራጎቱም ደስታና ብዙ መንፈሳዊ በረከቶችን ከማጨድ ባልታገደው በጋይዮስ ላይ ታይቷል።—ሥራ 20:35፤ 3 ዮሐንስ 1-10
በጉባኤው ውስጥ ያሉትን የእምነት አጋሮቻችንን ለማገልገል የምንመኝ ከሆነና ሌሎች ከእኛ በፊት ሽማግሌዎች ወይም ዲያቆናት ሆነው ሲሾሙ እኛ ከታለፍን ብስጭት ሊያስከትልብን ይችላል። ይሁን እንጂ ቅሬታ እንዲውጠን ከመፍቀድ ይልቅ ራሳችንን በመንፈሳዊ ማጠናከራችንን እንቀጥልና የአምላክ መንፈስ በከፍተኛ ደረጃ በውስጣችን ፍሬ እንዲያፈራ እንፍቀድለት። (ገላትያ 5:22, 23) አምላክ ሙሴ በምድያም ባሳለፋቸው 40 ዓመታት ወቅት የእሥራኤላውያን መሪ ቢሆን የሚያጋጥሙትን ችግሮችና ብስጭቶች ለመቋቋም የሚያስፈልጉትን ከፍተኛ ትሕትና፣ ትዕግስትና ሌሎችንም ባሕሪያት በውስጡ እንዲያሳድግ አድርጎታል። በተመሳሳይም እኛ በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን ከቆየንና ለብስጭት ስሜት ካልተሸነፍን ወደፊት ለምንቀበላቸው የአገልግሎት መብቶች ይሖዋ እያዘጋጀን ሊሆን ይችላል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከብስጭት ግልግል ይገኛል!
ለብስጭታችን ምክንያት የሆነው ነገር ምንም ይሁን ምን ፍጻሜ ይኖረው ይሆን? ሁኔታችን ለራሳችን በጣም ተስፋ ቢስ መስሎ ይታየን ይሆናል፣ ለፈጣሪያችን ለይሖዋ አምላክ ግን ተስፋ የሌለው ሁኔታ የለም። እርሱ ብስጭት የሚደርስበት አምላክ አይደለም። በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 55:11) ይሖዋ ሁሉን የሚችል ኃይልና ሥልጣን ስላለው ለእርሱ የሚሳነው ነገር የለም። (ማርቆስ 10:27) ለሕዝቡ ማለቂያ የሌለው በረከት ለማምጣት የገባው ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ ነገር ነው።—ኢያሱ 21:45
ብስጭት ሲያጋጥም ጥርጣሬና በነገሮች ላይ እምነት ማጣት ይኖራል። በአንፃሩ ግን “እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” (ዕብራውያን 11:1) በአምላክ ማመን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት ተስፋዎቻችን በሙሉ እንደሚፈጸሙ ዋስትና ይሰጣል። ጠቅላላው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት መሬት ጻድቃን ሰዎች በደስታ ለዘላለም የሚኖሩባት ፍጹም ገነት የምትሆንበትንና ይሖዋ ተስፋ የገባለትን የመንግሥት አገዛዝ የሚያጎላ ነው። (መዝሙር 37:11, 29) በዚያን ጊዜ አምላክ ‘ሕይወት ላለው ሁሉ ፍላጎቱን ስለሚያረካለት’ ተስፋ መቁረጥን ጨምሮ ማንኛውም መጥፎ ነገር ይወገዳል።—መዝሙር 145:16
እነዚህ በረከቶች ፍጻሜያቸውን እስኪያገኙ ድረስ ሁላችንም በየበኩላችን ብስጭት ሊያጋጥመን ይችላል። ነገር ግን ቅዱስ ጽሑፋዊው ተስፋ ለመጽናት የሚያስችለንን ብርታትና ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው እውነተኛና አስተማማኝ ምክር ለሕይወታችን መረጋጋትንና ለልባችን ደግሞ ሰላምን በሚያመጣ መንገድ በጥሩ ሚዛናዊነትና በምክንያታዊነት እንዴት እንደምንጠቀም ሊያሳየን ይችላል። ብስጭት ቢያጋጥመንም “አእምሮን ሁሉ የሚያልፈውን [ከሰው ማስተዋል በላይ የሆነውን (የ1980 ትርጉም)] የእግዚአብሔር ሰላም” ልንቀምስ እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ስለዚህ ብስጭትን ለማሸነፍ የምናደርገው ትግል ተስፋ ቢስ አይደለም። በይሖዋ እርዳታ ብስጭትን ዛሬም ልንቋቋመውና ለወደፊቱም ድል ልናደርገው እንችላለን።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ ኢዮብን፣ ሙሴን፣ አቢጋኤልንና ጳውሎስን እንደረዳቸው ሁሉ አንተም ብስጭት ሲያጋጥምህ ሊረዳህ ይችላል